Sunday, August 14, 2011

ስለሚያስቷችሁ ሰዎች ይህንን ጽፌላችኋለሁ 1ኛ ዮሐ.2፥27

ሐሰት አንናገርም፤ እውነትንም አንደብቅም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተነጣጠረው የ”ተሐድሶ” ዘመቻ ውጥን ብዙ ዐሥርት ዓመታት ያለፉት ቢሆንም ከ1992 ዓ.ም. የካቲቲ ወር ጀምሮ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ተጨባጭ በሆኑ የምስልና የድምፅ ማስረጃዎች ዘመቻውን በማጋለጥ የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ ውግዘት ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ ከዚያ በኋላ “ተሐድሶ” ስልቶቹን በመቀያየር ሃይማኖታችንን ለማጥፋትና በሌላ ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ለመተካት የሚያደርገውን ሩጫ ቀጥሏል፡፡ በመሆኑም ማኅበረ ቅዱሳን ካለፈው ነሐሴ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ይፋዊ የሆነ ከእነዚህ ሴረኞች ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ እንቅቃሴ ጀምሯል፡፡ የሐመር መጽሔት ልዩ እትምን በማዘጋጀት የተጀመረውን አገልግሎት በሌሎችም በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ከካህናቱ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ፊት ለፊት በተደረጉ ውይይቶች በመታገዝ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም የ”ተሐድሶ”ን ምንነት፣ መሠረት፣ ግብና ዓላማ፣ ስልት፣ ያለበትን ደረጃ፣ በሌሎች እኅት አብያተ ክርስቲያናት ፈጥሮት የነበረውን ቀውስና መዘዝ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዒላማ ለማድረግ በይፋ በተለያዩ የኅትመት ውጤቶች እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማብራራት ጥረት ተደርጓል፡፡


ይህንን በማድረግ ሂደት ውስጥ ይህንን ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቁን እንቅስቃሴ ለማጨናገፍ የተሐድሶ” አራማጅ ቡድኖች የተለያዩ ስያሜዎችንና አካላትን በመጠቀምና “የተሐድሶ” እንደ ሸረሪት ድር ሠርቶት የነበረውን የጥፋት መረብ ሳይበጣጠስና በውስጥም በውጭም የሠራው መሠረት ሳይናድ ለማስቀጠል ባለ በሌለ ኃይሉ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ምእመን በእግዚአብሔር ረድኤት የዕለት ከዕለት ተግባሩን ከማከናወን ጋር የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በንቃት መከታተልና መቆጣጠር በሚችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡

በዚህ ተስፋ እየቆረጠ ያለው የ”ተሐድሶ” መሠሪ ኃይል ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ተላላኪዎቹ በኩል ሊነዛ የፈለገው ተራ ማታለያ “ተሐድሶ የለም”፣ “ተሐድሶ” የሚል ነገርን የፈጠረው ማኅበረ ቅዱሳን ነው” የሚለውን አባባል ነው፡፡ ይህን አካሔድ ተራ ማታለያ ነው የምንለው የ”ተሐድሶ” መኖር ሊስተባበልበት የማይችልበት ደረጃ ላይ መሆኑን ራሱ “ተሐድሶ” አለመረዳቱ ነው፡፡ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመባቸው መነኮሳትና ካህናት በየፕሮቴስታንቱ አዳራሽ ሲጨፍሩ እየታየ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የቅዱሳንን ገድልና ድርሳን እንደልቦለድ የሚቆጥሩ ጋዜጣና መጻሕፈት እንዳሸን እየተሠራጩ፣ ዕቅድና ስልት አውጥቶ እየሠራ መሆኑን ራሱ “ተሐድሶ” በሚዲያዎቹ እየገለጸልን፣ ቤተ ክርስቲያን ከዕለት ዕለት እየተፈተነችበት፣ ከጥቅመኞችና የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው በቤተ ክርስቲያንኒቱ አስተዳደር ውስጥ ካሉ አንዳንድ ግለሰቦች ጋር በማበር አያወካት እየታየ “ተሐድሶ የለም” የሚለው ልፈፋ የዘገየ ስልትና ተራ ማታለያ ከመሆን አይዘልም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የታየው ሌላው አስደንጋጭ ነገር በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት “ተሐድሶ የለም” በሚለው ሐሳብ ተስማምተው በአንዳንድ መድረኮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይህንኑ አስተሳሰብ የሚያጸና አስተያየት ሲሰጡ መታየታቸው ነው፡፡ እነዚህ አካላት ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም የችግሩን መኖር አምኖ፣ አሳማኝ ማስረጃዎች ቀርበውለት ውግዘት ማስተላለፉን ዘንግተውና በተለያዩ ዘመቻዎች “ተሐድሶ” ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚወረውረውን ፍላጻ ከምንም በመቁጠር የ”ተሐድሶ” ሴራ ታይቶ እንዳልታየ፣ ተሰምቶ እንዳልተሰማ ሆኖ በምእመናን እንዲታለፍ በመቀስቀሳቸው ብዙዎችን ከማሳዘናቸውም ባለፈ ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡ እነዚሁ ወገኖች ሐሰትን ሊነግሩን እውነትንም ሊደብቁን የፈለጉበት ምክንያት በሂደት ግልጽ እየሆነ የሚሔድ ሆኖ ሁሉም አካላት ግን የእነዚህን ወገኖችና የመሰሎቻቸውን አቋም እንዲያጤኑ ማኅበረቅዱሳን መልእክት ለማስተላለፍ ተገዷል፡፡

“ተሐድሶ የለም” እያሉ በተለያየ መንገድ ለሚነዙት ማደናገሪያዎች ማብራሪያና ማስተባበያ እንዲሰጥባቸው የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያነሡትን ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ማኅበራችንም ያምንበታል፡፡ እነዚሁ አካላት በዚሁ አቋማቸው የመጽናት ፍላጎት ካላቸው ግን “ተሐድሶ” በአደባባይ በሠራቸው ፀረ ቤተ ክርስቲያን ዐዋጆች፣ ስድቦች፣ በጋዜጣ፣ በመጽሔትና በመጻሕፍት በሚያሠራጫቸው የተደበላለቁ ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮዎች ይስማማሉ ወደሚል መደምደሚያ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በተሐድሶ ላይ የምናደርገውን ዘመቻ የሚያደናቅፍ ለየትኛውም ፀረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ በር የሚከፍት በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና፣ አስተምህሮ እና ሥርዐት በመቆም ችግሩን በመቅረፍ ሂደት ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የድርሻውን ለመወጣት ያለውን መንፈሳዊ ቅናት ምን ጊዜም ይገልጻል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ማኅበር ሆኖ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተቋቋመበት ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ነው፡፡ የአገልግሎቱ መገለጫ ደግሞ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲሁም ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ካልቻልን የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን ወዴት አለች? በመሆኑም የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የያዙትን “ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” የሚለው የቅዱሳን መሓላ በእኛና በሁሉም አማኝ ክርስቲያን ደም ውስጥ ማደሩ የግድ ነው፡፡ ስለዚህ በዚሁ ረገድ እውነት እንዲደበቅ፣ ሐሰትም እንዲነገር የሚወዱ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን መገሰጽ፣ መምከርና ከአባቶች ጋር በመመካከር አስፈላጊውን ክርስቲያናዊ እርምጃ በየደረጃው መውሰድ የሁሉም የክርስቲያን ወገን ግዴታ ነው፡፡ በመሆኑም “ተሐድሶ” በሚል ሥያሜ በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን የረጅም ጊዜ ዕቅድና ስልት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ለመፈታተን፣ አስተምህሮዋንና ሥርዐቷን ለመናድ በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እና ዕቅድ እየተደረገ ያለው ዘመቻ ያለና ተጨባጭ እውነታ እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን ከመሬት ተነሥቶ ያወራው አለመሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን በአጽንኦት ያሳስባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡- ሐመር 19ኛ ዓመት ቁ.3 ሐምሌ 2003 ዓ.ም
‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ››

No comments:

Post a Comment