Tuesday, April 4, 2017

የዋልድባውን መነኩሴ የአባ ገብረ ኢየሱስን በመንግሥት ታጣቂዎች ታፈኑ



ጉዳዩ  የዋልድባውን መነኩሴ የአባ ገብረ ኢየሱስን በመንግሥት ታጣቂዎች መታፈን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
“. . . እንግዲህ አትፍሩአቸው የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሀነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። . . .” ማቴዎስ ፲ ከ፳፮ - ፳፰

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኃይማኖታቸውን በምንም የማይለውጡ ፣ ለእምነታቸው እራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ፣ ወንጌሉን በተግባር የሚተረጉሙና በሕይወታቸው የሚያሳዩ እውነተኞች ቅዱሳን አባቶች የነበሩባትና ያሉባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። እነዚህ አባቶች በሕዝብ ላይ ግፍና በደል ሲፈጸም፣ ፍርድ ሲጓደል ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃትና ጉዳት ሲደርስ ምንም ሳይፈሩና ሳይሰቀቁ ሁኔታውን ለሕዝበ ክርስቲያን በማጋለጥ በየዘመኑ ከሚነሱ ዐላውያን ነገሥታት ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጡ በሥጋቸው መከራን በመቀበል ከፈጣሪያቸው የክብር አክሊልን ተቀዳጅተዋል። ይህንን ለማወቅና ለመረዳት የሰማዕታቱንና የጻድቃኑን ገድልና ድርሳን መመልከት በቂ ምስክር ነው።

ዛሬም የእነዚህን ጻድቃንና ሰማዕታት አሰረ ፍኖት ተከትለው ከላይ የጠቀስነውን የወንጌሉን ቃል በሚገባ የተረዱ፣ ለኃይማኖታቸው እራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡና ሕይወታቸውን በስቃይ የሚያሳልፉ የተመረጡ ንጹሐን አባቶች አሉ። ከእነዚህ ንጹሐን እውነተኞች አባቶች መካከል ለዚህ መግለጫ ምክንያት የሆኑን የዋልድባው መነኩሴ አባ ገብረ ኢየሱስ አንዱ ናቸው።
አባ ገብረ ኢየሱስ በ፳፻፬ ዓመተ ምሕረት መንግሥት በልማት ሰበብ የዋልድባን ገዳም በደፈረበትና የቅዱሳኑን አጽም ባፈለሰበት ጊዜ የገዳማውያኑን አቤቱታ ወደ ቤተ መንግሥቱና ወደ ቤተ ክህነቱ ይዘው ሔደው ተቀባይና ሰሚ ባለማግኘታቸው በመጨረሻ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ አማካኝነት ጉዳዩን ሕዝብ እንዲያውቀው ያደረጉ ጥብዓትን የተሞሉ እውነተኛ አባት ናቸው። እኚህ አባት ቅዱስ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነው የዋልድባ ገዳክብሩ አይደፈርም፣ ይዞታው አይነካም በማለታቸውና በልማት ሽፋን የተሸረበውን የመንግሥት ሤራ በማጋለጣቸው ለረዥም ዓመታት ከኖሩበት በዓታቸው እንዲወጡ ተደርጎ ከአምስት ዓመታት በላይ መቆሚያና መቀመጫ አጥተው ከአንዱ ገዳም ወደ ሌላው ገዳም ሲንከራተቱ ከቆዩ በኋላ ባለፈው ጥር ወር ፳፻፱ ዓመተ ምሕረት ሱባዔ ከያዙበት ጎንደር ውስጥ ከሚገኝ አንድ ገዳም በመንግሥት ኃይሎች ታፍነው መወሰዳቸው ታውቋል። በተያዙበት ወቅት ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው በቦታው የነበሩ አባቶች ገልጸዋል። ነገር ግን ታፍነው ከተወሰዱ ሰዓት ጀምሮ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ፍንጭ አልተገኘም።
ስለሆነም ተቋማችን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት እኚህ እውነተኛ የኃይማኖት አባትና ጽኑ የእምነት አርበኛ የት እንደሚገኙ ለማወቅ በተለያየ መንገድ ክትትል እያደረገ ቢሆንም እስ አሁኗ ሰዓት ድረስ ፍንጭ  ሊገኝ ባለመቻሉ ጉዳዩን ካህናትና ምዕመናንም አውቀውት የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ለታመነበት ይህንን መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል
በዚህም መሠረት ከዚህ የሚከተለውን ጥሪዎች ለአባቶች፣ ለመንግሥት አካላትና በአጠቃላይ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በሙሉ እናቀርባለን።
፩ኛ እኛ ክርስቲያኖች ችግርን የምናልፍበትና መከራን የምንሻገርበት ብሎም ድል የምንነሳበት ትልቁና ዋናው መሣሪያችን ጸሎት እንደመሆኑ መጠን አሁንም እኚህን እውነተኛና ቆራጥ መንፈሳዊ አባት ሁላችንም በጸሎት እንድናስባቸው እንጠይቃለን።
ገዳማዊው አባታችን አባ ገብረ ኢየሱስ እዚህ ፈተና ውስጥ የገቡት ሥልጣን ወይም ሹመት፣ ገንዘብ ወይም ጥቅም ፈልገው ሳይሆን ገዳሜ አይደፈርም፣ ይዞታው አይነካም በማለታቸው ነው። ስለዚህ ማንኛውም የዋልድባ ገዳም ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ እኝህ አባት በነጻ እስኪለቀቁ ድረስ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለምዕመናንና ለተለያዩ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የኃይማኖት ተቋማት በማሳወቅ ከታፈኑበት ቦታ በነጻነት እስከሚለቀቁ ድረስ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።
፫ኛ አባ ገብረ ኢየሱስ ታፍነው የተወሰዱት በመንግሥት ታጣቂዎች በመሆኑ በማንኛውም መንገድ በአካላቸውም ሆነ በሕይወታቸው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂው መንግሥት ብቻ ይሆናል። በዚህም የተነሣ መንግሥት ከሕዝበ ክርስቲያኑና ከገዳማውያኑ መነኰሳት ጋር ምንጊዜም የማይፋቅ ቅራኔ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ለማስገንዘብ እንወዳለን።
እኚህ አባት የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው ኃይማኖታዊ ግዴታቸውንና መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ውጪ ምንም የፈጸሙት ወንጀል ስለሌለ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲለቃቸውና ወደ ገዳማቸው እንዲመልሳቸው አጥብቀን እንጠይቃለን።


፭ኛንግሥት የቅዱሱን ቦታ ዋልድባ ክብር ደፍሮ ቅንጣት ታህል ጥቅም ያለው ልማት ሊሰራ አይችልም።  ቤተክርስቲያንና ገዳማትን እያፈረሱ የሚሠራ ልማት በምንም መመዘኛ ቢሆን በተለይ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ትርጉም ሊኖረው አይችልም ። ስለዚህ መንግሥት አሁንም ቆም ብሎ አስቦ በዋልድባ ገዳም ይዞታ ላይ የጀመረውን ሥራ በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን።
፮ኛየዋልድባን ገዳም ቅድስና ከማንም በበለጠ ሁኔታ የምታውቀው የትግራይ፣ የጎንደርና፣ የወሎ ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ መንግሥትን “ተው በእሳት መጫወት አይጠቅምህም” ሊለው ይገባል ።
፯ኛበዚህ ወቅት ለእውነት የሚቆሙና ለኃይማኖታቸው የሚቀኑ አባቶች ታፍነው ደብዛቸው ሲጠፋ ቅዱስ ሲኖዶስ በዝምታ መመልከት ስለማይገባው የእኚህን አባት ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል ሁኔታውን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች እንዲያሳውቅ በትሕትና እንጠይቃለን።


              ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት

                                                   ከመንፈሣዊ ሰላምታ ጋር
Source :- Savewaldba

No comments:

Post a Comment