Tuesday, July 31, 2012

እረ ጉድ ነው


አንድ አድርገን በኢትዮጵያ ውስጥ መነበብ አልቻለችም
www.andadirgen1.wordpress.com  በዚህ ያግኙን (አንድ አድርገን ሐምሌ 24 2004 ዓ.ም)፡- በአሁኑ ጊዜ የማይሰማ ነገር የለም ፤ በየቦታው የሚሰማው ነገር ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ነገሮች እየሆኑ ለመስማትም ሆነ ለመጻፍ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ፤ የዛሬ ዓመት ወር ገደማ “እኔ እየሱስ ክርስቶስን የምወልደው ሴት ነኝ” ብላ የተነሳች ሴት መከሰቷን በጊዜው በቦታው ተገኝተን በአይናችን ካየነው ፤ በጆሯችን ከሰማነው ፤ ከጋዜጦች ካነበብነው እና ከፖሊስ መረጃ ጋር በማመሳከር አንድ ጽሁፍ ማቅረባችን ይታወሳል ፤ በጊዜው የተከሰተችው ሴት ከዚህ በፊት ተሰምቶም ሆነ ታይቶ የማይታወቅ ተግባር ስለፈጸመች ብዙዎችን ጉድ አሰኝታ ነበር ፤ ከሰማይ የወረደ  መና ነው በማለት ብዙዎችን ምንነቱ ያልታወቀ ምግብ አብልታቸዋለች ፤ ይህ ሁሉ ሲደረግ ስለ እሷ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ብዙ ነጫጭ የለበሱ ሴቶችን አስከትላ ገድሏን ሲመሰክሩላት ሲመለከቱ ይህ ነገር ህልም እንጂ እውን አይመስሎትም ፤ እኛ ከተደረጉት ነገሮች ሁሉ ለእናንተው ጆሮ ለዘብ ያለውን ጉዳይ ብቻ አቅርበናል ፤ ይች ሴት የተነሳችበት ዓላማ በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎችን “እኔ እግዚአብሔር የመረጠኝ ክርስቶስን የምወልደው ሴት ነኝ” በማለት በቤተክርስትያን ውስጥ በርካቶችን ያወዛገበች ፈት ሴት መሆኗን ለማወቅ ተችሏል ፤  በአዲስ አበባ አስኮ መንገድ የሚገኝው የአባታችን የአቡነ ሐብተማርያም ቤተክርስትያን በበአላቸው ቀን በመገኝት አውደ ምህረት ላይ በመውጣት ስትናገር የነበረው ነገር በርካታ ወጣቶችን በማስቆጣቱ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ የሚታወቅ ነው ፤ በጊዜው ያልተገባ ነገር ስትናገር የሰሙ ወጣት ምዕመናን ከአውደ ምህረት ላይ ውረጂ ሲሏት ባለመስማቷ አንጠልጥለው ሊያወርዷት ወደ አውደ ምህረቱ ሲያመሩ የሚመጣውን ጉዳት ከግምት በማስገባት ተሸቀንጥራ በግብር አበሮቿ አማካኝነት በመታጀብ  ቤተክርስቲያኑ ጎን  የሚገኝው መሰብሰቢያ አዳራሽ በመግባት ከተቆጡት ወጣቶች ማምለጥ ችላለች ፤  ይህ በእንዲህ እያለ በአዳራሽ ውስጥ አብረዋት የገቡት ግብር አበሮቿ ፖሊስ ዘንድ በመደወል ከሚደርስባት ጉዳት ሊያድኗት ችለዋል ፤ በጊዜው የነበሩ ወጣቶች ሁኔታውን ሲያስረዱ ስለ ቤተክርስቲያንና በድፍረት በአውደ ምህረት ላይ ስለተናገረችው ቃል እንባ እየተናነቃቸው ምግባሯንና ያደረገችውን ነገር መናገርና መግለጽ እስኪያቅታቸው ድረስ ደርሰው ነበር ፡፡

ይህ ከመሆኑ ከዓመት በፊት በ2002 ዓ.ም መጋቢት ወር አካባቢ ይችው ሴት ከግብር አበሮቿ ጋር በመሆን በደብረብርሃ ከተማ ተገኝታ ነበር ፤  ከተማውን በአግባቡ በማጥናት ማረፊያቸውን እያሰቡ ሳለ በሰዎች ጥቆማ አንድ የዋህ የእግዚአብሔር ሰው ጋር በመሄድ እንዲህ ይላሉ “ቤትህ እንድናድር እግዚአብሔር አመላክቶናል ፤ ሥላሴዎች ጠቁመውናል ፤ በጉራጌ ሀገር ከሚገኝው ገዳም ተልከን ነው የመጣነው ፤ በመላ ሃገሪቱ እንድንዞር ታዘናል ፤ ከበአታችን ከተነሳን አንድ ወር አልፎናል ፤ የእግዚአብሔር መልአክ እየጠቆመን እዚህ ደርሰናል ፤ አሁንም ምን ያህል ጊዜ እዚህ እንደምንቆይ አናውቀውም ፤ ተነሱ ስንባል ነው የምንነሳው” በማለት በጣም ትህትና በሞላበት ሁኔታ ይጠይቁታል፡፡ ያም ሰው እውነት መስሎት እግዚአብሔር የላካቸው ሰዎች ናቸው በማለት በመሰራት ላይ ያለውን ቤት ያልተጠናቀቀውን መኖሪያ እንካችሁ እስከፈለጋችሁ ጊዜ ድረስ ቆዩበት በማለት ይሰጣቸዋል ፤ ቢያንስ በቁጥር ከአስራ አንድ የሚበልጡት እነዚህ ሰዎች ካለማቅማማት በተከፈተላቸው ቤት በመግባት ለሁለት ሳምንት በላይ መቆየታቸውን ለማወቅ ችለናል ፤ የፈለጉትን ያህል ጊዜ በቤቱ ከቆዩ በኋላ “አሁን እግዚአብሔር በጸሎት ስንጠይቀው ወደ ሌላ ቦታ እንድንሄድ አመላክቶናልና መሄጃችን ደርሷል” በማለት ለ15 ቀን ያለ ክፍያ በማታለል የቆዩበትን ቤት አመስግነው ሊወጡ ሲሉ “ባዶ እጃችሁንማ አትሄዱም በረከታችሁ እኛ ላይ ይደርብን” የሚሉ ጥቂጥ ሰዎች  ብር በማዋጣት በሶና ስኳር ሰጥተው ሸኝተዋቸዋል ፤ አብሯው የሚሄደውን ህጻን “ይህ ልጅ በምን አቅሙ ነው ከእናተ ጋር በርሃ ለበርሃ የሚጓዘው?” በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሱን በፈገግታ መመለሳቸው ሁኔታውን ካስረዱን ሰዎች ለማወቅ ችለናል ፤ በሚሄዱበት ቦታ ውሃ እንዳይጠማቸው የሚጠጣ ነገር በመቅዳት ፤ ምግብ እንዳይርባቸው  ስንቅ ቋጥረው እንደላኳቸው ጭምር በቦታው ከነበሩ ሁኔታውን ከመጀመሪያ እስከ ፍጻሜ የሚያውቁ በሶና ስኳር ከሰጧቸው ሰዎች መካከል በአካል በማነጋገር ለማወቅ ችለናል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል 10፤16 ላይ “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” በማለት ተጽፏል ፤ እኛ ግን እንደ እባብ ልባም መሆኑ እንዳለብን ዘንግተን እንደ ርግብ የዋህ ብቻ በመሆን ራሳችን ተሰናክለን ሰዎችን እያሰናከልን እንገኛለን ፤

እነዚህ ሰዎች በአዲስ አበባ በተክለ ኃይማኖት ቤተክርስቲያን ያደረጉትን ነገር ህዝቡ እንዴት እንደተቃወማቸው ፤ ፖሊሶች በጊዜው ሁኔታውን በማረጋጋት ወደ እስር ቤት እንዳወረዷቸው የሚያሳየውን ቪዲዮ ይህ ነገር ለተፈጸመባቸው ሰዎች በሲዲ ሰጥተን አሳይተናቸዋል፡፡ ሰዎቹም ተመልክተው ካበቁ በኋላ “እግዚአብሔር የስራቸውን ይክፈላቸው” ብለው ለእግዚአብሔር አሳልፈው ሰጥተዋል ፤ እነዚህ ሰዎች ባደረጉት ተግባር በምዕመናን ጥቆማ ፖሊስ ሰዎቹን በተክለኃይማኖት በተክርስቲያን በመገኝት በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነበር ፤ ፖሊስ በጊዜው በወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንደሚጠይቃቸው ቢያሳውቅም ካለምንም ክስ ከቀናት በኋላ ሊለቃቸው ችሏል ፤

በአሁኑ ሰዓት ከሁለት ቀናት በፊት የአዲስ አበባው አልሳካ ያላቸው ሰዎች ቀን በመቁጠር ጊዜ በመውሰድ ወደ ደብረ-ሊባኖስ አቡነ ተክለኃይማኖት ገዳም በማምራት የሰላም አየር ሲተነፍስ የነበረው ገዳም “እኔ ቅድስት ማርያም ነኝ” በማለት ስትናገር ጸብ መነሳቱን ለማወቅ ተችሏል ፤ የአካባቢው ፖሊስ በቦታው በመገኝት ሁኔታውን በማረጋጋት ዳግም ወደ እስር ቤት አውርዷዋል ፤ ይችን ሴት ከግብ አበሮቿ ጋር በጉልበት ለማስወጣት በተደረገው ኃይል አንድ ፖሊስ በድንጋይ ጭንቅላቱ ላይ የመፈንከት አደጋ ደርሶበታል ፤ ሁኔታው ብዙ መነኮሳትን እጅጉን አስቆጥቷል ፤ ከአዲስ አበባም ጉዳዩን ለማጣራት ሰዎች ወደ ቦታው አምርተዋል ፤ ከዚህ በተጨማሪ ፖሊስ ጣቢያ ሆነው የሰጡት ቃል ብዙዎችን አስገርሟል ፤

በዚህችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የዋሓንን አማኝ  በማታለል የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ እና ስርአት ለማጥፋት የሚጥሩ ብዙ ተኩላዎች እንዳሉ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ከውጪ ያለችበት ከፍተኛ ፈተና ከፊት ተጋርጦ ሳለ እዚሁ በየገዳማቱ በየአድባራቱ ያሉትን የዋሀንን በፈለጉት ሀሳብ በመስበክ ሕዝቡን እያሳቱ እንዳለ ይህ እውነተኛ ምስክር ነው፡፡

አካሄዳቸው ቀላል የሚባል አይደለም አንድ ሰው ተነስቶ ስለ እሷ ሲመሰክር ሌላው ስለ እመቤታችን ፍቅር ብሎ ቁጭ ብሎ ያለቅሳል፡፡ ሰውን ለማሳመን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይወጡት ዳገት አለመኖሩ ደግሞ በጣም ይገርማል ፡፡ የማያቁት ገዳም የማይጠሩት በረሀ አለመኖሩን ሲያውቁት ደሞ ጉድ ይላሉ:: በጣም ብዙ ተከታዮችን ሲያዩ ደግሞ ይደነግጣሉ ፡፡ የደጋፊዎቹ ስብስብ ደሞ ህፃን ፤ ወጣት አሮጊቶች መሆኑን ሲያስተውሉ ‹‹ እረ ጊዜው ከፍቷል›› እግዚኦ…. ይላሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው በቤተክርስትያን ፤ በአውደ ምህረቷ ላይ መሆኑን ፤ በቅፅሯ ውስጥ መሆኑን ሲያውቁ የእግዚአብሔር ትዕግስቱ ይገርሞታል ፡

ጉዳዩ ምን ደረጃ እንደደረሰ ተከታትለን እናቀርብሎታለን..ይጠብቁን

ደብረ ብርሃን ላይ እነዚህ ሰዎች ያደረጉትን ነገር የቤቱን ባለቤት መልካም ፍቃደኝነት ጠይቀን ለሌላው መማሪያ ይሆነው ዘንድ ወደፊት እናቀርብሎታለን ፤

እግዚአብሔር ቤተክርስትያናችንን ይጠብቅ

No comments:

Post a Comment