Tuesday, October 30, 2012

የቡቤ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን


(አንድ አድርገን ጥቅምት 20 2005 ዓ.ም)፡-  ቡቤ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሀብሮ ወረዳ ውስጥ ትገኛለች ፤ አካባቢው ደጋማ የአየር ንብረት አለው ፤ ወደዚህ ቦታ ለመድረስ ከአዲስ አበባ አዋሽ ፤ ከአዋሽ ቦርደዴ ፤ ከቦርደዴ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤ/ን በአዲሱ የገለምሶ መንገድ ቡቤ ኪዳነምህረት በማለት መሄድ ይቻላል ፤ ጠቅላላ ከአዲስ አበባ በ290 ኪሎ ሜትር አካባቢ ትገኛለች ፤ እዚህ አካባቢ የሚገኙ ምዕመናኖች ከ50 ዓመት በላይ አካባቢያቸው ቤተክርስትያን እንዲሰራላቸው በጽኑ ይፈልጉ ነበር ፤ በየጊዜው ቤተክርስትያን ለመስራት መቃኞ አቁመው ሲያበቁ በንፋስ ይፈርስባቸው እንደነበር ለማወቅ ችለናል ፤
የዘመናት ፍላጎታቸው ቤተክርስትያን ታንጾ ማየት ቢሆንም በአካባቢው ያለመረጋጋት ሁኔታ ቤተክርስትያን መስራት ሳይቻል እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል ፤ ቀድሞ ልጆቻቸውን ክርስትና ለማስነሳትና  ሰው ሲሞትባቸው ለቀብር ጉባ ቆርቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን መሄድ ግድ ይላቸው ነበር ፤ ጉባ ቆርቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ለመሄድ ቢያንስ ከአራት እስከ አምስት ሰዓት የሚወስድ የእግር መንገድ አለው ፤ አንድ የአካባቢው ክርስቲያን ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የቡቤ ቀበሌ ነዋሪዎች ይህን ክርስትያን ለመቅበር የአንድ ሙሉ ቀን ጊዜ ይወስድባቸው ነበር ፤ የተመቻቸ መንገድ እጦቱ እና አስከሬንን ለግብአተ መሬት ረዥም ርቀት ይዞ መሄድ ህዝቡን ምርር ያደረገና የዘወትር ችግራቸው ነበር ፤ ጠዋት ሶስት ሰዓት ላይ አስከሬን ይዞ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ቢያመሩ ቦታው ደርሶ ፍትሀት ተደርጎ እና ጉድጓድ ተቆፍሮ ግብአተ መሬት ፈጽመው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ቀኑ ይመሻል  ፤ ይህ ሁሉ ክርስቲያኖች ሲሞቱ የሚደርስ እንግልት ለክርስትያኖቹ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ላይ የሚኖሩ ሙስሊም ማህበረሰቦችን የሚያሳስብ ጉዳይ ነበር ፤ ክርስትያኖቹ በአካባቢያቸው ልጆቻቸውን ክርስትና የሚያነሱበት ፤ በትምህርተ ሀይማኖት የሚያንጹበት ፤ ቀብር የሚፈጽሙበትና የተለያዩ አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተክርስትያን እንደሚያስፈልጋቸው ከከተማዋ ከንቲባ አንስቶ ክርስትያን የሆነውም ሆነ ያልሆነው ማህበረሰብ የተስማማበት ጉዳይ ነበር ፡፡
ለሕንጻ ቤተክርስትኒቱ ማሰሪያ የሚሆን ቦታ በወረዳው አስተዳዳሪ መልካም ፍቃድ መሰረት ከአካባው ከሚገኝ አንድ የሙስሊምን ቦታ  በመግዛት  ቡቤ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን የመስራት ስራ ከተጀመረ በኋላ በጥቂት ወራት ውስጥ ስራዋን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ የዛሬ ሁለት ዓመት የካቲት 16 ቀን 2003 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ ሊከብር ችሏል ፤ ይህ ሲሆን ከ50 ዓመት በላይ አብሯቸው የቆየው ችግራቸው የተቀረፈላቸው የአካባቢው ምዕመናን ደስታቸው ከፍተኛ ነበር ፤ በህይወት ዘመናቸው ከተደሰቱበት የመጀመሪያው ቀን ሕንጻ ቤተክርስትያናቸው የተመረቀበትና ቅዳሰ ቤቱ የከበረበት ቀን  ነው  ፤ ቅዳሴ ቤቱ በከበረበት ወቅት አብረዋቸው የሚኖሩ ሙስሊም ማህበረሰቦች እና የወረዳው አስተዳዳሪ በመገኝት በሺህ የሚቆጠር ብር ለቤተክርስቲያኒቷ መለገስ ችለው ነበር ፤ በአሁኑ ሰዓት ይች ቤተክርስትያን የምትተዳደረው በአካባቢው በሚገኙ በግብርና ሙያ ላይ በተሰማሩ ምዕመኖች አማካኝነት ነው ፤ እነዚህ ክርስትያኖች ለዓመታት  ቤተክርስትያን ሳይኖር ቃለ ወንጌል ሳይሰበኩ ቁጭ ብለው ቤተክርስትያኒቱ እስከምትሰራ ድረስ እምነታቸውን ሳይለውጡ በቀናችው በአንዲቱ መንገድ ቆመው ተገኝተዋል ፤ የአካባቢው ክርስትያኖች ከሙስሊሞችና እምነት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ለረዥም ዘመን ቢቆዩም ወንጌል  ሳይሰብካቸው መጀመሪያ በነበሩበት እምነት ከ50 ዓመት በላይ ቆይተው እግዚአብሔርም ፍቃዱ በሆነበት ጊዜ ሕንጻ ቤተክርስትያናቸው አልቆ አንድ ዲያቆንና ሁለት አባቶችን በመቅጠር የክርስትና ፤ የስብከት አገልግሎት ፤  የቀብር እና መሰል አገልግሎቶችን በአሁኑ ሰዓት እያገኙ ይገኛሉ ፡፡ ይህን ያደረገ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን” መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 25 ፤32
እህል እንደ መተዳደሪያ
ይች ቤተክርስትያን የምትተዳደረው የአካባቢው ምዕመን በሚያዋጣው ገንዘብ እና እህል አማካኝነት ነው ፤ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን ፤ ገንዘብ የሌለው ደግሞ ካመረተው የዓመት እህል ላይ አንድ አስረኛውን ለቤተክርስትያን በመስጠት ቤተክርስትያኒቱን ያስተዳድሯታል ፤ ይህ እህል ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ለቤተክርስትያኒቱ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ጧፍ ፤ እጣን ፤ ዘበቢ እና የካህናት ደመወዝ የሚከፈልበት ይሆናል ፤ 
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 31 ፤5 ላይ እንዲህ ይላል  በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ።ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በኵራት ሰጡ የሁሉንም አሥራት አብዝተው አቀረቡ። በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አኖሩት።” አንድ ክርስትያን አስራት የሚያወጣው ካገኝው ከአስር አንድ እጁን መሆኑ ይታወቃል ፤ አሁን ባለንበት ሰዓት እህልን እንደ አስራት የሚያቀርቡ አካባቢዎች ውስጥ የቡቤ ኪዳነምህረት አካባቢ ምዕመናን ይገኛሉ ፡፡  ካህናት እንደ ብርቅ
የዚህ አካባቢ ክርስትያኖች ለዘመናት በአካባቢው ካህን አይተው አያውቁም ፤ በአካባቢያቸው ካህናት ሲያልፉ “ይግቡ” ብለው ቤታቸውን ጸበል የሚረጭላቸው ካህን አልነበረም ፤ ሰው ሲሞትም ቢሆን ቤት ድረስ ካህናት መጥተው ፍትሀት የሚያደርጉላቸው ሁኔታም የማይታሰብ ነው ፤ የካህናትን ክብርና ከአምላክ ስለተሰጣቸው ስልጣን  በአግባቡ የሚያውቁት የቡቤ ቀበሌ ምዕመናን ናቸው ፤ በተቻላቸው መጠን ቤተክርስትያናቸው በካህናት እጥረት እንዳትዘጋ የአቅማቸውን ያህል እያደረጉ ይገኛሉ ፤ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ቤተክርስትያን ለእነርሱ ምን እንደሆነች በህይወታቸው ስላዩት እና ስለገባቸውም ጭምር ነው ፡፡ ያለ ቤተክርስትያን እና ያለ ካህናት የኖሩባቸው እነዚያ 50 ዓመታት ደግመው ሲመጡ መመልከት ስለማይፈልጉ ካህናትን ለማቆየት ብዙ መስዋዕትነትን ይከፍላሉ፡፡
የቤተክርስትያኒቱ ችግር
ይህ አካባቢ ከከተማ ራቅ ስለሚል ማንም ትዝ የማይለው ቦታ በመሆኑ በርካታ ነገሮች ጎለው ተመልክተናል ፤ እንደ አካባቢው አብያተ ክርስትያናት የጧፍ ፤ የእጣን ፤ የዘቢብ እና መሰል መገልገያዎች እጥረት ይታይበታል ፤ በጣም በሩቅ ቦታ እና በጥቂት ክርስትያኖች መሀል የምትገኝው ቤተክርስትያን የሚያስፈልጋትን ነገሮች ማሟት ብንችል አንድም በረከትን ከእግዚአብሔር ስንቀበል በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው ክርስትያኖችን “አለንላችሁ ከጎናችሁ ነን” የሚል መልዕክት ማስተላለፊያ ይሆናል የሚል እምነት አለን፡፡ በበረሀ እና በሩቅ ቦታ ላይ የሚገኙ አብያተክርስትያናት ዋናው ችግራቸው ከንዋየ ቅድሳት በላይ የተመልካች ችግር ነው ፤ ማንም ዞር ብሎ ስለማያያቸው ወገን የማጣት ስሜት ውስጣቸው ይፈጠራል ፤ በበረሃ አካባቢ ባለ አንድ ቤተክርስትያን በአንድ ወቅት ስንሄድ አንዲት እናት አንዱን የቤተክርስትያን ጠርዝ ይዘው ሲያለቅሱ ተመለከትን ፤ ከዚያ ጠጋ ብለን ለምን እንደሚያለቅሱ ብንጠይቃቸው “እስከዛሬ ድረስ እዚህ ቤተክርስትያን ይህን ያህል ምዕመን መጥቶ አያውቅም ፤ ለካስ እኛም ወገን አለን ?፤ ለካስ እኛን አይዟችሁ የሚለን ክርስትያን አጠገባችን አለ ፤ ደስታው ነው ያስለቀሰኝ” ብለውናል:: እኛ በጊዜው በአንዲት ቅጥቅጥ አይሱዙ ወደ ቦታው ያመራነው ሰዎች ከ30 አንበልጥም ነበር ፤ 30 ክርስትያን ብዙ የሆኑባቸው በየገጠሩ እና በየበረሃው የሚገኙ አብያተክርስትያኖች በርካታ ናቸው፡፡
ብዙ አብያተ ክርስትያናት እና በርካታ ካህናትና መምህራን የሚገኙበት ቦታዎች ላይ ተመሳስለውን የገቡ የእኛን ልብስ የለበሱ ፤ ላያቸው የእኛን የሚመስሉ ከነጣቂ ተኩላዎች ምዕመኑን መጠበቅ ሲያቅት ተመልክተናል ፤  በየጊዜው ቅዳሴ የሚቀደስበት ፤ ስብከት የሚሰበክበት ፤ በዓላት የሚከበሩበት ፤ ቅዱሳንና ሰማዕታት በስራቸው የሚዘከሩበት ቦታዎች ላይ ምዕመኑን ከመናፍቃን መጠበቅ ሲከብደን እናስተውላለን ፤ እንደዚህ አይነት በረሃ እና በገጠር አካባቢ ያሉ ክርስትያኖችን በእግዚአብሔር ጠባቂነት ወንጌል በአግባቡ ሳይሰበክላቸው በያዟት ጥቂት ነገር ጸንተው ሲቆሙ ተመልክተናል፡፡ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ትንቢተ ኤርምያስ 6 ፤16
እነዚህ በመሰሉ ቦታዎች ዋናው ችግር የተመልካች እጦት ነው ፤ ለዘመናት እርስ በእርስ የሚተዋወቁ ከ100 የማይበልጡ ክርስትያኖች ስለሆኑ የሚኖሩት ችግራቸውንም የሚያካፍሉት ክፍተታቸውን የሚተነፍሱለት ፤ አይዟችሁ የሚላቸው ምዕመን ይፈልጋሉ ፤ በክርስትናቸው ጠንክረው እስከ መጨረሻ ስቅታቸው ድረስ እምነታቸው እንዲጠብቋት የሚያስተምሯቸው ካህናትን ይፈልጋሉ ፤ አሁን ግን እኛም እያየን እና እየተመለከትን ያለነው ነገር እነዚህ ቤተክርስትያኖች ጋር ለማገልገል ፍቃደኛ የሆነ ሰው እና እነዚህን ቤተክርስትያኖች አስታውሰው በዓመት አንድ ጊዜ የሚሄድ ምዕመንን ነው ፤ ቁልቢ ገብርኤል ፤ ግሸን ማርያም፤ ጽዮን ማርያም እና መሰል ቦታዎች አንሂድ ክብረ በአላትንም አናክብር እያልን ሳይሆን ወደ እነዚህ አድባራት ስንጓዝ መሃል ላይ የሚገኙትን ፤ በረሃ ላይ የተጣሉትን ፤ በርከት ያለ ምዕመንን ማየት የናፈቃቸውን ፤ በአህዛብ እና በመናፍቃን ተከበው ጥሎ ለመሄድም ሆነ ጸንቶ ለመቀመጥ ግራ የገባቸውን አብያተክርስትያናት እናስታውሳቸው እያልን ነው ፤ ዳራችን እነርሱ ናቸው ፤ እነርሱ ጠፍተው ሁሉም አማኝ መሀሉን ቢመርጥ መሀሉም ዳር የማይሆንበት አንዳች ነገር አይኖርም፡፡
ጥቂቶች ትላልቅ ገዳማት እና አድባራት ሲሄዱ በየመንገዱ ለሚገኙ አብያተክርስትያናት ትንሽ ቆም በማለት ጧፍ እና ገንዘብ በአቅማቸው እየሰጡ የሚሄዱ አሉ ፤ ብዙዎች ግን መንገድ ላይ የሚቆሙት ከሰል  ፤ ፍራፍሬዎችን ለመግዛት ብቻ ነው ፡፡ 
በመጨረሻም
“አንድ አድርገን” በዚህ አካባቢ የሚገኝውን ችግር በማየት ሰዎች አንብበው የአቅማቸውን እንዲረዱ ማድረግ ችላለች ፤ በተገኝው አጋጣሚም ከሰዎች ጋር በመነጋገር ችግራቸውን ማስረዳት በመቻል ሰዎች የቤተክርስትያናቱን ቀዳዳ በአቅማቸው እንዲደፍኑ መንገድ በመክፈት አመላክታለች ፤ ከዚህ በፊት አንድ ዙር ጧፍና እጣን መላክ ችላለች ፤ በአሁኑ ሰዓትም 5ሺህ ብር የሚደርስ ንዋየ ቅዱሳት በመግዛት ወደ ቦታው ልከናል ፤ በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ የሚገኙ ምዕመናን አካባቢው ላይ የሚገኙት አብያተክርስትያናት ለመርዳት ቃልም እየገቡ ይገኛሉ ፤ ስለዚህ አሰቦት ቅድስት ሥላሴ  እና ቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል  ለማክበር ለምትሄዱ ሰዎች በመንገዳችሁ ላይ እነኝህን ቤተክርስትያናት ታስቧቸው ዘንድ መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡
እንደ እኛ ሀሳብ ከሆነ ለኮራ ገብርኤል ፤ ለቅዱስ ሚካኤል ፤ ለቦርደዴ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን እና ለቡቤ ኪዳነ ምህረት ገንዘብ ሰጥቶ መንገድ ከመቀጠል ይልቅ ፤ ጊዜ ካለና የሚቻል ከሆነ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ያሉበትንና የኖሩበትን ሁኔታ ማየት የሚቻል ከሆነ ምዕመናን እነዚህን ቤተክርስትያናት ቢመለከቷቸው ቀረብም ብለው ያለባቸውን ችግር ቢያደምጧቸው መልካም ነው የሚል መልዕክት አለን፡፡  ይህ ለእነርሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡
 የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን የሚገኝው ከመንገድ 400 ሜትር ገባ እንዳሉ ሲሆን ኮራ ገብርኤል ደግሞ ከመንገድ 7 ኪሎ ሜትር በስተቀኝ በኩል እንደገቡ ነው ፤ ቅዱስ ሚካኤልን እና ኪዳነ ምህረትን ለማየት ግን ለእነዚሁ ብለው አስበው ካልመጡ በቀር እግረ መንገድ የሚታዩ አብያተክርስትያናት አይደሉም ፡፡
እነዚህ ቤተክርስትያናት ለመርዳት የቤተክርስትያናቱን የባንክ አካውንት አስቀምጡልን ያላችሁ በስተመጨረሻ ላይ በተቀመጠው የባንክ አካውንት በመጠቀም መርዳት ትችላላችሁ ፤ ቦታው ድረስ በመሄድ ቦታውን እንመለከታለን መርዳትም እንፈልጋለን ካላችሁ በተቀመጠው ስልክ ቁጥር በመደወል እንዴት ወደ ቦታዎቹ ማምራት እንደምትችሉ የተሻለ መረጃ ማግኝት ትችላላችሁ ፤ ለቁልቢ አመታዊ ክብረ በአል ሲከበር ጎራ ብለን እናያለን የአቅማችንንም ረድተን እናልፋለን ካላችሁም ከቤተክርስትያናቱ አስተዳዳሪ ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደምትችሉ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የአርባ ቦርደዴ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን
የባንክ የሂሳብ ቁጥር 6329
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዋሽ ሰባት ኪሎ ቅርንጫፍ
አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ
ስልክ 0913-833532 (የአስተዳዳሪው የሞባይል ቁጥር)
የሌሎቹን አድራሻ ጠይቀን ሌላ ጊዜ ፖስት እናደርጋለን
በሌላ ጊዜ በየበረሀውና በየገጠሩ ያሉትን አብያተክርስትያናት ያሉበትን ሁኔታ እናስቃኝዎታለን…..
ቸር ሰንብቱ

1 comment:

  1. Good job! God and Mother Virgin St. Mary help you!

    ReplyDelete