- ‹‹የራበውን ሰው ለዛሬ ዓሳ አብላው፣ ለሕይወት ዘመኑ እንዲጠቅመው ግን ዓሳ ማጥመድ አስተምረው፤›› የሚባለው የቻይናውያን ታዋቂ አባባል ማስታወስ እንደ ግለሰብም፣ እንደ አገርም ጠቃሚ ነው፡፡
- ሆዱን በሆዱ ይዞ የሚኖር ሕዝብ ውስጥ በአደባባይ የሚደረግ የታይታ ልገሳ ኃፍረት ይፈጥራል
- ዕርዳታ ተቀባዮች ከአቅም በላይ ሆኖባቸው በአደባባይ ልገሳ ይቀበላሉ እንጂ፣ ከኢትዮጵያዊ ኩራታቸውና ማንነታቸው ጋር የሚጋጩ ስሜቶች ይታዩባቸዋል
ሕዝባችን እንደ እምነቱ፣ ባህሉና ልማዱ የተለያዩ በዓላትን ያከብራል፡፡ በዓላት እጅግ የተከበሩና የሚወደዱ በመሆናቸውም በሕዝባችን ውስጥ የመረዳዳት ባህሉና መስተጋብሩ የዚያኑ ያህል ትልቅ ክብረት አለው፡፡ ወትሮም የተቸገረን ባለ አቅም መርዳትና በበዓላት ወቅት አብሮ መብላት፣ መጠጣትና መደሰት ዘመናትን የተሸጋገረ የሕዝባችን ፀጋ ነው፡፡ ይህ ወደር የማይገኝለት የጋራ እሴት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከትና በመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገደብ የቀጠለ አኩሪ ተግባር ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ጨዋነት፣ ሥነ ምግባርና ርህራሔ የሚታይበት ይህ የሕዝባችን የመረዳዳት ባህል የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የጥንካሬ መንፈስ ማሳያም ነው፡፡ ዛሬ አቅም ያለው የተቸገረን ሲረዳ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በተራው በሌሎች ይረዳል፡፡ መስጠትና መቀበል የበላይነትና የበታችነት ማሳያ ሳይሆን፣ ይልቁንም ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጫ ቱባ ባህል ነው፡፡ በቀደመው ትውልድም ሆነ አሁን ባለው ዘንድ የሚከበር ተምሳሌታዊ መስተጋብር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነት መኩሪያ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ እሴት እየተሸረሸረ ነው፡፡ መነጋገር ይገባል፡፡
በዚህ ዘመን በዓላትን አስታከው ዜጎች መኖሪያ ቤት ድረስ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚቀርቡ ‹‹ልዩ ዝግጅቶች›› የሕዝባችንን ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች እየተፈታተኑ ነው፡፡ የተቸገረን መርዳት የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚቀጥል ሰብዓዊ ተግባር ቢሆንም፣ የልመና ማስፋፊያና አዲሱን ትውልድ የተረጂነት ምርኮኛ እንዲያደርጉ መፈቀድ የለበትም፡፡ በስመ ዕርዳታ ልመናን የሚያበረታቱና በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ድጋፎች አቅጣጫቸውን እየሳቱ፣ ሙያተኞችን ሳይቀር ልመናና ብልሹ ድርጊቶች ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጎች እንዴት ተረድተው ወደ አምራችነት ይሸጋገሩ ከማለት ይልቅ፣ ከቀናት አስፔዛ የማያልፍ ሳንቲም ጣል አድርጎ የበለጠ ጠባቂ እንዲሆኑ ማድረግ መቆም አለበት፡፡ ወላጅ አልባ ሕፃናት በተቻለ አቅም መሠረታዊ የሚባሉትን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከማግኘት በተጨማሪ ትምህርት ቤት ገብተው የነገ አገር ተረካቢ ዜጋ መሆን ሲገባቸው በስማቸው መነገድ የለበትም፡፡ በአረጋውያን፣ በአካል ጉዳተኞችና በአቅመ ደካሞች ስም መነገድ መቆም አለበት፡፡ በተለይ በዓላትን ተንተርሶ በየአዳራሹ የሚከናወኑ አጓጉል ትወናዎች ሃይ የሚላቸው አካል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ‹‹ልዩ›› የሚባሉ ፕሮግራሞችን ሳይወዱ በግድ እንዲከታተሉ የሚደረጉ ዜጎች ጭምር በቃ ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ በልመና አገር መዋረድ የለበትም፡፡ ያለፈው ይበቃል፡፡
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ስም ከፍተኛ የአገርና የሕዝብ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ሪል ስቴቶች፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ራሳቸውን በቅጡ መፈተሽ አለባቸው፡፡ በተለይ በስመ ጋዜጠኝነት፣ ተዋናይነት፣ ወይም በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎችም ከራስ ግላዊ ጥቅምና ዝና በላይ ለዜጎች ክብርና ደኅንነት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያዊ ጨዋነትና መልካም ሥነ ምግባር ራሳቸውን ማስገዛት አለባቸው፡፡ ይህ ታላቅ የጋራ እሴት በግል ጥቅም እየተጠለፈ በምስኪኖች ስም የሚገኝ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ባለሙያዎችን ጭምር ማባለግ የለበትም፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነት ማለት በሥነ ምግባር ላይ በመመሥረት ለማኅበረሰቡ የጋራ ጥቅም አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡ አስተዋጽኦው ቢያንስ መግባባት መፍጠር አለበት፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነት በዓላትን ተንተርሶም ሆነ በሌላ ጊዜ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ኃላፊነት የሚሰማው ተልዕኮ ማስፈጸሚያ እንጂ፣ የይስሙላና የታይታ ድርጊት እየፈጸሙ የአገርና የሕዝብ ሀብት ያላግባብ ማባከን አይደለም፡፡ የጨዋነት እሴቶችን መደፍጠጥ አይደለም፡፡ በተለይ በዓላትን ዒላማ ያደረጉ ‹‹ልዩ›› የሚባሉ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉ ዝግጅቶች ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወይም ከቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛዎች የተመረቁ ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ገቢ በማግኘት ራሳቸውን ማሻሻል መጀመራቸው መወደስ አለበት፡፡ ሕዝብ እንዲያውቃቸውም መደረግ እንዲሁ፡፡ ነገር ግን በስመ ስፖንሰርሺፕ ከተገኘ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ላይ እነዚህን ወጣቶች በማንኪያ እያቀመሱ ለማሳነፍ መሞከር መወገዝ አለበት፡፡ ይኼ ልመናን ማወደስ (Celebrating Poverty) የሚመስል ተግባር የበዓላት ማዳመቂያ እየሆነ እንዴት ይቀጥላል? ሙያተኞች ሳይቀሩ በተቸገሩ ሰዎች ስም የተዘጋጁ ድጋፎችን የሚቀራመቱበት መድረክ መፍጠርስ ምን ይሉታል? ታዳጊዎችንና ወጣቶችን የዚህ ዓይነቱ ተፅዕኖ ሰለባ እንዲሆኑ መገፋፋት አይሆንም ወይ? በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ከቤተ እምነቶች አልፎ ጎዳናውን የወረረው ልመና ላይ በቂ ጥናትና ምርምር ተደርጎ ለመፍትሔ የሚሆን ውጤት እንዲቀርብ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ይሻላል? ወይስ በኮሚሽን ተቀራማቾች የተሸራረፈና አንጀት ላይ ጠብ የማይል የዕለት ከንቱ ልገሳ ላይ መሰማራት? ‹‹የራበውን ሰው ለዛሬ ዓሳ አብላው፣ ለሕይወት ዘመኑ እንዲጠቅመው ግን ዓሳ ማጥመድ አስተምረው፤›› የሚባለው የቻይናውያን ታዋቂ አባባል ማስታወስ እንደ ግለሰብም፣ እንደ አገርም ጠቃሚ ነው፡፡ የተቸገሩ ወገኖችን በአግባቡ የመርዳት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አዋጭ ያልሆኑ ድርጊቶች ውስጥ ላለመግባት ይረዳል፡፡
በሌላ በኩል ሕዝባችን በዓላትን ባለ አቅሙ እየተረዳዳ በፍቅር ሲያከብር ቤቱ ተቀምጦ መመፃደቅ በውስጣቸው ያመቁ የተሳሳቱ የዕርዳታ መልዕክቶችን በግድ ማየትም መስማትም የለበትም፡፡ መስጠትና መቀበል የጋራ መስተጋብሩ በሆነ ሕዝብ ውስጥ፣ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ ሆኖ መቅረብ የራሱ ሥነ ልቦናዊ ጫና አለው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደታየው ዕርዳታ ተቀባዮች ከአቅም በላይ ሆኖባቸው በአደባባይ ልገሳ ይቀበላሉ እንጂ፣ ከኢትዮጵያዊ ኩራታቸውና ማንነታቸው ጋር የሚጋጩ ስሜቶች ይታዩባቸዋል፡፡ ይህ መላምት ሳይሆን ትዕይንቱን በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚከታተሉ ዜጎች ላይ ጭምር በሚገባ ስለሚንፀባረቅ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ዕጦት ቢፈጠር የሆዱን በሆዱ ይዞ የሚኖር ሕዝብ ውስጥ በአደባባይ የሚደረግ የታይታ ልገሳ ኃፍረት ይፈጥራል፡፡ እዚህ ላይ መሳሳት አያስፈልግም፡፡ የተቸገሩ አይደገፉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ድህነት ከመጠን በላይ በበዓላት ቀናት እየተራገበ የሰጪና የተቀባይን ግንኙነት የበላይና የበታች እንዳያደርግ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ በበዓላት ሁሉም እንዳቅሙ ያዘጋጀውን በመረዳዳትና በፍቅር ስሜት በሚቃመስበት አገር ውስጥ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ስም የተረጂነትና የበታችነት ስሜት የሚፈጥሩ አጓጉል ድርጊቶች ሲበዙ ጥሩ አይደለም፡፡ የቀኝ እጅ የመፀወተውን የግራ እጅ እንዳያይ እንዲል መጽሐፉ ማገዙም፣ መደገፉም፣ መተሳሰቡም ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ጨዋ ባህል መሞርከዝ አለበት፡፡ ይህ ያግባባል፡፡
በአጠቃላይ የሕዝብን ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ልማድ፣ አማካይ ፍላጎትና ስሜት በማጤን ልመናን መቀነስ ብሎም ማስወገድ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡ እጅግ በጣም አሳፋሪና አንገት አስደፊ የሆነው ድህነት ጎዳና ላይ በይፋ በሚታዩና በሥውር ልመናዎች በግልጽ ይታያል፡፡ ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀምሮ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ድረስ ልመናን መልክ የማስያዝ ኃላፊነት ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ኃላፊነት እነማን መረዳት አለባቸው ከሚለው ጀምሮ፣ በተደራጀና በተጠና መንገድ መፍትሔ ለማፍለቅ ግልጽና የማያሻማ ውይይት መኖር አለበት፡፡ ልመናን በማስወገድ ስም ያልተገባ ጥቅም የሚያጋብሱ አደብ ገዝተው፣ ወጥና የተደራጀ ዘለቄታዊ መፍትሔ በሳይንሳዊ ሥነ ዘዴ እንዲገኝ መሠራት አለበት፡፡ ጊዜ መስጠት አይገባም፡፡ መንግሥትም ሆነ የሕዝብ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ኩባንያዎች ከአጉል ልታይ ባይነት ወጥተው ለዘለቄታዊ መፍትሔ እየሠሩ፣ እግረ መንገዳቸውን ዕርዳታ የሚሹ ወገኖችን መደገፍ ይችላሉ፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ሲኖረው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማካተት በሕግ ጥላ ሥር መሆንን ጭምር የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የተቸገሩ ወገኖች በተጨማሪ፣ ባለሙያዎችን ጭምር የተረጂነት አባዜ ውስጥ የከተተው አጓጉል አካሄድ ለአገር አይበጅም፡፡ ለታዳጊዎችና ለወጣቶች ክፉ ምሳሌ ነው፡፡ ከሕዝባችን ጨዋነት ጋርም አይጣጣምም፡፡ በመሆኑም በዓላት የልመና ማስፋፊያ አይደረጉ!
source :- Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment