- በቤተክርስቲያኗ ስም የሚተላለፉ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች ፈቃድና እውቅና አላቸውን?!
በዲ/ን ኒቆዲሞስ
ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ያላት በዓለም አቀፍ ደረጃም ወንጌልን በቀደምትነት የተቀበለች ሐዋርያዊትና ጥንታዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን የዕድሜዋንና የአንጋፋነቷን ያክል ስለ ጥንታዊ መንፈሳዊ አስተምህሮቿ፣ ስለ ቀኖናዋ፣ ትውፊቷና ሥርዓቷ ለራሷ ልጆችም ሆነ ለሌላው ዓለም የምታሳውቅበት የተጠናከረ የመገናኛ ብዙኃን/ሚዲያ መድረክ አላት ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በርካታ የተማረ የሰው ኃይል፣ አቅምና ሀብት ያላት ቤተ-ክርስቲያን ለዚህን ያህል ዓመታት ለምን የራሷ የሆነ መንፈሳዊ መገናኛ ብዙኃን/ሚዲያ እንደሌላት በራሱ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው።
በሚሊዮኖችን የሚቆጠር ሀብት በሚመዘበርባትና በሚባክንባት ቤተ ክርስቲያንና በዚህ ሚዲያ የመረጃ መለዋወጫ ዋና የደም ሥር በሆነበት ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቷ የራሷ የሆነ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ሊኖራት አለመቻሉ ከማስገረምም አልፎ በእጅጉ ቁጭትን የሚያጭር ነው። ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ዓለም አቀፋዊትና ነጻ አፍሪካዊ እናት ቤተ ክርስቲያን በሚል ቅፅል የምትታወቀው የኢትዮጵያ ቤ/ን አንድ እንኳን የራሷ ድምፅ የሆነ የመገናኛ ብዙኃን/ሚዲያ ተቋም የሌላት መሆኑ በእጅጉ ያሳፍራል።
ለነገሩስ እንደው እንነጋገር ከተባለማ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለተናዊ አቅም በማሳደግና ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በማጠናከርና በማስፋፋት ረገድ ሊያግዝ የሚችል ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ መንፈሳዊ የትምህርት ተቋም/ዩኒቨርሲቲስ አላት እንዴ?! በብዙ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ችግሮች ከተተበተበው ‹‹አንድ ለእናቱ›› ብለን ልንጠራው ከምንገደድበት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በስተቀርስ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተምህሮና ቀኖና፣ የረጅም ዘመናት ታሪኳንና አስደናቂ የሆኑ ቅርሶቿን በሚገባ ለመጠበቅ፣ ለማጥናትና ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ የጥናትና የምርምር እንዲሁም የልቀት ማዕከል አለመቋቋሙም ኀዘናችንና ቁጭታችን የሚያባብስ ነው።
የኢትዮጵያን ዕሥራ ምዕት በዓልን አስመልክቶ ነፍሰ ኄር ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በእንጦጦ ኤልያስ ቤ/ን አካባቢ ለቤተ ክርስቲያኒቷ አስተምህሮና የረጅም ዘመን ታሪክ የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ በኢትዮጵያዊው ሊቅና ማሕሌታይ በቅዱስ ያሬድ ስም የሚጠራ የሥነ-መለኮት ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። ግና አሳዛኙ ነገር ይኸው ለላፉት ሰባት ዓመታት ስለዚህ ዩኒቨርሲቲ ወሬውም ተነሥቶ አያውቅም። አሁን ያሉት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም ሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ ስለዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጉዳይ አንዳች ነገር ብለውንም አያውቁም።
በዛሬው ጽሑፌ ላነሳው ስለፈለኩት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የሚዲያ አጠቃቀምና ችግሮቹ ጉዳይ ልመለስና አንዳንድ የመወያያ አሳቦችን ላንሳ። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ አስተዳዳር ወጥታ ራሷን በቻለችባቸው ዓመታት ከሦስት ከማይበልጡ የሕትመት ውጤቶች ሌላ በተጨማሪ ብስራተ ወንጌል የተባለ መንፈሳዊ ዝግጅቶች የምታስተላልፍበት የራዲዮ ጣቢያ እንደነበራት ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ የራዲዮ ጣቢያ የዘውድ አገዛዙን ገርሥሦ ወደ ሥልጣን በመጣው በደርግ መንግሥት አማካኝነት ዕጣ ፈንታው ሙሉ በሙሉ መዘጋት ሆኖ ነበር።
ደርግ የቤተ ክርስቲያኒቱን እንቅስቃሴ በመገደብ ገና ከጠዋቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ በማጋዝና በግፍ በመግደል ጠንካራ ክንዱን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አሳርፎ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ። ይህ ደርጉ ያራምድው የነበረው ፀረ-ሃይማኖት የሆነ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮዋንና ታሪኳን ለማጥፋት ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም የደርግ ሥርዓት በቤ/ቱ ሁለተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ ተፅዕኖና አሉታዊ የሆነ ውጤት እንደነበረው ግን የማይካድ ሐቅ ነው።
በዚህ ግፍና መከራ ውስጥ ያለፈችው ቤተ-ክርስቲያን ከደርግ መውደቅ በኋላም በአገሪቱ በታወጀው የሃይማኖት ነጻነት ምክንያት አንጻራዊ የሆነ ሰላምንና ነጻነትን ለመጎናጸፍ በቅታለች። ይህ የሃይማኖት ነጻነት አዎንታዊ ፍሬዎች እንደበሩት ሁሉ በተቃራኒው ደግሞ በቤተ እምነቶች መካከል እርስ በርሳቸው በእኔ እበልጥ በእኔ እበልጥ ፉክክር፣ በስም ማጥፋት ዘመቻ፣ በውግዘትና በክርክር ውስጥ እንዲገቡ በር መክፈቱም አይዘነጋም። በዚህ የሃይማኖትን ካባ በለበሰ ዘመቻ ሂደት ውስጥ ደግሞ አንዳንድ የሕትመት ሚዲያዎች በዋና አቀጣጣይነትና አጋዥነት ውክልናውን ወስደው ሢሰሩ ቆይተዋል።
ያለ ልክ ስሜትና እልክ ውስጥ የገቡ ሰዎች በእነዚህ የሕትመት ሚዲያዎች ላይ በሚያስነብቧቸው ጽሑፎች በቤተ እምነቶች መካከል ፍቅር፣ መከባበር፣ ውይይትና መነጋገር እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ ልዩነቶችን በማስፋት አንዱ የአንዱ ጠላት እንደሆነ በመስበክ እስከ ደም መፋሰስ ድረስ የደረሱ ግጭቶች ምክንያት ሆነው እንደነበርም ቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ ወደሶሻል ሚዲያው የተሻገረውና በየዕለቱ የምናነባቸው ጠብ ያለሽ በዳቦ ዓይነት ጽሑፎችና አስተያየቶች በቤተ እምነቶች መካከል በእጅጉ እያደገና እየተስፋፋ ያለውን ጽንፈኝነትና አክራሪነት በአደባባይ ሣይቀር የሚጋልጥ እየሆነ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ የሕትመት ሚዲያው በቤተ እምነቶች መካከል ተከስቶ የነበረውንና አሁንም ያሳደረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በተመለከተ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አዘጋጅቶት በነበረውና ‹‹የክርስቲያናዊ ሚዲያ አገልግሎት›› በተሰኘው ሲምፖዚየም ላይ ‹‹የመረጃ/የመገናኛ አውታርና ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር›› በሚል ርእስ መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ባቀረቡት በጥናታዊው ወረቀታቸው ላይ ከሥነ ምግባር አንጻር የክርስቲያን ሚዲያው ያሉበትን ችግሮች እንዲህ ይገልጹታል፡-
‹‹የእኛ የክርስቲያኖች ሚዲያ (በዋናነት የሕትመት ሚዲያውንና እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ስም የተቋቋሙ ብሎጎችንና ሶሻል ሚዲያውንም ጨምሮ መሆኑን ልብ ይሏል) በዓለማውያን ዘንድ ብዙም የማይታየውን፣ ከማያምኑ ሰዎች እንኳን የማይጠበቀውን ሥራ በማስተናገድ፣ የስድብ፣ የድብድብ፣ የጠብ፣ የጥላቻ፣ የነገር፣ የሥጋትና የትርምስ፣ የሐሰት፣ ኃላፊነት የጎደለው፣ የስንፍናና የደካማነት መገለጫ በመሆን እንኳን የምናመለክውን አምላክ ክብርና የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሊገልጽ ይቅርና አንድ በሰለጠነ ዓለም የሚኖር የ፳፩ኛው ክ/ዘመን አዋቂ ሰውን ገጽታ የሚያስገምቱ ሆነው ይገኛሉ።››
የመምህር ዳንኤል ጥናት ምንም እንኳን ትኩረቱን ያደረገው በአጠቃላይ በክርስትና የሃይማኖት ተቋማት ጥላ ሥር በሚታተሙ የሕትመት ውጤቶች ላይ ቢሆንም በጥናቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን በኩል የሚወጡ የሕትመት ውጤቶቹም ተዳሰውበታል። እነዚህ የአንድ እጅ ጣት ያህል እንኳን ቁጥር ያነሰ ብዛት ያላቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ የሚታተሙት ጋዜጦችና መጽሔቶችም ከይዘታቸው እስከ ስርጭታቸው፣ ጥራታቸውና ወቅታዊነታቸው ድረስ በርካታ ጥያቄዎች የሚነሳባቸው ናቸው።
የሕትመት ሚዲያውን ለጊዜው እንተወውና ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን የሆነውን የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን ጉዳይ ስንቃኝ ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የሉም የሚባልበት ደረጃ ላይ ከመሆናችንም ባለፈም አሉ የሚባሉትም መንፈሳዊ ሚዲያዎች ከመንፈሳዊነት፣ ከሞራል፣ ከጋዜጠኝነት ሙያና ከሥነ ምግባር አንጻር ሰፊ ክፍተት ያላቸው መሆናቸው የመንፈሳዊ ሚዲያዎቹ ችግሮቹ ምን ያህል የሰፉ መሆናቸውን ያስገነዝበናል። ግን ያም ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ዘንድ ሕጋዊ ህልውና አግኝቶና ሙሉ ፈቃድ ተሰጥቶት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ዘመኑን የዋጀና ሚዲያው የደረሰበትን ዕድገትና የቴክኖሎጂ ግሥጋሤ በግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ማኅበሩ ሚዲያውን ለመጠቀም የበኩሉን ቢጥርም ከአቅምና ውሱንነትና ከቤተ ክህነቱ ዘመን ያለፈበትና የተወሳሰበ ቢሮክራሲያዊ አሠራርና ንቅዘት የተነሣ የሚገባውን ያህል እየሠራ እንዳልሆነ ግን በሚገባ ይታወቃል።
ማኅበረ ቅዱሳን አሉ የሚባሉትን ውስጣዊና ውጪያዊ ችግሮችና ግፊቶች ሁሉ ተቋቁሞም ቢሆን በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሚያስተላላፍው የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በተጨማሪም በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያና ካናዳ ላሉ ምእመናን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን ሚዲያውን በመጠቀም ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ረገድ የበኩሉን ሰፊ ጥረትና እገዛ እያደረገ ነው። በተጨማሪም የማኅበሩ የጥናትና ምርምርና የኤሌክትሮኒከስ ሚዲያው ማእከል የቤተ ክርሰቲያኒቷን ዶግማ/አስተምህሮ፣ ቀኖና፣ ታሪክና ባህል እንደ ኦሮሚፋ ባሉ የአገራችን ቋንቋዎችና በውጭ አገራት ቋንቋዎች ለማስፈፋት እያደረገ ያለው ሰፊ የሆነ የተቀናጀ ጥረትም ሳይዘነጋ ማለት ነው።
ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድና ዕውቅና ካለው የሚዲያ መንፈሳዊ አገልግሎት ማኅበረ ቅዱሳን እስከቅርብ ድረስ ጊዜ በኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በማኅበረ ቅዱሳን አማካኝነት የሚቀርብ አንድና ብቸኛ የቴሌቪዥን ዝግጅት ነበር። በአሁን ሰዓት ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን ስም የሚተላለፉ ሦስት የቴሌቪዥን ዝግጅቶች አሉ። በእነዚህ ዝግጅቶች ላይም ከሰሞኑን በሶሻል ሚዲያው፣ በተለያዩ ድረ ገጾችና ብሎጎች ላይ በርካታዎች ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው።
የተቃውሞው አንድምታም እነዚህ ቴሌቪዥኖች ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቃቸው፣ ፈቃድም ሆነ ዕውቅና ያልሰጠቻቸው በመሆኑ የሚለው አንዱ ምክንያት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በዋነኝነት በእነዚህ ቴሌቪዥኖች የሚቀርቡት ዝግጅቶች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና፣ ትውፊትና ሥርዓት ያፈነገጠ ፈጽሞ ኦርቶዶክሳዊም ሆነ ኢትዮጵያዊ መዓዛና መልክ የሌለው ነው ሲሉ ትችታቸውን ያጠናክራሉ።
ይህ ወቀሳ፣ ተችትና ተቃውሞ እየደረሰባቸው ካሉ የቴሌቪዥን ዝግጅቶች መካከል ደግሞ ታዖሎጎስና ቃለ-አዋዲ የተባሉት የቴሌቪዥን ዝግጅቶች ዋነኞቹ ናቸው። በተለይም ደግሞ ከሰሞኑን የቃለ-አዋዲ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን በየሳምንቱ እሑድ በሚያቀርበው መንፈሳዊ የስብከት ፕሮግራሙ ላይ፣ ‹‹አንድ ወልዳ ስሙን አበዛችው የሚለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን የእናቶቻችን ዝማሬ የወንጌል መሠረት የሌለው፣ መንደርተኛ የሆነ ዝማሬ ነው።›› በማለት ያቀረበው ትችትና ስላቅ ብዙዎችን የቤተ ክርስቲያኒቱን ምእመናን ያሳዘነና ያስቆጣ ኾኗል። ይህ ቁጣም ተባብሶ የተቃውሞ ድጋፍ እስከ ማሰባሰብና የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ እነዚህን ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ ዝግጅቶችን በቤተክርስቲያኒቱ ስም ማስተላለፋቸውን እንዲያቆሙ ጥሪያቸውን እስከ ማስተላለፍ ድረስ የዘለቀ ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ነው።
እስቲ በመንፈሳዊ ሚዲያዎቹ ዙርያ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን እናንሣ። ለመሆኑ እነዚህ በኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን የሚተላለፉ መንፈሳዊ ጣቢያዎች ሲቋቋሙ ምን ያህል ጥናት ተደርጎባቸዋል? ወይስ ስምን፣ ገንዘብንና ዝናን መሠረት ተደርጎ እንደው ዘው ተብሎ የተገባበት ጉዳይ ነው? እነዚህ ጣቢያዎችስ በዝግጅቶቻቸው ላይ የሚያቀርቧቸው መርሐ ግብሮች ከመንፈሳዊነታቸው ባሻገርስ ከሚዲያ ሙያና ሥነ ምግባር አንጻር የሚተዳደሩበት፣ የሚዳኙበት ኢዲቶሪያል ቦርድና አማካሪ አላቸውን? ወይስ በጣቢያው መስራችና ባለቤት ፈላጭ ቆራጭነት እዳሻቸው የሚዘወሩ ናቸው?!
እነዚህ የመንፈሳዊ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሚያስተላልፏቸው መርሐ ግብሮቻቸው በሚቀርቡ ትምህርቶች፣ ውይይቶች፣ ዝማሬዎችና ሌሎች መንፈሳዊ ዝግጅቶችስ ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና ምሁራን ማስተካከያና ትችት ይደረግባቸዋልን ወዘተ… ብለን ብንጠይቅ መልሱ አሳፋሪ ሊሆን እንደሚችል ነው የምገምተው። ለነገሩስ በመንፈሳው ሚዲያ ዘርፍ ብቁ የሆኑና ሓላፊነት የሚሰማቸው ባለሙያዎችና አገልጋዮች በብዛትና በጥራት አሉን ወይ የሚለውም ነገር አጠያያቂ ነው።
ለአብነት ያህል ለ፲፻፮፻ ዓመታት ያህል ጳጳሳት ስትሾምልን የነበረችው የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ንን እስቲ እናንሳ። ከ፲፭ ዓመታት ያላሰለሰ ጥረትና ድካም ድካም በኋላ እ.ኤ.አ. በ፳፻፭ አጋፔ በሚል ስም የተቋቋመው የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ን መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በነፍሰ ኄር አቡነ ሺኖዳና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የተመሰከረላቸውና እስከ ፒ.ኤች.ዲ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ባላቸው ባላቸው ፲፫ ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ ጥናት የተቋቋመ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ከዛ በኋላም በአሜሪካን በኒውጄርሲ የተቋቋመው የቅዱስ ማርቆስ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አስከትሎም ደግሞ በአንድ ግብጻዊ ክርስቲያን ባለ ሀብት የተቋቋመው የኮፕቲክ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ን ከአገር ውጪም በደቡብ አፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በካናዳ በርካታ መንፈሳዊ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሏት።
እንግዲህ ከግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ን ንጽጽር ወደ እኛ ቤ/ን መንፈሳዊው ሚዲያው ስንመለስ ያለው እውነታ የሚያስቆጭና ወዴየት እየሔድን ነው የሚያሰኝ ነው። እነዚሁ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአንድ ሰዓት አየር ገዝተው በሚያስተላልፉት መርሓ ግብሮችም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ቀኖና፣ ከታሪክና ከባህል አንጻር በርካታ ጥያቄዎች የሚነሳባቸው እየሆኑ ነው። በተጨማሪም ደግሞ እነዚህ አሉን የምንላቸው የቴሌቪዥን መርሓ ግብሮች ዘንድ የሚታየው ምዕራባውያኑን ለመምሰል ከመጣር ጀምሮ ምድራዊን ተስፋ፣ ምቾትና ተድላ የሙጥኝ ያሉ፣ መጋቢ ሐዲስ እሸቱ በአንድ ወቅት እንዳሉት የምዕራቡን ዓለም የክርስትና ሕይወት በቁም ባወረደው በብልጽግና ወንጌል አሰተምህሮና የአዲሱ ዓለም እንቅስቃሴ /The New Age Movement የተቃኙ ወደመሆን እየተሸጋገሩ ያሉነው የሚመስለው።
እነዚህ የቴሌቪዝን ጣቢያዎች የሚሰብኩ አገልጋዮች ነን ባዮች እርስ በርሳቸው አንዱ ከሌላው የሚወዳደሩበትና የሚፎካከሩበት፣ የለየለት ትወናቸውን የሚተውኑበትን፣ የቁንጅና እና የሀብት ውድድር የሚያሳዩበት መድረክ እየሆነ እንደመጣ እያየን እየታዘብን ነው። ከተግሣጽና ከንስኃ ስብከቶች ይልቅ አይዞህ ይሳካልሃል፣ ጌታ ከአንተ ጋራ ነው፣ ትሻገራለህ፣ ታልፈዋለህ፣ ባለ ድል ነህ… ወዘተ በሚል ስሜትን ያለ ቅጥ ከፍ በሚያደርጉ፣ በምድራዊ ሀብትና ምቾት ብቻ ላይ የተንጠለጠሉ ስብከቶችን እንጂ ለንስኃ፣ ለጸጸት፣ ለለቅሶ፣ ለፍቅርና ለበጎ ሥራ የሚያነቃቁና የሚያበረታቱ ስብከቶችን ለምእመኑ ልብና ጆሮ በማድረስ ረገድ በጣሙን ወደኋላ የቀሩ ናቸው።
እነዚህ በኢትዮጵያ ቤ/ን ስም የተቋቋሙና ግን ደግሞ በአንድ ሃይማኖት ጥላ ሥር ነን እያሉ እርስ በርሳቸው ስምምነትና ፍቅር ሌላቸው የቴሌቪዥን መርሓ ግብሮች ዋና ተልእኮአቸውና ተደራሽነታቸው ለማን እንደሆነ ይታወቃል። በከተማና በውጩ ዓለም ለሚኖሩ ሕዝቦች እንጂ ከ፹፭ ከመቶ በላይ በገጠር ለሚኖረውና የወንጌል ቃል ብርቅ ለሆነበት ሕዝባችን ተደራሽነት እንደሌላቸው መቼም ለማንኛችንም ግልጽ ነው። እንደሚታወቀው በከተማና በውጭ አገር የሚኖሩ ምእመናን ወንጌልን ለመስማት በርካታ አማራጭ አላቸው።
እናስ በእርግጥ እነዚህ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዋና ዓላማቸው ወንጌልን መስበክ ከሆነ ለምን በነፍሱም በሥጋውም በአስከፊ ድህነትና ጉስቁልና ተመቶ በቀቢጸ ተስፋ ተውጦ ግራ ለገባው ሕዝባችን ለመድረስ የሚችሉበትን ሌላ አማራጭ ለመውሰድ አልፈለጉም። የዚህ ምላሹ አጭርና ግልጽ ነው። ዋጋና መሥዋዕትነትን መክፈል ስለማይፈልጉና በተቃራኒው ወንጌሉን የራሳቸውን ምቾትና ተድላ፣ ስምና ዝናቸውን የሚያደላድሉበት መወጣጫ መሰላል ስላደረጉት ነው።
እንጂ እውነት እንዴት ለጠብና ለክርክር፣ ለእኔ እበልጥ ለእኔ እበልጥ ውድድርና ፉክክር ሲባል በአንዲት ቤ/ን ጥላ ሥር ነን የሚሉ ወገኖች ጎራ ለይተው ለራሳቸው ጥቅምና ዝና ሲሉ በሚሊዮኖች የሚገመት ብር እየተከሰከሰ በወንጌል ስም በለየለት እንዲህ ዓይነት ትወና ይህን ከድኃ መቀነቱ ለራሴ ሳይል የሚያበላቸውንና የሚያለብሳቸውን ምስኪን ምእመናን ግራ ያጋቡታል።
በእርግጥ እነዚህ ቴሌቪዥን መርሓ ግብሮች ዋና ዓላማቸውና ተልእኮአቸው ወንጌል ከሆነ እንቆምላታልን በሚሏት ቤ/ን ደጃፍና አጥር ስር አንጀታቸው ታጥፎ፣ በመጦሪያ ዘመናቸው የቀኑ ፀሐይ የሌሊቱ ቁር እየተፈራረቀባቸው ያሉ አረጋውያን አባቶችንና እናቶችን፣ ነገ ከወገናቸውና ከአገራቸው ለይተው ወደማያውቁት አገርና ሕዝብ ለሞትና ለጥፋት የሚወስዷቸውን ፈረንጆችን በተስፋ የሚጠባበቁትን ምስኪን ሕፃናት ወገኖቻችንን በቋሚነት ለመደገፍ፣ ለማቋቋምና ለመርዳት የሚችሉበትን ፍቅር፣ አንድነትና ትብብር አያደርጉም፣ ከጠብና ከጥላቻ ይልቅ። ለእኔ እንደሚገባኝ ወንጌል በተግባር የሚገለጽ ፍቅር- እውነት እንጂ የመድረክ ላይ ትወና፣ ፉክክር ወይም ውድድር አይደለም።
በመጨረሻም አሁን እየታየ ያለውን የተዘበራረቀ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ቀኖና፣ ታሪክና ባህል አንጻር ሲታይ ጥያቄ የሚነሳባቸውንና ከልካይ ያጡትን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚተላለፉትን እነዚህን የቴሌቪዥን መርሓ ግብሮችን መርምሮና ገምግሞ ፈቃድና ዕውቅና ከመስጠት አንሥቶ ወጥነትና ሰፊ ተደራሽነት ባለው መልኩና እንዲሁም ዘመኑን በዋጀ አካሔድ በሚገባ በማደራጀትና በማጠናከር በአገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊና ዋና ተልእኮ የሆነው ወንጌል እንዲፋጠንና እንዲስፋፋ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን የእርምት ዕርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። በርካታ የተማረ የሰው ኃይል፣ ሰፊ አቅምና ሀብት ያላት የኢትዮጵያ ቤ/ን ለአስተምህሮዋና ለቀኖናዋ፣ ለትውፊቷና ለሥርዓቷ፣ ሺሕ ዓመታትን ላስቆጠረው ታሪኳና ባህሏ የሚመጥን የራሷ የሆነ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲኖራትም ልታስብበት ይገባል።
(ምንጭ ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ)
ለፅድቅ ያልታደለች ነፍስ ስለ ያዙ ናቸው
ReplyDelete