Wednesday, October 31, 2012

አባ ናትናኤል ዳግም በፖሊስ ተይዘው ዘብጥያ ወረዱ

(አንድ አድርገን ጥቅምት 21 2005 ዓ.ም)፤- አባ ናትናኤል ትላንት ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2005 . በድጋሚ ታስረው ከአዲስ አበባ ወደ አዋሳ ተወስደዋል፡፡ ግለሰቡ ባለፈው ከመኖሪያ ቤታቸው አዋሳ ድረስ ታስረው ከተወሰዱና በዋስ ከተፈቱ በኋላ ጥቅምት 11 ቀን እሁድ በአየር ጤና ኪዳነ ምህረት / አውደ ምህረት ላይ ሰዎች በክፋት ወንጅለውኝ ነበር፣ የህግ አካላት ግን አባታችን ይቅርታ ብለው አሰናብተውኝ መጥቻለሁ፡፡ እነኝህ የሚሳሳቱ ሰዎችን እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው ምዕመናን ጸልዩላቸው ብለው ነበር፡፡ በዕለቱም ሲወጡና ሲገቡ ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉላቸውና በየምክንያቱ ህገወጥ እገዳ በሚያደርጉባቸው ምዕመናን ላይ መሳሪያ ይዘው እንዲያስፈራሩ ከቀጠሯቸው 5 ዘበኞች አንዱ፣ ከጽጌ ማዕድ ትርፍራፊ ለመቃረም ከተሰበሰቡ ነዳያን መካከል አንድ ምስኪን በዱላ አንገቱን መትቶ ገሏል፡፡ ሁኔታው እንደተፈጠረ አባ ናትናዔል ግቢውን ትተው ቢሸሹም ጥበቃውና አንድ ካህን፣ እንዲሁም የሟች አስክሬን በፖሊሶች ተወስዷል፡፡

Tuesday, October 30, 2012

የቡቤ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን


(አንድ አድርገን ጥቅምት 20 2005 ዓ.ም)፡-  ቡቤ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሀብሮ ወረዳ ውስጥ ትገኛለች ፤ አካባቢው ደጋማ የአየር ንብረት አለው ፤ ወደዚህ ቦታ ለመድረስ ከአዲስ አበባ አዋሽ ፤ ከአዋሽ ቦርደዴ ፤ ከቦርደዴ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤ/ን በአዲሱ የገለምሶ መንገድ ቡቤ ኪዳነምህረት በማለት መሄድ ይቻላል ፤ ጠቅላላ ከአዲስ አበባ በ290 ኪሎ ሜትር አካባቢ ትገኛለች ፤ እዚህ አካባቢ የሚገኙ ምዕመናኖች ከ50 ዓመት በላይ አካባቢያቸው ቤተክርስትያን እንዲሰራላቸው በጽኑ ይፈልጉ ነበር ፤ በየጊዜው ቤተክርስትያን ለመስራት መቃኞ አቁመው ሲያበቁ በንፋስ ይፈርስባቸው እንደነበር ለማወቅ ችለናል ፤
የዘመናት ፍላጎታቸው ቤተክርስትያን ታንጾ ማየት ቢሆንም በአካባቢው ያለመረጋጋት ሁኔታ ቤተክርስትያን መስራት ሳይቻል እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል ፤ ቀድሞ ልጆቻቸውን ክርስትና ለማስነሳትና  ሰው ሲሞትባቸው ለቀብር ጉባ ቆርቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን መሄድ ግድ ይላቸው ነበር ፤ ጉባ ቆርቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ለመሄድ ቢያንስ ከአራት እስከ አምስት ሰዓት የሚወስድ የእግር መንገድ አለው ፤ አንድ የአካባቢው ክርስቲያን ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የቡቤ ቀበሌ ነዋሪዎች ይህን ክርስትያን ለመቅበር የአንድ ሙሉ ቀን ጊዜ ይወስድባቸው ነበር ፤ የተመቻቸ መንገድ እጦቱ እና አስከሬንን ለግብአተ መሬት ረዥም ርቀት ይዞ መሄድ ህዝቡን ምርር ያደረገና የዘወትር ችግራቸው ነበር ፤ ጠዋት ሶስት ሰዓት ላይ አስከሬን ይዞ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ቢያመሩ ቦታው ደርሶ ፍትሀት ተደርጎ እና ጉድጓድ ተቆፍሮ ግብአተ መሬት ፈጽመው ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ቀኑ ይመሻል  ፤ ይህ ሁሉ ክርስቲያኖች ሲሞቱ የሚደርስ እንግልት ለክርስትያኖቹ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ላይ የሚኖሩ ሙስሊም ማህበረሰቦችን የሚያሳስብ ጉዳይ ነበር ፤ ክርስትያኖቹ በአካባቢያቸው ልጆቻቸውን ክርስትና የሚያነሱበት ፤ በትምህርተ ሀይማኖት የሚያንጹበት ፤ ቀብር የሚፈጽሙበትና የተለያዩ አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተክርስትያን እንደሚያስፈልጋቸው ከከተማዋ ከንቲባ አንስቶ ክርስትያን የሆነውም ሆነ ያልሆነው ማህበረሰብ የተስማማበት ጉዳይ ነበር ፡፡

Monday, October 29, 2012

ለበረሃ ቤተክርስትያኖች መልዕክታችሁን አድርሰናል

(አንድ አድርገን ጥቅምት 19 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- በበረሀ ያሉትን ጥቂት አብያተክርስትያኖች ተመልክተናል ፤ ምዕመናን እንዲረዷቸው ለማድረግ ትንሽ ስራ በመስራት ጥቂት ብር አግኝተናል ፤ ይህን ብር ምን አይነት ነገር ላይ እንደዋለ ሰጪዎቹ ማወቅ ስላለባቸው ብሩ የተገዛበትን ንዋየ ቅዱሳት ዋጋቸው ያለበትን ደረሰኝ ብናቀርብ ሌሎች ለመርዳት ይነሳሳሉ የሰጡትም ሰዎች ብራቸው ምን ነገር ላይ እንደዋለ ይገነዘባሉ ፤ ለእነዚህ አራት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ለኮራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ፤ ለቦርደዴ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ፤ ለቡቤ ኪዳነ ምህረትና ለቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያናት የሚሆን ከ12 ኪሎ ግራም በላይ አንደኛ ደረጃ እጣን ፤ 5 ኪሎ ዘቢብ ፤ 500 ደረጃው የጠበቀ የሰም ጧፍ ፤ 2 ሞጣሂት፤ መስቀል እና ለቤተክርስቲያ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በመግዛት ወደ ቦታዎቹ ተልኳል ፤ ከሁለትና ከሶስት ቀን በኋላም ንዋየ ቅዱሳቱ ለአብያ ክርስትያናቱ ይደርሳቸዋል ፤ በዚህ አጋጣሚ የተረዳነው ነገር ቢኖር እጣንና ጧፍ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠርባቸው ለወራት ሙቀትን መቋቋም ሲችሉ ዘቢብ ግን በሙቀቱ ምክንያት በየጊዜው እንደሚበላሽ ፤ እንደሚሻግትና አገልግሎት የማይሰጥበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ነው ፤ በዚህ ምክንያት ዘቢብ በአንድ ጊዜ በርከት አድርጎ በረሀ ላይ ለሚገኙ አብያተክርስትያናት ከመስጠት ይልቅ ዘቢቡ ስያልቅባቸው እንዲገዙበት መግዣ ብሩን መስጠት ያለበለዚያ ደግሞ በየጊዜው እርጥብ የሆነ ዘቢብ ገዝቶ መላክ የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ 

Thursday, October 25, 2012

በርሀ ላይ ላሉት አብያተክርስቲያናት የተደረገ እርዳታ




 (አንድ አድርገን ጥቅምት 14 ፤ 2005 ዓ.ም)፡-ጊዜው ከሁለት ዓመት በፊት ነው ፤ ቦታው ሀረር ድሬዳዋ መንገድ አዋሽ አለፍ ብለው አውላላ በረሀ ላይ የሚገኙ አብተክርስቲያናት ናቸው ፤ ከነርሱም ውስጥ ኮራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፤ ቦርደዴ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን፤ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እና በቅርብ የተሰራችው ኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያና ናቸው ፡፡ ሁሉም አንድ የሚያደርጋቸው በርሀ ላይ መገኝታቸውና በጣም ጥቂት የሚባሉ ምዕመናን በመኖራው ነው ፤ በአራቱም ቦታ የሚገኙ ምዕመናን ቢደመሩ ሶስት መቶ አይሞሉም ፤ ሁሉም ለቤተክርስትያናቸው ያላቸው ቅንአትም አንድ ያደርጋቸዋል ፤  በወቅቱ ከአራቱ ሁለቱን ቤተክርስትያኖች የማየት እድል ገጥሞን ነበር ፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ካህን እንደገለጹልን ከሆነ ቅዳሴ ለመቀደስ ጧፍ አጥተው በኩራዝ ወንጌልን ያነበቡበት ጊዜ መኖሩን አጫውተውናል ፤ እነዚህ ቤተክርስትያናት ንዋየ ቅዱሳት የሚያገኙት በምዕመኑ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮ በሚዋጣ ጥቂት ገንዘብ አማካኝነት ነው፡፡ በየጊዜውም አሰበ ተፈሪ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ብር በመሰብሰብ ለቅዳሴ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አቅም በፈቀደ መጠን እንደሚያመጡላቸው ነግረውናል ፡፡ 

Tuesday, October 23, 2012

ላያቸው ተዋህዶ ፤ ውስጣቸው ተሐድሶ የሆኑ መጻህፍት




(አንድ አድርገን ጥቅምት 13 2005 ዓ.ም)፡- ባሳለፍነው ዓመት በወርሀ ግንቦት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ አንድ ወሳኝ ውሳኔ መወሰኑን ይታወቃል ፤ በውሳኔውም በርካቶች የተወገዙበት ቀሪዎቹ ደግሞ መዝገባቸው በይደር እንደቆየ የምናስታውሰው ነው ፤ በጊዜው  በፕሮቴስታንቶች እየተደገፉ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት፣ ክርስቲያናዊ ትውፊትና ታሪክ በኅቡእና በገሃድ ተደራጅተው ለማፍረስና ለማፋለስ እየተንቀሳቀሱ  ድርጅቶች ፍጹም ውግዘት የሚገባቸውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ማኅበራትና ግለሰቦች በመለየት ማኅበረ ሰላማ፣ ማኅበረ በኵር፣ የምሥራች አገልግሎት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት፣ አሸናፊ መኰንን፣ አግዛቸው ተፈራ፣ ጽጌ ስጦታው እና ግርማ በቀለ የመሰሉት ሰዎችና ላያቸው ማር የተቀቡ ውስጣቸው ግን ነጣቂ የሆኑ ተቋማት ተለይተው መለየታቸው ይታወቃል፡፡


በጊዜው የተወገዙት ሰባቱ  ድርጅቶች ውስጥ  ከሣቴ ብርሃን ፤ ማኅበረ ሰላማ ፤  የምሥራች አገልግሎት ፤ የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር ፤  አንቀጸ ብርሃን (ከድርጅቱ ጋራ አሸናፊ መኰንንና ዳንኤል ተሾመ) ፤ የእውነት ቃል አገልግሎት ፤ ማኅበር በኵርና የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት ይገኙበታል ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ከተወገዙት 16 ሰዎች  የክህነትና የክብር ማዕርጋቸው ተሽሮ የበፊቱ አቶ የሚለው ስም ከተመለሰላቸው ውስጥ በግንባር ቀደምነት  አቶ አሸናፊ መኰንን ይገኝበታል፡፡

ይህ ሰው ለዘመናት ኦርቶዶክሳዊ በመምሰል የእኛ ያልሆነ ትምህርት ኑፋቄ የተቀላቀለበት መጽሃፍቶችን በመጻፍ በርካታ ብሮችን መሰብሰብ ከመቻሉም በተጨማሪ ምንፍቅናውን በበርካታ መጽሃፍቶች መዝራት ችሏል ፤ አሁን ግን ይህ ሰው ስራው ታውቆበት ከቤተክርስትያን ከተባረረም በኋላ የመጽሀፍት ነጋዴዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መጽሀፍቶቹ ከትክክለኛ መጽሀፍቶች ጋር በመደባለቅ በገበያ ላይ ይዘዋቸው  ይገኛሉ ፤ ስለዚህ ምዕመናን የዚህን ሰው ትምህርት እና መንገድ ቤተክርስትያን ስላወገዘች መጽሀፍቶቹን እና ትምህርቱን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንዲሉ “አንድ አድርገን” መልዕክቷን ታተላልፋለች፡፡ ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ መጽሀፎቹን ላያቸው ተዋህዶ ፤ ውስጣቸው ተሐድሶ የሆኑ መጻህፍት የፊት ሽፋን በመውሰድ በቀላሉ መለየት እንድትችሉ በዚህ መልክ አቅርበንላችኋል፡፡”የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።” የማቴዎስ ወንጌል 7፤15

እነዚህ ሁሉ መጻህፍት በአቶ አሸናፊ የተጻፉ ናቸው ፤ ስለዚህ የምንሰማው ስብከት እና የምናነባቸው መንፈሳዊ መጻህፍት የእነማን እንደሆኑ ለይተን ማወቅ መቻል አለብን ፡፡

እነዚህ በጣም ጥቂቶች ናቸው..ሌሎቹን በሌላ ጊዜ እናቀርባለን

Monday, October 22, 2012

በግብፅ የፓትርያርክ ምርጫ አምስት ኢትዮጵያውያን ድምፅ እንደሚሰጡ ታወቀ

በሔኖክ ያሬድ(Reporter)

ባለፈው መጋቢት ያረፉትን የግብፅ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳን የሚተኩትን አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥ ከመጨረሻዎቹ አምስት ዕጩዎች ሦስቱን ለመለየት በሚደረገው አገራዊ ምርጫ አምስት ኢትዮጵያውያን ድምፅ እንደሚሰጡ ታወቀ፡፡
የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅሶ አልመስሪ አልዩም በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ የመጨረሻዎቹ ሦስት ዕጩዎች ለመለየት ድምፅ የሚሰጠው ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡

ምርጫውን ከሚያከናውኑት 2,405 መራጮች ውስጥ በግብፅ የምትገኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አምስት ተወካዮች እንደሚገኙበት አስያ ኒውስ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡

ሌሎቹ መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ መላው አባላት፣ በግብፅና በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የምዕመናን፣ የካህናትና የመነኮሳት ተወካዮች ናቸው፡፡ ተጠባባቂ ፓትርያርኩ አቡነ ጳኩሚየስ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ ለፓትርያርክነት ለመወዳደር ከቀረቡት 17 አባቶች ውስጥ አምስቱን የመረጠው ሁለቱን ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሦስቱን ደግሞ ከመነኮሳት መካከል በመለየት ነው፡፡ በዕድሜ ትልቁ 70 ሲሆን አነስተኛው ደግሞ 49 ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና በአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ድንጋጌ መሠረት ከመጨረሻዎቹ ሦስት ተወዳዳሪዎች አሸናፊ ሆነው ለፓትርያርክነት የሚመረጡት የሚለዩት በዕጣ ነው፡፡ እስክንድርያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል እሑድ ጥቅምት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ከሦስቱ አንዱ ፓትርያርክ ሆኖ የሚመረጠው ዓይኑ በጨርቅ የተሸፈነው ሕፃን ዕጣውን ካወጣ በኋላ ነው፡፡

Thursday, October 18, 2012

የቤተክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ዕውቅና እንዲያገኝ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ

በታምሩ ጽጌ(reporter)


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት መንፈሳዊ ጉዳዮችን የምትከታተልበት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የሚያገኝበት ሁኔታ መመቻቸቱንና ለተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ እየተመረመረ መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ያለው ግንኙነትና እንዴት ማጣጣም እንደሚቻል ረቂቅ ሕጉ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ በትናንትናው ዕለት የተጀመረውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ 31ኛ መደበኛ ስብሰባን አስመልክቶ የቤተክህነቱ የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረክርስቶስ፣ ‹‹ቤተክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አላት፡፡ መንፈሳዊ ቦታ በመሆኗ ግን እስር ቤት የላትም፡፡ ፖሊስም የላትም፡፡ ፍርድ ቤቱ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራው መንፈሳዊ ተግባራትን ነው፤›› ብለው፣ የተጋጩ ሰዎችን በእርቅና በስምምነት እንዲፈቱ ማድረግ ነው፣ ከመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ውጭ የሆነ ጉዳይ ካጋጠመ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

Wednesday, October 17, 2012

ቂል የያዘው ሰይፍ




(ፕሮፌሰር መስፍን ጥቅምት 2005 ዓ.ም):-  በቅርቡ አቶ ስብሐት በአደረገው ቃለ መጠይቅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሾመው ወያኔ ዱሮም አስቦበት ወንበሩን ከአማርኛ ተናጋሪዎችና ከኦርቶዶክስ አማኞች ለማጽዳት በተዘጋጀበት እቅድ ነበር ብሎአል፤ ልብ ላለው አነጋገሩ በሁለት በኩል ስለት ያለው ቂል የያዘው ሰይፍ ነው፤ ከፊት ለፊት የተሰነዘረው አማርኛ ተናጋሪውንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኙን ለመምተር ነው፤ ቂል የሚያደርገው አማራ የሚባል ጎሣ ቢኖርም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በአማርኛ ተናጋሪዎች ታጥሮ ትግሬንና ኦሮሞን፣ ወላይታንና ጉራጌን፣ ሌሎችንም የማይነካ መስሎት ከባድ ስሕትት ላይ መውደቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ እሱን የሚያህል ሰው የተክለ ሃይማኖትን ታሪክ አለማወቁ ያሳዝናል፡፡

አማራንና የኦርቶዶክስ ተከታዮችን መትሮ ሲመለስ ደግሞ ሰይፉ የሚቀላው ወላይታንና ጴንጤነትን፣ ምናልባትም እስልምናን ይሆናል፤ አቶ ስብሐት በፊት ለፊት የተናገረው ገና የዛሬ ሀያ አንድ ዓመት ‹‹እንዳያንሰራራ አድርገን አከርካሪቱን እንሰብረዋለን›› ተብሎ ያለቀለትን አማራ ዛሬ ወንበር ማጣቱን ለማብሰር አልነበረም፤ ይህ በጣም ግልጽና ከማንም ያልተሰወረው እውነት ነበር፤ ስውር ዓላማም አለው፤ ያንን ብዙ ሰው አይገነዘበውም ይሆናል፤ በአቶ ስብሐት አነጋገር ውስጥ ዋናውና ተንኮልን ያዘለው ዓላማ ወንበሩን የያዘው ዋናው የወላይታ ጴንጤ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ እስላም መሆናቸውን ለመናገር ያለው ፍላጎት ላይ ነው፤ ከአቶ ስብሐት ነጋ በቀር የአዲሶቹን ሹሞች ዘርና ሃይማኖት ከጉዳይ ያስገባ ያለ አይመስለኝም፤ አቶ ስብሐት በፊት-ለፊት ዓላማው ተስፈንጣሪ ተራማጅ ሲመስል በስውሩ የተንኮል ዓላማው ግን ኋላ-ቀር ወግ-አጥባቂ ይሆናል፤ በዘርና በሃይማኖት ላይ ሲያተኩር ዋናውን ቁም-ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ ሰዎች፣ ከዚያም ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ፈጽሞ ዘንግቶታል፤ ለእኛ ትልቁ ነገር ይህ ነው፤ በሁለታችን መሀከል ያለው ልዩነት ስብሐት ኢትዮጵያውያንን የሚያዛምዳቸውን ሁሉ አያይም፤ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን የሚለያያቸውን ሁሉ አላይም፡፡


መጥፎ ልማድ 

(አንድ አድርገን ጥቅምት 7 2005 ዓ.ም)፡- የዛሬ ዓመት ግድም ቅዱስ ሲኖዶስ መርጦ ያስቀመጣቸውን ብጹአን አባቶቻችንን አቶ ስብሐት ተነስቶ የስድብ ውርድብኝ ሲያወርድባቸው ቤተክርስትያኒቱንም ሆነ አባቶችን ወክሎ መናገር የደፈሩ አባቶችን አልተመለከትንም ፤ “ቤተክርስትያኒቱ በጳጳሳቱ አማካኝነት ገደል አፋፍ ላይ ናት” ፤ ጳጳሳት እንዲህ ናቸው…” በማለት አቦይ ስብሐት ሲናገር መልስ የሰጠ አካል አልነበረም ፤  ሰውየው ሳይናገር ሳይሆን ተናግሮ እንደሚያስብ የሚያውቁት ይናገራሉ ፤ ይህ የመሰለው ያለአግባብ ዘለፋ በምዕመኑ ዘንድ የሚያሳድረውን የውስጥ መሰበር ማንም አልተመለከተውም ፤ አፉን ለከፈተ ሁላ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ብጹአን አባቶች መልስ ይስጡ እያልን ሳይሆን ከአንድ ትልቅ የሚባልና የመንግስትን ቁልፍ ቦታ የያዘ ሰው ያለ አግባብ ንግግር በቤተክርስቲያን እና በአባቶች ላይ ሲናገር ግን ዝም ተብሎ መመልከት ያለበት አይመስለንም ፤ የተሰደቡት አባቶች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ጭምር መሆናቸው መዘንጋት የለበትም ፤ ዝምታችንን ጥቅሙንና ጉዳቱን በአግባቡ ያወቅነው አይመስለንም ፤ “ዝም አይነቅዝ” የሚለው የሀገራችን ብሂል የሚባልበት ቦታ እንዳለ ሁላ ዝምታም የሚነቅዝበት ውሎ አድሮም ችግር የሚያመጣበት ሁኔታም እንዳለ መዘንጋት መቻል የለብንም ፤ 


በየጊዜው ከመንግስትም ይሁን ከተለያዩ አካላት የሚነሱትን ዘለፋዎች እና ስም ማጥፋቶች በጊዜው መልስ መስጠት ካልቻልን ውሎ አድሮ የምንሰጠው ምላሽ ውሃ ያዘለ ላይሆን ይችላል የሚል እምነትም ስላለን ጭምር ነው ፤ እስከ አሁን ድረስ ቤተክርስቲያኒቱ ስትሰደብ ዝም ፤ ጳጳሳቱ ሲሰደቡ ዝም ፤ ማህበራት ስማቸው  ሲጠፋ ዝም ፤ ምዕመኑም ስም እየተሰጠው ሲንገላታ ዝም ካልን ነገ ህዝቡ ላይ የሚያመጣው Psychological impact ሊናጤነው ይገባል ፤ ሰው ዝም ሲል ሁለት አይነት ምልከታ አለው አንድም “ጉዳዩ አያገባኝም ፤ ጉዳዬም ጉዳዬ አይደለም” በማለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጡ እየተቃጠለና በነገሩ እየተንቦገቦገ አቅም ስለሌለው ብቻ ዝም ማለቱ ነው ፤ ብዙዎች በየትኛው ውስጥ እንዳሉ ማወቅ አዳጋች አይሆንም፡፡