Saturday, September 17, 2011

የማይታዩ እጆች በቤተ-ክርስቲያን ላይ


by ገብር ኄር   በሙላቱ ደቦጭ

  • አባ ሰረቀብርሃን ወልደሳሙኤል (እምነት ሳይለይ የሚያገለግለው ካህን!)
  • በጅብ ትከሻ የአህያ ሥጋ መጫን መሆኑን ሳያውቁት ከባድ ኃላፊነትን ሰጥተዋቸዋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊት ታሪካዊትና አማናዊት ናት እየተባለ የሚነገረውን እውነት እየበለቱ ማሳየት ብቃቱ ባይኖረኝም እውነታው ግን ቅንጣት ታህል ሳልጠራጠረው የምቀበለው ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊው ታሪክ እንደሚያስረዳን ይህቺ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሁለት አይነት ጠላቶች አሏት ቀለል ባለ አማረኛ ለማስቀመጥ የውጭና የውስጥ ልንላቸው እንችላለን በፋሺሽት ኢጣሊያን ዘመን የሀገሬ አርበኞች ተናገሩት የተባለ ነገር ትዝ አለኝ
ጠላትማ ምንግዜም ጠላት ነው፣
አስቀድሞ መምታት አሾክሿኪውን ነው፡፡
የሚል በወቅቱ ለሀገራቸው አንድነት ለባንዲራቸው ክብር ለሃይማኖታቸው ጽናት እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለጦር፣ ግንባራቸውን ለሀሩር፣ በመስጠት በነፍሳቸው ጨክነው ከጠላት ጋር አንገት ላንገት ይተናነቁ ለነበሩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ለነበሩት አርበኞች ትልቁ ፈተና የባንዳው /የጠላት ቅጥረኛው፣የከዳተኛው/ ጉዳይ ነበርና ይህንን አሉ፡፡ ለማለት የፈለኩት ለአንባቢዎቼ ግልጽ የሆነ ይመስለኛል ከውጭው ጠላት ይልቅ የሚበረታው የውስጥ ጠላት ጡጫ ነው፡፡

      እነዚህ የማይታዩ እጆች ዛሬም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ እስከ መከር ተውአቸው² ተብሏልና፡፡ ነገር ግን በቅሎ እጸዳዳለሁ ስትል ገላዋን /ነዋየ ውስጧን/ ታሳያለች እንደሚባለው በገዛ እጃቸው ሲንፈራገጡ አንዳንዴም ንፁሕ ነን ለማለት /ለማስተባበል/ ሲሞክሩ ከሚያነጥቧቸው ድብቅ አጀንዳዎቻቸው የተነሳ እራሳቸውን እራሳቸው ሲገልጡት ይስተዋላል፡፡
      በዚህ መሠረት ከማይታዩ እጆች አንዱ የሆነውና የተሐድሶ መናፍቃን ቁልፍ ሰው ስለሆነው አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤል በአሁኑ ሰዓት ናቸው፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ ማለት የፈለኩትን ሳይሆን ማለት ያለብኝን ለማለት አሰብኩ፡፡ በቅድምና ሐተታ በማብዛት አንባቢያንን ግራ ማጋባት አልፈልግም በእያንዳንዱ ጉዳይ ከበቂ በላይ መረጃ ስሰበስብ በመቆየቴ በውጭም በሀገርም ውስጥ የአባ ሠረቀብርሃንን የጀርባ ማንነት ወደ ማስታወቁ ልግባ፡-
    አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤል
 አሁን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰ/ት/ቤቶች ማ/መ/ኃላፊ ነው፡፡ይህ ልምድ ሲሆን ከልምዱ ሥር ያለውን አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤልን አብረን እንይ፡፡
      በቅድሚያ አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤል በራሳቸው አንደበት ስለ ራሳቸው የተናገሩትን ላስቀድም እኔ ስለእራሴ የምነግራችሁ አንድ ነገር ብቻ ነው እምነቴን ልነግራችሁ እችላለሁ ፍፁም የኢትዮጵያ ኦ/ተዋህዶ ልጅ ነኝ… እኔ በሰሜን አሜሪካ እሠራ የነበረው የክህነት አገልግሎት ነው …. ዘር አልለይም እምነት አልለይም … ኦርቶዶክሳውያን ከሆኑ በመስቀል እባርካቸዋለሁ እጸልይላቸዋለሁ ፕሮቴስታንት ከሆኑም አገለግላለሁ … ይህ እንግዲህ ሐምሌ 14 ቀን 2001 ዓ.ም መሰናዘሪያ ለተባለ ጋዜጣ የሰጡት ቃለ ምልልስ /interview/ ነው፡፡
አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤል እምነትዎ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አይደለም ሳይባሉ አለመሆናቸው ለራሳቸው ስለሚታወቃቸው ብቻ ሌሎች አውቀውብኝ ይሆን? በሚል ስጋት ለማስተባበል ሲሞክሩ ራሳቸውን እምነት ሳይለይ የሚያገለግል ካህን አድርገውት አረፉት፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ከላይ በተጠቀሰው ጋዜጣ ላይ ሎሳንጀለስ በነበሩበት ጊዜ በመጀመሪያ በአቡነ አረጋዩ ስም ቤተክርስቲያን ከፈትኩ በማለት ቤተክርስቲያንን እንደ ካፍቴሪያ ከፈትኩ ብለው መኩራራታቸው ሳያንስ እኔ በፍጹም የግል ቤተክርስቲያን የሚባል ነገር የለኝም ብለው ይሞግታሉ፡፡ ይህንን ውሃ ምን ያጮኸዋል ቢሉ እውስጡ ያለው ድንጋይ አሉ ይባላል፡፡ አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤልን ምን እንዲህ ያዘባርቃቸዋል ቢባል እውስጣቸው ያለው ….  ነዋ! ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡
ለየተሐድሶ መናፍቃን ማኅበረ ቅዱሳን የተባለውን ማኅበር አጠፋለሁ ሲሉ ቃል እንደገቡና ለዚሁ ማስፈጸሚያ በርከት ያለ ገንዘብ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት እንደገቡ የሚታሙት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደሳሙኤል ሐሜቱን ሲያረጋግጡልን በዚሁ ዙሪያ በመሰናዘሪያ ጋዜጣ ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ አንድ ማኅበር በድንገት ቢፈርስ የዚያን ማኅበር ንብረት ማን ነው የሚወርሰው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አባ ሠረቀብርሃን እንደሚያፈርሱት እርግጠኛ ስለሆኑት ግን ደግሞ ንብረቱ ለማን እንደሚሆን ስላስጨነቃቸው ማኅበር መምጣታቸውን ራሳቸው ያሳብቃሉ፡፡ በጥር ወር 1997 ዓ.ም ከወደ ሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት አንድ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ይጻፋል፡፡ ጉዳዩ እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆነና የኑፋቄ ትምህርትን የሚያወግዝ ነበር፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነበር፡፡
በወቅቱ በሰሜን አሜሪካ ካንሣሥ ሲቲ ውስጥ ለምትገኘው ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አገልጋይ የነበሩት መልአከ ብርሃን አስተርአየ ጽጌ የተባሉ ቄስ ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ /የውርስ (የአዳም) ኃጢአት/ አለባት የሚል ትምህርት በማስተማራቸው ውዝግብ በመነሳቱ በሕዝበ ክርስቲያኑ ጥያቄ መሠረት የክፍሉ ሊቀ ጳጳስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አባቶች ወደስፍራው በመንቀሳቀስ ሕገ ቤተክርስቲያኗ በሚፈቅደው መሠረት ውሳኔ ያሳልፋሉ፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ውሳኔ የሚቃወምና ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት ነበረባት የሚለውን የቀሲስ አስተርአየ ጽጌን አሳብ የሚደግፍ ጉባኤ በዚያው በሰሜን አሜሪካን ይካሔዳል፡፡ ከጉባኤው አባላትም መካከል አባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤል አንዱ ነበሩ፡፡ እንግዲህ ለቅዱስ ሲኖዶስ የተላከው ደብዳቤ የቄሱ የኑፋቄ ትምህርት ማስተማሩ ሳያንስ ትምህርቱ ልክነው ብለው በጉባዔ ወስነው ስለተነሱት ስለእነ አባ ሠረቀብርሃን ጉዳይ ነበር፡፡
ሲኖዶሱ ይህንን የክፍሉን ሊቀጳጳስ ደብዳቤ አይቶ ይወስን አይወስን ባላውቅም አባ ሠረቀብርሃን ግን ከነኑፋቄ ሃሳቡ ጠቅላይ ቤተክህነት መጥቶ ተቀምጦአል፡፡
የዛሬን አያርገውና በአንድ ወቅት የቤተክርስቲያኒቷ ሕጋዊ ወኪል ነኝ ሲሉ የነበሩት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዮኒ ሕዳር 5 ቀን 2002 ዓ.ም በራሳቸው እጅ ጽሑፍ ለአባ ሠረቀ ብርሃን ብለው በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፈው በተነጋገርነው መሠረት ጉዳዩን እየሔድኩበት እገኛለሁ … በእርስዎ በኩል ያለውን ሁኔታና መንገድ ማጠናከር ይጠበቅቦታል ምክንያቱም በርካታ ሰ/ትቤቶችን በመምሪያው ሥር ማግኘት ስለሚችሉ ቤተክርስቲያንን በወጣት ኃይል ነውና ማደስ የሚቻለው ጠንክረን መሥራት እንችላለን …  በማለት የማይታዩ እጅ ሆነው ለተሐድሶ መናፍቃን መሥራታቸውን አሳብቀዋል፡፡
ይህ ብቻም አይደለም አባ ሠረቀ ብርሃን እኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ ነኝ እያሉ የተሐድሶ መናፍቃን የማይታዩ እጅ ከመሆናቸውም ሌላ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ኅብረት ማኅበርን በማቋቋም ይንቀሳቀሱ እንደነበር የመረጃ መስታውቶች አጥርተው ያሳያሉ፡፡
አባ ሠረቀብርሃን ወልደ ሳሙኤል የተሐድሶ መናፍቃን የማይታዩ እጅ ለመሆናቸው አንድ የመጨረሻ ማሳያ ልጥቀስ፡፡ ሰውየው አባ ኃይለ ሚካኤል ተክለሃይማኖት ይባላሉ ቀንደኛ የተሐድሶ መናፍቅ እንደሆኑ አውቃለሁ
በኮምቦልቻ መቅደሰ ማርያም ቤተክርስቲያን  በምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት በተለያዩ አብያተክርስቲያናት በጌዲኦ ዞን ቤተክህነት እንዲሁም በሌሎቹም ሀገረስብከቶችና አጥቢያዎች አየተዘዋወሩ ሲሰሩና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በነበሩበት ጊዜ በኑፋቄ ትምህርታቸው ከየቦታው ሲባረሩ ቆይተው በአባ ሠረቀብርሃን ወልደሳሙኤል ሥር የማደራጃ መምሪያው የሥርዓተ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ በቁጥር 1/1384/99 በቀን 13/11/99 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ተቀጠሩ ምክንያቱን ባላውቀውም ወዲያው ደግሞ ከመምሪያው ተነሱና ሰሜን ሸዋ ስላሴ ሀ/ስብከት እንዲዛወሩ ተደረገ ይኼኔ አባ ሠረቀ ብርሃን ሰውየው መዛወር የለባቸውም ብለው መከራከር ጀመሩ የምን ምስክር ምን² ይባል የለ መከራከርም ብቻ ሳይሆን ከመምሪያው ተነስተው ያሉትን ሰውዬ አባ ሠረቀ ብርሃን የበላዩን አካል በመናቅ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያው የኅትመት ውጤቶች ሥርጭት ሥራን እንዲሠሩ ደብዳቤ ይጽፉላቸዋል፡፡ በኋላም ከጠቅላይ ቤተክህነት ይሁንታ ሲነፈጋቸው ከየሀገረስብከቶቹ ካህናትና ምዕመናን እንዲሁም የየሀገረ ስብከቶቹ አስተዳደር ጉባዔያት በሰውየው ኑፋቄ ላይ እየወሰኑ የላኳቸው መረጃዎች አፍጠው ባሉበት ሁኔታ በኑፋቄው መስመር አጋራቸው ስለሆኑ ብቻ አባ ኃ/ሚካኤልን አባ ሠረቀ ብርሃን በአሜሪካን አገር በሚገኘው የራሳቸው ቤተክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ አድርገው ቀጥረዋቸዋል፡፡
አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ያላሳሳቷቸው ክፍሎች የሉም በአሜሪካን የሚገኙ የዋሃን ምዕመናን በአባ ሠረቀ ብርሃን የጥፋት ገጽታ ብቻ ተታለው ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ ለግሰዋቸዋል፣ቅዱስ ፓትርያርኩም በአባ ሠረቀ ብርሃን ውጫዊ ገጽታ ተማርከው በጅብ ትከሻ የአህያ ሥጋ መጫን መሆኑን ሳያውቁት ከባድ ኃላፊነትን ሰጥተዋቸዋል፡፡ መናፍቃንን እያጋለጠ ሲያስነብበንና ሲያሳየን የቆየው ማኅበረ ቅዱሳንም ቢሆን የመምሪያው ኃላፊ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ የአባ ሠረቀ ብርሃን ኩርኩም ባይቀርለትም የተመሠረተበትን ዓላማ በመዘንጋት ይመስላል ምሥጢሩን ሳይሰወረው እየተሞዳሞደ መሥራቱን ተያይዞታል፡፡ በአንድ ወቅት የመንግስት አካላትንም ጭምር አሳስተው በመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ እስከመሆን የደረሱበትን ሁኔታ አንዘነጋውም፡፡
      በዚህ መሠረት የኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስቲያን በተለይም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተወለደ በሚነገርለትና የጀርመናዊው ማርቲን ሉተር ጽንስ ሀሳብ በሆነው የተሐድሶ /የኑፋቄ አስተምህሮ/ እጅጉን ስትታመስ ቆይታለች፡፡ የቅርቡን ማሳያዎች ብቻ እንኳን ብንጠቅስ ከራሷ ት/ቤት ድርጐ እየተሰፈረላቸው በጀት ተመድቦላቸው ተምረው በረሷ ዓውደምህረት አለቃ ተደርገው በመሾም በሌላም ልዩ ልዩ ክፍሎች በኃላፊነት ቦታ በመቀመጥ ዝም ያሉት ሙጃ ዋርካ ነኝ ይላል እንደተባለው አድራጊና ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ደሞዝ እየተከፈላቸው የማይታዩ እጆች በመሆን ለአጽራረ ቤተክርስቲያን የባንዳነታቸውን ሥራ ሲሠሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ … የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና ባለው መሠረት ጊዜ ጥሏቸው ግብራቸው ገልጧቸው እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ራሳቸው ራሳቸውን አጋልጠው በቤተክርስቲያኒቷ ወሳኝ አካል ተወግዘውና አቶ ተብለው ለመለየት የበቁትን የተሐድሶ መነኮሳት ታሪክ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡

1 comment:

  1. wow how come anybody don't get this,. This is as clear as white...Amlak yitebiken.. How come our church Synod couldn't get the strength to say enough is enough. There will be time for God to clear our church from menafikan...

    ReplyDelete