Sunday, February 7, 2016

‹‹ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል››

(አንድ አድርገን 29-05-08) :-  " አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት ወዲያው ወታደሮች በሩምታ ተኩሰው ገደሉዋቸው ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ "

" ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወትበዚህ ቄስ መገደል እኮ ሕዝቡ ተደስቷል› አለኝ እንዴት? › ብለውአላየህም ሲያጨበጭብ› አለኝ እኔምባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል› አልኩት ‹‹እንዴት?›› ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት ፡፡
(ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን / መርሻ አለኸኝ ገጽ 79-80)



ነገ ዕሁድ ጥር 29/2008 - ጠዋት 300 ላይ 5ኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም ጀምረን የጀግናችንን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ የምሥክር ሐውልት አጅበን ፒያሳ ወደሚገኘው የቀድሞ ክብር ቦታው ዳግም ልናቆመው እነሆ ሰዓታት ብቻ ይቀሩናል

ስለዚህም በዚህ መርሐ ግብር ላይ የምንገኝ ሁላችን የምሥክር ሐውልቱ እቦታው ደርሶ ከሥፍራው እንደቀደመው በሚቆምበት ሰዓት ጀግናችንን በጭብጨባ እናንግሣቸውፋሽስት ኢጣሊያ አባታችንን በግፍ በገደላቸው ጊዜ ከላይ እንዳነበብነው ሕዝቡ በግድ እንዲያጨበጭብ ተደርጎ ነበር የሕዝቡን ባሕል ያልተረዳው የፋሽስት ሰው ግን ስንናደድና ስንቆጣ እንደምናጨበጭብ አልገባውም ነበር

ታዲያ
- የአቡነ ጴጥሮስን በጭካኔ መገደልና የፋሽስት ጣሊያን አረመኔያዊ ተግባርን የምንቃወም መሆናችንን ለማስገንዘብ
- የዛሬ 80 ዓመት በፊት በፋሽስቶቹ ተገዶ አደባባይ የወጣውና በጻድቁ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ መገደል እንዲያጨበጭብ የተገደደው ሕዝብ አካልና አጋር መሆናችንን ለማሳየት
- በባቡር መንገድ ሥራ ምክንያት ተነሥቶ የነበረው የምሥክር ሐውልታቸው ዳግም ተመልሶ በክብር ቦታው መቆሙ አስፈላጊና ግዴታም መሆኑን ለማረጋገጥ
- እንደ እሳቸው ያለ የሕዝብና የሀገር ፍቅር የሚገደው ከራሱ በላይ ለወገኑ የሚኖር የሃይማኖት አባትና የሀገር መሪ ዛሬም የምንናፍቅ መሆናችንን ለማሳየት
- ለጀግናው የጀግና ክብር ለአርበኛው የአርበኛ ዝክር መስጠትና ማድረግን ግድየለሽ በሚሆኑ የቤተ ክህነት የቤተ መንግሥት እና የማኅበረሰብ አካላት በጨዋ አካሄድ የምንቆጣና የተናደድን መሆናችንን ለማሳሰብ
- በአጠቃላይ ለአቡነ ጴጥሮስ ያለንን አድናቆትና ክብር ከፍ ባለድምፅ ጀግናችንን በጭብጨባ እናንግሣቸው !

ጀግናችንን በጭብጨባ እናንግሣቸው !
ጀግናችንን በጭብጨባ እናንግሣቸው !
/የጎርባቾቭ ማስታወሻ ጥር 27 ቀን 2008 -/


1 comment:

  1. ባታውቀው ነው እንጂ የህዝቡ ባህል ሲናደድም ያጨበጭባል፡፡ የአባታችንን የአቡነ ጴጥሮስን የሐይማኖትንና የሀገርን ፍቅር እግዚአብሔር አምላክ ለዚህኛውም ትውልድ ይስልን፡፡ በረከታቸው አይለየን፡፡

    ReplyDelete