(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም.)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ይፃረራል፤ ያሉት የትግርኛ ቋንቋ
ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከሥርጭት እንዲታገድላቸውና እንዲወገድላቸው፣
የመቐለ ምእመናን የጠየቁ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በበኩሉ፣ “ትርጉሙ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት የተሠራ ነው፤ ስሕተት አለው፤ የሚል
እምነት የለንም፤” ብሏል፡፡
ከ40 በላይ
የሆኑ ምእመናን የተፈራረሙበት
ማመልከቻ፤ ለትግራይ አህጉረ ስብከት 4 ሊቃነ
ጳጳሳት በግንቦት 2008 ዓ.ም
ያቀረቡ ቢሆንም፤ ለጥያቄያቸው እስከ አሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው
ምዕመናኑ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ እና የወንጌላውያን
ኅብረት አብያተ ክርስቲያናት አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያሳተመው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ፤ “ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ በተፃራሪ፡- የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚክድ፣ የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያዛባ፣ ሥልጣነ ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል፣ የቤተ
ክርስቲያኗን ፊደልና ቁጥር አቆጣጠር የማይቀበል እንዲሁም፣ ቤተ ክርስቲያኗ የምትቀበላቸውን 81 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ጎን በመተው 66 መጻሕፍትን ብቻ ያካተተ በመሆኑ፣ እምነትን የሚያስክድ ነው፤
ይወገድልን፤” ብለዋል - ምዕመናኑ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ ታትሞ በገበያ ላይ ከዋለ በኋላ፣ 92 በመቶ
የሚሆነውን የክልሉን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ግራ እያጋባ መሆኑንም ምዕመናኑ በማመልከቻቸው
ጠቁመዋል፡፡ የቤተ
ክርስቲያኒቱን ዶግማ
ይፃረራል፤ የተባለው ይኸው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደተለያዩ የከተማና እና
የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዳይሰራጭና ዳግመኛም እንዳይታተም እንዲታዘዝላቸው ምዕመናኑ ጠይቀዋል። የትርጉሙን ስሕተት የሠሩ አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑና ርምጃ እንዲወሰድባቸው
ምዕመናኑ አያይዘው ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጠቅላይ ጸሐፊ፣ መምህር ይልማ ጌታሁን፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በግልጽ የቀረበ አቤቱታ እንደሌለ ገልጸው፣ አቤቱታ አቅራቢዎች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅሬታ አቅርበው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዩን እያየችው መሆኑን መረጃ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ትርጉሙ፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ሊቃውንት በጥንቃቄ የተሠራ መሆኑን የጠቆሙት መምህር ይልማ፣ “ሥራው ስሕተት አለው
ብለን አናምንም፤ አለው ቢባል እንኳ ሊቃውንቱን ነው
መጠየቅ ይችሉ
የነበረው፤” ብለዋል፡፡ የትርጉም ሥራው፣ በሊቃውንት ተመርምሮ ፓትርያርኩ ባሉበት ተመርቆ እንዲሰራጭ መደረጉንም መምህር ይልማ አስረድተዋል፡፡
“ትርጉሞች፣ በቤተ ክርስቲያን ፈቃድና ተሳትፎ የሚሠሩ ናቸው እንጂ፣ ማኅበሩ በራሱ ተነሣስቶ የሚያደርገው አይደለም፤” ያሉት መምህር ይልማ፤ እስከ አሁንም፣ የትርጉም ስሕተት አለበት፤ የሚል ጥቆማ ለማኅበሩ እንዳልቀረበ አስታውቀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment