Thursday, May 17, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ስድስተኛ ቀን ውሎ ሪፖርታዥ

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሎጋችንን ለማንበበብ ይህን ሊንክ ይጠቀሙ

ከደጀ ሰላም፤ ግንቦት 9/2004 ዓ.ም
·ኮሚቴው ፍጹም ውግዘት የሚገባቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች ለይቷል - ማኅበረ ሰላማ፣ ማኅበረ በኵር፣ የምሥራች አገልግሎት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት፣ አሸናፊ መኰንን፣ አግዛቸው ተፈራ፣ ጽጌ ስጦታው እና ግርማ በቀለ ይገኙባቸዋል።
·“ሃይማኖቴ እንደ አባቶቼ ነው” ያሉት የአባ ሰረቀ እና “የቅን ልቦና የመንፈሳዊና የፈውስ አገልግሎትን ያቋቋምኹት ልጆቼን የማበላቸው ስለተቸገርኹ ነው” ያሉት የ‹ሊቀ ካህናት› ጌታቸው ዶኒ ጉዳይ ያለውሳኔ ሐሳብ ለምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ቀርቧል።
·አባ ጳውሎስ ከጥንተ አብሶ ጋራ በተያያዘ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና እንዲመሰክሩ ሊጠየቁ ይችላሉ።

·ሊቃውንት ጉባኤው ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጎለት ያልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ዛሬ ጠዋት የሊቃውንት ጉባኤውን ሰብሳቢ በእጅጋየሁ በየነ አማላጅነት ሲለማመጥ ታይቷል፤ ሊቃውንት ጉባኤው “በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ኢየሱስና ዲያቢሎስ ቁማር ተጫወቱ . . . ዲያቢሎስም በጨበጣ ገባ” የሚለውና ሌሎቹም ጥንቃቄ የጎደላቸው ንግግሮቹ ፍጹም ውግዘት የሚገባቸው እንደኾኑ አመልክቷል።
·የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አመራርና መዋቅር ይሻሻላል፤ በጠቅላላ ጉባኤና በቦርድ ይመራል፤ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር እንደሚኾኑ ተጠቁሟል።
·የማኅበራት መመሪያ ረቂቅ ለውይይት ቀርቧል፤ አሁን ባሉበት አኳኋን ከቀጠሉ “ሌላ ሲኖዶስ ይኾናሉ፤ የፖሊቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይኾናሉ፤ በቀኝ ዘመምና ግራ ዘመም አቋም ቤተ ክርስቲያኒቷን ይውጣሉ/ይከፍላሉ” የሚል ስጋት የቀረበባቸው ማኅበራት ንብረት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ተጠቃልሎ እንዲተዳደር ሐሳብ ቀርቧል፤ የመመሪያውን ረቂቅ በጥንቃቄ የተመለከቱት የምልአተ ጉባኤው አባላት ጉዳዩ በይደር እንዲታይ አድርገዋል።

(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 9/2004 ዓ.ም፤ May 17/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በግንቦት 8 ቀን 2004 . ስድስተኛ ቀን ውሎው በፕሮቴስታንት ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት ለማፋለስ፣ ሥርዐተ እምነቷን ለመለወጥ፣ አገልጋዩንና ምእመኑን ለመከፋፈል በቡድንና በድርጅት ኾነው በመንቀሳቀስ ላይ ስለሚገኙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች የተዘጋጀውን ሪፖርት አዳምጧል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ በአጀንዳ . (13) ላይ ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በተመለከተው ርእሰ ጉዳይ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ከሊቃውንት ጉባኤ ጋራ በመኾን የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምረው የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርቡ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ኮሚቴ ሠይሞ ነበር፡፡

በወቅቱ የኮሚቴው አባላት እንዲኾኑ ተመርጠው የነበሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስና ብፁዕ አቡነ ያሬድ ነበሩ፡፡ ጥቅምት 20 ቀን 2004 . ከተሠየመው ከእኒህ የኮሚቴው አባላት መካከል ሦስቱ (አቡነ ናትናኤል፣ አቡነ ቄርሎስ እና አቡነ እንድርያስ) በተለያየ ምክንያት መቀጠል ስላልቻሉ ቋሚ ሲኖዶሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስንና ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስን ተክቷል፡፡

ኮሚቴው ከሊቃውንት ጉባኤው የቀረበለትና መርምሮ በትናትናው ዕለት ከቀትር በኋላ በጸሐፊው በኩል ለቅዱስ ሲኖዶስ በንባብ ያሰማው ሪፖርት ባለ 60 ገጽ ሲኾን በዛሬው ዕለት ምልአተ ጉባኤው በሪፖርቱ ላይ በመወያየት የውሳኔ ሐሳቡን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርቱ በፕሮቴስንታንት ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው ኦርቶዶክሳውያን መስለው በሁሉም የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ እና የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ በመሰግሰግ ፕሮቴስታንታዊ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ከሚንቀሳቀሱት ማኅበራት መካከል በስምንቱ ላይ ያተኮሩ የኅትመት ውጤቶችን፣ የድምፅ እና ምስል ማስረጃዎችን መርምሯል፡፡

የፕሮቴስታንት እምነት ተቋማት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያላቸውን የመሠረተ እምነት /ዶግማ/ ልዩነት /ድንበር/ አጥፍተው ቤተ ክርስቲያናችንን በቁጥጥር ሥር አውለው ባለችበት ፕሮቴስታንታዊ ማድረግ ወይም ቤተ ክርስቲያናችንንየጦርነት ቀጣና በማድረግ እንደ ሕንድ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት መክፈል ዓላማ ያላቸው ማኅበራቱ በአሁኑ ሰዓት በሚያወጧቸው መጻሕፍትና መጽሔቶች እንዲሁም በራሪ ወረቀቶች የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በግልጽ ይቃወማሉ፤ አገልጋዩና ምእመኑ በማይመች አካሄድ እንዲጠመድ እና በዘረኝነት እንዲከፋፈል ጭምር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህም በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ በመኾኑ ፍጹም መወገዝ ያለባቸው ማኅበራት ተለይተው ቀርበዋል፡፡

ከእኒህም ውስጥ ኮሚቴው ፍጹም ውግዘት እንዲተላለፍባቸው የውሳኔ ሐሳብ ከቀረበባቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራት መካከል፡-

1. ማኅበረ ሰላማ - በክልል ትግራይ ፍትሕ ቢሮ ተመዝግቦ ፈቃድ ባወጣበት ስሙ ማኅበረ ሰላማ ምትሕግጋዝ ማኅበር (Abune Selama Self Help Association) እየተባለ የሚጠራና ዋና /ቤቱ መቐለ የሚገኝ ነው፡፡ ባወጣው ፈቃድ መሠረት በልማት ሥራ ላይ መሳተፍ ሲገባው ከሕገ ወጥ ባሕታውያንና ሌሎች የተሐድሶ ማኅበራት ጋራ በመቀናጀት ‹‹በገዳማት ላይ ጥናት ማድረግ›› በሚል ሰበብ በቅርሶች ላይ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ ማንነትን ለማጥፋትና በአቋራጭ ለመክበር ይንቀሳቀሳል፤ ዘረኝነትን ያስፋፋል፡፡ የአሲራ መቲራው ገዳም አበምኔት ነኝ ባዩ አባ ገብረ መድኅን ገብረ ጊዮርጊስ ከማኅበሩ መሪዎች ጋራ በድብቅ በመገናኘት ዕቅዱን ለማስፈጸም ይንቀሳቀሳል፡፡

2. ማኅበረ በኵር - 1983 . የተመሠረተ ሲኾን መሥራቹ 1953 . ከቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተባረረው መሠረት ስብሐት ለአብ ነው፡፡ ከምሥረታው ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በፕሮቴስታንቶች ድጋፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሌሎች የተሐድሶ ኑፋቄ ማኅበራት ‹‹አርኣያችን ነው›› ይሉታል፡፡ ጮራየተሰኘ መጽሔት ያሳትማል፡፡ መጽሔቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለሰንበት /ቤቶችና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ግባኤያት ይልካሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትአግዛቸው ተፈራ የተባለው በዋና አዘጋጅነት በሚሠራበት መጽሔት የጸሎት መጻሕፍትን ይቃወማሉ፤ አባቶችን ይዘልፋሉ፤ አዋልድ መጻሕፍትን አይቀበሉም፤ ‹‹ቅዱሳት ሥዕላት አያስፈልጉም›› ይላሉ፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም አማላጅ ነው›› ሥልጣነ ክህነትን አይቀበሉም፤ የእምነት ልዩነት ድንበርን ያፈርሳሉ፤ ‹‹ቅዱስ ቍርባን መታሰቢያ ነው፤ ውላጤ ኅብስት የለም›› ይላሉ፤ ምስጢረ ሜሮንን ይቃወማሉ፤ ‹‹ሥጋ በተዋሕዶ የባሕርይ አምላክ አልኾነም›› ይላሉ፡፡

3. የምሥራች አገልግሎት - 1990 . የተመሠረተና አሸናፊ ሲሳይ በተባለ ግለሰብ የሚመራ ሲኾን ‹‹ቤተ ክርስቲያን የውጊያ ቀጣና ናት›› በማለት ለእንቅስቃሴው የሚረዱ 34,000 ‹‹እርሾዎችን›› በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመሰግሰግ ከፍተኛ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ የሚደረግለት፣ እያንዳንዳቸው 100 - 160 አባላት ባሉት ኅቡእ ቡድን (Cell based) የሚንቀሳቀስ አካል ነው፡፡ ‹‹ፕሮቴስታንት እና ኦርቶዶክሳውያን በመሠረተ እምነት አንድ ናቸው›› ከሣቴ ብርሃን ከተባለው ድርጅት ጋራ አንድ ዐይነት ዓላማ ያራምዳል፤ የክርስቶስን አምላክነት በአግባቡ አያምንም፤ ምንኵስናን ይቃወማል፤ አዋልድ መጻሕፍትን አይቀበልም፡፡

4. አንቀጸ ብርሃን - ከሰበታ መካነ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት /ቤት ተለይቶ የወጣው አሸናፊ መኰንን የሚያሳትማቸውን የኑፋቄ መጻሕፍት ያስተዋውቃል፡፡ በሌላ ስያሜው ራሱን ‹‹ማኅበረ መንፈስ ቅዱስ›› እያለ ይጠራል፡፡ ‹‹የኢ////ያን እምነትና ሥርዐት የጠበቀ መንፈሳዊ ጽሑፍ›› በሚል በኅቡእ በሚያሰራጫቸው ጽሑፎቹ ምሥጢረ ሥላሴን አፋልሶ ያስተምራል፤ ምስጢረ ሥጋዌን በማፋለስ ቅብዐትን ይሰብካል፤ በካህን ፊት የሚደረግ ኑዛዜን ይቃወማል፡፡

5. የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር - በኑፋቄያቸው ከማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰንበት /ቤት የተሰናበቱ ተወግዞ የተባረረው የሃይማኖተ አበው ማኅበር ሰለባዎች ነው፡፡ አቶ መስፍን በተባለ ግለሰብ ይመራል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ወደ ፕሮቴስታንትነት መቀየራቸውን ሳያውቁት ሃይማኖታቸውን የሚያስክዱ የርቀት ትምህርቶችን ይሰጣል፤ ኅትመቶችን ያሰራጫል፤ ቤተ ክርስቲያንን በግልጽ ይዘልፋል፤ የሥጋ ወደሙን አማናዊነት አያምንም፡፡

6. የእውነት ቃል አገልግሎት - ድርጅቱ ይህን ስያሜ ከመያዙ በፊት በመጀመሪያ BGNLJ (Brothers Gathered Unto Lord Jesus) በኋላም (Bible Truth Ministry) እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ መሪ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ማኅበረሰብ ብርታት የተባረረው ግርማ በቀለ ነው፡፡ ሌላው ተጠቃሽ ግለሰብ ሥዩም ያሚ የሚባለው ነው፡፡ ድርጅቱ ከእንግሊዝኛ በሚተረጉማቸው መጻሕፍት የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ክፉኛ ያብጠለጥላል፤ በየክልሉ በከፈታቸው ቅርንጫፍ ማከፋፈያዎች ጽሑፎችን በነጻ በማደል፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ታሪክን በማዛባትና በአዋልድ መጻሕፍት ላይ የማይገባ ትችት በመሰንዘር አገልጋዮችን ያደናግራል፡፡

የድርጅቱ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ መቀየር እንደ ኾነ ከኅትመቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ከፕሮቴስንታን ኮሌጅ የተመረቁ መናፍቃንን ቀጥሮ በደብረ ዘይት፣ ጅማ፣ በደሌ፣ ጎባ፣ ወናጎ፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ፣. . .ወዘተ በከፈታቸው ቅርንጫፎች የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን ሥራ እንዲያቀላጥፉ ያደርጋል - በራሪ ጽሑፍ ማሰራጨት፣ የርቀት ትምህርት መስጠት፣ ወደ ገዳማት እና አድባራት ተመሳስሎ በመግባት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተመሳስሎ በመስረግ በጎችን ለመንጠቅ እየተሯሯጠ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ የሚያስፋፋቸው ኑፋቄዎች ‹‹ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ ለአንድ ሺሕ ዓመት ይነግሣል›› ይላል፤ ‹‹ወልድም መንፈስ ቅዱስም አማላጆች ናቸው›› ይላል፤ አጽዋማትን ይቃወማሉ፤ ሥልጣነ ክህነትን አይቀበሉም፤ የቅዱሳንን አማላጅነት አይቀበሉም፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት›› በሚል ስያሜ የሚጠራውና ነሐሴ 10 ቀን 1996 . በፍትሕ ሚኒስቴር ተመዝግቦ በአዲስ አበባ ገርጂ /ቤት ከፍቶ ኑፋቄ የሚያስፋፋ፤ በደሴ፣ ከላላ፣ ጎንደር፣ ጎጃም እና ደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ /ቤቶች ከፍቶ በሚንቀሳቀሰው ማኅበር ላይ (የቦርድ ሰብሳቢው / ሙሉጌታ ደምሴ ይባላል) የቀረቡት ማስረጃዎች ተጠናክረው ምርመራው እንዲቀጥል ኮሚቴው ሐሳብ አቅርቧል፡፡

በተለይም የዚህ ማኅበር አባል እንደ ኾነ የሚታወቀውና ‹‹በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን?›› በሚል ርእስ የኑፋቄ መጽሐፍ የጻፈውመጋቤ ጥበብሰሎሞን ጥበቡ ፍጹም ውግዘት ከሚገባቸው ግለሰቦች መካከል እንደኾነ የኮሚቴው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት በግለሰብ ደረጃ ከተዘረዘሩት መካከል፡-
1. ጽጌ ስጦታው - ቅዱስ ሲኖዶስ በነገረ ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ስሕተት መፈጸሙን አጣርቶ ጥያቄና መልስ ሲያካሂድበት ‹‹ተሳስቻለኹ፤ ልመለስ›› በማለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በቀን 29/11/2003 . በቁጥር 4560/136/90 በጻፈው ደብዳቤ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የሐዲሳት መምህር አባ ገብረ ኢየሱስ ዘንድ ልኮት ከጓደኛው ጋራ በፈጸመው ተመሳሳይ ጥፋት ከገዳሙ የተባረረ ነው፡፡



ግለሰቡ ከቀድሞው በባሰ እኵይ ተግባር ተጠምዶ ይገኛል፤ የራሱን ድርጅትና ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አቋቁሞ ንግዱን በሃይማኖት ስም እያጧጧፈ ‹‹ይቅርታ አድርጉልኝ›› ያላቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እያንቋቋሸና እየዘለፈ ይገኛል፡፡ ከብዙ ኑፋቄው መካከል ‹‹ይነጋል›› በተሰኘው መጽሐፉ ‹‹እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት፤ ተኣምረ ማርያምን የጻፉት ፀረ - ወንጌሎች ናቸው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመነ ሁሉ ካህን ነው፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግራቸው የተቆረጠው በጦርነት ነው፤ በቅዱሳን ስም መዘከር አግባብ አይደለም፤…›› እያለ ይወሸክታል፡፡

በሌሎችም ጽሑፎቹ የመነኰሳትን ክብር አቃሏል፤ ‹‹ደርግ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ቴዎፍሎስን በመግደሉ ሲኖዶሱ ተስማምቶበታል›› በማለት ምእመኑ በሲኖዶስ ላይ ያለው እምነት ለመሸርሸር ሞክሯል፡፡ ‹‹ለታቦት፣ ለመስቀል እና ለሥዕል መስገድ፤ የጾም መብዛት፣ በሕግ በኾነ ጋብቻ በተወሰኑ ቀናት ከሩካቤ ሥጋ መከልከል በሕዝቡ ላይ የተጫነ የአማራ ቀንበር ነው፤›› ይላል፡፡

2. አሸናፊ መኰንን - አንቀጸ ብርሃን በሚል ስያሜ በሚያሳትመው መጽሔት ለአብነት ያህል ‹‹በእኛ ቤተ ክርስቲያን አምላክነቱን አጉልቶ የሰውነቱን ቅርበት መዘንጋት፣ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሥጋውን ቅርበት አግንኖ የመለኮቱን ክብር መርሳት የተለመደ ነው፡፡ መጽሐፉ ግን ያቻችለዋል፤›› የሚሉና የመሰሉ በርካታ ክሕደቶችን ጽፏል፡፡
በመመሪያ ሓላፊ ደረጃ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና መዝገብ ቤት ሓላፊ ከኾነችውና ሙሉ ወንጌልቤተ እምነት ከምታዘወትረው / ዐጸደ ግርማይ ጋራ ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው ይነገራል፡፡ በወ/ እጅጋየሁ በየነ አማካይነት በፓትርያሪኩ ልዩ /ቤት መሽጎ በበዓለ ሢመት፣ በዐበይት በዓላት፣ በደቀ መዛሙርት ምረቃ መርሐ ግብሮች ላይ በፓትርያሪኩ ስም የሚተላለፉ መልእክቶችን እስከ መጻፍ መድረሱ ይነገርለታል፡፡

3. ደረጀ ገዙ - በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያየ ደረጃ ኑፋቄውን ሲያራምድ ከቆየ በኋላ ሲነቃበት ወደ አዲስ አበባ ተዛውሮ በከሣቴ ብርሃን የተሐድሶ ድርጅት ውስጥ በዋና /ቤት ተቀጥሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ በድብቅ ለካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ደባትራንና መዘምራን በተከራየው ቤትና ‹‹በሰሜን ምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት /ቤት›› ሥልጠና ሰጥቷል፤ ከኑፋቄዎቹ መካከል ‹‹ጽዮን የሚለው ስም ከእመቤታችን ጋራ ዝምድና የለውም፤ የተራራ ስም ነው፤ ለቅዱሳን ይኹን ለመላእክት ስግደት አይገባም፤ ለቤተ ክርስቲያን ስግደት ይገባል ማለት ክርስቲያን ለኾነው ሁሉ ይሰገድለት ማለት ነው፤ እንደ ኦሪታውያኖች የዕጣን ጭስ እንድንወዝውዝ አልታዘዝንም፤›› በሚል ግልጽ ድፍረት በዐውደ ምሕረት በድፍረት ተናግሯል፤ በመጽሐፍ ጽፏል፡፡ በውስጥ አጋፋሪዎቹ እየተረዳ እርሱም ባለቤቱም መናፍቅ መኾናቸው እየታወቀ 27/09/98 . በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሥርዐተ ተክሊል›› ፈጽሟል፡፡

4. በዛ ስፍርህ - ከቤተ ክርስቲያናችን ኮሌጅ ተመርቆ በባሕር ዳር ከሣቴ ብርሃንየኑፋቄ ተልእኮውን ሲወጣ ከቆየ በኋላ አሁን ወደ ሱዳን መሻገሩ ይነገርለታል፡፡ ደቀ መዝሙር በዛ በሚል ስም ‹‹መቅደስ የገቡ መናፍቃን›› በሚል ርእስ ከደረጀ ገዙ ጋራ በጻፈው የክሕደት መጽሐፍ ከላይ የተገለጹትን ኑፋቄዎች ከመናገሩም በላይ ‹‹የጥንታዊቷ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ›› በማለት የቤተ ክርስቲያንን መብት በመጋፋቱ በሕግም ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡

5. ግርማ በቀለ - ከጽጌ ስጦታው ጋራ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመለወጥ ሲሯሯጥ ተደርሶበት የተባረረ ነው፡፡ ከኑፋቄው መካከል ‹‹ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቲያኖች ተሰብስበው አምልኮ የሚፈጽሙበት ቦታ አይደለም፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ በእውነተኛዪቱ መቅደስ አገልጋይ ነው፤ አሁንም ይማልዳል፤ እንደ ሊቀ ካህንነቱ ከዚያ ኾኖ ቤተ ክርስቲያንን ያስተዳድራል፤ ኢየሱስ ሊቀ ካህን ከኾነ እኛ ሁላችን ካህናት ነን፤ እንደ ወረቀት ይቆጠር የነበረው ሰሌዳ ታቦት ተብሎ አሁን ወደሚገኝበት ደረጃ ተሸጋግሯል፤. . .›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

6. አግዛቸው ተፈራ - በአሰላ ከተማ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ሰንበት /ቤት የነበረ፣ በነፋቄ መርዝ ከተነደፈ በኋላ በሰንበት /ቤቱ ትጋትና በሰበካ ጉባኤው ጥብቅ ክትትል ተጋልጦ አልመለስ በማለቱ የታገደ ነው፡፡ የክሕደት ትምህርቱን ‹‹የተቀበረ መክሊት›› ‹‹የለውጥ ያለህ›› ‹‹ጥላና አካል››. . .በተባሉ መጻሕፍቱ ያሰራጫል፡፡ ከጥር 2002 . ጀምሮ የመናፍቃኑ ማኅበረ በኵር መጽሔት የኾነው ጮራ መጽሔት ዋና አዘጋጅ በመኾን ተቀጥሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ከኑፋቄው ጥቂቶቹ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጉባኤ ኒቂያና ቁስጥንጥንያ ከረቀቀው የእምነቷ መሠረት ከኾነው ጸሎተ ሃይማኖት ውጭ ሌሎች ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች ስላሏት የአስተምህሮ ለውጥ ያስፈልጋታል፤ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀል ያልተገባ ክብር ሰጥታለች፤ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አምልኮተ ዕፀ መስቀልን በቤተ ክርስቲያን እንዳስፋፉ የእርሳቸውን ሥራ ዕውቅና ለመስጠት 2000 . ቤተ ክርስቲያኗ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳዘጋጀች ሲተች ይታያል፤ በዓለም ላይ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታቦት እንደሌለ ይታወቃል፤ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ብቻ እንጂ ኦሪትንና ወንጌልን በአንድ ላይ እንድታስኬድ የታዘዘችበት ኹኔታ ፈጽሞ የለም፤. . .›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

7. መጋቤ ጥበብሰሎሞን ጥበቡ - ‹‹በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን?›› በሚል የኑፋቄ መጽሐፍ የጻፈ ሲኾን ‹‹የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት›› አባል ነው፡፡ በማኅበሩ ላይ የሚደረገው ተጨማሪ ክትትል እንደተጠበቀ ኾኖ ይህ ግለሰብ ግን ራሱን ችሎ ፍጹም ውግዘት እንዲተላለፍበት ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ /ቤት በኩል ለሊቃውንት ጉባኤው በቀረበው የሰነድ ማስረጃ .(8) ላይ የተመለከተው በጋሻው ደሳለኝ በሪፖርቱ እንደተመለከተው ሊቃውንት ጉባኤው ለጥያቄና መልስ ተደጋጋሚ ጥሪ በቃልና በጽሑፍ ቢያደርግለትም ጥሪውን አክብሮ ባለመቅረብ አጉራ ዘለልነቱን በድጋሚ አረጋግጧል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ለሠየመው አካል ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው በጋሻው ግን በሃይማኖቱ ሕጸጽ ዙሪያ የቀረበው ሪፖርት በትናንትናው ዕለት አጀንዳ ኾኖ እንደሚታይ ከውስጥ ተባባሪዎቹ ባገኘው መረጃ ይመስላል ገና በጠዋቱ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ቅጽር ከተፍ ብሏል፡፡ በጋሻው በቅጽሩ በራፍ ላይ ደርሶ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ከኾኑት መጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን ቆሞ እንደተነጋገረ በአቅራቢያው የተከታተሉ ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ለደጀ ሰላም ተናግረዋል፡፡ የበጋሻው ንግግር የልምምጥ ቃና ያለው ‹‹በእንተ እጅጋየሁ›› ዐይነት ተማጥኖ ነበር፡-


በጋሻው ጠየቀ - ‹‹/ እጅጋየሁ ልከውኝ ነው፤ አልነገርዎትም?››
መጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን - ‹‹ከሌላ ነገር ጋራ አታገናኘው፤ ንጹሕ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው››

ከቀትር በኋላ በቀረበው የኮሚቴው ሪፖርት ግን በጋሻው የተላከበት የወ/ እጅጋየሁ ሞገስና በመጋቤ ምስጢር ዓምደ ብርሃን ምላሽ ውስጥ ግልጽ ኾኖ የወጣው የትእዛዝ መልእክት አልነበረም የተሰማው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ጠባይ የሌለው በጋሻው በተለያዩ ጊዜያት እጅግ ጥንቃቄ በጎደለውና ድፍረት በተሞላበት ኹኔታ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ያስተምር ስለነበር ብዙ ሕዝብ አሳስቷል፡፡ አባቶችን ከመዝለፍ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ክብር በማዋረዱ ቀርቦ ሊጠየቅ ይገባው ነበር፡፡

በተለይም ‹‹ሳንጠነቀቅ መንፈስ እንዳቀበለን/እንዳዘዘን እናስተምራለን›› በሚለው የዘወትር መርሑ ‹‹በአንድ ወቅት በራስ ቅል ኮረብታ ላይ ክርስቶስና ዲያቢሎስ ቁማር ተጫወቱ፤ የቁማሩ አሸናፊ በሰው ልጆች ልብ ላይ ዙፋኑን ዘርግቶ ለዘላለም ይነግሣል፤ ይህ ሲኾን ተስማምተው ጫዋታውን ለመጀመር ያላቸውን ሲያስይዙ ዲያብሎስ ብልጣብልጥ ቢጤ ነበርና በጨበጣ ገባ(የሚያስይዘው ሳይኖረው) ክርስቶስ ግን የዋህ ነበርና የሚያስይዘው ቢያጣ ቅድስት ነፍሱን በአደባባይ አስያዘ፡፡ በመጨረሻ ግን በነፍሱ የተወራረደው ጌታ ጨዋታውን በርግጥ አሸነፈ፤›› እያለ ለተናገረው መልስ እንዲሰጥ ይፈለግ ነበር፡፡ የስብሰባው ምንጮች እንዳሉት ኤሽታኦል /2001 ./ በተሰኘው መጽሐፉ ገጽ 30 ላይ የሰፈረው ይኸው ቃሉ የሚያስጠይቀው እንደኾነና ተጠርቶ አለመቅረቡ ጭምር ከግምት ተወስዶ ውሳኔው በምልአተ ጉባኤው ደረጃ እንዲተላለፍ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታ 131 የአዲስ አበባ ሰንበት /ቤቶች አንድነት በአባ ሰረቀ እና ጌታቸው ዶኒ ላይ ባቀረቧቸው ማስረጃዎች የግለሰቦቹ የሃይማኖት ሕጸጽ መመርመሩን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

አባ ሰረቀ በሰሜን አሜሪካ ሳሉ ‹‹እመቤታችን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ከኃልዮ፣ ከነቢብ ከገቢር የለያት፣ የጠበቃት ስትኾን የአዳም በመኾኗ /እንደመኾኗ/ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፍ ከነበረው የውርስ ኃጢአት ግን የተለየች እንዳልነበረች፤ ከዚህ የውርስ ኃጢአትም መንፈስ ቅዱስ አንጽቶና ቀድሶ የእግዚአብሔር ቃልን/ወልድን/ ለመቀበል ዝግጁ አደረጋት›› ከሚሉ ወገኖች ጋራ በመተባበር ‹‹እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት›› እንደሚሉ ነበር የሰነድ ማስረጃ የቀረበባቸው፡፡
በመስከረም ወር 1997 . በዋሽንግተን ዲሲ የደብረ ብርሃን ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በተነሣው የነገረ ሃይማኖት ውዝግብ የአጥቢያው ካህን ቀሲስ አስተርኣየ ጽጌ ‹‹እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአዳማዊ ዘር በኩል ከሚተላለፈው የውርስ ኀጢአት መንፈስ ቅዱስ አንጽቷታል›› ሲሉ የያዙትንና የቤተ ክርስቲያን ያልኾነውን እምነት በመቃወም ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ይህ መናፍቅነት መኾኑን ገልጸው ምላሽ ሰጥተዋል - ‹‹እመቤታችን ከአዳም የውርስ ኀጢአት የነጻችው ከመወለዷ በፊት ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን የምታምነውና የምታስተምረው፡- አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት፣ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሐሣብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት፡፡››

ከጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በኋላ ራሳቸው አባ ሰረቀ ይህንኑ ጉዳይ በታኅሣሥ ወር 2004 . ‹‹እውነትና ንጋት›› በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ መሰል ጥራዝ በቀሲስ አስተርኣየ ጽጌ እና በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ መካከል የተደረገውን ምልልስ ባስረዱበት ክፍል ነገሩን በንጽጽር በማቅረብ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

ይህ ልዩነት ወደ ሊቃውንት ጉባኤና ቅዱስ ሲኖዶስ ተልኮ ውሳኔ እንዲያገኝ በሰሜን አሜሪካ ከነበረው ማኅበረ ካህናት ጋራ በመኾን ኅዳር 16 ቀን 1997 . በጻፉት ደብዳቤ መላካቸውን ለሊቃውንት ጉባኤ ማስረዳታቸው የተነገረው አባ ሰረቀ÷ ‹‹በአባቶቼ ሃይማኖት ነው የማምነው፤ ርእሰ መንበር የኾኑት አባት [አባ ጳውሎስ] እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤ እናንተ የምትሉት የእኔም እምነት ነው፤ በተላከው ደብዳቤ ይኹን በመጽሐፌ የገለጽሁት ያሉትን ሐሳቦች ነው፤ አስታርቃችኹ ንገሩኝ›› በማለት መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡

ንት በተሰማው የኮሚቴው ሪፖርትም አባ ሰረቀ የእነ ቀሲስ አስተርኣየን አቋም በመቃወም እመቤታችን ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈባት መኾኗን እንደሚያምኑ በመመስከራቸው ‹‹ምልአተ ጉባኤው ውሳኔ ይስጥበት›› ማለቱ ተዘግቧል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ የሚያሳልፈው ውሳኔ የሚጠበቅ ኾኖ÷ አባ ሰረቀ የሰበሰቧቸውን ማስረጃዎች በመጽሐፍ መልክ ከማሳተምና በይፋ አስመርቀው የውይይት ርእሰ ጉዳይ ከማድረግ ይልቅ የተጠረጠሩበትን የሃይማኖት ሕጸጽ ለሚመረምረው ኮሚቴ ማቅረብን ለምን አልመረጡም? የሚለው ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

ጌታቸው ዶኒ
ሊቀ ካህናትጌታቸው ዶኒ ከሦስት የእምነት ተቋማት ጋራ የተጻጻፏቸውንና ለአንዳንዶቹም አባል መኾናቸውን የገለጹባቸው ስማቸውንና ሙሉ ፊርማቸውን የያዙ ደብዳቤዎች የእርሳቸው አለመኾናቸውን በመካድ በፊርማና አሻራ ምርመራ እንዲረጋገጥላቸው ለሊቃውንት ጉባኤው ጥያቄ አቅርበዋል - ‹‹አሻራዬ በአባ ዲና ይታይ›› ብለዋል ጌታቸው ዶኒ፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ /ቤት በቁጥር /////8/2000 በቀን 14/01/2000 . ‹‹የቅን ልቡና የመንፈሳዊና የፈውስ አገልግሎት የእምነት ተቋም›› ተመዝግበው የተቋሙ መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ በመኾን በአቃቂ ቃሊቲ / ቀበሌ 02/04 በተከራዩት ግቢ ለኦርቶዶክሳዊ እምነትና ሥርዐት ተቃራኒ የኾነ ነገር ለማራማዳቸው ሲጠየቁም አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል - ‹‹ልጆቼን የማበላው ተቸግሬ ነው፡፡››
‹‹ከጊዜ በኋላ ለቅዱስ ፓትርያሪኩ የይቅርታ ደብዳቤ ጽፌ ሥራ ሰጥተውኛል›› ያሉትሊቀ ካህናትጌታቸው እርሳቸው የጻፉትን የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤና በምላሹ ፓትርያሪኩ የጻፉላቸውን ደብዳቤዎች በማስረጃነት ማቅረባቸው ተገልጧል፡፡

ኮሚቴው በአዲስ አበባ ሰንበት /ቤቶች በኩል 67 ግለሰቦች ከእኒህም ውስጥ በሕይወት ያሉና የሌሉ፣ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የሃይማኖት ሕጸጽ እንዳለባቸው የሚጠረጠሩ ግለሰቦች ሥራዎች ማስረጃዎች መቅረቡን በሪፖርቱ ገልጧል፡፡ ሪፖርቱ አያይዞም የአንዳንዶቹ ስም ዝርዝር ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት /ቤት ተልኮ በአድራሻ ተፈልገው እንዲጠሩ ተደጋጋሚ ጥያቄ የቀረበ ቢኾንም ሀገረ ስብከቱ አግኝቶ ሊያቀርባቸው እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡ በመኾኑም ወደፊት ማስረጃው እየተጠናከረ ምርምራውን ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ከቀትር በፊት በነበረው የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አዲስ አመራርና አወቃቀር ማሻሻያ ላይ ተነጋግሯል፡፡ የአመራርና አወቃቀር ለውጡ ኮሚሽኑ በዐዋጅ ቁጥር 621/2001 እና ደንብ ቁጥር 168/2001 በሚደነግገው መሠረት በዳግም ምዝገባ በሰርቲፊኬት ቁጥር 1560 ‹‹ኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት›› ኾኖ መመዝገቡን ተከትሎ ከሃይማኖት አገልግሎት ጋራ ሳይቀላቀል ራሱን የቻለ የልማት ድርጅት ኾኖ ለመሥራት የሚያስችለው ነው፡፡

በዐዋጁ ላይ የማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄነራል በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኮሚሽኑ በዐዋጁና ደንቡ መሠረት እንደ ልማትና በጎ አድራጎት ተቋም ጠቅላላ ጉባኤና ቦርድ ያዋቅራል፤ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ብዛት 20 ሲኾን የቦርዱ አባላት ደግሞ ዘጠኝ ናቸው፡፡ ከኻያው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ዐሥሩ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ሲኾን የተቀሩት ዐሥሩ ደግሞ ከምእመናን የሚመረጡ ባለሞያዎች ይኾናሉ፡፡

ለማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ ማናቸውንም የሥራ እንቅስቃሴና የኦዲት ሪፖርቶች፣ የንብረት ይዞታ፣ የዓመት ዕቅድና ሌሎችም ተዛማጅ ሰነዶች እያቀረበ ያስገመግማል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውና ቦርዱ ለኮሚሽኑ አመራር በመስጠትና ቁጥጥር በማድረግ ሙሉ ሥልጣን የሚኖራቸው በመኾኑ እንደ ችግር የሚጠቀሰውን የፓትርያሪኩን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡

ኮሚሽኑ 90 በመቶና ከዚያም በላይ ገቢውን ከውጭ የሚያገኝ ሲኾን በአዲሱ አሠራር መሠረት 70 ከመቶ ወጪውን ለፕሮጀክት/ዓላማ ማስፈጸሚያ/ ብቻ፣ 30 ከመቶ ገቢውን ደግሞ ለአስተዳደር ወጪ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጠሪ የኾነው ጠቕላላ ጉባኤው ከተሰበሰበ በኋላ የቦርዱ አባላቱን የሚመርጥ ሲኾን ‹‹የኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ›› የሚለው መዋቅር ቀርቶ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር እንደሚኾኑ ተጠቁሟል፤ የሊቀ ጳጳሱ ምክትል በበጎ አድራጎት ድርጅት ባሕርይን በመገንዘብና በልማት አመራር ብቁ ልምድ ያካበተ ባለሞያ እንደሚኾን ተመልክቷል - ‹‹ስንት ምሁራን ያሏት ቤተ ክርስቲያን እንዴት የጡረታ መውጫ ትኾናለች?›› ብለዋል እርጅና የተጫጫናቸውን የወቅቱን ኮሚሽነር ድክመት የተቹት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፡፡
የአሁኑ ምልአተ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት የሚኾኑ 10 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን የመረጠ ሲኾን እነርሱም፤ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና አሁን የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ኾነው የሚመሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ናቸው፡፡

ፓትርያሪክ አባ ጳውሎስ በየጊዜው ከለጋሾች የሚሰጠውን የኮሚሽኑን የፕሮጀክት በጀት በየምክንያቱ በመጠየቅ ማባከናቸውን በመከላከላቸው የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ፊርማ ተሰርዞ የኮሚሽኑ የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳብ በኮሚሽነሩና በፋይናንስ መምሪያ ሓላፊው ጣምራ እንዲንቀሳቀስ ለአምስት ባንኮች የተለያዩ ቅርንጫፎች ያስተላለፏቸው ትእዛዞችም በዚህ የአመራርና አወቃቀር ለውጥ መሠረት ተቀባይነት እንደማይኖረው ተገልጧል፡፡

በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዙሪያ በመወያየት እስከ አሁን የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ኾነው ሳለ ያልተመለሱትን 283 ቤቶች በማስመለስ ረገድ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ጥረት በአግባቡ አጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቷል፡፡ እስከ አሁን ድርጅቱ 16 ሕንፃዎችን፣ 271 ቤቶችንና 10 መጋዘኖችን ያስተዳድራል፡፡
ተጨማሪ ዜናዎቻችንን ይከታተሉ፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

3 comments:

  1. glorious information thanks a lot. be hold with such like detailed and quick information. i also expect your quickness too. God be with us.

    ReplyDelete
  2. what about begashew ? Sereke ? There is evidence that reveals begashaw is ordinated by pastor melese.
    What about asegid ? Those associations are already out of church .

    ReplyDelete