Tuesday, August 9, 2011

የዚህ መልስ ግን ለአባ ጳውሊ አልመጣለትም



     አባ እንጦንስ አባ ጳውሊን ሊጠይቀው በሄደ ጊዜ አባ ጳውሊን ‹‹ እስኪ ይህ ሥርዓተ ምንኩስና ከእኔ በኋላ ይቀራል ወይስ ይቀጥላል የሚለውን ከእግዚአብሔር ጠይቅልኝ›› አለው፡፡ አባ ጳውሊም በጸሎት እግዚአብሔርን ጠየቀለት፡፡ ከጸሎቱም በኋላ የአባ ጳውሊ ገጽ በደስታ ተሞላ፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ ምን አየህ›› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ጳውሊም ‹‹ ነጫጭ ርግቦች አንተ እየመራኻቸው በጠፈር ላ ሲሄዱ አየሑ›› አለው፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ ምንድን ናቸው›› ሲል ጠየቀው፡፡ ‹‹ በቆብ የምትወልዳቸው ንጹሐን ጻድቃን መነኮሳት ናቸው›› አለው፡፡
      አባ እንጦንስም ‹‹ እስኪ ደግመህ አመልክትልኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ በድጋሚ ሲጸልይ የአባ ጳውሊ ፊቱ በሐዘን ተሞላ፡፡ ‹‹ምነው›› ሲል አባ እንጦንስ አባ ጳውሊ ጠየቀው፡፡ በክንፋቸው ላይ ጥቁር መልክ የጠቀላቀለባቸው ርግቦች አየሑ አለው፡፡ እነዚህ ደግሞ ምንድናቸው ሲል አባ እንጦንስ ጠየቀ፡፡ ጽድቅና ሐጢአት እየቀላቀሉ የሚሰሩ መነኮሳት ናቸው አለው፡፡ እስኪ ለሶስተኛ ጊዜ አመልክትልኝ አለና ለመነው፡፡ ኣባ ጳውሊም ጸለየለት፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ጳውሊ ድምጹን ከፍ አድርጎ ጮኾ አለቀሰ፡፡ አባ እንጦንስም ምነው ምን ሆንክ አለው፡፡ እንደ ቁራ ጠቁረው አየኋቸው ሲል መለሰለት፡፡ ምንድን ናቸው ቢለው ሹመት ፈላጊዎች፡ ገንዘብ የሚወዱ፡ ጠዋት ከመኳንንቱ ጋር ለማዕድ የሚቀመጡ ኃጥአን መነኮሳት ናቸው አለው፡፡ አባ እንጦንስም ንስሐ ሳይገቡ በሞት እንዳይወስዳቸው እስኪ ለምንልኝ አለው፡፡ የዚህ መልስ ግን ለአባ ጳውሊ አልመጣለትም፡

No comments:

Post a Comment