Sunday, August 7, 2011

ማመንዘር-የኅሊና ካንሰር

በንጉሡ ጊዜ ነዉ፤ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፡፡ ዐራት ኪሎ አሁን መቅደሰ እግዚእ (በተልምዶ ባለወልድ እየተባለ) በሚጠራዉ ቤተ ክርስቲያን የዐመታዊ በዓሉ ዕለት የተገኙት ንጉሡ ታቦት ወጥቶ መዘምራኑ ወረቡን እያቀረቡ ሳለ በዕለቱ ሊያስተምሩ ወደ ተገኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ (የትግራዩ ታላቁ አቡነ ዮሐንስ)‹‹ቤተ መንግሥት እንግዳ ስላለብኝ የዛሬዉን ትምህርት ያሳጥሩት›› ብለዉ መልእክት ይልካሉ፡፡ ጳጳሱም ‹‹እኔ አጭር ትምህርት የለኝም፤ አጭር ትምህርት ላለዉ ይስጡት›› ብለዉ ለንጉሡ መልእክት ይልካሉ፡፡ መልእክቱን የሚያደርሰዉ ወታደር ግን ከአቡነ ዮሐንስ የተቀበለዉን ለንጉሡ እንዳያደርስ ፈርቶ እንዳይጣሏቸዉም ተጨንቆ መልእክቱን የተቀበሉት እንዲመስልለት ዝም ብሎ እቦታዉ ይቆማል፡፡ ሁኔታቸዉን በርቀት ሲከታተሉ የነበሩት ንጉሡ ግን ያሉትን ንገረኝ ብለዉ ያስገድዱታል፡፡ መልሱ በተነገረቸዉ ጊዜም ንጉሡ ‹‹ይህን ልሰማ ነዉ የላኩህ በል ሒድና ምንም እንግዳ የለብኝም ትምህርትዎን ልብዎ እንዳሰበ አድርገዉ በሰፊዉ ያስተምሩ ብለዋል ብለህ ንገራቸዉ›› ብለዉ መልሰዉ ይልኩታል፡፡ እርሱም እንደታዘዘዉ ይፈጽማል፡፡ጳጳሱም እንዳሰቡት ያስተምራሉ፡፡ ይህ ታሪክ ንጉሡ ካህናቱ ለእግዚአብሔር ወይም ለእምነታቸዉ ያላቸዉን ቁርጥ ኅሊና እና አምላካቸዉን በዚህ ዓለም ክብር እና አድር ባይነት ይለዉጡታል፣ ለጥቅም ያመነዝሩበታል ወይስ ኅሊናቸዉን ለአምላካቸዉ እንደሰጡ ከዚህ ዓለም የእበላ ባይነት ዝሙትና የእከብር ባይነት ማመንዘር ይጠብቁታል? የሚለዉን የለኩበት አንድ አጋጣሚ እንደሆነ በጊዜዉ በነበሩ ሰዎች በአድናቆት ይተረክላቸዋል፡፡በርግጥም ማመንዘር ከሥጋዊ ሩካቤ በላይ ማንነትን (personality) የሚያሳይ የኅሊናችን መጠን አንድ መገለጫ ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ታላቁ አባት አቡነ ዮሐንስም በንጉሡ ምርመራ ከዚህ የኅሊና ደዌ (ከፍርሃት፣ ከአልተገባ ይሉኝታና ከመጥፎዉ ቫይረስ ከአድርባይነት)ነጻ መሆናቸዉ ተረጋገጠ፡፡ ሁሉም ግን የአመንዝራነት ዋና መገለጫዎች ናቸዉ፡፡
ለመሆኑ የማመንዘር ቀጥተኛ ትርጉም ምንድን ነዉ ልንልም እንችላለን፡፡ ከምሳሌ ተነሥተን እንመልከተዉ፡፡ ሕግ እና ትእዛዝ እየተወራረሱ ጥቅም ላይ ቢዉሉም ከመሠረቱ የተለያዩ እንደሆኑ የግእዝ ሊቃዉነት ይናገራሉ፡፡ ሕግ አታድርግ አታድርግ የሚለዉን ከልካዩን አንቀጽ ሲያመለክት ትእዛዝ ደግሞ አድርግ አድርግ የሚለዉን አዛዥ አንቀጽ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ በአማርኛዉ መጽሐፍ ቅዱስ ዉስጥ አንዱ ሌላዉን እየወከሉም ተተርጉመዋል፡፡በማኅበረሰቡ ዘንድ ደግሞ የልዩነታቸዉ ምልክት ለመኖሩም ማስረጃ ማግኘት የሚቻል አይመስልም፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ማመንዘር፣ መሴሰን እና መዘሞትም የሚወራረሱ፣ በተለምዶ አንዱ ሌላዉን እየተኩ የሚጻፉና የሚነገሩ ነገር ግን የተለያዩ አሳቦችን የሚወክሉ ቃላት ናቸዉ፡፡ ዝሙት በገቢር የሚፈጸመዉን ሕገወጥ ሩካቤ ሲያመለክት መሴሰን ግን በትዳር ዉስጥም ሊፈጸም የሚችልና ከሰብኣዊነት የወጣዉን ወይም የማይጠበቀዉን ግንኙት ሁሉ የሚያመለክት ቃል ነዉ፡፡ ማመንዘር ደግሞ ከእነዚህ ሁሉ በተጨማሪ የሚያሳየን መልእክት አለ፡፡ ማመንዘር በጉልሁ የአንድን ሰዉ በአሳብ ወይም በኅሊና የሚፈጸመዉን ፍትዎትና ያልተገባ ምኞት ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል›› የሚለዉ የዝሙትን ምንነት በግልጥ ያስረዳል/ማቴ 532/፡፡ ‹‹በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል››/ያዕ 55/ ከሚለዉ ደግሞ ሴሰኝነት በርግጥም ምን እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለ ማመንዘርም ‹‹አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል ይህስ እስከ መቼ ነው?››/ኤር 1327/ የሚል ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ ሦስቱም በየራሳቸዉ የቆሙ ታላላቅ አሳቦችን እንደሚወክሉ በቀላሉ መገንዘብና መረዳት ይቻላል፡፡
ስለዚህ ማመንዘር በኅሊናችን ዉስጥ ያለዉን ማንኛዉንም ያልተገባና ነፍስን ሚያረክስ አስተሳሰብና ድርጊት ከነፍሳችን ጋር ሚፈጽመዉ ጋብቻ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ ሰዎች ሥልጣንን፣ ገንዝብን፣ ክብርንና የመሳሰሉትን በተሳሳተ መንገድ ለማግኘት የሚተገብሩአቸዉ ሒደቶች ሁሉ ማመንዘር እንደሆኑ ተገልጽዋል፡፡ቅዱስ መጽሐፍም በኅሊና ዉስጥ ያለ አስተሳሰብ መሆኑን ‹‹ ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና›› /ማቴ 15 19/ ሲል መስክሮልናል። ከዚሁ በማስከተል ‹‹ አታመንዝር እንደተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል›› /ማቴ 5 27/ የሚለዉም ማመንዘርን በግልጥ እንድናየዉ የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡
እሥራኤል እግዚአብሔርን ትተዉ ለባዕድ አምላክ ወይም ለጣዖት የሚፈጽሙት ድርጊት በብዛት የተገለጠዉ በዝሙትነቱና በምንዝርነቱ ነዉ፡፡‹‹ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የምንዝርናን ስፍራ፣ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ ሠራሽ፡፡ በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል፤ በየአደባባዩም ከፍ ያለዉን ቦታሽን አድርገሻል ፡፡ ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ ሆነሻል›› /ሕዝ 1624/ ሲል ነቢዩ ሕዝቅኤል የገለጸዉ እሥራኤላዉያን የሚፈጽሙትን የአምልኮ ዉስልትና የሚያሳይ ነዉ፡፡ በነቢዩ ኤርምያስም ‹‹አስጸያፊ ሥራሽን፥ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል ይህስ እስከ መቼ ነው?›› /ኤር 13 27/ ተብሎ ተጽፎአል፡፡በተለይ በዚህ ጥቅስ እንደምንመለከተዉ ማመንዘር በጊዜዉ የነበሩ እሥራኤላዉያን እግዚአብሔርን በማምለክ ስም የሚፈጽሟቸዉን የማታለልና የማጭበርበር ድርጊቶች ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ማመንዘርን በትክክል እንረዳዉ ካልን እዉነተኛ በሆነዉ ሕይወትና ሥራ ዉስጥ እዉነት መስሎ የሚፈጸም ለጊዜዉ የሚያስደስት የሚመስለን ነገር ግን ሰዉንም የማይጠቅም እግዚአብሔርንም የሚያሳዝን ድርጊት ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ከነዚህና ከሌሎቹም ጥቅሶች ማመንዘር ምን እነደሆነ ከተረዳን መገለጫዎቹን እንመልከትና እናጠቃልለዉ፡፡
ማመንዘር በዝሙት፣ በሥልጣን፣ በአምልኮና በመሳሰሉት የሚፈጸም ኃጢኣት እንደመሆኑ መጠን ለሦስቱም የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡
ከሩካቤ ሥጋ ጋር ለሚገናኘዉ ምንዝር ጌታችን በወንጌል ከተናገረዉ የተሻለ መገለጫ የለዉም፡፡ በዐይን የተመለከቱትን ሰዉ እያሰቡ በመኝታ ጊዜ የሚፈጸመዉን በኅሊና በማዉጣትና በማዉረድ ከተመለከቱት ሰዉ ጋር እንደተኙ ማሰብ ነዉ ማመንዘር የተባለዉ፡፡በዚህ አስተሳሰብ ዉስጥ ያለ ሰዉ አስተያየቱና አነጋገሩ ይለወጣል፡፡ ልቡ ያለዉ ሌላ አሳብ ላይ በመሆኑም እንኳን ሰዉ መልአክ ተገልጦ ቢያናግረዉም አያስተዉልም፡፡ ይቅነዘነዛል፣ ይነጫነጫል፣ ለሚጠይቁትም የተስተካከለ መልስ መስጠት አይችልም፡፡ አስተያየቱም ሆነ አነጋገሩ፣ እንዲሁም ሌላዉ ድርጊቱ ሁሉ መለዋወጥ ይጀምራል፡፡ አመንዝራ ሰዎች ልባቸዉ አርፎ አይተኛም፤ የያዙትንም ነገር መጨረስ አይቻላቸዉም፡፡ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸዉ›› /1 ጴጥ 214/ሲል እንደ ገለጸዉ ምንዝራቸዉ በዐይናቸዉና በሚያባብል ቁልምጫቸዉ በደንብ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የስካር መንፈስ እንዳልተለየዉ ሰዉ ካገኙት ጋር ያጣላቸዋል ወይም በሽታ የያዛቸዉ ያህል ይታመማሉ፡፡ እንዲህ ያለ ለብ ያላቸዉ ሰዎቸዉ በጊዜዉ ከሚሰማቸዉ ስሜት የተነሳ ማንኛዉንም የሚወዱትን ነገር ሁሉ ሊጥሉ ይችላሉ፡፡ በዚህ በሽታ ከተለከፉት አንዱ የነበረዉ አምኖን የአባቱን ልጅ እህቱን ትእመርን ወድዶ ብዙ ጊዜ አእምሮዉን አጥቶ ቆይቶአል፤ እሥራኤልም በጉዞ ላይ እንዳሉ ለምድረ ርስት ሳይበቁ የቀሩት በዚሁ በሽታ ናላቸዉ ዙሮ ነዉ፡፡
የሥልጣን ምንዝር ደግሞ ምልክቱ ለየት ይላል፡፡ የሥልጣን ምንዝር የሚባለዉ በአንድ ሀገር ወይም ተቛም ዉስጥ ያለዉ የአስተዳደር ጉድለት፣ የሀገር እድገትና የኅብረተሰቡ የሕይዎት ለዉጥ ግድ በሎአቸዉ ራሳቸዉን ሰዉተዉ ቢያንስ የአቅማቸዉን ለማድረግ የሚታገሉትን የሚመለከት አይደለም፡፡የሥልጣን ምንዝር በተሿሚዎች ወንበር፣ መኪና፣ አለባበስ፣ ፕሮቶኮል አንዳንድ ጌዜም ለራስ ከሚሰጥ ተሳሳተ ግምትና ከዚሁ ከማይለየዉ የዝና በሽታ ወይም እንዲሁ ለሹመት ብቻ ከመጎምጀት የሚመጣ በሽታ ነዉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች እነርሱ በኃላፊነት ካልተቀመጡ ሌላዉ ሁሉ አቅመ ቢስና ወንጀለኛ እንደሆነ ከማዉራት አይመለሱም፡፡አንዳንዶቹን ደግሞ የተቀመጠባትን ሳልቀመጥባት፣ ሳላስጎበድደዉ፣ ሳላሰግደዉ፣ ሳላነቀጠቅጠዉ፣ የሚሉትን የሚያዘምር ትልቅ ፍትዎት አለባቸዉ፡፡ በዚህ ምንዝር ዉስጥ ያሉ ሰዎች የሚጎመጁለት ወንበር ላይ የተቀመጠዉ ሰዉ ያለበትን ሓላፊነትና የሚጠበቅበትንም ለዉጥ የሚያስብ አእምሮ የላቸዉም፡፡ ይልቁንም በየዕለቱ የሚያዩት የሚለብሱትን ሱፍ፣ያደረጉትን ጫማ፣የመሳሰለዉን የሚያስቡትም ዝናዉን ወንበሩን ብቻ ነዉ፡፡እንዲህ ያሉ ሰዎች ዐይናቸዉን እንደ ማይክሮስኮፕ ዙሙን እያጠበቡና እያሰፉ መንጥረዉ የሚመለከቱት የአለባበስንና የአካሔድን ነገር ስለሆነ አእምሮአቸዉ ስለ ሓላፊነትና ስለለዉጥ ትግበራ የሚቀበልበትን የዕዉቀት መስኮት እንደዘጉት ይኖራሉ፡፡ እዉነት እንነጋገር ከተባለ በእኛ ሀገር የንጉሡን ክብር አግብተዉ ከተቀመጡበት ሓላፊነት በሚቃረን ካልተሰገደላቸዉ የተጠሉ የሚመስላቸዉ ሰዎች እስካሁን ድረስ አሉ፡፡ አንዳንዶቹማ ባሉበት ተቛም ዉስጥ የሚዘጋጅ በዓል እንኳ ካለ በንጉሥ ፕሮቶኮል አቀባበል ካልተደረገላቸዉ የበዓሉ ትርጉምም ሆነ ሥነ ሥርዓት የተበላሸ ይመስላቸዋል፡፡ከተሾሙት ደግሞ ያልተሾሙት ይብስባቸዋል፡፡ በተለይ ሥልጣኑን የሚያገኙት ከመሰላቸዉ የሚፈልጉት ወንበር ላይ የተቀመጠዉን ሰዉ ማጣጣልና ማናናቅ ዋና መገለጫቸዉ ነዉ፡፡ እንደሰዉ ሁኔታ እያዩ ማንኛዉንም የተንኮል ሥራ በመሥራት ጊዜያቸዉን ያሳልፋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ብቻ በብልህነት የተሻሉ ለመምስል የማስመሰል ሥራ ይሠራሉ፡፡ የእሥራኤል ንጉሥ የነበረዉ የዳዊት ልጅ የአቤሰሎም ግብር ይህን የሚያመለክት ነዉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዉ የተቀበለዉ በመሰለዉ ጊዜ በአባቱ ላይ ተነሣሥቶ መፈንቅለ ሥልጣን አድርጎ ነበር፡፡እንዲህ ያለዉ ሰዉ ጥንቱንም ፍላጎቱ ሥልጣን ስለሆነ የፈለገዉን የሚያገኝ ከመሰለዉ ልክ እንደ አቤሴሎም ለአባቱም ቢሆን አያዝንም፡፡ በሥልጣን ምንዝር ዉስጥ ያለዉ ሰዉ ደግሞ የሓላፊነትን ምንነት እንኳ የማያዉቅና በታላቅ ቀርቶ በታናሽ ሓላፊነትም ሠርቶ የማያዉቅና ቀረቤታም የሌለዉ ከሆነ ደግሞ በኅሊናዉ ያለዉ ያዉ የክብሩና የጥቅሙ ፍትዎት ብቻ ስለሆነ በሽታዉ ይጸናበታል፡፡ የመሾም ዕድል ከገጠመዉ ደግሞ ሀገር ወዮላት ያሰኛል፡፡በመጽሐፍም ‹‹ በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፤ ዐራተኛዉንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም፡፡ ባሪያ በነገሠ ጊዜ፣…›› /ምሳ 30 22/ ተብሎ የተጻፈዉ መደቡን ለመግለጽ ሳይሆን የቤተ መንግሥት አገልጋይ የነበረ ሰዉ ቢነግሥ እርሱ የለመደዉ መስገዱን መታዘዙን እንጂ አሰተዳደሩን ስላልሆነ የሚፈጽመዉ ጥፋተዉ ታላቅ ይሆናል፤ ከታላቅነቱም የተነሣ ምድር ትጨነቃለች የተባለዉ ለዚህ ነዉ፡፡ የሥልጣን ምንዝር ሀገር ካላጠፋ ማን ያጠፋ?
ሦስተኛዉና ሌላዉ ምንዝር በሃይማኖት ሰዎች የሚፈጸመዉ ምንዝር ነዉ፡፡ ይህ ምንዝር ዘማ ሴት ወንድ፣ ወይም ዘማ ወንድ ሴት እንዲለዋወጡላቸዉ እንደሚፈልጉት ሁሉ አማኞችም በአመኑበት ነገር መጽናት ሲሳናቸዉ፣ ወይም ጾሙ ጸሎቱ ሲከብዳቸዉ፣ ካለበለዚያም በሌላ ምክንያት ሀብት ንብረት ሥልጣን ማግኘት የሚቻላቸዉ ሲመስላቸዉ በአምላካቸዉ ላይ ያመነዝራሉ፡፡ በመጽሐፍ ‹‹ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ›› /ሕዝ 16 15/ ተብሎ የተጻፈዉ የሃይማኖቱን ምንዝር የሚመለከት ነዉ፡፡ ምክንያቱም በመጣዉ በሔደዉ የፖለቲካ ርእዮት፣ በባለሥልጣኑ ፍላጎትና ጥቅም ወይም ደግሞ በየዘመኑ ፍልስፍናና አኗኗር እየተሳቡ በሃይማኖታቸዉ የማይጸኑት ሥርዓተ ቤተ ክርስጢያናቸዉን የሚረሱት ሁሉ እነዚህ አመንዝራዎች ይባላሉ፡፡እሥራኤል ብዙ ጊዜ በዚህ ተወቅሰዋል፡፡ነቢዩ ኤርምያስም ‹‹ አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል ይህስ እስከ መቼ ነው?›› /ኤር 1327/ እያለ የወቀሳቸዉ በዚሁ ግብራቸዉ ነዉ፡፡የዚህ መገለጫዉም በራስ እምነት ያሉትን የድኅነት ትእዛዛት መናቅ፣ ማቅለልና ለራሥ ሠልጥኛለሁ የሚል ሽንገላ በመስጠት የከበዱትን ሁሉ አያስፈልጉም እያሉ ማጥላላት ነዉ፡፡
በአሁኑ ጊዜም ምንዝርና በሦስቱም ዘርፍ ይታያል፡፡ አንዳንዶቻችንንማ እግር አዉጥቶ ሊሔድብን ምንም አልቀረዉ፡፡ በሦስቱም ዓይነት ግን ማንነታችን እስክነረሳ ድረስ ያቅበዘብዛል፡፡በሦስቱም ዘርፍ በሽታነቱ የኅሊና ነዉ፡፡ ከርሱ ከተነሣ በኋላ ግን እንደ ካንሰር መላ ማንነትን ያረክሳል፡፡ ልክ እንደ ካንሰርም በፍጥነትና በጊዜዉ ካልታከሙት ሊድን የሚችል አይደለም፡፡ ፍጻሜዉም ማንነታችንን አጥፍቶ በኅሊና ሞት መግደል ነዉ፡፡ነቢዩ ሆሴዕ ‹‹እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል ደምም ወደ ደም ደርሶአል›› /ሆሴ 42/ ሲል እንደተናገረዉ ምንዝር ብቻዉን አይኖርምና ሁለንተናን በሌሎች የኅሊና በሽታዎችም ይገድላል። ስንቶቻችን ከዚህ ትልቅ የኅሊና በሽታ አምጭ ቫይረስ(ስግብግብነት) ነጻ እንሆን ይሆን? እንደ ትልቁ አቡነ ዮሐንስ ነጻ መሆናቸዉን የሚያረጋግጡ ባይጠፉም በአሁኑ ጊዜ ያለዉ ሰዉ ግን በብዙ ይጠረጠራል፡፡ እስኪ እንመርመርና ለሁሉም ይለይልን፡፡ ተመርመሩ፣ ተመርመሩ፣ ተመርመሩ፤ የሚባለዉ ኤች አይ ብቻ አይመስለኝምና እስኪ አበሾች እንመርመር፡፡
በብርሀኑ አድማስ

No comments:

Post a Comment