Wednesday, October 21, 2015

ምንፍቅናና አመጣጡ


በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
(አንድ አድርገን ጥቅምት 10 2008 .)- መናፍቅናፈቀካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን የቋንቋው ሊቅ ትርጒሙን ሲፈቱት የሚጠራጠር፣ የሚያጠራጥር፣ አጠራጣሪ፣ ሃይማኖቱ ግማሽ የኾነ፤ ምሉእና ፍጹም ትክክል ያይደለ፤ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የሚክድ ማለት ነው፡፡ በጽርዕ ቋንቋ ኤሬቲክ፤ በእንግሊዘኛ ሄሬቲክ፤ በግእዝ ደግሞሐራ ጥቃይባላል፤ ትርጒሙን በቋንቋው የተራቀቁት ሊቅ በመዝገበ ቃላታቸው ሲገልጡት መናፍቅ፣ ጠዋየ ሃይማኖት፣ ባህሉና ትርጓሜው ከመጽሐፍ ከንባብ የማይገጥም፤ መጻሕፍት ነው ያሉትን፤ አይደለም፤ አይደለም ያሉትን ነው የሚል የርሱን ሐሳብ ብቻ የሚከተል፤ ነገሩ ካልተማሩት የሚስማማ ከሊቃውንት የማይስማማ ብለውታል፡፡


ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ምዕ 844 “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውናእንዳለ፤ የመጀመሪያው መናፍቅ ዲያብሎስ ሲኾን በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ኅልውና በመጠራጠር፤ ሌሎቹን ነገደ መላእክት ለማጠራጠር ሞክሮ፤ በጥቂቶቹ ተሳክቶለታል፤ ዛሬም እንክርዳዱን የዘራበት የርሱ መንፈስ ያደረበት ሰው አስቀድሞ ነገረ እግዚአብሔርን አጠራጥሮ ካስካደው በኋላ፤ ሌሎችን ለማስካድ መሣሪያ ያደርገዋል፤ አዳምንና ሔዋንን ከገነት ለማስወጣት በእባብ ሰውነት እንዳደረና እንደተሳካለት፡፡
 
በመጨረሻም ዲያብሎስ በሰማይ እያለ ልዑል እግዚአብሔርንና ነገደ መላእክትን ለመስደብ ጀመረ፤ ዛሬም ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ላስካዳቸው መናፍቃን የስድብ መንፈስ በውስጣቸው ልኮ ሥልጣን ያላቸውን እንዲንቁ እግዚአብሔር ያከበራቸውን እንዲያቃልሉና እንዲሳደቡ የስድብ መንፈስን ይሰጣቸዋል ይህነንም ዮሐንስ በራእዩ በምዕ 134-7 ላይለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት፤ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው፤ እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ፤ ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠውይላል፡፡

ሆኖም ግን ይህ ጠላት ዲያብሎስ ሲሳደብ ቅዱሳን መላእክት ዝም ብለው አላዩትም ይልቁኑ ከቅዱስ ሚካኤል ጋር በመኾን ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው አሳቹን ዘንዶ ተፋልመው፣ ተዋግተው ወደ ጥልቁ እንዲወረወር አደረጉት እንጂ (ራእ 137-9) ይህ ለእኛ አብነት ነው፤ ዛሬም ከእውነተኛው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትምህርት ፈቀቅ ያለውን፤ ብንችል መምከር፣ መገሠጽ ሲገባ እንቢ ካለ ግን ሌላውን አካል በክሕደቱ መርዞ እንዳይጥል በውግዘት ቈርጦ መጣል ይገባል፤ ጌታችን እንኳ መናፍቁ ዲያብሎስ ሁለቴ ፈትኖት በሦስተኛው ገንዘብ ወርቅ እሰጥኻለኊ ብሎ በአምልኮት ቢመጣበትኺድ አንተ ሰይጣንበማለት ነበር የመጨረሻ ቃል ተናግሮት የለ! (ማቴ 410)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በገላ 17 ላይየሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ፤ ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን፤ አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁንበማለት በአጽንዖት ተናግሯል፡፡

በዘመነ ሊቃውንት የነበረው የጥንቱ መናፍቅነት እና ያሁኑን ስናስተያየው የሰማይና የምድር ያህል ሰፊ ርቀት አለው፤ አበው በብኂላቸውቀን አይጥለው፣ ጠጅ አያሰክረው፣ የቀለም ሠረገላ አያሰነካክለው የለምእንዲሉ የጥንቶቹ መናፍቃን ከስመ ጥር መምህራን የተማሩ፣ ብዙ መጻሕፍት የጻፉ እጅግ ከመማራቸው የተነሣ ከመጠን ከተጻፈው አልፈው በመመራመር ተጠራጥረው የካዱ ሲሆኑ፤ የአሁኑ ግን ከቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ቤት በፍጹም ያልዋሉ፣ ምስጢር ያላደላደሉ፤ አንብበው የማይተረጒሙ፤ በሚገርም መልኩ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!!! እንዲሉ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ለማንቋሸሽ የማያውቁትን ግእዝ ሲጠቅሱ እንኳ የማያፍሩ፤ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ብቻ የሚመላለሱ፣ የቤተ ክርስቲያን የሴቶችና የወንዶችን መግቢያ እንኳ ያለዩ መሆናቸውን ስናይ እንኳን መናፍቅ ሊባሉ ቀርቶ እንደው ለአቅመ መናፍቅነት (ለመጠራጠር ደረጃ) ራሱ ደርሰዋል ወይ ሲባል፤ በፍጹም አልደረሱም ቢያንስ ለመጠራጠር እኮ ማንበብ፣ መመራመር፣ መፈላሰፍ ያስፈልጋል፤ አኮ!!!

ጌታችን በወንጌልወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነውበጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምናበማለት እንዳስተማረ፤ በዘመነ ሊቃውንት የነበሩ ምእመናንም እረኞቻቸውን ስለሚያውቁ በድፍረት ሳይማር ላስተምራችሁ የሚላቸው አንድም አልነበረምና ከዚህ ዘመን ጋር ሊነጻጸሩ አይችሉም፤ ምክንያቱም እረኞቻቸውንና የቀናውን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን ጠንቅቀው ያውቁ ነበርና በስሜት ዝም ብለው የሚነዱ አልነበሩም፤ ጌታችን እኮ ሐዋርያትን ለስብከተ ወንጌል ከመስደዱ በፊት 3 ዓመት 3ወር በቃልም በተግባርም ካስተማረ በኋላ ነበርሑሩ ወመሐሩ” (ሒዱ አስተምሩ) ያላቸው፤ እንኳን በመንፈሳዊው ዓለም ቀርቶ በዓለማዊው ጥበብ እንኳ ሰው በድፍረት ስለማያቀው ነገር መለፍለፍ አይችልም፤ በሠለጠነው ዓለም አንድ ሰው ሌክቸር ከማድረጉ በፊት የተማረበት ተቋም፤ የትምህርት ደረጃው ከቀረበ በኋላ ነው መልእክቱን (ጥናቱን) በሰዎች ፊት የሚያቀርበው፤ በእኛ ጊዜ ግን ጸጋ በሚል ሽፋን ሰው ስለማያውቀው በድፍረት ሲናገር ብዙዎች ዐውቀው ሳይሆን በስሜት ብቻ ሲያዳምጡ ሲታይ፤ በዘመነ ሊቃውንት የነበሩ በዐፀደ ነፍስ ሕያው የሆኑት አበው እና ክቡራን ምእመናን ለጥቂት ቀናት ከሞት ተነሥተው ዐብረውን ሆነው ቢያዩን ምን ይሉን ይሆን!!! ፡፡
 
እስቲ የሦስቱን ዓለም ዐቀፍ ጒባኤያትን እንኳ ብንዳስስ በኒቅያ ጒባኤ የተወገዘው ዲያቆኑ አርዮስ በታዋቂዎች ሳይሆን በዐዋቂዎች ሊቃውንት በተመላው በእስክንድርያ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ከእስክንድሮስ፣ ከአኪላስ ጋር ሆኖ ከተፈጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ሥር ሲማር የነበረ ነበረ፤ በኋላ ግን ከምርምር ብዛት መምህሩ ያላስተማረውን፤ መጻሕፍት ያላሉትን ዐዲስ ክሕደት ይዞ ብቅ ሲል፤ መጀመሪያ ጓደኞቹ ገሠጹት፤ በኋላም መምህሩ ጴጥሮስ አስጠርቶ መከረው፤ እንቢ ቢል ግን አወገዘው፤ በኋላም 325 .. በኒቅያ 318 ሊቃውንት በተገኙበት በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት፤ በነቅዱስ አትናቴዎስ የነገረ መለኮት ተንታኝነት፤ በቃልም በመጽሐፍም ረትተውት አውግዘውጸሎተ ሃይማኖትንአርቅቀዋል፡፡

381 . በተካኼደው ኹለተኛው ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ ክሕደቱ ወደ ጳጳስ ደረጃ እያደገ ኼዶ የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው መቅዶንዮስሎቱ ስብሐትመንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው የሚል ዐዲስ ክሕደትን ቢያስተምርም፤ 150 ሊቃውንት በቊስጥንጥንያ ተሰብስበው መናፍቁን ጳጳስ ረትተው አውግዘው ለይተውታል፡፡
431 . ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ደግሞ ክሕደቱ እጅጉን አድጎ አነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በተማሩባት በአንጾኪያ የነገረ እግዚአብሔር ትምህርት ቤት ከነድያድርስ ተምሮ በኋላ የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው መናፍቁ ፓትርያርክ ንስጥሮስ የኹለት አካልና ባሕርይ የክሕደት ትምህርትንና በእመቤታችን ወላዲተ አምላክነት ላይ ተቃውሞን ቢያመጣ፤ 200 ሊቃውንት በኤፌሶን ተሰብስበው እነ ቅዱስ ቄርሎስ የተዋሕዶን ነገር በቃል በመጽሐፍ አመስጥረው ንስጥሮስን 12 ቃለ ግዝት ለይተውታል፡፡

451 .. ላይ ደግሞ የሮሜው ልዮን ንጉሡ መርቅያንንና ንግሥት ብርክልያን ይዞ ከቅዱስ ቄርሎስ አንድ አካል፤ ከመናፍቁ ንስጥሮስ ኹለት ባሕርይ የሚለውን ወስዶ በኬልቄዶን ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ሰዎችን ይዞ ተሰበሰበ፡፡

የእስክንድርያው ጳጳስ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ይኽ የክሕደት መልእክት የያዘውን የልዮንን ደብዳቤ በመቅደድ ልዮንንየአባቶቼን ሃይማኖት ብትከተል በእውነት አባቴ ነህ፤ ከሐዋርያት ጀምራ እስካሁን ድረስ ቀንታ የመጣችውን እምነት ብትለውጥ ግን አባቴ አይደለህም፤ ሳጥናኤል ከመካዱ በፊት ከሊቃነ መላእክት እንደ አንዱ ይከበር ነበር፤ ከካደ በኋላ ግን ክብሩ ሁሉ ተገፍፎ ወደ እንጦርጦስ ወድቋልበማለት የክርስቶስን አንድ አካል አንድ ባሕርይ አምልቶ አስፍቶ ሲናገር፤ ከትምህርቱ ታላቅነት የተነሣ ከተሰበሰቡት ውስጥ ሊከራከረው የደፈረ አንድ ስንኳ አልነበረም፡፡ወተምዑ ላእሌሁ ንጉሥ ወንግሥት ወአዘዙ ይዝብጥዎ ወበእንተዝ ዘበጥዎ ወነጸዩ ጽሕሞ ወሰበሩ አስናኒሁ ወከመዝ ገብሩ ቦቱይላል ንጉሡና ንግሥቲቱ ግን በርሱ ተቈጥተው እንዲደበደብ አዝዘው ስለዚኽም ደብድበው ጽሕሙን በመንጨት ጥርሱን ሰብረውታል፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን የተነጨውን ጢሙን የወለቁትን ጥርሶቹን ሰብስቦናሁ ዝንቱ ፍሬ ሃይማኖት ርትዕት” (እነሆ የቀናች ሃይማኖት ፍሬ ይኽ ነው) ብሏቸዋል፡፡ ከዚያም አባቶቻችን ሐዋርያት ካስተማሩት ቅዱሳን አበው በሦስቱ ጉባኤያት ከወሰኑት የሚወጡ ኹሉ የተለዩ የተወገዙ እንደኾኑ በደብዳቤው ግርጌ ላይ ጽፎታል፡፡

ሊቁ አርከ ሥሉስም ይኽነን የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ተጋድሎ፡-
ሰላም ለዲዮስቆሮስ ሃይማኖተ ንጉሥ ዘተሣለቀ
ተዋሕዶተ አምላክ ወሰብእ አመ ለክልኤ ነፈቀ
ያስተጻንዕ ህየ እለ ሀለዉ ደቂቀ
ዘተነጽየ እምነ ጽሕሙ ወእምአስናኒሁ ዘወድቀ
ፍሬ ሃይማኖቱ ፈነወ ብሔረ ርኁቀ

(ሰው የኾነ የአምላክን ተዋሕዶ ለኹለት በከፈለ ጊዜ በንጉሥ ሃይማኖት ላይ የተሣለቀ ለኾነ ለዲዮስቆሮስ ሰላምታ ይገባል፤ በዚያ ያሉትን ልጆች ያጽናና ዘንድ ከወደቁ ጥርሶቹ ከተነጨ ጽሕሙ የሃይማኖት ፍሬ አድርጎ ወደ ሩቅ ሀገር ላከ) በማለት አመስግኖታል፡፡

በመኾኑም ሐዋርያው ይሁዳ በምዕ 1 ላይለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፤ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉእንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፤እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉእነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸውበማለት እንደመከረን ሾልከው ከገቡ ውሃ ከሌለባቸው ባዶ የተራቆቱ ደመናዎች እንድንጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

ልዑል እግዚአብሔር በከበረ ደሙ የመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡

6 comments:

  1. This is very important and must read subject. Thank you Memhir, may God give you long and blessed service years

    ReplyDelete
  2. kalehiwot yasemalin Wondimachen Egthiabher tsegawen yabizalehi

    ReplyDelete
  3. ከሌሎቹ ተሸለው ተገኝተዋል ማለት እችላለሁ ይልከው ወንድማችን አባ ሳሙኤልን በደንብ አታውቃቸውም ማለት ነው፡፡ ይልቅስ አሁን ያሉት ጳጳሳት በሙሉ የመንፈሳዊ ብቃት ምዘና (በመንፈሳዊነት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አጠባበቅ እና በሁለገብ እውቀት) ተደርጎላቸው እንደገና ጵጵስና ይሰጣቸው ቢባል የተሻለ ነው፡፡

    ReplyDelete
  4. አሜን ፤ የዘንድሮውን የሐይማኖት ሕፀጵ ፤ የማያሸንፈው ለስጋው ቅድሜያ ሳይሰጥ የሜወድቅልንና ፣ የሜያዋድቀን መንፈሰ ጠንካራ አባት የድንግል ልጅ ኦየሱስ ክርስቶስ ይጣልልን።

    ReplyDelete
  5. Memhir Rodas kale hiywot yasemalin

    ReplyDelete