Thursday, May 3, 2012

ሰበር ዜና - የዋልድባ ገዳም ተመዘበረ!!

  • የገዳሙ ዕቃ ቤት በሮች ተሰባብረው 65,000 ብር ተዘርፏል፤ ሙዳየ ምጽዋት እና የመጻሕፍት መያዣ ሣጥኖች ተገለባብጠዋል፤ አርድእቱ ተንገላተዋል።
  • የማይ ፀብሪ ወረዳ ፖሊስ "እናንተው ራሳችኹ ኾነ ብላችኹ የፈጠራችኹት ችግር ቢኾንስ" በሚል መነኰሳቱን ተዳፍሯል።
  • ሕዝቡ በዛሬማ አቅጣጫ ወደ ፕሮጀክቱ ቦታ መትመሙን እንደቀጠለ ተገልጧል።
(ደጀ ሰላም፤ ሚያዚያ 25/2004 .ም፤ May 3/2012) ከዋልድባ ገዳም ዕቃ ቤት እና የአትክልት ቦታ ይዞታዎች አንዱ የኾነው ማይ ለበጣ ትናንት፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2004 . ሌሊት ማንነታቸው ባልታወቁ ኀይሎች መመዝበሩ ተገለጸ፡፡

የገዳሙ መነኰሳት ለዜና ሰዎች እንደተናገሩት÷ መዝባሪዎቹ ማይ ለበጣ ወደሚገኘው የገዳሙ ዕቃ ቤት የገቡት መንፈቀ ሌሊት ላይ ነው፡፡ ለሁለት ሰዓት ያህል ሥፍራውን ድራሽ አምላኩን እያጠፉ የቆዩት እኒህ አፍራሽ ወራሪዎች አርድእቱንና መነኰሳቱን አግተው ከዕቃ ቤቱ ስድስት በሮች ሦስቱን በመሰባበር ለኑግ መግዣ የተቀመጠውን ብር 65,000 ዘርፈዋል፤ ከቦታው ሞቃታማነት የተነሣ በሜዳው የዕንቅልፍ ዕረፍት ላይ የነበሩትን ዐሥር አርድእት ቤት ውስጥ አስገብተው ከዘጉባቸው በኋላ "የምንፈልገው ሰው አለ" በሚል ፊታቸውን በባትሪ ብርሃን እያዩ አንገላተዋቸዋል፡፡
ስለ ዘራፊዎቹ አኳኋን እንዲገልጹ የተጠየቁት አንድ አባት፣ "ቁጥራቸው 5 - 7 ይሆናሉ፤ በአለባበሳቸው ሚሊሻ ይመስላሉ፤ እንዳንለያቸው ፊታቸውን በጨርቅ ሸፍነውታል፤ ያልከፈቱት ሙዳየ ምጽዋትና መጻሕፍት መያዣ ሣጥን የለም" በማለት አስረድተዋል፡፡
መዝባሪዎቹ ስፍራውን ለቀው ከሄዱ በኋላ ከመነኰሳቱ ለማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር በስልክ በተገለጸው መሠረት ዛሬ ጠዋት ወደ ማይ ለበጣ የመጡት ሓላፊዎች "እናንተው ራሳችሁ ኾነ ብላችኹ የፈጠራችሁት ችግር ቢኾንስ" በሚል መነኰሳቱን መዳፈራቸው ተዘግቧል፡፡
ባለሥልጣናቱ ወደ ማይ ለበጣ በመጡበት መኪና ወደ ወረዳው የፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ ያመሩት ገዳማውያኑ ኹኔታውን በዝርዝር በማስረዳት ማመልከታቸውንና "ጉዳዩን እንከታተለዋለን" የሚል ምላሽ ብቻ ተሰጧቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዋልድባ ገዳም ከቀናበት 485 . ጀምሮ ገዳማውያኑ በተለያዩ ወቅቶች ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ 875 . ዮዲት ጉዲት መነኰሳቱን በሰይፍ አስፈጅታቸዋለች፤ 1277 . ገዳሙ በተተኪ መጥፋት ጠፍ ኾኖ ከቆየ በኋላ 1319 . በጻድቁ አቡነ ሳሙኤል እንደገና ተቋቁሟል፤ 1870ዎቹ ተከዜን እየተሻገሩ በገዳሙ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ይሰነዝሩ በነበሩ ደርቡሾችና ኢአማንያን ምክንያት በተለይም ማይ ለበጣ በኩል አትክልት የሚያለሙ በርካታ አርድእት - መነኰሳት በሰይፍ ማለቃቸውን የገዳሙ ታሪክ ይናገራል፡፡
ታላቁና ጥንታዊው የዋልድባ ገዳም ከሌሎች የኢትዮጵያ ገዳማት የሚለየው በዋናነት በገዳሙ መሬት እህል ስለማይበላበት ሲኾን አትክልትና የሥራ ሥር ተክሎች በብዛት የሚገኙበት ሰፊ መሬት ያለው መኾኑም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ማይ ለበጣ በቁጥር እስከ 30 የሚደርሱ ሰፊና ውኃ ገብ የአትክልት ቦታዎች ይገኛሉ፤ በተለይ በበጋ ወራት የመነኰሳቱ ምግብ የኾነውን ፍራፍሬና ሥራ ሥር ተክሎች በመስኖ የሚያለሙት አርድእት አትክልተኛ ወይም ወንዘኛ ተብለው የሚጠሩ ሲኾን ምግቡን በቋርፍ መልክ የሚያዘጋጁት ደግሞ ተለሽ ይባላሉ፡፡
ይህም ገዳሙ አበው መናንያንና መነኰሳት መቲረ ፈቃድን በማሳየት የሥጋ መሻቱን የዐይን አምሮቱን በልቡናቸው ወስነው ለእግዚአብሔር በመገዛት የሚኖሩበት፣ ሠርተው በሚያገኙት ገቢ የሚተዳደሩበት የሥራ እና የሕርመት ቦታ እንጂ የሰነፎች መጦርያ አለመሆኑን በተግባር የሚመሰክር ነው፡፡
በሌላ በኩል ሕዝበ ክርስቲያኑ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ ጀምሮ ከዓዲ አርቃይ፣ ደባርቅ ዙሪያ እና ዳባት ወረዳዎች ከሚገኙ የሳንቅ፣ ቀላ ወገራ፣ አጅሬ፣ አሳቦ፣ ዳልዲማ፣ ኮታ፣ ድምጦ፣ ጅሮ ሳም፣ ቦዛ፣ አንጓ፣ ቀርነጃ እና ዓሊ ከመሳሰሉት ገጠር ቀበሌዎች የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ወደሚካሄድበት ስፍራ ማቅናቱን እንደቀጠለ የገዳሙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በገዳሙ ላይ ስለሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ሕዝቡ በየሰንበቴው፣ በየማኅበሩ እና በየልቅሶው ሲመክርበት መቆየቱን የሚገልጹት ምንጮቹ÷ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ ሚያዝያ 18 ቀን 2004 . አንሥቶ የሰማው ላልሰማው እያሰማ ከነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ጀምሮ ዲጅኖ፣ ፋጤ ፋስ፣ ገጀራ፣ አካፋ እና ዶማ በመያዝ፣ ደረቅ ስንቁን (ድርቆሽ፣ በሶ፣ ቆሎ) በመጫን በቡድን በቡድን መትመሙን ተያይዞታል፡፡
በማይ ፀብሪ - ማይ ለበጣ በኩል የሚያልፉ መንገደኞች ከአምስትና ስድስት ጊዜያት በላይ መታወቂያ በተደጋጋሚ እየተጠየቁ ጥብቅ ፍተሻ ስለሚካሄድባቸው ሕዝቡ ወደ ፕሮጀክቱ ስፍራ እየወረደ የሚገኘው በዛሬማ በኩል መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዓዲ አርቃይ ወረዳ /ቤት አባላት እና የብአዴን /ቤት ሓላፊዎች የተወሰኑ ተጓዦችን በመኪና ተከትለው ዓሊ በተባለው ቀበሌ (ከዋልድባ ዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ዝቅ ብሎ የሚገኝ) ላይ ደርሰው ያነጋገሯቸው ሲኾን ሕዝቡ "እናንተ አይመለከታችኹም፤ ከእኛ ጋራ መሣርያ መዋረድ ትፈልጋላችኹ ወይ? የእኛ ጥያቄ ገዳሙን ከደፈረውና ካረሰው አካል ጋራ በመኾኑ እዚያው ደርሰን ይህንኑ በዐይናችን አይተን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤" በሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተገልጧል፤ ሓላፊዎቹም መልሰው "ወደ ገዳም የሚኬደው ጦርና ጎራዴ ተይዞ ነው ወይ?" ላሉትም "እናንተስ ገዳሙን እያፈረሳችሁ አይደለም ወይ?" በሚል እንደተመለሰላቸው ተዘግቧል፡፡ ለወረዳው ፖሊሶችም "ግድቡ ቆሞ ቦታው ከተለቀቀ እኛ ሌላ ጠብ የለንም፤ ከእኛ ጎን ሆናችሁ የገዳሙን ክብር ማስጠበቅ አለባችሁ፤" የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል - በሕዝቡ፡፡ ከወረዳው ባለሥልጣናት አንዳንዶቹም "ፕሮጀክቱ ገዳሙን የሚጎዳ ኾኖ ከተገኘ ሁላችን የድርሻችን መወጣታችን አይቀርም፤ ከጎናችኹ እንቆማለን፤" ሲሉ መደመጣቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
በምዕራብ ትግራይ የማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ የሕዝቡ ተመማ ወሬ እንደተሰማ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ሥራውን አቁመው ከአካባቢው ዘወር እንዲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፤ ሥራውም ለጊዜው ቆሟል ተብሏል፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ ትናንት ለቪኦኤ የአማርኛ አገልግሎት ሲናገሩ የሕዝብ ተመማ አለ የሚባለው መረጃ ፈጽሞ የተሳሳተ መኾኑን በማስተባበል የፕሮጀክቱ ሥራ ሌት ተቀን እየተፋጠነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለው የአህጉረ ስብከት አወቃቀር መሠረት የዋልድባ ገዳም አጠቃላይ ይዞታ በሦስት አህጉረ ስብከት ውስጥ ተከፋፍሎ የሚገኝ ነው፡፡
የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳመ ዋሊ ቅድስት ደቂቁ ለሳሙኤል እና የዋልድባ ዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ዓዲ አርቃይ ወረዳ የሚገኙ ናቸው፤ ሊቀ ጳጳሱም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ናቸው፤ ከዋልድባ አብረንታንት ገዳም፣ አባ ነጻ እስከ ዛሬማ ወንዝ ድረስ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት የሚገኝ ሲሆን ሊቀ ጳጳሱም ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ናቸው፤ ከዛሬማ ወንዝ ማዶ የወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ሀገረ ስብከት ሲሆን የገዳሙ ሞፈር ቤቶች ያሉባቸው፣ እርግና የተጫናቸው፣ ከሕመም የተነሣ ቋርፍ የከበዳቸው አባቶች እና ሴት መነኰሳዪያት የሚገኙባቸው ሦስቱ ተነሺ አብያተ ክርስቲያን ያሉባቸው ናቸው፤ ሊቀ ጳጳሱም ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ናቸው፡፡
ግድቡ ከሚሠራበት ዛሬማ ወንዝ በመኪና 30 ደቂቃ፣ በእግር የአንድ ሰዓት መንገድ ርቆ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት /ቤት እና የሠራተኞች መኖርያ ካምፕ (በወልቃይት ጠገዴ ሁመራ ሀገረ ስብከት) ይገኛል፡፡
ዋነኛው የዋልድባ ገዳም ይዞታ የሆነው የአብረንታንት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ቦታ ላይ (ከባሕር ጠለል በላይ 1270 ሜትር) የሚገኝ ሲኾን በግድቡ ውኃ የተነሣ በመጥለቅለቅ ስጋት ውስጥ የሚገኘው የአባ ነጻ አካባቢ ደግሞ በዝቅተኛ (ከባሕር ጠለል በላይ 1073 ሜትር) ላይ ይገኛል፡፡
ዓዲ አርቃይ በኩል ወደ ገዳሙ ሲገባ የዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለምን ለሁለት በመክፈል ሰፊና ለሙን የገዳሙን ክልል በስተቀኝ የያዙት የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት ሲኾኑ በስተግራ ደግሞ የቤተ ጣዕማ መነኰሳት ናቸው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

6 comments:

  1. እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤የሚያስደነግጠኝ ማነው ?
    ክፉዎች፥አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ። ሠራዊትም ቢሰፍርብኝ ልቤ አይፈራም፤ሰልፍም ቢነሳብኝ በዚህ እተማመናለሁ። መዝ ዳዊ. ፳፯፥፩፡፫
    ወገኖቼ ሀይማኖት ለነፍሳችን መጠጊያ፣ ማረፊያ የነጻነታችን መገለጫ ናት። ነገር ግን መንግስት የነፍሳችን ማረፊያ የነጻነታችን አርማ የሆነቺውን ቤታችን ሲያፈርስ እስከመቼ በዝምታ እናያለን? ጊዜው አሁን ነውና በዋልድባ ገዳም ላይ እየተሰራ ያለውን በስሙ ልማት ተብየ እንቃውም። ልብ በሉ ቤተ መቅደስ ወይም ቤተክርስቲያን የጸሎት ቤት እንጅ የንግድ ቦታ አይድለችም። የሰማይ ቤታችንን ይዘጋብን ዘንድ ይሔ መናፍቅ መንግስት ማነው? ለሀይማኖታችን እንታገል!! ክርስቶስ ያለውን ማንስ ያሸንፈዋል!!! የአባቶቻችን ፈለግ እንከተል!!!

    ReplyDelete
    Replies
    1. አነተ/ቺ ጸሀፊ ምን ልማለት ፈልገህ/ሽ ነው፡፡ ምን እናድርግ እያልክ ነው? ምንስ አይነት ተቃዉሞ ማለትህ/ሽነው? ጦርነት ውስጥ እኮ መግባት የለብንም፡፡ መንግስት እስኪረዳንና ሀሳብ ለሀሳብ እስክንግባባ ድረስ በመነጋገርና በመወያየት በጾምና በጸሎትም የእግዚአብሔርን አዳኝነት በመማጸን ልንበረታ ይገባናል እንጂ ስሜታዊነት ሊገዛን አይገባም፡፡ I doubt that if you are not an Orthodox christian don't try to lead us in to unwanted way. You can go your own way because our Lord has said to st.Peter "ሰይፍህን ወደ አፎቱ መልስ ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉና፡፡"

      Delete
  2. ብርሃነ ሕይወትMay 4, 2012 at 2:32 AM

    የቤ/ክ/ችን ሰላም ለሀገራችን ሰላም መሆን ዋና ነው፡፡ የሀገራችን ሰላም መሆን ለቤ/ክ/ችን ሰላም እንዲሁ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ የ3000 ዓመታት ታሪክን ረስቶ፣ አንድነትን ጠብቃ እና ዛሬ ሙሉ ኢትዮጲያን እንዲገዛ ያቆዬች ቤ/ክርስቲያን በምን እዳዋ ይሆን የራሷነን ይዞታ የምትነጠቀው!ግን ሀገር ወይም ንጉስ በሀብት/በሰራዊት በብዛት አይድንም እንዲል መንግስት እዝነ-ልቦናው ይከፈትለት፡፡ ዛሬ በአረቡና በውጪው አለም የምንሰማውና የምናዬው ሰቆቃነና ጦርነት፣ በሀገራችን ቢሆን መልካም አይሆንም!ለቤ/ክርስቲያናችንም ሰላም እንዲሀሁ!ቢሆንም መንግስታችን በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረገ ያለው ስራ እድሜውን የሚያሳጥር እና ለቤተ ክርስቲያን ፈተና ከመሆን ውጪ ሌላ ትርጉም አልሰጠውም፡፡ ይልቁንስ ክርስቲያነን ይነሳል! ይጠነክራል፡፡ እስኪ ፀሎት እንነሳ...

    ReplyDelete
  3. እናንተ ይህ የስኳር ልማት ያገሩ ተወላጅ የሆኑት የወ/ሮ አዜብ መስፍን ነው እንጂ የኢትዮጵያ ንብረት እንዳልሆነ ሲነገር ሰማሁ፡፡ እስኪ ይህንም አጣርታችሁ አስነብቡን እግዚአብሔር አምላክ ልቦናቸውን ቀና እንዲያስብ ይርዳቸው፡፡ ለሃጥአን የወረደ ለፃድቃን ይባለል አሁን አባቶቻችን ለኛ በፀለዩ ምን በደሉ፡፡

    ReplyDelete
  4. እናንተ ይህ የስኳር ልማት ያገሩ ተወላጅ የሆኑት የወ/ሮ አዜብ መስፍን ነው እንጂ የኢትዮጵያ ንብረት እንዳልሆነ ሲነገር ሰማሁ፡፡ እስኪ ይህንም አጣርታችሁ አስነብቡን እግዚአብሔር አምላክ ልቦናቸውን ቀና እንዲያስብ ይርዳቸው፡፡ ለሃጥአን የወረደ ለፃድቃን ይባለል አሁን አባቶቻችን ለኛ በፀለዩ ምን በደሉ፡፡

    ReplyDelete
  5. እናንተ ይህ የስኳር ልማት ያገሩ ተወላጅ የሆኑት የወ/ሮ አዜብ መስፍን ነው እንጂ የኢትዮጵያ ንብረት እንዳልሆነ ሲነገር ሰማሁ፡፡ እስኪ ይህንም አጣርታችሁ አስነብቡን እግዚአብሔር አምላክ ልቦናቸውን ቀና እንዲያስብ ይርዳቸው፡፡ ለሃጥአን የወረደ ለፃድቃን ይባለል አሁን አባቶቻችን ለኛ በፀለዩ ምን በደሉ፡፡

    ReplyDelete