Monday, October 22, 2012

በግብፅ የፓትርያርክ ምርጫ አምስት ኢትዮጵያውያን ድምፅ እንደሚሰጡ ታወቀ

በሔኖክ ያሬድ(Reporter)

ባለፈው መጋቢት ያረፉትን የግብፅ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳን የሚተኩትን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ ከመጨረሻዎቹ አምስት ዕጩዎች ሦስቱን ለመለየት በሚደረገው አገራዊ ምርጫ አምስት ኢትዮጵያውያን ድምፅ እንደሚሰጡ ታወቀ፡፡
የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅሶ አልመስሪ አልዩም በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ የመጨረሻዎቹ ሦስት ዕጩዎች ለመለየት ድምፅ የሚሰጠው ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡

ምርጫውን ከሚያከናውኑት 2,405 መራጮች ውስጥ በግብፅ የምትገኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አምስት ተወካዮች እንደሚገኙበት አስያ ኒውስ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡

ሌሎቹ መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ መላው አባላት፣ በግብፅና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የምዕመናን፣ የካህናትና የመነኮሳት ተወካዮች ናቸው፡፡ ተጠባባቂ ፓትርያርኩ አቡነ ጳኩሚየስ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ ለፓትርያርክነት ለመወዳደር ከቀረቡት 17 አባቶች ውስጥ አምስቱን የመረጠው ሁለቱን ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሦስቱን ደግሞ ከመነኮሳት መካከል በመለየት ነው፡፡ በዕድሜ ትልቁ 70 ሲሆን አነስተኛው ደግሞ 49 ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና በአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ድንጋጌ መሠረት ከመጨረሻዎቹ ሦስት ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ሆነው ለፓትርያርክነት የሚመረጡት የሚለዩት በዕጣ ነው፡፡ እስክንድርያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል እሑድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ከሦስቱ አንዱ ፓትርያርክ ሆኖ የሚመረጠው ዓይኑ በጨርቅ የተሸፈነው ሕፃን ዕጣውን ካወጣ በኋላ ነው፡፡

ከነገረ መለኮት ትምህርት ሌላ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሕግ፣ በሕክምና፣ በሥነ ትምህርት፣ በሳይንስና በፋርማሲ የተመረቁት አምስቱ ዕጩዎች በየሚዲያው የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉና ይህም በሦስቱ የየኮፕቲክ ቴሌቪዥን ማሰራጫዎች እንዲሁም በአገሪቱ ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንደሚሰራጩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቃል አቀባይ ሊቀጳጳሱ አቡነ ጳውሎስ ለጋዜጠኞች ባለፈው ረቡዕ አስታውቀዋል፡፡

118ኛው ፓትርያርክን ለመምረጥ የሚደረገው ጥረት የተሳካ እንዲሆን በግብፅ የሚገኙ ልዩ ልዩ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት በመስከረም መጨረሻ የሦስት ቀናት ጾም ጸሎት በጋራ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

ቃለ አቀባዩ ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ለአሕራም እንደተናገሩት፣ የሦስቱ የመጨረሻ ዕጩዎች ስም ይፋ ከመሆኑ በፊት የግብፅ ኮፕቶች ለሦስት ቀናት ከጥቅምት 12 እስከ 14 እና ከጥቅምት 21 እስከ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ይጾማሉ፡፡

የአዲሱ ተመራጭ ፓትርያርክ በዓለ ሲመትም ኅዳር 9 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደሚፈጸም የቤተ ክርስቲያኒቱን ምንጭ ጠቅሶ አልምስሪ አልዩም ከትናንትና በስቲያ ዘግቧል፡፡

በበዓለ ሲመቱም ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሞርሲ እንደሚጋበዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳትና አንዳንድ የአውሮፓ  መንግሥታት መሪዎችና አምባሳደሮች፣ ደራስያንና ምሁራን እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የግብፅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተመሠረተ ሲሆን፣ እስከ 1943 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሊቀ ጳጳስነት ይመሩ የነበሩት ግብፃውያን ጳጳሳት ነበሩ፡፡ በግብፅ የተለያዩ ከተሞች የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ሲገኙ፣ በርካታ ምዕመናን መነኮሳት በዚያው ይኖራሉ፡፡

የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸውና በቀኖና ከመዘገበቻቸው ቅዱሳን አንዱ ኢትዮጵያዊው አቡነ ተክለሃይማኖት ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በስማቸው የሰየመችው ድረ ገጽም አላት፡፡ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በክርስቲያናዊ ሥነ ጽሑፍ ከጥንት ጀምሮ የተሳሰሩ ሲሆን፣ በተለይ በመካከለኛው ዘመን በርካታ መጻሕፍት ከዓረቢኛ ወደ ግእዝ ቋንቋ ተርጉመዋል፡፡

የቅዱሳንን ታሪክ የሚያወሳው ስንክሳር መጽሐፍ ወደ ግእዝ የተተረጐመበት ዋናው የዓረቢኛ መጽሐፍ በመጥፋቱ ምክንያት የግብፅ ቤተ ክርስቲያን እንደገና ከግእዝ ወደ ዓረቢኛ በማስተርጐም ተጠቃሚ መሆኗ በኮፕቲክ ኢንሳይክሎፒዲያ ተመልክቷል፡፡

በ1964 ዓ.ም. በግብፅ 117ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በ88 ዓመታቸው ያረፉት መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡

በሌላ ዜና ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በ96 ዓመታቸው ያረፉት በኢየሩሳሌም የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቶርኮም ዳግማዊ ሥርዓተ ቀብር ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም እንደሚፈጸም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጋራ እምነት ያላት የአርመን ቤተ ክርስቲያን በአገሯ ውስጥና በውጭ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናቷን በበላይነት የሚመሩት ልዕለ ፓትርያርክ (ሱፕሪም ፓትርያርክ) ካሬኪን ዳግማዊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ 

No comments:

Post a Comment