Monday, July 30, 2012

ፖሊስ በዋልድባ 49 መነኮሳትን ለማሰር እየፈለገ ይገኛል

አንድ አድርገን በኢትዮጵያ ውስጥ መነበብ አልቻለችም
www.andadirgen1.wordpress.com  በዚህ ያግኙን 


 (አንድ አድርገን ፤ ሀምኔ 24 2004 ዓ.ም)፡- መንግስት አሁንም የዋልድባን መነኮሳት ማወከብ ማሰርና መደብደቡን አላቆመም ፤ ከዚህ በፊት በርካታ መነኮሳትና ወጣቶች መታሰራቸው በጊዜው ገልጸናል ከተለያዩ ድረ-ገጾች እና የዜና ማሰራጫዎችም ሰምተናል ፤ ከዚህ በፊት የታሰሩት መነኮሳት ስብእናቸውን በሚያዋርድ ሁኔታ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና ክብርን ዝቅ በሚያደርግ መልኩ እጅጉን አሸማቀው በክልሉ ፖሊስና በመከላከያ ሃይል አማካኝነት እያዳፉና በሰደፍ እየደለቁ ወስደዋቸው ፤ ከጥቂት ቀናት እስር በኋላም ደግመው ሊለቋው ችለዋል ፤ አሁን ግን መንግስት የያዘው አሰሳ በገዳሙ የሚገኙ ሁሉን አባቶችን የሚያሰጋ እየሆነ ይገኛል ፤ በገዳሙ የሚገኙትን መነኮሳት በጠቅላላ በሂደት ለመልቀም እንዲመቸው በመጀመሪያ ዙር 49 መነኮሳትን ማደን ተያይዞታል ፤ ከሚፈልጋቸው 49 መነኮሳት ውስጥ ሶስት ያህሉን ይዞ ወደ እስር ቤት አውርዷቸዋል ፤ ባሳለፍነው አርብ ከ3 እስከ 10 የሚደርሱ የመነኮሳትን ቤት ሲፈትሽ ውሏል ፤ ክፍት የሆኑት ቤቶች ላይ በቀጥታ በመግባት ፤ የተቆለፉትን ቤቶች ላይ ደግሞ ቁልፎቻቸውን ሰብሮ በመግባት ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ቤቶቹን ሲበረብር ውሏል ፤ በጊዜውን “ከደጀ ሰላም” እና “ከአንድ አድርገን” ድረ-ገጾች ላይ ስለ ገዳሙ በተለያዩ ጊዜ የተጻፉ እና ፕሪንት የተደረጉ ጽሁፎች ፤ ስለዋልድባ ገዳም “ፍትህ” ጋዜጣ የዘገበችውን ዘገባ ጨምሮ ያስፈልጉኛል ያላቸውን ነገሮች ሁሉ አግበስብሶ ሊወስድ ችሏል ፤ በመሰረቱ የአንድ ሰው ቤት ወንጀለኛ ቢሆን እንኳን በህግ መሰረት መፈተሸ ያለበት ከፍርድ ቤት የወጣ ትእዛዝን መሰረት ተደርጎ ቢሆንም በማን አለብኝነት የተቀመጠው የሀገሪቱን ህግ የራሱ ጀሌዎችን በመላክ አፍርሶ ቤቶችን በጠራራ ጸሀይ ያለ ፍቃድ ሲያስበረብር ውሎ አምሽቷል ፤


 አሁንስ የት ሄደን አቤት እንበል ? አቡነ ጳውሎስ ቢመዘብሩት አላልቅ ያላቸውን ቤተክርስትያኒቱን ሃብት አንዴ ሸራተን አዲስ ሆቴል ፤ አንዴ ክራውን ሆቴል አንዴ ኢንተር ኮንቲነንታል እያሉ እንደጉድ እየዘሩት አሞራ ደግሰው እያበሉ ፤ የቁም ተስካራቸውን እያወጡ ይገኛሉ ፤ እርሳቸው ክብራቸውን ለመጨመር ሌት ተቀን ሲታትሩ ይታያሉ ፤ እርሳቸው በወንበሩ አይምጡባቸው እንጂ ስለ ዋልድባ ምን ጨንቋቸው ፤ ታዲያ በእምነታችን ውስጥ ቤተክህነቱ እና መንግስት ተባብረው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ እኛ የት ሄደን አቤት እንበል ? ድሮ ድሮ እንደ አባቶቻችን ስርዓት በእምነት ውስጥ የሚፈጠርን ችግር የበላይ ሆነው የመፍትሄ ሃሳብ የሚያፈልቁት ፓትርያርኮች ነበሩ ፤ አሁን ግን ይህን ሁኔታ በመቃወም ምእመናን የእዝ ሰንሰለቱን በመጠበቅ አቡነ ጳውሎስ ጋር ቢሄዱ ፌደራል ፖሊስ ጠርተው እንደሚያሳስሯቸው አሳልፈው እንደሚሰጧቸው እርግጠኞች ነን ፤ እና የት እንሂድ ?

ይህ በጅምላ የማፈስ አካሄድ አደገኛ ነው ፤ ትላንት ሶስቱን መነኮሳት አስሯል ፤ በቀጣይ ቀናት 46 መነኮሳትን ከያሉበት የመልቀም ስራውን ይሰራል ፤ እያለ እያለ የገዳሙን መነኮሳት በአታቸውን እስር ቤት የማድረግ ስራውን አጠናክሮ ይሰራል ፤ ይናገራሉ ይቃወማሉ የተባሉት ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ዳራቸውን የማጥፋት ስራ እየተሰራ ይገኛል ፤ ታዲያ እኝህን የመሰሉ መነኮሳት እጣቸው እስር ቤት ከሆነ ማንስ ሄዶ ስራቸው ይቃወማል ? ማንስ ስለ ገዳሙ ከፊት ይቆማል ?  በጣም የሚገርመው ነገር የትግራይ ተወላጅ የሆኑና መንግስትን የሚደግፉ በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ነገሩን ከሃይማኖት ጥያቄ አሳልፈው የብሔር ጥያቄ እያደረጉት ይገኛሉ ፤ እነዚህ አካላት የዋልድባል ልማት የሚቃወሙ አባቶችን “ ትግራይ እንዳትለማ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው” በማለት የገዳሙ መነኮሳትን ለፖሊስ እየጠቆሙ ይገኛሉ ፤ እነዚህ ጥቂት ሰዎች እና መነኮሳት አብረው ስብሰባ በመግባት ስብሰባው ሳይበተን የተያዘውን አጀንዳ ፤ ተነጋገሩበት ጭብጦች ፤ የተወሰደውን አቋም ሳይቀር በደቂቃዎች ውስጥ በሞባይል አማካኝነት ለመንግስት ባለስልጣናት ለክልሉ የፖሊስ አዛዦች ጭምር ያደርሳሉ ተብሏል ፤ ይህን ምን ይሉታል ?  “ጠላቴን እኔ እጠብቀዋለለሁ ወዳጄን አንተው ጠብቅልኝ” የሚያስብል ዘመን የመጣ ይመስላል ፤ ለዛውም ዋልድባ…..

እረ እባካችሁ በእግዚአብሔር እጅ የተያዘች ነፍስ እያለች ግፍና በደላችሁን አታብዙት ፤ “በማንም ግፍ አትሥሩ” ሉቃስ 3፤14 እግዚአብሔር ዝም የሚለው አላማ ስላለው ነው ፤ መጽሀፈ መክብብ 3፤7 ላይ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል አሁን ጊዜው የእግዚአብሔር የዝምታ ጊዜ ሊሆን ይችላል ፤ የሚናገርበት እጁን የሚያነሳበት ኃይሉን የሚያሳይበት ጊዜም እንዳለው አትርሱ ፤  “እኔንም ስማ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ።” መጽሀፈ እዮብ 33፤31 እግዚአብሔር ጊዜው ሲደርስ እንደሚናገር እናምናለን ፡፡ እኛ ግን ዘወትር ”አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል።” መዝሙረ ዳዊት 83፤1 እያልን ስለ ገዳማችን በእንባ እንጸልያለን፡፡

ፈርኦን ልቡ አብጦ ተው ሲባል አልሰማ ብሎ እስራኤላውያንን ከኋላቸው በፈረስ ሊያጠፋቸው ሲከታተላቸው ባህሩን የከፈተ እግዚአብሔር ሰራዊቱ ጠቅልሎ እስኪገባ ድረስ ዝም አለ ፤ የፈርኦርን ሰራዊትም በፍጥነት ለእስራኤላውያን በተከፈተው ባህረ ኤርትራ ላይ ጠቅልለው ገቡ ፤ የእስራኤል እግር ከባህሩ ሲለቅ የፈርኦን ሰራዊት እግር ጠቅሎ ሲገባ የተመለከተ ሁኔታዎችን ሁሉ ዝም ያለ እግዚአብሔር የተከፈተውን ባህል በላያቸው ላይ ከደነባቸው ሁሉም በባህር አለቁ ፤ የእግዚአብሔር ዝምታ ጊዜ የሚጠብቅ መሆኑን እወቁ አሁንም እኮ አምላካችን እያስተማራችሁ ይገኛል ፤ የሚማር ልቦና ባይኖራችሁም ፤ ላይቀጣችሁ እየራራላችሁ ከስህተታችሁ እንድትመለሱ በመፈለግ ዝም ብሏችሁ ይገኛል ፤ የማንንም ውድቀት የማይፈልግ አምላክ የተሰጣችሁን እድል ካልተጠቀማችሁበት እንደ ፈርኦር ሰራዊት ባህሩን እንዳይከድንባችሁ ተጠንቀቁ ፤ እኛ እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው በዋልድባ ላይ ግድብ ተሰርቶ ሰላም እንደማትሆኑ ብቻ ነው ፤ እግዚአብሔር ቀን አለው……….

ስለ ዋልድባ በመጪው ሱባኤ በርትተን እንጸልይ

1 comment:

  1. metseleyun enetseleyalen neger gen kemehalachew erm yewesede endale erasachewen bifeteshu teru new bay negn

    ReplyDelete