Wednesday, September 28, 2011

የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ አደጋ በቅኔም ሲጋለጥ



መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ

  • “በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን ስብከተ ወንጌል እንደበረታው ሁሉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክናም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ ትምህርት ተስፋፍቶ መሰጠት ይኖርበታል፤” /መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ በዘመን መለወጫ - ቅዱስ ዮሐንስ የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር ላይ ቅኔያቸውን ሲያብራሩ ከተናገሩት/
  • “በቅኔው ካነሣችሁት አይቀር ስላሉት ችግሮች መናገር እፈልጋለሁ፤ የትኛው እግዚአብሔር ነው ያረጀው? የትኛዋ ቤተ ክርስቲያን ናት ያረጀችው? የሊቃውንቱ ዝምታ ምንድን ነው? አባቶችስ የማይገባ ትምህርት ሲሰጥ ዐውደ ምሕረታችሁን የማትጠብቁት ለምንድን ነው? ዝምድና፣ ጓደኝነት ወይስ ውለታ ይዟችኋል?. . . በ2004 ዓ.ም መሠራት የሚገባው ሥራ ይህችን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ፣ በሚገባ ማስተዳደር ነው፤” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቅኔውን መሠረት አድርገው ከተናገሩት)
(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 17/2004 ዓ.ም፤ ሰፕቴምበር 28/2011)፦፦ መስከረም አንድ ቀን 2004 ዓ.ም በተከበረው የዘመን መለወጫ - ርእሰ ዐውደ ዓመት-እንቁጣጣሽ-ቅዱስ ዮሐንስ በዓልበመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስን እንኳን አደረ ለማለት የሚዘጋጅ ዓመታዊ መርሐ ግብር አለ። በዚሁ በዓል ላይ የዜና ቤተ ክርስቲያንጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆኑት መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ ቀርበው ከሰጧቸው ቅኔዎች መካከል ከፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ የተነሣ ቤተ ክርስቲያናችን አደጋ እንደተጋረጠባት በመጠቆም የሐዋርያ እና ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስን ረድኤት የሚማፀነው አንዱ ቅኔ ዘመኑን የዋጀ ሆኗል።


ይኸው ጉባኤ ቃና ቅኔ እንዲህ ይላል፡-
ዘንስር ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ዕቀባ
ለኦርቶዶክሳዊት ቅድስት እስመ ተሐድሶ ከበባ

መጋቤ ምስጢር መልደ ሩፋኤል ለቅኔያቸው በሰጡት ማብራሪያ፣ “በዚህ ዘመን እንደ ቀደሙት ሊቃውንት ተምሮ መገኘት ያስፈልጋል፤ አሁን ይህ እየታየ አይደለም፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን ስብከተ ወንጌል እንደበረታ ሁሉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመንም [ዘመነ ፕትርክና] ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ ትምህርት ተስፋፍቶ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ተዋሕዶን-ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ እየፈተናት ነው፤” ብለዋል፡፡

በእዚህና በመሳሰሉት የመጋቤ ምስጢር ቅኔዎች መከፋት የሚነበብባቸው አቡነ ጳውሎስም ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች አሻሚ መልእክት የሚያስተላልፍ፣ በአንዳንዶች አገላለጽ ምርቅና ፍትፍት የሆነ ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፤ ይህም በንግግራቸው መካከል ከታዳሚው በተሰማው ጉምጉምታ ግልጽ ሆኗል፤ መጋቤ ምስጢርንም ‹የትኛው ኦርቶዶክስ ነው በተሐድሶ የተከበበው? ቅኔው በአሉባልታ እና ባልተረጋገጠ ወሬ ላይ የተመሠረተ ነው› በሚያሰኝ የቃለ ምዕዳናቸው መንፈስ ሊገሥጧቸው ሞክረዋል፡፡

“በዚህ ዕለት እንኳን አደረሳችሁ ማለት ነው የሚገባኝ” በማለት ቃለ ምዕዳናቸውን የጀመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ የፕሮቴስንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አደጋ ካለ መንሥኤው “የሊቃውንቱ ዝምታ” እና “የአባቶች /መምህራን/ ዐውደ ምሕረታቸውን ያለመጠበቅ” መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይሁንና ይህች ቤተ ክርስቲያን ዝም ብላ የመጣች ባለመሆኗ በሃይማኖት ጉዳይ ቸልታን አስወግዶ እስከ ሰማዕትነት ሊደረስ እንደሚችል መክረዋል፡፡

በቃለ ምዕዳናቸው መጨረሻም “አባቶች፣ አስተዳዳሪዎች፣ አለቆች ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻችሁን የክብር ልብስ ለብሳችሁ ቅዳሴ ማስቀደስ፣ የትኛው ቀደሰ/ አልቀደሰም ብሎ መቆጣጠር፣ ቢሮ ገብቶ መውጣት ብቻ አይደለም ተግባራችሁ፤ በ2004 ዓ.ም መሠራት የሚገባው ሥራ ይህችን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ፣ በሚገባ ማስተዳደር መሆን ይኖርበታል፤” ብለዋል፡፡

ፓትርያኩ ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን በሚመለከት በተለያዩ መድረኮች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዋነኛው የማስረጃ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በማኅበረ ቅዱሳን፣ በሐዋሳ ምእመናን፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተዘጋጁ በርካታ ማስረጃዎች በገለጻ መልክ ቀርበውላቸዋል የተባለ ሲሆን፤ በጽሑፍ እና በምስል ወድምፅ ተጠናቅረው በሲኖዶሱ ጽ/ቤት አማካይነት እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

ግልጽ እና ቅርብ እየሆነ የመጣውን አደጋ ለማየት የተከፈተ ዐይን፣ የሚሰማ ጆሮ እና የሚያስተውል አእምሮ ካለ ደግሞ ባለፈው ዓመት በተለያዩ አካላት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት ከዐውደ ምሕረት በወሳኝ መልኩ የተመታው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ኀይል ከልዩ ጽ/ቤታቸው ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች፣ በሀገር ውስጥ እና በባሕር ማዶ አህጉረ ስብከት ቢሮዎች/መዋቅሮች እና በትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተሰገሰገ፣ የአቋምም ሽግሽግ እያደረገ መሆኑን መገንዘብ በተቻለ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዐቢይ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀርብ በሚጠበቀው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጉዳይ በደብዳቤ መመሪያ እስከ መስጠት ድረስ ሲጠይቋቸው በቆዩትና ስለቀረቡላቸው የሚታዩና የሚጨበጡ ከደርዘን በላይ ማስረጃዎች ምን አቋም እንደሚይዙ በወቅቱ የምናየው ይሆናል፡፡  

ቀጣይ የፀረ-ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ እንቅስቃሴ አገልግሎትም ስብከተ ወንጌሉን እና ትምህርተ ወንጌሉን በተለያዩ አገባቦች ከማጠናከር ጎን ለጎን ቢሮክራሲያዊ መልክ እየተላበሰ የመጣውን የተሐድሶ-ኑፋቄ ምንደኛ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በየደረጃው በሚወሰዱ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ርምጃዎች በማጋለጥ ማፍለስ/ማጥራት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment