Thursday, October 18, 2012

የቤተክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ዕውቅና እንዲያገኝ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ

በታምሩ ጽጌ(reporter)


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት መንፈሳዊ ጉዳዮችን የምትከታተልበት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የሚያገኝበት ሁኔታ መመቻቸቱንና ለተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ እየተመረመረ መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያለው ግንኙነትና እንዴት ማጣጣም እንደሚቻል ረቂቅ ሕጉ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ በትናንትናው ዕለት የተጀመረውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ 31ኛ መደበኛ ስብሰባን አስመልክቶ የቤተክህነቱ የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረክርስቶስ፣ ‹‹ቤተክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አላት፡፡ መንፈሳዊ ቦታ በመሆኗ ግን እስር ቤት የላትም፡፡ ፖሊስም የላትም፡፡ ፍርድ ቤቱ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው መንፈሳዊ ተግባራትን ነው፤›› ብለው፣ የተጋጩ ሰዎችን በእርቅና በስምምነት እንዲፈቱ ማድረግ ነው፣ ከመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ውጭ የሆነ ጉዳይ ካጋጠመ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

ትናንትና በተጀመረው ጉባዔ ላይ “መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥቱ ያለው ድርሻ” በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚቀርብና ከ650 በላይ የሚሆኑት የስብሰባው ታዳሚዎች 12 ቦታ ተቧድነው ውይይት እንደሚያደርጉበትም ጠቁመዋል፡፡

በዓቃቤ መንበር ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል ፀሎት በተከፈተው 31ኛው መንፈሳው ጉባዔ ላይ፣ በአገር ውስጥና በሌሎች ዓለማት ያሉ የሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሥራ አስኪያጆች፣ የምዕመናን ተወካዮች፣ የመምርያ ኃላፊዎች፣ የአስተዳዳሪዎችና ሌሎችም ገዳማትና አድባራት ተገኝተዋል፡፡ የ2004 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውም በ34 ገጽ ተጠቃሎ ቀርቧል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሁሉም ሀገረ ስብከት የተከናወኑ የሥራ አፈጻጸሞች ሁሉም ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነው መፈጸማቸውን የሚያወሱ ቢሆንም፣ ስምንት ያህል እንቅፋቶች ገጥመዋቸው እንደነበር በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በበጀት የተደገፈ የሰው ኃይል አደረጃጀት አለመኖሩ፣ ለአቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ እንደማይሰጥ፣ የቅርስ ዘረፋ፣ በብሔራዊ በዓሏ ላይ ሌላ በዓል እንዲከበር መደረጉና ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ምክንያት የዋልድባ ገዳም ከሚያገኘው ገቢ ለጠቅላይ ቤተክህነት ፈሰስ አላደርግም ማለቱ፣ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ተገልጿል፡፡

ዓመታዊ ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው፣ በበጀት ዓመቱ የባዕድ እምነት ተከታይ የሆኑ ባለሥልጣናት በመንግሥት ስም በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፅዕኖና አድልዎ ያደርጉ እንደነበር፣ በወንዶ ገነት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር ‹‹ፕሮቴስታንቶች›› በግዳጅ እንዲቀበሩ በመደረጉ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሪፖርት ቢደረግም ምላሽ አለመስጠቱ፣ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት አራት አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ‹‹በመናፍቃን›› መዘረፋቸውና ሌሎችም ያጋጠሙ ችግሮች እንዳሉ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ጨምሮ ከሁሉም ሀገረ ስብከቶች ለመንበረ ፓትርያርክ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ፈሰስ ማድረጋቸውንም የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምርያ ኃላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጨ ተናግረዋል፡፡ ለአምስት ቀናት የሚቆየው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ 31ኛ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ እንደሚጀመር ታውቋል፡

2 comments:


  1. Good for you Ato Eskindr. keep going with it, because you are the man of the year. maybe one day you will be a bishop of Betkhnet. any way where is the voice of MK? I think they are fasting from eatting and drinking aren't they?

    ReplyDelete
  2. ብላቴናዋ ከጀርመንOctober 20, 2012 at 10:22 AM

    ሰላም አንድአድርገኖች እንደምን ከረማችሁ ስላቀረባችሁን ዘገባ እያመሰግንኩ የምለውነገር ቢኖር የዋልድባ ገዳም ለጠቅላይ ቤተክህነቱፈሰስ አላደርግም አለብለው የሚሉት ቤተክህነት በመጀመሪያ ስለዋልደባ ችግር መች ግድሰጣትና መንገላታታቸውና በታሰራቸው ብሎም ግርፋታቸው መች አመማቸውና ነው አሁን ገንዘብ አምጡ የሚሉዋቸው ለዚያውስ እድሜለመንግስት ገብተው ዘርፈዋቸው የለም እንዴ እኔ የምለው ዋልድባዎች ከቤተክህነት አስተዳደር ስርይዉጡ ሳይሆን በችግራቸው ግዜ ያላሰበቻቸው ቤተክህነት ምነው ለጥቅሙዋ ፈለገቻቸው ለማለት ፈልጌ ነው ለዚያውስ ዋናዋ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ቤተክርስቲያን ሁና እያለ ችግርየለም ብላ የምትሸፋፍነዋም እራሱዋ መሆኑዋ ያሳዝናል ለማንኛውም እንደፓርላማዎቹ ወይም እንደዘመኖቹ ሜልኮሎች ካልሳቃችሁብኝ እግዛብሄር ቤተክርስቲያንና ህዝቡዋን ከክፉ ነገር በረድኤቱ ይጠብቅልን አሜን!

    ReplyDelete