+++
(ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባሳለፈው ውግዘትና ውሳኔ ተንተርሶ ውይይትና ምክክር ድርጓል!
የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳም በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሶዶ ዳጩ ወረዳ፣ ሀሮ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሦስት ግለሰቦች መሪነት ቀኖና ቤተክርስቲያንን በጣሰ፣ በሕገ-ወጥ እና ኢ-ሲኖዶሳዊ በሆነ ድርጊት የ፳፮ መነኰሳትን "የኤጲስ ቆጶስነት" ሢመት በመስጠትና ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ መመደቡን ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጥር 18/2015 ዓ/ም ባስተላለፈው የውግዘትና ባለ ፲፪ ነጥብ ውሳኔ መሆኑን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ ገልጸዋል።
ድርጊቱም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣የጥንታዊት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ያቆሰለ፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ያሳዘነ መሆኑን ገልጸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ እንደሚደግፋ ተናግረዋል።
በውይይቱ የተገኙት ተሳታፊዎችም ውሳኔውን እንደሚደግፉ ገልጸው ለትግበራው በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ በተፈጠረው ድንገተኛ ክስተት በእጅጉ ማዘናቸውን በመግለጽ ፈተናው ይቀጥላል እኛም ነቅተን ቤተ ክርስቲያናችን እንጠብቃለን ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በሁለት ማልያ የሚጫወቱ እንዳሉ በመጥቀስ በሁለት ማልያ የሚጫወቱ አካላት ከድርጊታቸው ካልተመለሱ እንደማይታገሱ በመግለጽ በድርጊቱ ተገኝተውም ሆነ በተለያየ ምክንያት የተሳተፉት ሁሉ ንስሐ ገብተው ከድርጊታቸውን እንዲቆጠቡና ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል።
አክለውም ብፁዕነታቸው ሁሉም ነቅቶ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠብቅ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የውይይትና ምክክር መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።
በውይይቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሄኖክን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የ7ቱ ክፍላተ ከተሞች ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች፣ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ የሁሉም ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
በመ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ፦ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ
No comments:
Post a Comment