Monday, May 14, 2012

ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፍርድ እና ውሳኔ እንዲሰጠኝ" ቀሲስ ዶክተር መስፍን ተገኝ


ቀን ግንቦት 5 ቀን 2004 ዓ.ም ቁጥር EOTCDC/135/2004
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ጉዳዩ ፦ ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፍርድ እና ውሳኔ ንዲሰጠኝ ስለመጠየቅ

በቅድሚያ የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት የሆናችሁ አባቶቼ ሁሉ ቡራኬያችሁ ይድረሰኝ እያልኩኝ ፤ ለቀደሙት አባቶቻችን እውነተኛ የሃይማኖትን ገድል እንዲፈጽሙ ጽናትንና ትእግሥትን የሰጠ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር እናንተንም በተቀመጣችሁበት ሐዋርያት መንበር ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ዘላቂ ሰላም የሚጠቅም እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ለገጠማትን ዘርፈ ብዙ ችግር መፍትሔ ለመስጠት እንድትችሉ እግዚአብሔር ይርዳችሁ እላለሁ :፡

ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ የተገደድኩት የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል ከሆነው ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ እና ፍርድ እንድጠይቅ የሚያስገድድ ጉዳይ ስለገጠመኝ ነው ። እንደሚታወቀው የቤተ ክርስቲያንን እምነት ሥርዓትና መዋቅር መጠበቅና ማስጠበቅ የሁላችን ግዴታ በመሆኑ ፤እኔም በምኖርበት በሰሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት በተሰጠኝ ኃላፊነት መሰረት የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በመጠበቅ በጽናት የቆሙ የአብያተ ክርስቲያን አቋም እንዲገለጽ በማድረጌ እና ይህንንም መዋቅር ለማፍረስ የተነሱት አቡነ ፋኑኤል የሚያከናውኑት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን የወጣ ተግባራቸው ጋር ተባባሪ ባለመሆኔ የተነሳ በክፋትና በጥላቻ መንፈስ ተይዘው ስም ለማጥፋትና ባይሳካላቸውም በቱሩፋት የማከናውነውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማደናቀፍ ደብዳቤ እስከመጻፍ ደርሰዋል ። ይህ የጥላቻ ተግባራቸው በዚህ አልበቃ ብሎ ለዚህ የክፋት ተግባራቸው ተባባሪ ከሆነው ከኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን እና ከዜና ቤተ ክርስቲያን አዘጋጆች ጋር በመሆን ቤተ ክርስቲያን መሪና ተቆጣጣሪ የሌላት የጥቂት ግለሰቦች መፈንጫ የሆነች በሚያስመስል መልኩ በዜና ቤተ ክርስቲያን እኔን በተመለከተ የተሳሳተ እና በሀሰት ላይ የተመሰረተ ዘገባ እና የስም ማጥፋት ተግባር ተፈጽሟል።

ደሃ እንዳይበደል ፍርድ እንዳይጓደል ታላቅ መንፈሳዊ አደራ የተሰጣችሁ አባቶች ለዚህ ችግር በመንፈሳዊ አግባቡ ከእናንተ የበለጠ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል አካል የለምና ፤ ይህንን የተፈጸመውን በደል ማለትም ሀሰትን መሰረት አድርጎ በአቡነ ፋኑኤል የተጻፈብኝን ደብዳቤ እና አቡነ ፋኑኤልና ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን በዜና ቤተ ክርስቲያን እንዲወጣ ያደረጉት ዘገባ በመመልከት ቅን ፍርድ እንዲሰጠኝ ይህንን አቤቱታ አቀርባለሁ። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በትክክል ጉዳዩን ከመረመረው አቡነ ፋኑኤል በተደጋጋሚ በፈጸሙት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የመተላላፍ ተግባር በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጭምር እየተነገራቸው የባሰ የቤተ ክርስቲያንን ሰላም የሚያናጋ ተግባር ውስጥ መገኘታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ንቀት የሚያመላክት ነው ።

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን ኃላፊነት ለመወጣት ባደረኩት ጥረት የተነሳ ለተፈጸመብኝ በደል አቡነ ፋኑኤል፤ ኃይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ፤የዜና ቤተ ክርስቲያን አዘጋጆች እና ከጀርባ ሆነው ይህ ጥፋት እንዲፈጸም ያደረጉ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲጠየቁና ለተፈጸመብኝ በደል በመንፈሳዊ አግባቡ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጠኝ ሃይማኖታቸው በቀና በኒቅያ በተሰበሰቡ በ318 ሊቃውንት ስም ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ ሰማዕትነትን በከፈሉ በኢትዮጵያን ቅዱሳን ስም እጠይቃለሁ ።

ቀሲስ ዶክተር መስፍን ተገኝ
የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጸሐፊ

ግልባጭ
ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት

1 comment:

  1. "ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፥ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል።"
    ኢሳ.11:4
    But with righteousness shall he judge the poor, and reprove with equity for the meek of the earth: and he shall smite the earth with the rod of his mouth, and with the breath of his lips shall he slay the wicked.
    Isaiah 11:4

    ReplyDelete