ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ጠቀሰው? - - - ዕብ.3:1 “ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ በእብራውያን መልእክቱ ያተኮረው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ማስረዳት ነው፡፡ ይህንንም የሚያስረዳው ደግሞ በንፅፅር ነው፡፡ ከነቢያት ስለመብለጡ የእነሱን ንግግርና የእሱን ንግግር በማነፃፀር አስረዳ፡፡ ከዚያም በኅላ ደግሞ ከመላእክት መብለጡን አስረድቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከካህናት መብለጡን ለማስረዳት ያመጣል፡፡ ከካህናት መብለጡንም ሲያስረዳ ዋናወቹ ምክንያቶች 1) በክህነቱ 2) በመስዋእቱ 3) መስዋእቱ በቀረበበት ድንኳን መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለክህነቱም በ ዕብ.5፡1-10 ፣ በዕብ. 6፡20 ፣ 7፡1-28 ፣ 8፡1-3 ባሉት አስረድቷል፡፡
ክህነት ምንድን ነው? - - - አገልግሎት ሲሆን መሾምን መመረጥን ያመለክታል፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስም ከአዳም ጀምሮ የተለያዩ ሰወች ለዚህ ክህነት በሰውም በእግዚአብሄርም ሲመረጡ ያሳየናል፡፡
መልከ ፄዴቅ ማነው? - - ዕብ.7:3 “አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ይህ ሲባል መልከ ፄዴቅ ሰው አይደለም ማለት አይደለም ፡ ዘሩ ከካም ዘር ነበረና በሙሴ መፃህፍት አልተገለፀም ለማለት ነው፡፡ ይህ የተመረጠ ሰው አፅመ አዳምን እንዲጠብቅ የታዘዘ በብህትውና የሚኖር ነው፡፡ የመልከ ፄዴቅ ክህነትም ሙሴ አሮንን በሾመበት ሥርአት ቅብዕ አፍልቶ ፡ መስዋእተ እንስሳ ሰውቶ ፡ልዩ ልዩ ህብር ያላቸውን አልባሳት አልብሶ የሾመው ሰው የለም፡፡ይልቁንም እግዚአብሄር መረጠው ፡ በማይታወቅ ግብርም ሾመው እንጂ፡፡ አሮንና ልጆቹ በሙሴ እጅ ፡ ሙሴም በመልአኩ እጅ እንደተሾሙ (ሐዋ ፡ 6፡6) መልከፄዴቅ ግን ሹመቱ ከእግዚአብሄር ነውና ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ያለው ለዚህ ነው፡፡ “ለዘላለም” ማለቱም እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ማለቱ ነው፡፡በዚህም ምክንያት ክህነቱ ከሌዋውያን ክህነት ፍፁም የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እንደሌዋውያን ክህነትም የእንስሳት መስዋእት አይሰዋም መስዋእቱ ንፁህ ስንዴና ወይን ነውንጂ፡፡ በዚህም ተነስቶ ቅዱስ ጳውሎስ - - ዕብ.7:11 እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ብሎ ይጠቅሰዋል፡፡
ነገር መልከ ፄዴቅ በእብራውያን - - -
- የሌዋውያን ካህናትን በክህነት ይቀድማቸዋል እርሱ ከአብርሃም በፊት ነበረና --- ዘፍ 14፡18-21
- ክህነቱ ዘላለማዊ ነው - ዕብ 7፡3 ለብዙ ዘመናት በብህትውና እንደኖረና ክህነቱም ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ስላልሆነ ይህ ተጠቅሷል፡፡ የሌዋውያን ክህነት ግን ሞት በየጊዜው አለባቸውና ዕብ.7:23 “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው” እንዲል፡፡
- ሌዋውያንን አስራት አስወጥቷል - - - ሌዋውያን ከህዝቡ አስራትን እንዲቀበሉ ስርአት አላቸው፡፡ ነገር ግን መልከ ፄዴቅ ከአብርሃም አስራትን በተቀበለ ጊዜ ከእነርሱ ክህነት የእርሱ ክህነት እንዲበልጥ ታወቀ፡፡
- ሌዋውያንን ባርኳል - - - እጃቸውን ዘርግተው ህዝቡን የሚባርኩት የሌዋውያን ካህናት በአብርሃም በኩል በመልከ ፄዴቅ ተባርከዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.7:6-7” ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል።ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው።”እንዲል፡፡
- መስዋእቱ የሚሞቱ እንስሳት አይደሉም - - - የሌዋውያን ካህናት መስዋእታቸው ከእንስሳት የሚዘጋጅ ሲሆን የመልከፄዴቅ መስዋእት ግን ከንፁህ ስንዴና ወይን የሚዘጋጅ ነው ፡፡ ይህም የክርስቶስ ስጋውና ደሙን የሚያመለክትልን ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉንም በዚህ ምእራፍ አጠቃልሎ እንዳስቀመጠው ክህነተ መልከፄዴቅ ክህነተ ሌዋውያንን ይበልጣል፡፡ የጌታችን የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክህነት ደግሞ ከመልከ ፄዴቅ ክህነት ይበልጣል፡፡ መልከፄዴቅ ለጌታችን አምሳል ነበርና፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር አባታችሁ አብርሃም አብርሃማዊ ካልሆነው ከመልከ ፄዴቅ የሚያንስ ከሆነ ይልቁንም ከመልከ ፄዴቅ አምላክ ከክርስቶስማ እንዴት አያንስም? የመልከ ፄዴቅ ክህነት ከእናንተ ከተሻለ ይልቁን የጌታማ እንዴታ! መስዋእታችሁ ከመልከ ፄዴቅ ካነሰ ይልቁን እንዴት ከጌታ ትበልጣላችሁ ፣ ለመልከ ፄዴቅ አስራት ካወጣችሁ ለጌታማ እንዴት አብዝታችሁ ማድረግ አይገባችሁ? በመልከ ፄዴቅ ከተባረካችሁ ይልቁንም መስጠትና መንሳት ለእርሱ ብቻ ከሚቻለው ከወልደ እግዚአብሄርማ እንዴት አብልጣችሁ መጠቀም ይገባችኅል ለማለት ተናገረው፡፡አላማውም የጌታን ታላቅነትና የባህርይ አምላክነት በመመስከር ልቆ ከሚልቁት እነርሱንም ያላቃቸው እርሱ መሆኑንና ይህ ስልጣን እንዳለው ለማስታወቅ ነበር፡፡
የጌታችን ክህነት በምን የተለየ ሆነ? - - -
- የባህርይው ስለሆነ - - - ክርስቶስ ሁሉንም ነገር ያደረገው በስልጣኑ ነው፤ ሙትን ያስነሳው ድውያኑን የፈወሰው ፡ ያስተማረው ፡ የሞተው ፡ የተነሳው ፡ ያረገው ፡ - - - በስልጣኑ ነው፡፡ የጌታችን የክህነት አግልግሎት ዋናው ራሱን በመስቀል ላይ መስዋእት አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይሄውም ስጋውን ቆርሶ ፡ ደሙን አፍስሶ ፡ ነፍሱን ክሶ አለሙን የመቀደስና የማንፃት ሞትንና የሞትን አበጋዝ ዲያቢሎስን በሞቱ ድል መንሳቱ ነው፡፡ ይህ ነው የጌታችን ከእርሱ ለእኛ የተደረገልን የክህነት አገልግሎት፡፡ ሞቱ ደግሞ በስልጣኑ እንደሆነ ሞቱን በስልጣኑ ፈፀመው መባሉ ደግሞ ክህነቱ የባህርይው መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ከማንም አልተቀበለውም ፡ ማንምም ከእርሱ አይወስድበትም፡፡ይህም ማለት ባህርይ መለኮቱ ባህርይ ትስብእቱን በተዋህዶ አከበረው እንጂ ሌላ የሚሰጠው እርሱም የተቀበለው የለም፡፡ ስለዚህ እርሱ እንደመልከፄዴቅ በስውር እንደ አሮን በገሃድ የተሾመ አይደለም ፡ እርሱ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለምና፡፡ዮሐ 1፡3 “ሁሉ በእርሱ ሆነ” እንዲል፡፡ ዕብ.5:5 “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው” ሲል የቃልን በስጋ መወለድ ሐዋርያው ተናግሯል፡፡ ይህም በእርሱ ፈቃድ ብቻ ሳይሆነ በአባቱም ፈቃድ መሆኑን ለመናገር ነው፡፡
- ዘላለማዊ ነው - - - “ዘላለም” የሚለው ቃል ለፍጡርና ለፈጣሪ ሲቀፅል አንድ እንዳልሆነ አንባቢ ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህም የመልከፄዴቅ ክህነት ህይወቱ እስኪያልፍ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የጌታችን ክህነት ዘላለማዊነቷ እርሱ ሽረትና ሞት የሌለበት አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ በስጋ ሞተ የምንለውም ነፍሱ ከስጋው ተለየች ለማለት እንጂ ከተዋህዶ በኅላ መለኮትና ትስብእት የተለያዩበት ቅፅበት የለም፡፡ስለዚህ ለክህነቱ ተቀባይ አያስፈልገውም ፡ የባህርይ ክህነትም ከእርሱ በቀር ገንዘብ ሊያደርገው የሚቻለው የለምና፡፡ ዕብ.7:24 “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው” ተብሎ ተፅፏልና፡፡ዕብ.7:24-25 “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” - - - እነዚህ ጥቅሶች ጌታችንን “አማላጅ” ነው በማለት የሚያስተላልፉት መልእክት የለም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት አምነው ሲመጡ የእግዚአብሄር ቤተመቅደስ ሆኑ የሚባሉት በስመ ስላሴ ተጠምቀው የክርስቶስን ስጋና ደም ሲቀበሉ ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስ ስጋና ደም ደግሞ እንደ ኦሪት መስዋእት በአንድ ቀን የሚያልቅ ፡ በጊዜ ብዛት የሚለውጥ ፡ የሚበላሽ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ አዲስና ለዘላለሙ በህይወት የሚኖር ነው፡፡ “ሕያው” መባሉም ነፍስ ስለተዋሃደው ሳይሆን “መለኮት” ስለማይለየው ነው፡፡ - - - ይህ ሕያው ስጋውና ደሙ ሁልጊዜ ሰውን ወደ እግዚአብሄር ሲያቀርብ የሚኖር ከእግዚአብሄርም ጋር የመታረቂያው ብቸኛ መንገድ በመሆኑ አማለደን (አስታረቀን) ሲል ገልፆታል፡፡ “ሊያማልድ በህይወት ይኖራል” የሚለውንም በጥሬ ንባቡ ከሆነ ጌታችን አሁንም በስጋ ህይወት በምድር አለ ያስብልብናልና፡፡
- ፍፁም ነው - - - የሌዋውያን ክህነት ፍፁም አይደለም ፤ የመልከ ፄዴቅም ዘላለማዊ እንጂ (አንፃራዊ) ፍፁም አልነበረም፡፡ ማንንም ወደ ገነት መመለስ አልተቻላቸውምና፡፡ እነርሱም ራሳቸው በአዳም የመጀመሪያ ሃጢአት ተይዘዋልና፡፡ “እርሱ ራሱ ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ” ዕብ 7፡28 ፣ ዕብ 5፡2 ተብሎባቸዋልና፡፡ ለጌታችን ግን ሃጢአት የለበትም ተብሏል፡ 1ኛ ዮሐ3፡5 ከዚህ የተነሳ ክህነታቸው ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 እርሱ ግን ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡ ቆላ.1:19-20 “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።”እንዲል
ታዲያ የጌታችን ክህነት በመልከ ፄዴቅ ክህነት ለምን ተመሰለ?
“የነገር ጥላ አለውና” ዕብ 10፡1 እንደ ተባለ ለሰው ረቂቁን በግዙፉ ፡ የሚታየውን በማይታየው መስሎ መናገርና ማስረዳት የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም እኛ የሰው ልጆች ከህሊናት በላይ የሆነውን እግዚአብሄርን መረዳት የቻልነው በምሳሌ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ ነበር፡፡ በዚህም አንፃር መልከ ፄዴቅ የወልደ እግዚአብሄር ምሳሌው እንጂ ራሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ምሳሌ የሆነውም መልከ ፄዴቅ ብቻ አልነበረም ፦ዮናስ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል ማቴ 16፡4 ፣ ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው እባብ ዮሐ 3፡14 ፣ ሙሴ ዉሃን ያፈለቀበት ዐለት 1ኛቆሮ 10፡1 እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሳሌወችም አሉት፡፡ በመልከ ፄዴቅ የመሰለበት ምክንያትም
የመልከ ፄዴቅ እናትና አባት በእብራውያን ዘንድ የታወቀ እንዳልሆነ የጌታችን ለቀዳማዊ ልደቱ እናት ለደሃራዊ ልደቱ አባት የለውምና
መልከ ፄዴቅ በስንዴ በወይን ያስታኩት ነበረ ፤ ጌታም ቅዱስ ስጋውን በስንዴ ክቡር ደሙን በወይን አድርጎ ሰጥቶናልና
መልከ ፄዴቅ በዚህ ጊዜ ተገኝ በዚህ ጊዜም አለፈ አይባልም ፤ ጌታም በዚህ ጊዜ ተገኝ በዚህ ጊዜም ያልፋል አይባልም፡፡ እና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ጌታችን ስለምን ሊቀካህናት ተባለ?
ከላይ በመልከ ፄዴቅ እንደተመሰለ አሁን ደግሞ በኦሪት ሊቀ ካህናት ተመስሏል፡፡ ስለ ምን? ስለጌታችን ክህነት የመልከ ፄዴቅ ምሳሌነት ያልገለጠው ነገር አለ ፤ ይሄውም አገልግሎቱ ነው፡፡ ጌታችንም ሊቀ ካህናቱን ምሳሌ ያደረገው ከዚህ አገልግሎቱና ከአለቅነቱ አንፃር ነው፡፡ ይሄውም ፦
- ሊቀ ካህናት ከሰው ተመርጦ ለሰው ይሾማል - - - ዕብ.5:1 “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና” እንዲል፡፡ ሊቀ ካህናት ሰው ነው ፡ ከሰው ይመረጣልና የሚሾመውም ለሰው እንጂ ለራሱ ክብር አይደለምና፡፡ ጌታችን ክርስቶስም ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ነው፡፡ የአብርሃም ልጅ የዳዊት ልጅ ተብሏልና፡፡ማቴ 1፡1 ሊቀ ካህናት ስለሰው እንደሚሾም ጌታችንም ሰው የሆነውና ክህነትን ገንዘብ ያደረገው ስለ ሰው ነው፡፡ የሰውን ሃጢአት ለማራቅ ሰው ሆኗልና፡፡ዮሐ.3:16-17 ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” 1ጢሞ.1:15 “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” እንደተባለ፡፡
- ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው ሊቀ ካህናት ብቻ ነው - - - ይህንንም በዘሌ16፡2 የተጠቀሰውን ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.9:6-7 “ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ገልፆታል፡፡ ጌታችንም የገባባት ቅድስተ ቅዱሳን በሰው ያልተተከለች በፈቃደ እግዚአብሄር የሆነች ከእርሱም በፊት ከእርሱም በኅላ ማንም ያልገባባትና የማይገባባት ናት፡፡ ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ ይገባል ፡ እርሱ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ገባ ፤ ለዓለምና ለዘላለም መስዋእቱ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እነዚያ በየዓመቱ የሚገቡት ሟች ስለሆኑ መስዋእታቸውም ሙት ነውና ሌላ አዲስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ዕብ.9:11-12 “ ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ተብሎ ተፅፏል፡፡ ጌታችን የገባባት ድንኳን የተባለችው “መስቀል” ናት፡፡ ድንኳን ያላት የዘላለም መስዋእት የሆነው የጌታ ቅዱስ ስጋ የተቆረሰው ክቡር ደሙም የፈሰሰው በመስቀሉ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚች ድንኳን “አንድ ጊዜ ፈፅሞ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገባ” በማለት ራሱን መስዋእት አድርጎ የወጣበት መስቀል መሆኑን በግልፅ አስረድቷል፡፡ “በሰው ያልተተከለች” ሲልም አይሁድ መስቀሉን ጌታን ለመግደል እንጂ መስዋእተ እግዚአብሄር ይቀርብበታል ብለው ስላልሆነ ነው፡፡ “ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች” ማለቱም በመስቀል ላይ እራሱን መስዋእት ሊያደርግ የሚችል ሰው የለም ፤ ቢኖርም እንኳ ሌላውን ራሱን ማዳን አይቻለውምና ፡ ለፍጥረት ባልሆነች ብሏታል፡፡
- ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መስዋእትን ሊያቀርብ ይሾማልና ዕብ 8፡3 -- -- የሊቀ ካህናት ዋናው አገልግሎት መባንና መስዋእትን ማቅረብ ነው፡፡ ጌታችንም የዓለምን ሃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ የተባለበት ዮሐ1፡29 ራሱን መስዋእት አድርጎ ያቀረበ ብቸኛ ሊቀ ካህን ነው፡፡ ራሱ መስዋእት በመሆኑም ሌላ የሚያቀርበው መስዋእት አላስፈለገውም፡፡ ሁለቱንም አንድ ጊዜ መሆን ይቻለዋልና፡፡ ዕብ.9:12 “የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ዕብ.10:12 “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” እንዲል፡፡ ዕብ.9:26 “- - - አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ዕብ.8:1-3 “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው።” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ “በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን” ሲለን የትሩፋተ ስጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪ በልእልና ሃይል ባለው እሪና የተቀመጠ አስታራቂያችን ነውና ስለዚህ ተናገረ አንድም የዚህ ሁሉ ደገኛ ነገሩ ሊቀ ካህናታችን በልእልና ሃይል ባለው እሪና የኖረው መኖርን ይገልፃል፡፡ “እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” የተባለውበሰው ፈቃድ ያይደለ በእግዚአብሄር ፈቃድ በተተከለች በደብተራ መስቀል ራሱን መስዋእት ፡ መስዋእት አቅራቢውም ራሱ ደግሞም መስዋእቱንም ተቀባይ ራሱ ሆኖ ለቅዱሳን ሲያገለግል ኑሮ ነበር፡፡ የክርስቶስ መስዋእትም “ሕያው” ማለትም ለዘላለም የሚኖር ሲሆን እንደ ሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት አንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ ቶሎ የሚበላሽ ስለዚህም እለት እለት መስዋእት ማቅረብ የሚገባበት አይደለም፡፡ የቀደሙት ሊቀካህናት በሰው በተተከለችው ቅድስተ ቅዱሳን በአመት አንድ ጊዜ መስዋእትን ሊያቀርቡ እንደሚገቡ ያይደለ ለክርስቶስ ግን በእግዚአብሄር በተተከለች ደሙን ባፈሰሰባት ፡ ስጋውን በቆረሰባት ፡ ነፍሱን ካሳ አድርጎ በሰጠባት እውነተኛይቱ መቅደስና ድንኳን በተባለች በመስቀል አንድ ጊዜ ፈፅሞ ገባ ማለት ተሰቀለ፡፡ መስዋእቱን ያቀረበው ክርስቶስ የቀረበው መስዋእት የክርስቶስ ክቡር ስጋው ቅዱስ ደሙ ስለሆነ መስዋእት አቅራቢው እንደሌሎቹ ሊቀካህናት በራሱ ህፀፀ የለበትምና መስዋእቱም የሚበላሽ ፡ የሚሞት ፡ የሚበሰብስ እንደሆነው የቀደመው መስዋእት አይደለምና ነገር ግን ነገር ግን ለዘላለም የሚኖር ክርስቶስ ራሱን መስዋእት አድርጓልና የማስታረቁ ተግባር ፍፁም ነው፡፡ እርሱም ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ይህንን አንድ ጊዜ ፈፅሞ አድርጓልና፡፡ ክቡር ደሙና ቅዱስ ስጋውም ለዘላለም አምነውና በስላሴ ስም ተጠምቀው የሚመጡትን ሰወች ከሃጢአታቸው አጥቦ የዘላለም ህይወትን ሊያወራሳቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ አንድም ዘወትር (አሁንም) መስዋእትን በሰማይ ያቀርባል ካልን እለት እለት በሰማያት ክርስቶስ ወደ እውነተኛይቱ ድንኳን (መስቀል) ይወጣል ማለት ይሆንብናል (ይህም ይሰቀላል ማለታቸን ነው) - - - ደግሞም የክርስቶስ መስዋእት እንደሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት ድካም አለበት ፍፁም አይደለምና አንድ ጊዜ የሰዋው መስዋእት አልበቃውም ማለት ይሆንብናል፡፡ - - - ሌላም ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰዋው መስዋእት ሙሉውን የሰው ልጅ እዳ በደል አላቀለለም ማለት ይሆንብናል፡፡ ይህም ሊባል አይገባም ክርስቶስም አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ሰውን ሁሉ ይቅር ብሏል ፡የማስታረቅንም ተግባር ፈፅሟል በሰማያትም በአባቱም ቀኝ ተቀምጧል ይህም መቀመጡን እንጂ ለአገልግሎት መቆሙን አያሳይም፡፡ ክርስቶስም ለሃዋርያቱ እንደተናገረ ውደ አባቴ የምሄደው አሁን እንዳደረኩ ስለሃጢአታችሁ ላማልድ አይደለም ይልቁንም ልፈርድ እንጂ በማለት ማማለድን በምድር እንደፈፀመው በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጦም የሚፈርድ እርሱ እንደሆነ አስቀድሞ ተናገረን፡፡ ይህንንም ዮሐ.16:26 “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም” ብሎ አስረግጦ ተናገረ፡፡
በአጭር ቃል ጌታችን ሊቀ ካህናት ሊባል የተገባው ፍፁም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ በእውነተኛይቱ ሰው በማይገባባት ቅድስተ ቅዱሳን (መስቀል) አንድ ጊዜ ብቻ ስለገባ ፡ በእርሷም እውነተኛውን መስዋእቱን (ራሱን) ስላቀረበና ሃጢአተ አለምን ስላራቀ ነው፡፡ የቀደመው ክህነት ግን ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 ጌታችን ግን ክህነቱ ”ፍፁም” መሥዋእቱም “ህያው” ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡ ምንጭ፦ “ሁለቱ ኪዳናት” በእብራውያን መልእክት ትርጓሜ ላይ የተመሰረተ
የአብ ፍቅር የወልድ ቸርነት የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment