Monday, August 8, 2011

እኛን ለመብላት ነው

             በጥንት ጊዜ ሁለት ውሾች ክፉኛ ይጋጩና በጨበጣ ውጊያ በክራንቻቸው ይቦጫጨቁ ጀመር።ጠቡ እየከረረ ሔዶ ምድር ስትጨነቅ ከበላያቸው ደግሞ ብዙ ጆፌ አሞሮች የተጣለ ግዳይ ለመዘንጠል ማንዣበባቸውን ቀጥለዋል።ይኼኔ የአሞሮቹን ማንዣበብ ያጤነው አንደኛው ውሻ ጠቡን አስታግሦ "ስማኝማ አንዴ እነዚህ አሞሮች ምን ነክቷቸው ነው ከበላያችን በማንዣበብ የሚዞሩን ?" ሲል ሌላኛውን ውሻ ይጠይቃል።ተጠያቂው ውሻም "እነዚህ አሞሮች የሚከታተሉት የእኛን ድብድብ ሲሆን የሚጠብቁትም የእኛን ሞት ነው። ከሁለት አንዳችን ወይም ሁለታችንም ስንሞት ይቦጫጭቁንና ይበሉናል።" አለው። የመጀመሪያ ጠያቂ ውሻ ቀበል አድርጎ "እንዲህ ከሆነ ታዲያ እኛ መጣላታችንን ለምን አንተወውም?"ሲል ሌላኛውም ውሻ በአሳቡ ተስማምቶ ሁለቱም ጠባቸውን ትተው በፍቅር ተነስተው ተጓዙ። ያንዣብቡ የነበሩ ጆፌ አሞሮችም የሚቦጫጭቁትና የሚዘነጣጥሉት ስላጡ አዝነው ተበታተኑ።ይባላል።


           ወገኖቼ ሆይ ዛሬ በዓለም ላይ ያለውን ሁከትና ሽብር ስንመለከት እየሆነ ያለው ይኸው ነው። በአንዱ ኪሳራ ሌላው ሲከብር ማየቱ የተለመደ ነው።እርስ በእርስ የተጣላችሁ የተኮራረፋችሁ እስኪ መለስ በሉና የጠቡን ጅማሬ ለመመልከት ሞክሩ ውጤቱ ምን ሆነ? ማን አዘነ? ማን ተጠቀመ? መቼም በእኛ የእርስ በእርስ ጠብ  ነፍሳችንን ወደ ሲዖል ለማውረድ የሚቋምጠው ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የመጀመሪያው ተደሳች መሆኑ አያጠራጥርም።ስለዚህ ጠላት ደስ አይበለው እኛው እንታረቅ፣እኛው እንስማማ፣እኛው ለእኛው እንወቅበት።


ምንጭ ፡ - ምጥን ቅመም ከተባለችው መጽሐፍ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment