Tuesday, October 16, 2012

የሀገረ ስብከት አዳራሽ የተከለከለው መጽሐፍ መንገድ ላይ ተመረቀ



በጋዜጠኛ፣ መምህርና ደራሲ ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር የተዘጋጀው ‹‹ብፁዓን እነማን ናቸው?›› የሚለው አራተኛ መጽሐፍ ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንገድ ላይ ተመረቀ፡፡ መጽሐፉ በመንገድ ላይ ሊመረቅ የቻለው፣ ደራሲው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽን ካስፈቀደ በኋላ በመከልከሉ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ለመጽሐፉ ምረቃ የጥሪ ወረቀት ይበትናል፡፡ የመጽሐፉ መመረቂያ ዕለት ደርሶ ወደ አዳራሹ ሲሄድ፣ ‹‹በጠቅላይ ቤተ ክህነት ታግዷል›› በመባሉና የጠራቸውን እንግዶች መመለሻ ጊዜ ስላልነበረው፣ ያለው አማራጭ በመንገድ ላይ ማስመረቅ መሆኑን አቶ ካህሳይ ገልጿል፡፡

በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በስተጀርባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት አዳራሽ በራፍ ላይ የተመረቀው ‹‹ብፁዓን እነማን ናቸው?›› መጽሐፍ ይዘት መንፈሳዊ መሆኑን የገለጸው ደራሲው፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን የቤተ ክርስቲያን አሠራር ቀድሞ ከነበው አሠራር ጋር በማነፃፀር የተጻፈ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጳጳሳትን፣ አስተዳዳሪዎችንና መነኮሳትን ለመምረጥ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ጉድለቶች እየታዩ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛ፣ መምህርና ደራሲ ካህሳይ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የራሷ ሕግ አላት፣ አዳዲስ የወጡ ሕግጋትም አሉ፤ ነገር ግን የቀድሞውን ይቃረናሉ፡፡ በመሠረቱ ግን መሠረታዊ ሕጉን መቃወም የለባቸውም፤›› በማለት መሠረታዊው የቤተ ክርስቲያን ሕግ መጣስ እንደሌለበት ተናግሯል፡፡

አዲስ የወጡት  ሕግጋት ጳጳሳትና መነኮሳት ንብረት የሚያፈሩበት ሁኔታን እንደሚፈቅድ የገለጸው ደራሲ ካህሳይ፣ ‹‹አንድ ሰው ሲመነኩስ ሞተ ተብሎ ተገንዞ ስለሆነ፣ ንብረት እንዲያፈራ ወይም እንዲኖረው አይፈቀድም፡፡ ምክንያቱም ዓለማዊ ነገርን ትቶ መንፈሳዊ ለመሆን በቁሙ ተስካር አድርጐ ነው የሚለወጠው፤›› ብሏል፡፡

ሕጉ ይደግፈናል በሚል የአሁኑ መነኮሳትና ጳጳሳት ቤት እንደሚገዙና ንብረት እንደሚያፈሩ ገልጾ፣ ‹‹ይኼ ነገር ሥርዓት መያዝ አለበት፤ ሕጉ ከሚለው ጋር ለምን ይጋጫል?›› በሚል በመጽሐፉ ውስጥ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኗ ቀደምት መጻሕፍት በማጣቀስ እንዳሰፈረ ገልጿል፡፡

‹‹ብፁዕ ለመባል የሚያበቁ መስፈርቶች አሉ›› የሚለው ደራሲው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ መስፈርቱን አሟልተው የሆኑት ምን ያህል ናቸው?›› በማለት ይጠይቅና፣ ‹‹አባቶቻችን መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ መሠረቶች ፈር እየለቀቁ ስለሆነ ጥንቃቄ ይደረግ፤›› የሚል መልዕክት በመጽሐፉ ማስፈሩን አስረድቷል፡፡

ሀገረ ስክበቱ በፈጸመው ድርጊት የመንፈስ ኪሳራ ባይደርስበትም የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደደረሰበት የገለጸው ደራሲ ካህሳይ፣ አደናቃፊዎች እየበዙ ቢሄዱም ሕይወቱ እስካለ ድረስ መጻፉን እንደማያቆም አስታውቋል፡፡

የ58 ዓመቱ መምህር፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ካህሳይ ‹‹ህብረ ብዕር አንድና ሁለት፣ ምንኩስና በኢትዮጵያ ዛሬና ትናንትና፣ ብፁዓን እንማን ናቸው?›› የሚሉ አጠቃላይ ዕውቀት ላይ የሚያተኩሩ መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡ በቅርቡም፣ ‹‹ባህልና ክርስቲያናዊ ትውፊቱ በኢትዮጵያ›› የሚል መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚታተመው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣም አዘጋጅ ሆኖ ይሠራል፡፡

ለደራሲው አዳራሹ ከተፈቀደለት በኋላ ለምን እንደተከለከለና ለምን ቀደም ብሎ እንዳልተነገረው ማብራሪያ ለማግኘት አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት በሚገኘው የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ተገኝተን ብንጠይቅም፣ ‹‹ሥራ አስኪያጁ የሉም›› በመባሉ ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡ 
 
በታምሩ ጽጌ  (From Reporter)

1 comment:

  1. ብላቴናዋ ከጀርመንOctober 16, 2012 at 10:31 AM

    እውነትን እንደሁ መቅበር አይቻል ተዋረዱ ማንነታችሁን ህዝብይወቅባችሁ ሲላቸው ነው እንጅ የተፈቀደን ወይም የተከራየን አዳራሽ በመከልከል ንቅዘታቸውን ላይሸፍኑ ለማንኛውም መምህር ካህሳይን በርታ ክርስቲያንና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃልና ስለውነት መስዋእትነት ለመሆን ቆርጠህ ስለተነሳህ የሚመጣብህን ነገር በጸጋ ለመቀበል የተዘጋጀህ የበቃህ እግዚአብሄር ያድርግህ አሜን

    ReplyDelete