Sunday, February 5, 2023

ድርድር የሚባለውን ነገር መሸሽ ግትርነት ሊሆን ይችላል?


ኦርቶዶክሳዊ ያልሆኑት ሁሉ ነገራችን በውል እንዲረዱት የቀረበ ትሑት ማብራሪያ።

  (ብርሃኑ  አድማስ አንለይ)

ብዙዎች በቅንነት ድርድር ምን ችግር አለው? መንፈሳዊ ሰዎች እንዴት ይህን እንቢ ሊል ይችላል? መነጋገር ምንድን ነው ችግሩ? እነዚህ እና ተመሳሳይ አሳቦችን አለመቀበል እንዴት እነካለሁ የሚል የአለመደፈር ስሜት የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉ ከአንዳንድ አስተያየቶች መረዳት ችያለሁ። ስለዚህ ድርድርን መቀበል ለምን አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት ጉዳዩ ምን እንደሆነ ማስረዳት እፈልጋለሁ።

ቤተ ክርስቲያናችን ተጥሷል ብላ ውግዘት ለመፈጸም ምክንያት የሆናት የትኞቹም ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚጠቀሙበት መንፈሳዊ ሕግ መጣሱ ነው። ይህ ሕግ አማኞች በልቡናቸው የሚያምኑትን ረቂቅ እምነት በተግባር በሥርዓተ አምልኮት የሚፈጽሙበት መንፈሳዊ ሥርዓት ማለት ነው። ይህ ሕግ ምን ምን እንደሚያካትት በዝርዝር ማስረዳት ባይቻልም ምን እንደሆነ ለመረዳት እንዲያግዘን ትንሽ ልዘርዝርለት ። ለምሳሌ የጾም ወቅቶችን ፣ ቀኖቹን እና ሰዓቱን የሚመለከተው፣ ቅዳሴ መቼ እንዴት በእነማን እንደሚቀደስ ፤ የክርስቶስ ዐበይት በዓላት እነማን እንደሆኑና እንዴት እንደሚከበሩ፣ ሥርዓተ አምልኮት የሚመሩ እና ቤተ ክርስቲያንን በማስተማርም ሆነ በማስተዳደር የሚያገልግሉ ካህናት እንዴት እንደሚሾሙ እና እንዴት እንደሚሻሩ፣ በስሐተት እና በኃጢአት የወደቁ ሰዎች እንዴት እንደሚመለሱ፤ ይህንን የመሳሰሉትን ብዙ የሥርዓተ አምልኮት ነገሮች በዝርዝር የያዘ መንፈሳዊ ሕግ ነው። 

ሰሞኑን የገጠመን ኤጲስቆጶሳትን መሾም እና በሀገረ ስብክት መመደብ የተመለከተውን ዋና የሥርዓተ አምልኮታችን ምሰሶ የሆነውን አስተምህሮ እና ቀኖና የተመለከተ ጥሰት ነው። ይህ ሲያጋጥም ምን እንደሚደረግ እና እንዴት እንደሚፈታ ሁሉ ደግሞ አሁንም ሥርዓቱ አስቀድሞ ደንግጎ እና አስቀድሞም አውግዞ ተቀምጧል። በየዘመኑ የሚደረገው ያንን መፈጸም እና ማስፈጸም ብቻ ነው።

ታዲይ ይህ ነገር ለድርድር እንደማይገባ በዚሁ የቀኖና መጻሕፍት ከተደነገጉት ውስጥ አንድ ሁለቱን ምሳሌ አድርጌ ላስረዳ። ለምሳሌ ያህል አጽዋማትን የተመለከተውን ላንሳ። ለምሳሌ አንድ ሊቀ ጳጳስ ብድግ ብሎ ዐርብ እና ረቡዕን መጾም አይገባም። ዐቢይ ጾምንም ለሃምሳ አምስት ቀናት ሳይሆን ለዐሥራ አምስት ቀናት ይበቃናል። ትንሣኤንም እሑድን ጠብቀን ማድረግ አይጠበቅብንም። ወቅቱንም ብንፈልግ በመስከረም ካልሆነም በጥር እንዳመችነቱ ማድረግ እንችላለን። ዋናው ዐቢይ ጾምን መጾማችን ብቻ ነው የሚበቃው። ይህን ቢያደርግ ይህን ያለው ሊቀ ጳጳስ በአጭሩ ሌላ እምነት መሥርቷል ማለት ይቻላል። ይህን ያደረገ ጊዜ በራሱ ፈቃድ ከነባሩ ኦርቶዶክስ ራሱን ለይቷል። የቀኖና መጽሐፋችን ደግሞ ይህን የሚያደርገውን ገና ቀድሞ አውግዞታል። የአሁኑ ሲኖዶስ ደግሞ ይሰበሰብና ይህን ለማስጠበቅ የተሾመው ጳጳስ ራሱ ስለሻረው ያን የቀደሙ አባቶች የፈጸሙት ውግዘት በተግባር ይፈጸምብሃል ይልና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ይለየዋል፣ ሥልጣኑን እና መዓርጉንም ይቀማዋል። 

ይህ ከሆነ በኋላ አሁን እንደሚባለው መንግሥት መጥቶ ይህ ምን ችግር አለው፣ በንግግር ይፈታል ቢል አባቶች እና አማኞች የምንለው ይህ ለድርድር አይቀርብም ነው። ምክንያቱም ዐርብ እና ረቡዕን የመሻር ወይም እንዲሻሩም ሆነ እንዲቀጥሉ የመደራደር ሥልጣን ያለው አካል የለም። ዐቢይ ጾምን በ55 ቀናት እና በ15 ቀናት መካከል ተደራድሮ 30 ወይም 45 ቀናት ብቻ የማድረግ ሥልጣን ያለው የለም። ትንሣኤን ከእሑድ ውጭ በሌላ ቀናት ቀርቶ የሚያዚያ ጨረቃ ሙሉ ከመሆኗ በፊት ባለው ሌላ እሑድ ውስጥ እንኳ ያደረገ ቢኖር ከሥልጣኑ ይሻር ነው የሚለው ቀኖናው። የመሰላችሁን ፍረዱበት እንኳን አይልም። ይህም ማለት ፍርዱ ያለቀ የደቀቀ ሆኖ በየዘመኑ የሚኖረው ሲኖዶስ ሥልጣኑ ያንን ተገባራዊ ማድረግ ብቻ ነው። 

ለሌሎቻቸሁ ድርድር አይቻልም የሚለው ያልገባቸሁ ክህነት መሾም ልክ እንደ መንግሥት ሥልጣን ስለመሰላችሁ በድርድር የሚያልቅ መስሏችሁ ሊሆን ይችላል። ነገሩ ልክ እላይ የገለጽኩት ዓይነት ብቻ ነው። ልክ ይህ ገብቷቸው ወይም በብዙዎች ዘንድ ይህ መሆኑ አለመታወቁን ጥላ አድርገው መሒዳቸውን ትተው አጥፈተናል ሲሉ ጥለውት ከወጡት ኦርቶዶክስነት ይመለሳሉ። ያኔ ነው መነጋገር የሚቻለው። ሀሳቡን ግልጽ አድርጌው ከሆነ ጉዳዩ ይህ መሆኑን እንድትረዱት እፈልጋለሁ። ልክ እንደሌላ መዋቅር አይደለም ያልነው ለዚህ ነው። ይህ የግትርነት ሳይሆን የእምነት ሕግን የመፈጸም እና ያለመፈጸም ጉዳይ ነው ማለት ነው። 

በአጭር ቋንቋ ኦርቶዶክስ እና ሄትሮዶክስ የመሆን ጉዳይ ነው። በእነዚህ መካከል ድርድር መደረግ ይችላል ማለት በፕሮቴስታንት እና በእስልምና መካከልም ይቻላል እንደማለት ያለ መሆኑን በውል መረዳት ተገቢ ነው።

መንግሥት ለምን አስከፋን ካላችሁ? በዚህ ውስጥ ገብቶ ላደራድር፣ እኔ የምሰጠውን ምክርም ስሙ ማለት ቅዱሳን በሠሩት ቀኖና ላይ እኔ የምሰጠው ሀሳብ ሥልጣን ይኑረው ማለት ስለሆነ ይህ ፍጹም ክህደት ነው። ሁለተኛ እነዚህ ሰዎች በቀኖናው መሠረት ተወገዙ እንጂ ሌላ እምነት እንዳይመሥርቱ የከለከላቸው የለም። የጎሣ ኦርቶዶክስ መመሥረትም መብታቸው ነው። ይህን ወደ ኦርቶዶክስ ለማስገባት መሞከር ግን ክህደት ነው፣ የተወገዘ ነው። ሦስተኛ አሁን መንግሥታዊ አካላት እያደረጉት ያሉት ከኦርቶዶክስ ወጥተው አዲስ ለተቋቋሙት ሌላው ቀርቶ ሕጋዊ ሰውነት እንኳ ለሌላቸው የኦርቶዶክስ የሆኑትን መቅደሶች፣ መንበረ ጵጵስናዎች እና ቢሮዎች በጉልበት እየቀሙ እየሰጡ ነው። ይሄ የእኛ የኦርቶዶክሶች ነው፤ እነርሱ እምነታቸውን ሰብከው ካፈሩት ምእመን ልክ እንደ ፕሮቴስታንት የራሳቸውን ይሥሩ ሲል እየገደለ፣ እያሠረ ፣ እየቀማ እየሰጠ ነው። የተጠየቀው ቀላል ጥያቄ ነው። የኦርቶዶክሶችን ለሄትሮዶክሶች ለምን በጉልበት ትሰጣለህ የሚል ቀላል ጥያቄ ነው።

እነዚህን ሰዎች እንደሆኑት ሆነው ተቀብላችሁ አብራችሁ አገልግሉ ማለትም በኦርቶዶክስ መቅደስ ፓስተሩ፣ በመስጊድም ቄሱ ይባርክ ከሚለው ምንም ልዩነት የለውም። ልብሱን ስለለበሱ አሁን ኦርቶዶክስ አድርጋችሁ እንዳትቆጥሩ። ይህን የምንለው እነርሱን በመጥላት እና በመናቅ አይደለም። ይህ እንዳልሆነ የምናመልከው አምላክ እርሱ ልዑል እግዚአብሔር ያውቃል። ይህን የምንለው ጉዳዩ መሠርታዊ የሥርዓተ አምልኮት ጥሰት መሆኑን በገላጭ ምሳሌ እንድትረዱት ብቻ ነው።

እግዚአብሔር ያሳያችሁ!! እንዲህ ያለ በደል በየት ሀገር በማን ላይ ተፈጽሞ ያውቃል? ታዲያ እምነቴን አትንካ፣ የሃይማኖት ተቋሜንም ለማያምኑበት አሳልፈህ አትስጥብኝ። ይልቁንም ሕግ አስከብረህ ከብጥብጥ አድነኝ ስለው በሁሉም በኩል እውነት አለ ማለት ምን ማለት ነው? ግትርነትስ የሚሆነው እንዴት ሆኖ ነው። ጉዳዩ ይሄው ነው። በሕያው እግዚአብሔር ስም እመሰክራለሁ ሌላ ምንም ነገር የለውም። ሀገር ወዳድ፣ እውነት ወዳድ የሆናችሁ ሁሉ ከመተቸታችሁ እና አስተያየት ከመስጠታችሁ በፊት ይህን ነገር በውል ተረድታችሁ እንድታስረዱ በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁ። አስተዋይ ኅሊና ያለው ሁሉ አይቶ ይፍረድ።

በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሻሸመኔ እስራትና ውክቢያው ቀጥሏል። ሀገረ ስብከቱን በወራሪ ለመመዝበርና ሰብሮሮ ለመቆጣጠረር እየተሞከረ ነው።


+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ብርሃኑ ወልደ ዮሐንስ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኢኦተቤ በስልክ እንደገለጹት ፣ ዛሬ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋትወደ ምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት የጸጥታ አካላት በመምጣት የሀገረ ስብከቱን  ሠራተኞችን ከሥራ በማስወጣት ሀገረ ስብከቱን ግቢ  ከሠራተኞች ነጻ እንዳደረገው ገልጸዋል።
ፖሊስ በአርሲ ነገሌ አራት የደብር አስተዳዳሪዎችን ሕገ ወጡን ቡድን ተቀበሉ በማለት ሲያስገድድ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን ነን በማለታቸው አራት አስተዳዳሪዎች ታስረዋል ብለዋል።
በመንበረ ጵጵስናው አብያተክርስቲያናት በታጠቁ ኃይሎች በፓትሮል በመዞር ምእመናኑን በማስፈራራት ላይ ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ 
ትናንት ምሽት በጸጥታ ኃይሎች የታፈኑት የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ ሊቀ ልሳናት ቀሲስ ወንድወሰን ጥላሁንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው መምህር ሰሎሞን ዘገየ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከበላይ ታዘን ነው በማለት በዛሬው ዕለት በድጋሚ  መታሠራቸውን እርሳቸውም ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነና የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ወደ ጽሕፈት ቤቱ እንዳይገቡ መከልከላቸውን አስታውቀዋል።
ሁነቱን ለዘረፋ ሊጠቀምበት ያሰፈሰፈ ኃይል አለ የዞኑ መንግሥት ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል በሃይማኖታችን ሊያስገድደን አይገባም ብለዋል። ትላንት አብረናቸው ሥንሰራ የነበሩ የፀጥታ አካላት እናዝናለን ግን ከበላይ ታዘን ነው በማለት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እየገለጹልን ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በሕገ ወጥነትና በዘረፋ ምእመናንን ማገልገል እንዴት ይቻላል? ሲሉ ጠይቀዋል። እኔም የአካባቢው ተወላጅና በኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎት የምሰጥ ነኝ ጉዳዩ ቤተክርስቲያንን ለሌላ ሃይማኖት መጠቀሚያ ለማድረግ የተሴረ ሴራ ነው ብለዋል። ሁሉም ወረዳዎች ሕገወጡን ሢመት አውግዘው በቅዱስ ሲኖዶሱ ሥር መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሻሸመኔ በሕገ ወጡ ሲኖዶስ የተሾመው ግለሰብ የወንጌላውያን አማኝ የሆነችው ዘጸአት አፖስትሊክ ቸርች የኪራይ ስምምነት አለኝ ስትል መግለጫ ያወጣችበት ግለሰብ መሆኑ ይታወሳል።
ሥራ አስኪያጁ የሰጡትን መግለጫ ከቆይታ በኋላ በዩቲዩብ ገጻችን ማግኘት ይቻላል።
EOTC TV
++

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሻሸመኔ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በትናንትናው ዕለት በጸጥታ ኃይሎች በተወሰደው እርምጃ የተጎዱ ምእመናንን ጎብኙ።


የሻሸመኔ ኦርቶዶክሳውያን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት የሕገ ወጡን ቡድን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አናስገባም በማለት ቅጽራቸውን ሲጠብቁ ቢውሉም ለሕገ ወጡ ቡድን ከለላ የሰጠው የጸጥታ ኃይል በንጹሃን ላይ እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።

በዚህም ሰማዕትነትን የተቀበሉ ምእመናን እንዳሉ ሁሉ በርካቶች ከፍታኛ እና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሐዋሳ የተለያዩ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

እስካሁን ባለን መረጃም በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል 6፣ በያኔት ሆስፒታል፣ በአላቲዮን ሆስፒታል 8 ምእመናን ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ።

የሲዳማ፣ ጌዲዮ፣ አማሮ፣ ቡርጂና ምዕራብ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የጆርጂያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እነዚህን ምእመናን በሐዋሳ በመገኘት አጽናንተዋል፤ ሀዘናቸውንም ገልጸዋል።
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ምንጭ
የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት

Sunday, January 29, 2023

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ


***********************
ጥር ፳፩ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም 
""""""""""""""""""""""""""
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ 
**************
የመግለጫው ሙሉ ቃል እነሆ፦

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ለሚመለከተው ሁሉ
እሁድ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሦስት ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት በተፈጸመው የሕግ ጥሰት 26 ኤጲስ ቆጶሳት በመሾማቸው፣ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቋሚ ሲኖዶስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ላሉት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት አስቸኳይ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው አባቶችም በቅጽበት ደርሰው ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ አድርገው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት ከላይ በተጠቀሰው ኢሕጋዊ ድርጊት ላይ ውሳኔ ማሳለፋቸው በዚያው ዕለት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም በተላለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ በሰፊው ተገልጿል፡፡
መግለጫውን ያዳመጡ በውስጥም በውጭም ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ሁሉ ብርቱ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት እና መንፈሳውያን ተቋማት ድጋፋቸው ከመግለጻቸው በላይ የታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ኅብረት ተጠብቆ እንዲኖርም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

እኛም ድጋፋቸውንና መልካም ምኞታቸውን ስለገለጹልን የላቀ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን፤ ምስጋናችን በያሉበት ይድረሳቸው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂዎች የክርስትናና የእስልምና መሪዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው ድንገተኛ ክስተት ተደናግጠውና ተጨንቀው መጥተው የችግራችን ተካፋይ መሆናቸውን በመንፈሳዊ ስሜት ገልጸውልናልና ምስጋናችን ይድረሳቸው፤ እግዚአብሔርም ያክብራቸው እንላለን።

አሁንም በድጋሚ ለመንግሥትና ለሰፊው ሕዝባችን የምናስተላልፈው የአደራ መልእክት አለን፤ እሱም፡-
1. የታሪካዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት (ቀኖና) እንዲከበርልን፤
2. ጸጥታ እንዳይደፈርስና የንጹሐን ክርስቲያን ደም እንዳይፈስ ከወዲሁ ብርቱ ጥንቃቄ የተመላበት ጥበቃ እንዲደረግ በእግዚአብሔር ስም በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡

            ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ 
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም 
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

Saturday, January 28, 2023

የቤተ ክርስቲያኑ ምርቃት ወደ ሌላ ቀን መዘዋወሩንም የደብሩ አስተዳዳሪና አሠሪ ኮሚቴው ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይፋ አድርገዋል።

የጂማ ኦርቶዶክሳውያን በዛሬው ዕለት ለዓመታት የለፉባትንና ቅዳሴ ቤቷ ይከበራል ተብሎ በተጠበቀው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ሲጠብቁ ቢውሉም ከአባታቸው ጋር ሳይገናኙ ቀርተዋል። 

የጅማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በስፍራው ስለማይገኙ ቆሞሳት ባርከው ቤተ ክርስቲያኗ ትመረቅ ቢባሉም ምዕመናኑና ማኅበረ ካህናቱ እሳቸው የደከሙበትን ቤተ ክርስቲያን በሌሉበት አናስመርቅም፤ ይህ የኛ ቀን ነው፤ በእግዚአብሔር ቀን አባታችን ባሉበት እናስመርቃለን፤ የሠራነው የእግዚአብሔርን ቤት ነው ለምን ተፈተንን አንልም ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያኑ ምርቃት ወደ ሌላ ቀን መዘዋወሩንም  የደብሩ አስተዳዳሪና አሠሪ ኮሚቴው ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይፋ አድርገዋል። ነገ በዓለ ንግሷ በቀድሞ ቤተ ክርስቲያን (በመቃኞ) ተከብሮ ይውላል።
በአሁኑ ሰዓትም በመምህር ዐብይ መኮንን ትምህርተ ወንጌል እየተሰጠ ነው።

Friday, January 27, 2023

"በሁለት ማልያ የምትጫወቱ ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ"...ብፁዕ አቡነ ሔኖክ


+++
(ጥር  19 ቀን 2015 ዓ.ም
  አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ) 

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባሳለፈው ውግዘትና ውሳኔ ተንተርሶ ውይይትና ምክክር ድርጓል! 

የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳም በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሶዶ ዳጩ ወረዳ፣ ሀሮ በዓለ ወልድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሦስት ግለሰቦች መሪነት  ቀኖና ቤተክርስቲያንን በጣሰ፣ በሕገ-ወጥ እና ኢ-ሲኖዶሳዊ በሆነ ድርጊት የ፳፮ መነኰሳትን "የኤጲስ ቆጶስነት" ሢመት በመስጠትና ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ መመደቡን ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጥር 18/2015 ዓ/ም ባስተላለፈው የውግዘትና ባለ ፲፪ ነጥብ ውሳኔ መሆኑን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ ገልጸዋል። 

ድርጊቱም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣የጥንታዊት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ያቆሰለ፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ያሳዘነ መሆኑን ገልጸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ እንደሚደግፋ ተናግረዋል። 

በውይይቱ የተገኙት ተሳታፊዎችም ውሳኔውን እንደሚደግፉ ገልጸው ለትግበራው በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ  በተፈጠረው ድንገተኛ ክስተት በእጅጉ ማዘናቸውን በመግለጽ ፈተናው ይቀጥላል እኛም ነቅተን ቤተ ክርስቲያናችን እንጠብቃለን ብለዋል። 

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በሁለት ማልያ የሚጫወቱ እንዳሉ በመጥቀስ በሁለት ማልያ የሚጫወቱ አካላት ከድርጊታቸው ካልተመለሱ እንደማይታገሱ በመግለጽ በድርጊቱ ተገኝተውም ሆነ በተለያየ ምክንያት የተሳተፉት ሁሉ ንስሐ ገብተው ከድርጊታቸውን እንዲቆጠቡና ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል። 

አክለውም ብፁዕነታቸው ሁሉም ነቅቶ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠብቅ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ባለ 6 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የውይይትና ምክክር መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።

በውይይቱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሄኖክን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የ7ቱ ክፍላተ ከተሞች ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች፣ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ የሁሉም ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።

በመ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ፦ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

Thursday, January 26, 2023

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ

አዲስ  አበባ: ጥር 18/2015 ዓ.ም (ኢሳት): 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣቴዎስ ፣ አባ ዜና ማርቆስና በእነሱ የተሾሙ 25 መነኮሳት ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነታቸውን ሽሯል። ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩም ወስኗል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ እንዲሁም በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 3 አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያደርግ በተደነገገው መሠረት ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ሕዝብና አሕዛብን፣ ሰውና መላእክትን፣ ፍጡራን እና ፈጣሪን ይልቁንም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ልዩነት አጥፍቶ የሰው ልጅ ሁሉ በቋንቋ፣ በቀለምና በጐሣ ሳይከፋፈሉ በአንድነት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ የተወለዱ በማየ ገቦ የተጠመቁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዲሆኑ ልዩነት የሌለባትን ዘለዓለማዊት መንግሥተ እግዚአብሔር እንዲወርሱ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የተነሣባትን ፈተና ሁሉ አልፋ ከእኛ ዘመን ደርሳለች፤ 

ምንም እንኳ ከቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ከኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በጐሣና በቋንቋ የመለየት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንግዳ ክስተት ቢሆንም ቤተ ክርስቲየን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጠባይዋ በተለየ፣ ታሪኳንና ሥርዓቷን በማይመጥን፣ ከሕግ መንፈሳዊ፣ ከሕግ ጠባይአዊ እና ከሕገ አእምሮ በወጣ መልኩ የደረሰባት ጥቃት፣ እና የመፈንቅለ ሲኖዶስን ተግባር ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ አሳዝኖታል፤ 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ውስጥ ለሀገር አንድነት፣ ለፍትሕ፣ ለጥበብ፣ ለሕዝብ ትስስር፣ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለጤና፣ ለሥነ-ምግባር መሠረት እና ዐምድ፤ ምሰሶ እና ማገር ሆና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈራች፣ የተከበረች እና የተወደደች፤ ዕሴቷ እና ዕምቅ የዕውቀት ሀብቷ በምሁራን የታወቀ፣ በትምህርተ ዓለም ሳይቀር የተቀረጸ፤ በእውነተኛ ሊቃውንት የተመሠከረ፣ ቅርሶቿ የተመዘገቡላት ስትሆን፤

በቅርቡ ራስዋ በሾመቻቸው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ከፍተኛውና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲወጡ አደራ በተሰጣቸው ሊቃነ ጳጳሳት መሠረተ እምነትን፣ ሃይማኖታዊ ቀኖናን፣ የአስተዳደር ሥርዓት ሁሉ በጣሰ፣ መንገድ በማኅበረሰብ ዕድገትና አስተዳደር ውስጥ ከሕዝብ ጋር የቆመች፣ ከፖለቲካ የጸዳች መንፈሳዊና ሕዝባዊት ተቋምነቷን በመካድ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊት፣ ተቋምን የመናድና መዋቅሯን የማፍረስ ተግባር ተከናውኗል፡- 

በዚሁ መሠረት፡-

ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጡ ወረዳ ከወሊሶ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አሮ ባለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን እጅግ አሳዛኝ እና ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፤ ሕገ ወጥ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አስመልከቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አስቸኳይ የምልዐተ ጉባዔ አድርጓል፤ 

ቅዱስ ሲኖዶስም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ መላው አህጉረ ስብከት፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ፣ የሊቃውንተ ጉባኤ፤ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፤ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የወጣቶች እና የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፤ የምእመናን እና አገልጋዮች ኅብረት፣ ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በደብዳቤ፣ በሚዲያ እና በአካል ከሰጡት ምክረ ሐሳብ እና የአቋም መግለጫ በመነሣት፤
በሀገር ውስጥ እና በውጪው ዓለም የሚገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወዳጆች፣ በተለይም የግብጽ እስክንድርያ ኮፕቲክ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ፓትርያርክ ውጭ የሚደረግ ሢመትን እንደማይቀበሉና ዕውቅና እንደማይሰጡ በላኩት የአቋም መግለጫ፣ የኤርትራ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን፣ እና የሌሎች አኀት ኦርቶዶከስ አብያተ ክርስያናት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ዓለም አቀፍ መንፈሳዉያን ተቋማት፣ የልማት እና የበጎ አድርጎት አጋር ድርጅቶች፤ ድርጊቱን በማውገዝ የማይቀበሉት መሆኑን የአቋም መግለጫ በመላክ ባሳዩት አጋርነት፤ 
አስቀድሞ እንደተገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈተና የኖረችበት ጊዜ እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍትና የታሪክ መዛግብት ሲመሰክሩ በዘመነ ሐዋርያት ቢጽ ሐሳውያን፣ በዘመነ ሊቃውንት የተለያዩ መናፍቃን፣… በየጊዜው እየተነሡ ሲፈታተኗት ኑረዋል፡፡ አሁንም በግልጽ እንደሚታየው ከውጭም ከውስጥም በተደራጁ ምንደኞች በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ 

ለዚህም ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ በሶዶ ዳጩ ወረዳ፣ ሀሮ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአባ ሳዊሮስ መሪነት እጅግ አሳዛኝ ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፣ ሕገ-ወጥ፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አንዱ ሲሆን፤ በአባ ሳዊሮስ መሪነት የተፈጸመው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ፳፮ መነኰሳትን ከቀኖና የወጣ ሢመት በመስጠትና ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ በመመደብ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ ሃይማኖትን የሚከፋፍል፤ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት … የሚያጋጭና ደም የሚያፋስስ ፀጥታን የሚያናጋ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝሟል፤ በመሆኑም፤ 

- ከላይ እንደተገለጸው ሐዋርያት በሦስተኛው ቀሌምንጦስ በሃያ አምስተኛው አንቀጽ “በአውራጃው ሁሉ ያሉ ኤጲስ ቆጶሳት አለቃቸው ማንም እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ አለቃ ያድርጉት፤ ያለ ፍቃዱ ጥቃቅኑንም ደጋጉንም ሥራ ምንም ምን አይሥሩ፤ እርሱም ዳግመኛ ኤጲስ ቆጶሳቱ ሳይፈቅዱ ደጋጉን ሥራ አይሥራ ጥቃቅኑን ቢሠራ እዳ የለበትም፡፡ ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ ሁነው በአንድነት ይኑሩ” ብለው ወስነዋል፡፡ እነዚህ ሕገ ወጥ አካላት ይህን የሐዋርያት ቀኖናን በመሻራቸው፡፡

- ሁለተኛም በአርባ አራተኛው አንቀጽ “ሊቀጳጳሳት (ፓትርያርክ) ኤጲስ ቆጶሳት በተሾሙባቸው አገሮች የሚሠሩትን ሥራ፣ የሚያዙትን ትእዛዝ ይመርምር፡፡ የማይገባ ሥራ ሠርተው፣ የማይገባ ትእዛዝ አዝዘው፣ ቢያኝ ለውጦ የተገለጸለትን ትእዛዝ ይዘዝ፡፡ እርሱ ለሁሉ የሹመት አባታቸው ነውና፤ እነሱም ልጆቹ ናቸውና…” ብለዋል፡፡ ይህን ኢ-ቀኖናዊ ሥርዐተ ሲመት የፈጸሙት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ በአደባባይ የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን እና የቅዱስ ፓትርያርኩን መብት በመጣሳቸው፡፡

- ሢመተ ክህነትን በተመለከተ “ወአልቦ ዘይነሥእ ክብረ ለርእሱ ዘእንበለ ዘጸውዖ እግዚአብሔር … እንደ አሮን በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ለራሱ ክብርን የሚወስድ የለም” (ዕብ 5፤4) እንደሚለው የእግዚአበሔር ቃል ከዲቁና ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ሹመት ድረስ ያለው ሹመት በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር መጠራቱን የሚጠይቅ ሲሆን እንኳንስ ለተሿሟዎች ለመራጮችና ለአስመራጮች በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስፈርት ያለው፣ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ይህንም ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው መልእክቱ በሰፊው ገልጾታል፡፡ (ጢሞ.3፣10፣ ቲቶ፣ 1፣5-7 ፍትሕ መን አንቀጽ 4) 

- ይህንም ቅዱሳን ሐዋርያት ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ በ3ኛው ቀሌምንጦስ “ኤጲስ ቆጶስ የሀገሩ ሰዎች፣ የሀገሩ ጳጳስ፣ ፈቅደውለት ይሾም፤ ቢገኙ ሦስት፣ ባይገኙ ሁለት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ሁነው ይሹሙት” ብለዋል፡፡ ይህም ቅዱስ ሲኖዶስ በሌለበት ሀገር፣ ፓትርያርክ በሌለ ጊዜ ምእመናን እንዳይበተኑ ተብሎ የሚደረግ ነው እንጅ በቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀመንበርነት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን የቅዱስ ሲኖዶስን ሉዓላዊ ሥልጣን በመጋፋት የሚፈጸም ከሆነ ግን ይህን ቀኖና በሕገወጥ መንገድ ለተፈጸመ ድርጊት መጥቀሱ በቅዱስ ወንጌል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል እንደመናገር ተቆጥሮ የማይሠረይ ኃጢአት መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ (ማቴ.12፣30-32 ሉቃስ 12፣10፣ ማርቆስ 3፡28-29 1ኛ ጢሞ 1፣13) የእነዚህ ሰዎች ተግባር በሥራ ላይ ያለውን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሕጋዊ የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ የመፈንቅል፣ የታላቋን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የመናድ፣ ሕጋዊ ተቋምን የማፍረስ ወይም የመናድ ተግባር በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዟል፣

- ሠለስቱ ምዕትም ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ በኒቅያ በጻፉት ቀኖና በዘጠነኛው አንቀጽ አንዱም አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾም ቢሻ፣ የሀገሩ ሰዎች ቢፈቅዱለት፣ የሀገሩ ጳጳስ ካልፈቀደለት ኤጲስ ቆጶስነት መሾም አይገባውም ይህን አፍርሶ ቢገኝ ሲኖዶስ ያወግዘዋል፤ ሹመቱም ይቀራል” ብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ወቅት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲየን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ስልጣን በመጋፋት በድፍረት ተፈጸመ የተባለው ሹመት አስቀድሞ በአበው ቅዱሳን የተወገዘ ነው፤ 

- ከዚህም ጋር ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት በሚፈጸምበት ጊዜ፣ ያለ ቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ማንም ወደ ቤተ መንግሥት እንዲሔድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይፈቅድም፡፡ ይህንንም የተላለፈ ቢኖር ከጳጳሳና ከኤጲስ ቆጶሳት ማንም ማን ሊቀጳጳሳቱ ሳይፈቅድለት ወደ ንጉሥ ቤት አይሒድ ወለኲሉ ዘዐለወ ዘንተ ሲኖዶስ ያወግዞ ይህን ትእዛዝ ያፈረሰውን ሲኖዶስ ያወግዘዋል” ተብሎ ስለተወሰነ ዛሬም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ውጭ የሚደረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ሕገወጥ በመሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘዋል፤ 

- በቀኖና ቤተ ክርስቲያን … ሰው ሁሉ ማዕርጉን ጠብቆ ይኑር እንጅ፣ አንዱ ወደ አንዱ ማዕርግ አይተላለፍ፤ ይህን የሠራነውን ሥርዐት ያፈረሰውን ሰው ሲኖዶስ ያወግዘዋል ተብሎ በተጻፈው መሰረት እነዚህ ሕገወጥ አካላት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘዋል፤ 

- በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 30 የአጲስ ቀጶሳት መሾም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ የመወሰን ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን የሚደነግገውን ክፍል በግልጽ የጣሰ በመሆኑ፤ 

- በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንዑስ ቁ.1 የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚፈጸመው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ብቻ እንደሚፈጸምና መደንገጉ፤ 

- በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 5 የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ሕግጋትንና ቀኖናን የሚያፋልስ ሊቀ ጳጳስ /ኤጲስ ቆጶስ/ ከአባልነት እንደሚሰረዝ በመደንገጉ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዟቸዋል፡፡ 
በአጠቃላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር በሕገ ሰብእም ሆነ በሕገ እግዚአብሔር ሚዛን የተወገዘ ከመሠረተ እምነት የተለየ፣ በአበው ቀኖና፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በአጠቃላይ ተቀባይት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ 

1ኛ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 138 መሠረት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጩ ወረዳ ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ 

፩ኛ. አባ ሳዊሮስ
2ኛ. አባ ኤዎስጣቴዎስ
3ኛ. አባ ዜና ማርቆስ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን 26 ኤጴስ ቆጰሳትን ሾመናል፤ ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለት በማኅህበራዊ እና በብሮድካስት ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ የተረጋገጠ በመሆኑ በዚሁ ድርጊታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ፤ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ ለይቷቸዋል፡፡

በመሆኑም፡- 
ሀ. ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ፤

ለ. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡

ሐ. በነዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አውግዞ በለያቸው ግለሰቦች ይመሯቸው በነበሩ አህጉረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎት በማከናወን ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ ብፁዐን አባቶችን

፩. ለደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት 
፪. ለኬንያ፤ኡጋንዳ፤ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ሀገረ ስብከት 
፫. ለኢሉ አባቦራ እና በኖ በደሌ ሀገረ ስብከት 
፬. በሰሜን አሜሪካ ለሜኒሶታ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት 
፭. ለጉጂ፤ምዕራብ ጉጂ እና ቦረና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከት 
፮. ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም 

በአባትነት የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመደቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ወስኗል፡፡

 ይሁን እንጅ ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል፤ 

2. የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ ግለሰቦች አማካኝነት የኤጲስ ቆጶስነት ሺመት አግኝተናል፤ ተሸመናል እያሉ የሚገኙ 25 መነኰሳት በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል፡፡

3. ከነዚሁ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ጸጋዘአብ አዱኛን ከቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ ስብሰባ በፊት የቀኖና ጥሰቱንና ሕገ ወጥ አድራጎቱን በመረዳትና በመጸጸት ድርጊቱን በመቃወም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ባቀረቡት የይቅርታ አቤቱታ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታውን የተቀበላቸው ሲሆን እንደሳቸው ሁሉ ከላይ የተወገዙት 25 ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን እንገልጻለን 

4. በዚህ ጸረ ቤተ ክርስቲያን እና ኢ-ቀኖናዊ ድርጊት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ እየኖሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወይም በቦታው በመገኘት የጥፋት ድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን በተመለከተ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተገቢውን ክትትልና አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ፤

5. ይህን ታሪክ ይቅር የማይለውን ሕገ ወጥ አድራጎት እና የቀኖና ጥሰት በሐሳብ፤ በገንዘብ እና በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ እና በማድረግ ላይ ያሉ ማናቸውም ተቋማት እና ግለሰቦች ከዚህ ሕገ ወጥ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያሳሰበ ይህ ባይሆን በሕግ አግባብ ተገቢው እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

6. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማህበራት እና ምእመናን እና ምእመናት ይህን ሕገ ወጥ አድራጎት ከመከላከል እና የቤተ ክርስቲያናችሁን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለዚህ ሕገ ወጥ አድራጎት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደረግ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከል ሥራችሁን እንድትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስምን ከፊትም ሆነ ከኃላ በመጨመር እና በመቀነስ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠቀም፤ ዓርማዋን፤ አድራሻዋን፤የአምልኮ እና የሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋያ ቅዱሳትንና አልባሳት እንዲሁም መጻሕፍት መገልገል የማይችሉ መሆኑ ታውቆ ይህንን ጉዳይ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በተጨማሪም ይህን ውሳኔ ተላልፈው በሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ተገቢውን ሕግ አግባብ ተከትሎ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለማት የሚያስፈጽም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች በመመደብ ተገቢውን ሁሉ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

8. አሁን የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ ዝርዝር ጥናት እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ አንድ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ እንዲሰየም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

9. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ ከክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጀምሮ በየደረጃው ላሉት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲከናወኑ እና ይህ ውሳኔ ከሸኚ ደብዳቤ ጋር እንዲደርሳቸው ተወስኗል፡፡

10. ይህን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ክፍለ ዓለማት ለሚገኙ የቤተ ክርስቲኒቱ አገልጋዮች እና ምእመናን የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መድረኮች እንዲካሔዱ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በማእከል የአህጉረ ስብከት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ታላቅ የንቅናቄ እና የግንዛቤ መድረክ እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ 

11. በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ መንግስታዊም ሆነ መነግስታዊ ያልሆነ ተቋማት፤ አኃት አቢያተ ክርስቲያናት፤ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፤ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት ጉባዔ እና ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ጉባኤዎች በሙሉ እነዚህ የተወገዙት ግለሰቦች የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ እና ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ ማናቸውም ግንኙነት በቤተ ክርስቲያኑቱ ስም እንዳያደርጉ በጽሑፍ አንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

12. እነዚህ ግለሰቦች ከሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ አንዱ እኩይ ተግባራቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እንደሆነ ማስመሰል ሲሆን ይኽ ተግባር ሃይማኖቱን የሚወድ፣ አባቶቹን የሚያከብር እና አስተዋይ የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ የማይወክል፣ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ያደረጉት ሕገወጥ የቀኖና ጥሰት መሆኑ እንዲታወቅ፤ በተጨማሪም ለሚያሠራጩት የሐሰት አሉባልታ ወደፊት ተገቢው መልስ እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤ 

እስከ አሁን ድረስ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን በመሆን አጋርነታችሁን ያሳያችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የበኩላችሁን በመወጣት መግለጫ የሰጣችሁ ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም እያመሰገንን ለወደፊቱም በጸሎታችሁ እና በመልካም አጋርነታችሁ ከጎናችን እንድትሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

ጥር 18 ቀን 2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Wednesday, January 25, 2023

"አባዬ ወዴት ወዴት"


ይድረስ ለአባ ዜና ማርቆስ 

ሊቀ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) ካልፈቀዱ ማንም ቢሆን ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይሾም ፍትሐ ነገሥቱ ይነግረናል። ከተሾመም ሲኖዶስ ያወግዘዋል ተብሎ በግልጽ አማርኛ ተጽፏል።
                             
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፭ ቁጥር ፺፩ ወለእመ ኀሠሠ አሐዱሂ ኤጲስ ቆጶስና ወሠምሩ ቦቱ ኵሎሙ ሰብአ ሀገሩ። አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾም ቢሻ ወሠምሩ ቦቱ ኵሎሙ ሰብአ ሀገሩ የሀገሩ ሰዎች ቢፈቅዱለት። ወኢሠምረ ቦቱ ጳጳሰ ብሔሩ ኢይደልዎ ኤጲስ ቆጶስና። የሀገሩ ጳጳስ ቢፈቅድ ነው እንጂ የሀገሩ ጳጳስ ካልፈቀደለት መሾም አይገባውም። ወዘንተ ለእመ ተዐደወ ሲኖዶስ ያወግዞ ይህን አፍርሶ ቢሾም ጉባዔ ይለየዋል። ወእመሰ ኀብሩ በእንቲአሁ ዘይበዝኁ ብዙዎች አንድ ሆነው ሹመቱን ቢፈቅዱለት ግን ወሠምሩ ቦቱ ጳጳስ ወሊቀ ጳጳሳት ይግበሩ በምክሮሙ ለእለ ይበዝኁ። ጳጳሱ ሊቀጳጳሱ ከወደዱ በብዙዎች ፈቃድ ይሾም። ሲሾምም "፪ ወይም ፫ ኤጲስ ቆጶሳት ይሹሙት" ተብሎ ቁጥር ፺፪ ተጽፏል። አቡነ ዜና ማርቆስ ይችኛዋን ብቻ ይዘው የላይኛውን ትተው እንደ መ*ና*ፍ*kan ግማሹን ይዘው ግማሹን ትተው ሕገወጥነትዎትን ለመሸፋፈን አይሞክሩ። ፍትሐ ነገሥትም ሌላውም ቅዱሳት መጻሕፍት በምልዐት ይጠቀሳሉ እንጂ አንዱን ትቶ አንዱን አንጠልጥሎ አይጠቀስም። ሊቀ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) ካልፈቀዱ ማንም ቢሆን ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይሾም ፍትሐ ነገሥቱ ይነግረናል። ከተሾመም ሲኖዶስ ያወግዘዋል ተብሎ በግልጽ አማርኛ ተጽፏል። ጵጵስና ሦስት መዓርጋት አሉበት። የመጀመሪያው ኤጲስ ቆጶስ ነው። አዲስ ተሿሚ ነው። ከዚያ የተወሰኑ ኤጲስ ቆጶሳትን አቅፎ መሪ የሆነው ጳጳስ (መጥሮጶሊስ) ይባላል። ከዚያ የጳጳሳትም የኤጲስ ቆጶሳትም የበላይ ደግሞ "ሊቀ ጳጳሳት (ፓትርያርክ)" ይባላል።
                                
ሌላው አቡነ ዜና ማርቆስ ሊያጭበረብሩ የሞከሩት ሥርዐት ስለሚሻሻል ማሻሻል እንችላለን የሚል ምክንያት ጠቅሰው የሰሩትን ሕገ ወጥነት ለማለባበስ ሞክረዋል። እውነት ነው ሥርዐት ከዘመን ዘመን ከቦታ ቦታ ሊለወጥ ይችላል። ለዋጩ ግን ማን ነው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፶፩ ቁጥር ፲፻፰፻፲፮ (1816) ወዘሰ ብውሕ ለሊቅ ዘውእቱ ሊቀ ጳጳሳት ከመ ይወስክ ዲቤሁ ወያንትግ እምኔሁ። በተጻፈው ላይ ይጨምር ዘንድ ከተጻፈው ይከፍል ዘንድ ለሊቀ ጳጳሳት የሚገባው ዝኒ ይህ ነው። ካለ በኋላ ዶግማ እንደማይለወጥ በቁጥር 1817 "በተጻፈው ላይ መጨመር ከተጻፈው መክፈል ግን ለማንም አይገባውም" ተብሎ ተገልጿል። ሊቀ ጳጳሳት ማሻሻል ይችላል የተባለውን ሥርዓት በቁጥር 1818 "ላይ ጉባኤ ያልቆመለት በመጻሕፍት ያልተገለጸ ሥርዐት ከሆነ ነው" ይላል። ይህንን የማድረግ ሥልጣን ያለውም ሊቀ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) እንጂ ጳጳስ አይደለም። ፓትርያርክ እንኳ ይህንን ለማድረግ ቅድመ መሥፈርቶች አሉት። እነዚህም ከቁጥር 1821 ጀምሮ ተጠቅሷል። የቅዱሳት መጻህፍትን ትርጓሜ የሚያውቅ ምሁር ይሁን። የቅዱሳን አባቶችን የጉባዔ ውሳኔዎች የሚያውቅ ይሁን። በተጨማሪም ትሩፈ ምግባር የሆነ ደግ ሊሆን ይገባል ይላል። ይህ ሁሉ ሲሆን እንኳ ጳጳሳት ሁሉ ተስማምተውበት እንጂ ብቻውን ፓትርያርክ እንኳ ሥርዐት መለወጥ አይችልም። ፍት. ነገ. ፶፩፣ ፲፻፰፻፳፮ "ይደሉ ከመ ይትጋብኡ በእንቲኣሁ ኤጲስ ቆጶሳት" ስለ ጉዳዩ ኤጲስ ቆጶሳት ይሰብሰቡና ይምከሩበት ተብሏል።
                            
ስለዚህ አቡነ ዜናማርቆስ ያነሱት ሐሳብ ፍጹም የተጭበረበረ። ሕገ ወጥነትዎን ለመሸፋፈን ያቀረቡት ነው። ነገር ግን ፍትሐ ነገሥቱ የእርስዎን ሕገ ወጥነት እንደማይፈቅድ ይመልከቱት።
                            ።
መ/ር በትረማርያም አበባው
(የፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ መምህር)

እውነቱን ተቀበል !!


---------------------
ከፍለህ የማትጨርሰው ውለታ አለብህ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  ሀገር፥ ታሪክ፥ ሚስት ጠብቃ የኖረች ገመና ከታች ናት።

፩ . . . ሐገር

ቋንቋ፥ ማንነት፥ ፊደል፥ ነፃነት ወዘተ ያለው ሐገር ሰጥተሃለች፡፡ የምትባጠስበትን ጓዳዋ እየነደደ ጠብቃለች፡፡ ከጠላት ተሞዳሙዳ ሐገር የወጋችበት እድፋም ታሪክ የላትም፡፡ ብሄሬ፥ ቋንቋዬ፥ ማንነቴ ቅብርጥሶ የምትለው፤ አንተ ጋ የደረሰው እሷ እየነደደች ነው፡፡ 

ቤተክርስቲያኒቱ ዓ/ዓቀፍ ነበረች፡፡ ከግብፅ፥ ከሮም፥ ከባዛንታይን፥ ከግሪክ ተላልሳ፥ ቋንቋህን፥ መሬትህን፥ ታሪክህን ልትፖሽርልህ ትችል ነበር፡፡ አላደረገችውም፡፡ በእቅፏ ያሉትን ዜጎች ጠብቃ ይዛለች፡፡ ይሄ ዥልጥ ፒፓ በየዘመኑ ርስ በርስ ሲናከስ መሃል ነበረች፡፡ ያላት የመከራ ታሪክ እንጂ የአሸሼ ገዳሜ አይደለም፡፡ 

፪ . . . ታሪክ

ኦቦሌሴ ብራና ዳምጣ፥ ቀለም ጨምቃ፥ መድሀኒት ምሳ ለዛሬ አድርስሃለች፡፡ ግደይ፥ ቶሎሳ፥ ኢብሳ፥ ዣንጠረር፥ እርገጤ፥ ፔን፥ ኡጁሉን አልቀማችህም፡፡ ጠብቃልሃለች፡፡ በለስ በቀናው ወራሪ ባህል ከመኖር ታድጋሃለች፡፡ እሷን ሲያወድሙ ግዜ አግኝተህ ተከላክልሃል፡፡ ለዛሬ ደርሰሃል፡፡ 

ያንተን የዕልቂት፥ የጥጋብ፥ የረሃብ ዘመን ከትባለች፡፡ አልከፈልካትም፥ አላስተማርካትም፥ አልነገርካትም፡፡ አንተ ስትኖር እሷ እንደምትኖር ስለምታውቅ ነው፡፡ ኦቦሌሴ የመጣህበትን ድልድይ አትስበር፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ትናንትህ ነች፡፡ የሃገሪቱ ትውስታ ጉያዋ ስር ነው፡፡ ያለ ትውስታ ብሄር፥ ሃገር፥ ቋንቋ፥ ማንነት ወዘተ አይቆምም፡፡ 

፫ . .  . ሚስት

"ሃይማኖትህን፥ ሚስትህን፥ ሐገርህን ጠላት ሊቀማ መጥቷል" ንቃ፥ ተበላህ የምትል ብቸኛ የሃገሪቱ ተቋም ነች፡፡ ውብ ሴቶችህ የአንተን ድድብና የሚታገሱት ከሷ በወረሱት ጨዋነት ነው፡፡

*

4ኛ መቶ ላይ ነው፡፡ ዲያቆን አትናቴዎስ ይባላል፡፡ ከአርዮስ ጋ በሃይማኖት ተከራከሩ፡፡ አትናቴዎስ ረታ፡፡ በመጨረሻም "እኛ አርዮስን አንጠላም፥ ትምህርቱን ግን እንጠላለን" አለ፡፡ ኦቦሌሴ አንተን አልጠላም፡፡ መንገድህን ግን እፀየፋለሁ፡፡ 

*

ጌታው ነገስታቱ፥ መሪዎች፥ ባለስልጣናት ሲገሉህ፥ ሲዘርፉህ፥ ሲወጉህ ስትችል "ተዉ" ብላለች፡፡ ሳትችል ዱላው ወደ ራሷ ዞሯል፡፡ የጥጋበኛ ውሪ ክንድ ሲደቁሳት ኖሯል፡፡ አልፋለች፡፡ ማለፍ ታውቃለች፡፡ ልምከርህ ጌታዬ እ ረ ፍ !

✍️ Natnael Hawk

እግዚአብሔር ይመስገን !!


********************
ከቀኖናና ከህግ ውጪ በተደረገው ሲመት ከተሾሙት መካከል መጋቤ ብሉይ ወ ሐዲሳት ቆሞስ አባ ጸጋዘአብ አዱኛ በመንበረ ፀባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ ጉባዔ ቤት መምህር  የነበሩ ሲሆን ከገቡበት  አገር የማፍረስ አደገኛ ሴራ ተልዕኮ ከያዘው ቡድን ራሳቸውን አግልለው በዚህ ሰዓት ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ለመጠየቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው ለብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የይቅርታ ደብዳቤ አስገብተዋል።

#አንድ_ሲኖዶስ ...የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን
                          ቅዱስ ሲኖዶስ 

#አንድ_መንበር ...(መንበረ ተክለሃይማኖት)

#አንድ_ፓትሪያርክ ...ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ !!!

#_ኩላዊት_እንጂ_ክልላዊት_ቤተክርስቲያን_የለችንም !!!

🙏ቅድስት ቤተክርስቲያኒቱ ለ3 ቀናት የሚቆይ ጸሎት አወጀች‼️


👉 በዛሬው ዕለት የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ማርያም ገዳም ከተጠናቀቀነ በኋላ ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ከዛሬ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የጸሎትና የሱባኤ ጊዜ እንዲሆን አዋጅ መታወጁን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።

የቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ማርያም ገዳም መከናወን ጀመረ፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማያውቀውና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ባልጠበቀ መንገድ የተሰጠውን ሕገ ወጥ "ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት" በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በአስተላለፉት ጥሪ ለሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የመክፈቻ ጸሎት ማድረግ ተጀምሯል፡፡

የጸሎት መርሐ ግብሩ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የመምሪያ ኃላፊዎች በተገኙበት በመከናወን ላይ ነው፡፡

©የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት

አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ መልእክት፤


+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመላው ዓለም ለሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳሳት ባስተላሐፉት መልዕክት እንደገለጹት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቤተክርስቲያናችን ላይ በተፈጸመው የቀኖና ጥሰትና ሕገ ወጥ ድርጊት ዙሪያ ለመወያየት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ መተላለፉን አስታውሰው  በአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ በጉዞአቸው ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ከቤተክርስቲያናችን በቀረበው ጥሪ መሰረት አየር መንገዱ ፍጹም ፈቃደኛና ተባባሪ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም የቤተክርስቲያንን ጥሪ ተቀብሎ ፈቃደኛነቱን በመግለጹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልባዊ ምስጋናዋን እያቀረበች በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የምትገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አየር መንገዱ የሰጠውን እድል በመጠቀም ወደ አገራችሁ በመምጣት ቤተክርስቲያናችን በረጅም ዘመን አገልግሎቷና በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀውን ችግር በጋራ ሆነን እንፍታ በማለት መልእክታቸውን  አስተላልፈዋል።

አቡነ አብርሃም ዛሬም ታሪክ ሰሩ


“እናንተ እዚህ አራት ኪሎ ተቀምጣችሁ፤ ሌላው ቦሌ ሆኖ መንግሥት መስርቻለሁ ቢል ዝም ብላችሁ ትቀበላላችሁ፣ በሽምግልና እንፍታው ትላላችሁ?”
||| 

በዛሬው ዕለት መደበኛ የቋሚ ሲኖዶስ ስብሰባ በሚደረግበት ወቅት የመከላከያ ሚንሰቴሩ አብርሃም በላይ እና የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ቀጠሮ ሳያስይዙ ድንገተኛ በሆነ መልኩ በመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በመሄድ አቡነ አብርሃምን ተጭነው የሹመቱን ጉዳይ ለማሳመን እና ጉዳዩ በሽምግልና ይፈታ ብለው ቢጠይቁም ሌሎችም የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በሽምግልና ስም የመጡትን ሃሳባቸውን ውድቅ አድርገው ዳግም በዚህ መልኩ መምጣት እንደሌለባቸው አሳስበው መልሰዋቸዋል፡፡ 

አቡነ አብረሃም፡- 
“ይሄ ጉዳይ የሃይማኖት፣ የቀኖና፣ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን እና የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በእርቅ የሚፈታ አይደለም፡፡” ብለው ቁርጥ አርገው ሲናገሩ፡፡ 

ሌሎቹም ጳጳሳት ለመከላከያ ሚንስቴሩ ለአብርሃም በላይ “እናንተ እዚህ አራት ኪሎ ተቀምጣችሁ፤ ሌላው ቦሌ ሆኖ መንግሥት መስርቻለሁ ቢል ዝም ብላችሁ ትቀበላላችሁ፣ በሽምግልና እንፍታው ትላላችሁ?” ብለው ምላሽ በማሳጣት ሽምግልና የመጡትን ሁሉም በአንድ አቋም ምላሽ አሳጥተው መልሰዋቸዋል፡፡

Tuesday, January 24, 2023

የቤተ ክህነታችን ሦስቱ አርእስተ ኃጣውዕ፤

Written by Dn. Birhanu Admass Anleye

የተፈጸመው ድርጊት ለብዙዎቻችን እጅግ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭ፣ አዋራጅ እና ቅስም ሰባሪም ነው። ይልቁንም ደግሞ አንዳንድ እጅግ የምናከብራቸው እና የምንወድዳቸው ብቻ ሳይሆን የምናምናቸውም አባቶች ጭምር መካተታቸው የበለጠ እንድናዝን አድርጎናል። ይህም የዕውቀታችንን ውሱንነት ብቻ ሳይሆን መታመን መጥፋቷን፣ ፈተና እና ችግር እንኳ ቢኖር እርሱን ተቋቁሞ ማለፍ የመቻል አቅም መሳሳቱን፣ ፍቅረ ሲመትም ክንፍ አውጥቶ መብረሩን ይፋ አድርጎ አስጥቶታል።

በርግጥ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይህን መሰል ጥፋቶች እንደማይቀሩም የመጣንበት መንገድ አመላካች ነበር። ጌታችን በወንጌል “አልቦ ዕፅ ሠናይ ዘይፈሪ ፍሬ እኩየ፣ ወአልቦ ዕፅ እኩይ ዘይፈሪ ፍሬ ሠናየ” ሲል እንደገለጸው የመጣንበት የሲመት መንገድ የዚህ ዓይነት ፍሬ ላይ ሊያደርሰን እንደሚችል ብዙዎች ተናግረው ነበር፤ ይታወቃልም። የመጣንበት የሲመት ባህልም እንበለው መንገድ እጅግ ብዙ ጉድለቶች እና ውሱንነቶች እንደነበሩበት ቢያንስ አሁን እንኳ ዝም ልንል አንችልም። ዛፉ መልካም ከሆነ ፍሬው መጥፎ ሊሆን አይችልም የሚለውን የጠቀስኩት ለዚህ ነው። እውነቱን ለመናገር ከልክ ያለፈ ይሉኝታ እና ምን አገባኝ ብዙ ጥፋቶችን እያከተተለ እንዳመጣብን ለመረዳት አይቸግርም። ከዚህ በኋላ ግን እንታገስህ ብንለው ራሱ ችግሩ አይታገሰንም። እንቻልህም ብንለው ሞልቶ ፈስሷል እና አንችልም። መጠን የለሽ የጎጠኝነት፣ የተንኮል፣ የበቀለኝነት፣ የሌብነት፣ የጉቦ እና የቡድነኝነት ዛፋችን ያፈራውን ፍሬ ነው ዛሬ የተመለከትነው። ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ “ዘዘርዐ ሰብእ የአርር” – ‘ሰው የዘራውን ያጭዳል' እንዳለ በገላትያ መልእክቱ ያጨድነው በዘመናት የዘራነውን መሆኑን ልንክድ አንችልም። በዚህ ጉዳይ አብረን ንስሐ ገብተን መታረም እንችላለን ብዬም አላምንም። ፈጽሞ ሲያጠፋን ግን ከዚህ በላይ ዝም ብለን ልናየው የሚገባን አይመስለኝም። ልምምጥም ሆነ ልመናም የሚያስፈልገው አይመስለኝም። የሚያስፈልገው ወደ ሕግ እና ሥርዓት ቀጥ ብሎ መግባት ብቻ ይመስለኛል። ይበቃል! በእውነት ይበቃል። ከዚህ በላይ ምን ልንሆን እንችላለን? ሹመትም ሆነ ምደባ በሕግ እና በሥርዓት ብቻ መፈጸም አለበት ። ይህ እስካልሆነ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል ብቻ ሳይሆን እንደጠፉት ሀገሮች እና ዛሬ እንዲህ ነበሩ እየተባለ እንደሚነግርላቸው እኛም እንጠፋለን። ዐፅመ ሐዋርያት እና ሰማዕታት ከተከማቹባት፣ ሦስቱ ዐለም አቀፍ ጉባኤዎች ከተካሔዱባት፣ እኛ ከምንቀድሳቸው ዐሥራ አራት ፍሬ ቅዳሴዎች ውስጥ ከስምንት ያላነሡት ካመጣንባት፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፣ ጎሮጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ካስተማሩባት እና ከገለገሉባት የቁስጥንጥንያ መንበር ሙሉ በሙሉ መጥፋት መማር ካልቻልን ከምን ልንማር እንችላለን በእውነት? እንደ እኔ ሕመማችንን በአግባቡ ካልታከምነው እንደ ጋንግሪትም በድን ያደረገውን ቆርጠን ካልጣልነው ሙሉ በሙሉ መጥፋታችን የሚቀር አይመስለኝም። ስለዚህ ከይሉኝታ መጋረጃ ወጥተን ነገር ግን ደግሞ ሕግ እና ሥርዐት ጠብቀን በችግሮቻችን ላይ መዝመት መጀመር አለብን ብዬ አምናለሁ።  ምን ምን ችግሮቻችን ላይ ቆራጥ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን? ለዛሬው እንደ አርእስተ ኃጣውዕ ያሰብኳቸውን ሦስቱን አነሣለሁ። 

1) ባዕድ እጅ 

አቡነ ቴዎፍሎስን ለማውረድ ደርግ አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር ይባላል። ኮሚቴው የተሐድሶ ኮሚቴ ይባል ነበር አሉ። ለዚህ ኮሚቴ በሰብሳቢነት የተሾሙት ደግሞ አንድ እጃቸው አርትፊሻል ነበረ። ታዲያ ብዙ የቤተ ክህነት ሊቃውንትን በደብዳቤ እያስገደዱ ወደ ኮሚቴው ሲያስገቡ መልአከ ብርሃናት ተስፋ ወርቅነህ የሚባሉት ሊቅ በእኒህ ሰብሳቢ የተፈረመ ደብዳቤ ሲደርሳቸው አዝነው ቤተ ክርስቲያን ባዕድ እጅ ገብቶባታል የምትሆነውን እንጃ ብለው ነበር፤ ቅኔም ተቅኝተውበት ነበር ይባላል። 
 
ይህች ባዕድ እጅ ከዚያ ዘመን አንሥቶ እስካሁን ድረስ ትበጠብጣለች። ምንም እንኳ በየዋሕ ምእመናን፣ በጉባኤ ቤት መምህራን፣ በስውራን ቅዱሳን እና በየቦታው ባሉ ደጋግ ካህናት እና አገልጋዮች መኖር ምክንያት ረድኤተ እግዚአብሔር ስላልተለየን ፈጽመን ባንጠፋም በየዘመናቱ እየወረድን፣ እየተዋረድን እዚህ መድረሳችን ግን ከማንም የተሰወረ አይደለም። 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ወደ መንበረ ፕትርክናው ከመምጣታቸው በፊት ጥሩ የምርጫ ሕግ እንዲኖረን እና በመጨረሻም በድምፅ ከተመረጡት ሦስት አባቶች መካከል ፓትርያርክ የሚሆነው በጸሎት እና በዕጣ ይለይ የሚለውን ረቂቅ ለማስቀረት ይህች ባዕድ እጅ ብዙ ሚና ተጫውታለች ። በተለይ አንተን ነው ፓትያርክ የምናደርግህ እያሉ ፖለቲከኞቹ ያባበሏቸው እና ቅዠት ውስጥ የከተቷቸው ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ያለ ይሉኝታ ተቃወሙት ። አሁንም ድረስ ልባቸው ተላላ የሆኑና ከዚያ የማይማሩ ሰዎችን ስናይ እጅግ እንገረማለን፣ እናዝናለንም። በእውነት ልብን ያደማል። እስከመቼስ ሲደበቅ ይኖራል? 

ይህች ባዕድ እጅ ከባድ የምትሆነው ደግሞ ሁሌም ቤተ ክህነት ውስጥ ባለ እና እጁ በተቆረጠችበት ሰው በተቆረጠችበት እጁ ምትክ በባለሞያዎች እውነተኛ እጅ መስላ የምትቀጠል በመሆኗ ነበር። ይህች እጅ እስካሁን ታቦካለች፣ ትጋግራለች፣ ትሾማለች ፣ ትሽራለች ። ተላላ ልቦችን እያባበለች ወደ ጥፋት ገደሏ ትከታለች። እከብር ባይ ልቡናዎችን በሕልም ዐለም ይዛ ትጠፋለች፣ በምናባዊ ሹመት ታሳብዳለች ። ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዳየሁት ዛሬ ከተሾሙት ውስጥ ከመሾማቸው በፊት እንደ ጳጳስ ለብሰው ፎቶ የሚነሡ ነበሩበት ፤ ይገርማል፣ ያሳዝናል። ይህች እጅ የቅባት ጳጳሳትን በጥንቃቄ አዋልዳለች ።  መንበረ ሰላማ የጵጵስና መንበረ ተክለ ሃይማኖት ደግም የእጨጌነት እንጂ የፓትርያርክ አለመሆኑን እንኳ የማያውቁ ሰዎችን አሰባስባ በትግራይም ታገሣለች ። ይህች ባዕድ እጅ አሁንም የልዩነት ገደላችን ትቆፍራለች፣ ታሰፋለች፣ ታስፋፋለች ።  በእነዚህ ዘመናትም በሕጉ እና በተግባሩ መካከል ያለውን ገደል አስፍታ አስፍታ በአብርሃምና በነዌ መካከል ያለውን ገደል አድርጋዋለች ። በእውነት ያሳዝናል። 

ይህች እጅ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለባት ። የምትወገደው ደግሞ እኛ ቆርጠን ስንነሣ ነው። ግብጾች አሁን ያላቸውን የምርጫ ሕግ ያወጡትን እና ብዙ ተደራራቢ የቆየ ችግራቸውን የፈቱት ሁሉም ምእመን በተሳተፈበት ሁለት ዐመት ተኩል በፈጀ ውይይት እና በመጨረሻም ሕግ አውጥተው በመፈጸም ነው። ቫቲካንም የፖፕ ምርጫውን በተዘጋ ቤት እና በጢስ ብቻ እንዲታወቅ አድርጋ በሯን የቆለፈችው ይህችን የባዕድ እጅ ላለማስገባት ነበር። ሌሎች አብያተክርስቲያንም ይህችን እጅ ቆርጠው ጥለው ቀኖናዊነታቸውን ለማስከበር በቅተዋል። እኛ ጋር ግን አሁንም ድረስ በየድስቱ እየገባች ታማስላለች ። እስከመቼ ግን እንዲህ ልንቀጥል እንችላለን? ይህች ባዕድ እጅ መሰብሰብ ይኖርባታል። 

2) የምእመናን ድርሻ የረሳ ኢቀኖናዊ ሲመት

በቀኖናችን በሚሾምበት ሀገረ ስብከት ያሉት ምእመናን ያለተቀበሉት ሰው በጵጵስና እንዳይሾም የተከለከለ ነው። እኛ ሀገር ግን ያለው የተገላቢጦሽ ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ከላይ ያነሣናትን ባዕድ እጅ ጉልበት የሰጣት ይሔው የክርስቶስን በጎች ምእመናንን ፈጽሞ የረሳ እና የተወ ኢቀኖናዊ ሹመት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ኢቀኖናዊ ድርጊት ቢያንስ ከዚህ በኋላ በፍጹም ሊኖር አይገባውም። ይህ ቀደም ብሎ ተጀምሮ ቢሆን ኖሮ እንዲህ በአንድ ሌሊት 25 ሰው ተሹሞ ሊያድር አይችልም ነበር። ምንም እንኳ ብቸኛ ምክንያቱ ይህ አለመኖሩ ባይሆንም ይህ ጉዳይ እስካሁን ለደረስንበት ውስብስብ ችግር አስተዋጽዖው ከፍተኛ መሆኑ ይታየኛል። ምክንያቱም በዘር የተሾመ በዘር ይሾማል። በፖለቲካም የተሾመ በፖለቲካ ይሾማል። በኮታ የገባ ኮታዬ ከዚህ በላይ ነው ብሎ ማሰቡ አይቀሬ ነው። በአንዱ ተገፍቻለሁ የሚለውም ወደ ሌላው ይጠጋል።
 
3) ጎጠኝነት

በአሜሪካን ሀገር እምነታቸውን ወደ ምሥራቅ ኦርቶዶክስነት የቀየሩ አንድ አሜሪካዊ አባት በአሜሪካ የሚኖሩ የተለያዩ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ሁኔታ ይተቻሉ። የሚተቹት አንድ ኦርቶዶክስ ከሆንን እና በአንድ ሀገር ከኖርን ለምንድን ነው የግሪክ፣ የሩሲያ ፣ የሰርቢያ፣ የሮማኒያ፣ ... እየተባባልን የምንለያየው? ለምን በአንድ መንበር እና አስተዳደር ውስጥ አንሆንም የሚለውን ሀሳባቸውን ለማስረዳት ያነሡት ጥያቄ አለ። አትናቴዎስ አሁን ቢመጣ የትኛው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው የሚሔደው? ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ኤፍሬም፣ ... ቢመጡ የትነው የሚሔዱት? እኛስ ማንኛውን ነው የምንጋብዘው ወይም የምንቀበለው የሚለውን ጥያቄ በማንሣት በተለያየ ሀገር እንኳ መከፋፈል እንደሌለባቸው ይሞግታሉ። 

እኛ ደግሞ በአንድ ሀገር እንኳ ሆነን ቅዱሳኑን ሳይቀር የዚህ እና የዚያ አካባቢ እያልን እናቃልላለን። እጅግ እጅግ ምሳሌ የማይግኝለት ጎጥኝነት ውስጥ መኖራችንን መደበቅ አይቻልም። በዚህ ገምተናል፣ ተግማምተናልም። ባለፉት ሹመቶች እንኳ እገሌ ከዚህ አካባቢ ዘር አለበት እየተባሉ ዕጩ ከሆኑበት ሀገረ ስብከት የተተውትን እንዴት መርሳት ይቻላል። ያ መራራ ሒደት ነው ዛሬ ይህን መራራ ውጤት ያመጣው። ዛፉ መራራ ከሆነ ፍሬውም መራራ ነው የተባለው ነዋ እየሆነ ያለው። እነዚህን ችግሮች ፊት ለፊት መግጠም እና ማሸነፍ እስካልቻልን ድረስ እየተነቃቀፍን፣ እየተማማን፣ እየተጠላላን፣ እየተነዋወርን እንደምንጠፋ ምንም ጥርጥር የለውም።  ይህን ሁሉ ለዚህ ከፍታ ያበቃችው ግን ያች ባዕድ እጅ መሆኗን አምናለሁ።  እነዚህ ለዚህች ባዕድ እጅ ጓንትና መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ስለሆነ በፍጥነት ካላሻሻልናቸው ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው እየተሳሳቅን እና እየተሳለቅን ልንጠፋ እንችላለን።

ድክመቶቻችን አርመን ከችግሮቻችን ወጥተን ለማየት እንድንችል ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ አሜን።

"መንግሥት ቤተ ክርስቲያንና አባቶችን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ልጆቻቸው ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል፤ በቂ ዝግጅትም አድርገናል።"የመንፈሳዊ ማኅበራትና የኅብረቶች የጋራ መግለጫ

ዛሬ ጥር 16 ምሽት ማኅበረ ቅዱሳን፣ አገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት፣ ምእመናን ኅብረት ፣ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት፣ የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት በጋራ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም የማኅበራቱ ተወካዮች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካጋጠማት ታሪካዊ ክስተት አንጻር  ከመቼውም ጊዜ በላይ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የምናስጠብቅበት እና ከአባቶቻችን ጎን የምንቆምበት ወቅት በመሆኑ በኅብረት መክረን አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል ብለዋል።

ማኅበረ ቅዱሳንን ወክለው የተገኙት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሙሉጌታ ሥዩም በመግለጫው እንደተናገሩት የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ያቃለለ የነገ የሐዋርያዊ አገልግሎትን ያሰናከለ በመሆኑ አባቶቻችን ይህንን ያማከለ ውስኔ እንዲወስኑ እንጠይቃለን ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም መንግሥት እጁን ከዚህ ሂደት እንዲያነሳ ይልቁንም የእሱ ግዴታ የሆነውን ጥበቃ እንዳያነሳ ይህ ካልሆነ ግን ኦርቶዶክሳውያን ቤተ ክርስቲያን እስከሰማእትነት ለመታደግ የታመኑ ናቸው ብለዋል። ምእመናንም ሳይደናገጡ በጸሎት እንዲተጉ እና ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከመንግሥት ጋርም በቀጣይ ችግሩን እንዲረዳና ቤተ ክርስቲያን የራሷን ችግር በራሷ እንድትፈታ እድል እንዲሰጣት መወያየታቸውን በመግለጽ የዜጎችን ደህንነት ካልጠበቀ ግን ከተጠያቂነት አይድንም ሲሉ ገልጸዋል።

አንድ ያደረገን ድርጊቱ ሕገ ወጥ መሆኑና ሀገርና ቤተ ክርስቲያን የሚንድ በመሆኑ ነው ያሉት ደግሞ አገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት ተወካይ አቶ ያሬድ ዮናስ ናቸው። ችግሩን ከማወገዝ ባለፈ ከእኛ የሚጠበቀውን ለማድረግ ተዘጋጅተናል፤በእያንዳንዳችን መዋቅርም ስራዎችን ለመስራትም ተነጋግረናል ብለዋል።

የምእመናን ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳ ቤጥ አምዴ በበኩላቸው ውይይት በአንድ ሃሳብና ልብ መከናወኑን ገልጸው ቅዱስ ሲኖዶስ ተደፍሯል፣አባቶች ተደፍረዋል፤ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ችግር ለማውጣት ሁላችንም በቁርጠኝነት ተነስተናል ብለዋል። በውይይታቸውም በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንደማይደራደሩ አፅንዖት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና በአባቶች ላይ የተቃጣውን ለመመለስ በአባቶቻችን ጥሪና መመሪያ ተመስርተን ለመሄድ ቃል ገብተናል ያሉት ደግሞ የጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ተወካይ አቶ አያልነህ ተሾመ ናቸው። አክለውም ይህ የህልውና ጉዳይ ሀገር የማፍረስ ጉዳይ በመሆኑም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት ተወካይ ወ/ት ፌቨን ዘሪሁን በበኩላቸው ዛሬ በነበረን ውይይት ሁላችንም ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንድንሆንና የድርሻችንን ለመወጣት መስማማታቸውን በመግለጽ ለዚህም የአባቶችን መመሪያ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቅድስት ቤተ ክርስትያንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተገኝተው ለማስረዳት ዝግጅት መጨረሳቸውንም በመግለጫቸው ገልጸዋል። 
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግስት ከለላውን አንስቷል ሲሉ ዛሬ ምሽት መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

ከማኅበረ ቅዱሳን ኤፍ ቢ ገጽ

‹‹ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ህልውና ለመጠበቅና ለፍጹም አንድነቷ ‹አንድ አድርን› blog ወደ ቀደመ ስራዋ የተመለሰች መሆኗን ለማሳወቅ እወዳለን፡፡ ››

 

(አንድ አድርገን ጥር  2015 ዓ.ም) ፡- ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን  ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት  የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ  ትምህርት ያስጀመረች፣  የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች ቤተክርስቲያን ሆና ሳለ ዛሬ ዛሬ በዘመናችን የምናየው እና የምንሰማው ነገር ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› በመሆኑ …... ፤  ምዕመና  ስለ  አንዲት  ቅድስት  ቤተክርስቲያንን በሚመለከት ዕለት በዕለት  የሚታየዉ ፤ የወደፊት ስጋት ምን እንደኾነ ኹሉም  የእናት ቤተክርስቲያን ልጆች እንዲያውቁት የበኩላቸውንም መፍትሔ እንዲፈልጉ ፤ ሐሳብ እንዲሰጡ  በክርስትናቸው የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ ፤ የክርስቶስን መስቀል ለመሸከም  የማይሰቀቅ ክሣደ ኅሊና አንዲኖራቸው  ለስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮዋ መሳካት ፤ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ህልውና መጠበቅና ለፍጹም አንድነቷ እንዲነሡ የበኩላችንን ኃላፊነት እንዲወጡ ‹አንድ አድርን›  blog ወደ ቀደመ ስራዋ  የተመለሰች መሆኗን ለማሳወቅ እወዳለን፡፡ 

Please share 

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

 ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ