---------------------
ከፍለህ የማትጨርሰው ውለታ አለብህ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገር፥ ታሪክ፥ ሚስት ጠብቃ የኖረች ገመና ከታች ናት።
፩ . . . ሐገር
ቋንቋ፥ ማንነት፥ ፊደል፥ ነፃነት ወዘተ ያለው ሐገር ሰጥተሃለች፡፡ የምትባጠስበትን ጓዳዋ እየነደደ ጠብቃለች፡፡ ከጠላት ተሞዳሙዳ ሐገር የወጋችበት እድፋም ታሪክ የላትም፡፡ ብሄሬ፥ ቋንቋዬ፥ ማንነቴ ቅብርጥሶ የምትለው፤ አንተ ጋ የደረሰው እሷ እየነደደች ነው፡፡
ቤተክርስቲያኒቱ ዓ/ዓቀፍ ነበረች፡፡ ከግብፅ፥ ከሮም፥ ከባዛንታይን፥ ከግሪክ ተላልሳ፥ ቋንቋህን፥ መሬትህን፥ ታሪክህን ልትፖሽርልህ ትችል ነበር፡፡ አላደረገችውም፡፡ በእቅፏ ያሉትን ዜጎች ጠብቃ ይዛለች፡፡ ይሄ ዥልጥ ፒፓ በየዘመኑ ርስ በርስ ሲናከስ መሃል ነበረች፡፡ ያላት የመከራ ታሪክ እንጂ የአሸሼ ገዳሜ አይደለም፡፡
፪ . . . ታሪክ
ኦቦሌሴ ብራና ዳምጣ፥ ቀለም ጨምቃ፥ መድሀኒት ምሳ ለዛሬ አድርስሃለች፡፡ ግደይ፥ ቶሎሳ፥ ኢብሳ፥ ዣንጠረር፥ እርገጤ፥ ፔን፥ ኡጁሉን አልቀማችህም፡፡ ጠብቃልሃለች፡፡ በለስ በቀናው ወራሪ ባህል ከመኖር ታድጋሃለች፡፡ እሷን ሲያወድሙ ግዜ አግኝተህ ተከላክልሃል፡፡ ለዛሬ ደርሰሃል፡፡
ያንተን የዕልቂት፥ የጥጋብ፥ የረሃብ ዘመን ከትባለች፡፡ አልከፈልካትም፥ አላስተማርካትም፥ አልነገርካትም፡፡ አንተ ስትኖር እሷ እንደምትኖር ስለምታውቅ ነው፡፡ ኦቦሌሴ የመጣህበትን ድልድይ አትስበር፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ትናንትህ ነች፡፡ የሃገሪቱ ትውስታ ጉያዋ ስር ነው፡፡ ያለ ትውስታ ብሄር፥ ሃገር፥ ቋንቋ፥ ማንነት ወዘተ አይቆምም፡፡
፫ . . . ሚስት
"ሃይማኖትህን፥ ሚስትህን፥ ሐገርህን ጠላት ሊቀማ መጥቷል" ንቃ፥ ተበላህ የምትል ብቸኛ የሃገሪቱ ተቋም ነች፡፡ ውብ ሴቶችህ የአንተን ድድብና የሚታገሱት ከሷ በወረሱት ጨዋነት ነው፡፡
*
4ኛ መቶ ላይ ነው፡፡ ዲያቆን አትናቴዎስ ይባላል፡፡ ከአርዮስ ጋ በሃይማኖት ተከራከሩ፡፡ አትናቴዎስ ረታ፡፡ በመጨረሻም "እኛ አርዮስን አንጠላም፥ ትምህርቱን ግን እንጠላለን" አለ፡፡ ኦቦሌሴ አንተን አልጠላም፡፡ መንገድህን ግን እፀየፋለሁ፡፡
*
ጌታው ነገስታቱ፥ መሪዎች፥ ባለስልጣናት ሲገሉህ፥ ሲዘርፉህ፥ ሲወጉህ ስትችል "ተዉ" ብላለች፡፡ ሳትችል ዱላው ወደ ራሷ ዞሯል፡፡ የጥጋበኛ ውሪ ክንድ ሲደቁሳት ኖሯል፡፡ አልፋለች፡፡ ማለፍ ታውቃለች፡፡ ልምከርህ ጌታዬ እ ረ ፍ !
✍️ Natnael Hawk
No comments:
Post a Comment