- ‹እኛ ራሳችንን ለሰይፍ አዘጋጅተን የተቀመጥን ሰዎች ነን ፤ እኛን ገድላችሁ ስኳር ፋብሪካውን መስራት ትችላላችሁ ፤ እኛ የዋልድባ አፈር ጠባቂ ነን እንጂ ጠባቂው መድኃኒዓለም ነው ፤ ዋልድባን ብታከብሩት ትከበራላችሁ ፤ ብታቀሉት ትቀላላችሁ ፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ ፤ እኛ ይግባኝ ለክርስቶች ሰጥተናል›› የገዳሙ አባቶች ከ4 ዓመት በፊት
(አንድ አድርገን መጋቢት 26
2009 ዓ.ም)፡- አባ ገብረ ኢየሱስ በዋልድባ ገዳም ላይ መንግሥት ሊሰራ ያሰበውን የስኳር ፋብሪካ ገዳሙን በመወከል የአባቶችን
ድምጽ በመያዝ ከአራት አመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እና በብጹ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር መልዕክት ይዘው
ከመጡት አባቶች እንዱ ናቸው ፤ እኚህ አባት ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ለገዳማቸው እጅግ ተቆርቋሪ ከመሆናቸው የተነሳ የመንግሥትን ማስፈራሪያ
፤ የደህንነቶችን ክትትል ፤ የትግራይ መስተዳደር ክልልን ጸጥታ ቢሮ ስር ያሉ ተቋማትን ዛቻ ወደ ጎን በማለት ገዳሙ ያጠላበትን
ችግር በመገንዘብ ገዳሙ ያለበትን የወቅቱን ሁኔታ ከገዳሙ ርቀው ለሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን እና የመገናኛ ብዙሃን በማሳወቅ ሃይማኖታዊ
ግዴታቸው የተወጡ ታላቅ አባት ናቸው ፡፡ ከገዳሙ በሺህ ኪሎሜትር ርቆ የሚገኝ ምዕመን በየጊዜው ስለ ገዳሙ ወቅታዊ አቋም ትክክለኛ
መረጃ የሚሰጡን አባ ገብረ ኢየሱስ ነበሩ፡፡
አባ ገብረ ኢየሱስ ከወር በፊት
ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ የፍርድ ቤት ማዘዣ ሳይቆረጥላቸው በደህንነት ሃይሎች ከፍተኛ ማንገላታት ፤ የዱላና
ሰደፍ ድብደባ ከደረሰባቸው በኋላ ታፍነው ሊወሰዱ ችለዋል ፤ እኚ አባት የተያዙበት ዋናው ምክንያት በየጊዜው ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን
የሚሰጡት መረጃ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ፤ ያሰራቸው አካል አባ ገብረ ኢየሱስ ያሉበትን ሁኔታ ፤ የታሰሩበትን ምክንያት
፤ ያሉበትን እስር ቤት የገለጸበት አግባብ የለም፡፡
ከወራት በፊት ከቦታው የተገኝ መረጃ
እንደሚያመለክተው በመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸው ማኅበራት አማካኝነት የገዳሙ ይዞታ የሆነውን ደን በመጨፍጨፍ የከሰል ማክሰል ሥራ
ላይ የተሰማሩ ሰዎች አካባቢውን መውረራቸውን አባ ገብረ ኢየሱስ ለቪኦኤ አሳውቀው ነበር፡፡ እነዚህ ከአድርቃይ ወረዳ ጽ/ቤት ፍቃድ
ያላቸው ግለሰቦች 5ሺህ ብር ከፍለው በመደራጀት በገዳሙ ይዞታ ላይ የሚገኝ ደን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው ታውቋል፡፡ በወቅቱም
በሕዝብ ተሳትፎ ሥራውን እስካቆሙበት ጊዜ ድረስ ከ1000 ኩንታል ማዳበሪያ ከሰል ማክሰል ችለው ነበር፡፡
ዋልድባ ገዳም ላይ የሚደርሱ የመብት
ረገጣዎችና ገፈፋዎች ከጊዜ ጊዜ መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸው ይስተዋላል ፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ መላው የእምነቱ ተከታይ ይህን
በገዳሙ ላይ እና በመነኮሳት ላይ የሚደርሱ በደሎችና ግፎችን እንዲቆሙ
ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል ፤ ትላንት አባቶች ከመንግሥትም ሆነ ከቤተክህነቱ ይህ ነው የሚባል መልስ ሳያገኙ ሲቀሩ ‹‹እኛ ራሳችንን
ለሰይፍ አዘጋጅተን የተቀመጥን ሰዎች ነን ፤ እኛን ገድላችሁ ስኳር ፋብሪካውን መስራት ትችላላችሁ ፤ እኛ የዋልድባ አፈር ጠባቂ
ነን እንጂ ጠባቂው መድኃኒዓለም ነው ፤ ዋልድባን ብታከብሩት ትከበራላችሁ ፤ ብታቀሉት ትቀላላችሁ ፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ማድረግ
ትችላላችሁ ፤ እኛ ይግባኝ ለክርስቶች ሰጥተናል›› ብለው ተናግረው ነበር፡፡
እኚህ አባት እውነታን መሰረት አድርገው
መረጃ ስለሰጡ ሊታሰሩ አይገባቸውም ፤ አሁንም ቢሆን ያሰራቸው አካል የተያዙበትን ምክንያት ፤ ያጠፉትን ጥፋት ፤ ያሉበት ቦታ የማሳወቅ
ግዴታ አለበት ፤ ቤተክርስቲያኒቱም ስለ አባ ገብረ ኢየሱስ ያሉበትን ሁኔታ ከመንግሥት አካል በመጠየቅ ለምእመኑ የማሳወቅ ግዴታ አለባት ፤ እኛም ምዕመናን የእኚህን አባት ስለ ዋልድባ ገዳማችን
እና ስለ አንዲት እምነታችን የከፈሉትን መስዋዕትነት በማሰብ ያሉበትን ቦታ ፤ የታሰሩበትን ሁኔታ የማወቅ መብት ስላለን በትክክል
አፋኙ አካል ሊያሳውቀን ይገባል እንላለን፡፡
እኛም አባታችን ያሉበትን ቦታ በትክክል
እስክናውቅ ድረስ አብዝተን እንጮሃለን …..
ተጨማሪ መረጃዎችን ተከታትለን የምናሳውቅ
ይሆናል…..
No comments:
Post a Comment