Wednesday, November 16, 2011

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፤ ፊሊጶስ Vs የዘመኑ ሰባኪዎች

  • እነሆም እናንተ በአለማዊ እና በግል ጉዳይ ተጠምዳችሁ ያላችሁ ሰባኪያን ሆይ፡- መንፈሳዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባችኋል፡፡ ከቶስ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ አስተማሪ ለእኛ እንዴት ሊገለጥልን ይችላል? እናንተ ካላስተማራችሁን እንደ ፊልጶስ ካልተረተራችሁልን ቅዱስ ቃሉን እንዴት ልናስተውለው እንችላለን? 
(አንድ አድርገን ህዳር 6 2004 ዓ.ም) :- የጌታም መልአክ ፊልጶስን፡- ‹‹ተነስተህ በደቡብ በኩል ከእየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ›› አለው፡፡ ተነስቶም ሄደ፡፡ እነሆም ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግስት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳለም መጥቶ ነበር ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነብዩን የኢሳያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊሊጶስን፡- ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፡፡ ፊልጶስም ሮጦ የነብዩን የኢሳያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው፡፡ እርሱም፡- የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው፡፡ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፡፡ ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፡-


እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ ህይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፤ ትውልዱንስ ማን ይናገራል?
ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ፡- እባክህ ነብዩ ይህን ስለማን ይናገራል? ስለራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ? አለው፡፡ ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፡- እንሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው፡፡ ፊልጶስም፡- በፍፁም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል አለው፡፡ መልሶም፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረደ፤ አጠመቀውም፡፡ ከውሃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና ፊልጶስ ግን በአዘጠን ተገኘ፤ ወደ ቂሳርያም እስከመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር፡፡.. የሐዋርያት ስራ .8 .26-40


እነሆ የሐዋሪያት ስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያው ጃንደረባ እና የፊልጶስ ግንኙነት ዛሬ በሀገራችን በተለይም በእምነታችን ዘንድ ላለው አሳዛኝ ችግር አስተማሪ ይሆናል በሚል ነው የዛሬው የጽሁፌ ይዘት በዚህ ላይ ያደረኩት፡፡

የኦርቶዶክስ እምነት ጥላ ስር የሚገኙ የተወሰኑ ሰባኪያኖች በአሁኑ ወቅት ማንን እያገለገሉ እንደሚገኙ የገባቸው አይመስልም፡፡ ከጥቂት የእግዚአብሔር አገልጋዮች በስተቀር ሌላው ወይ ቄሳርን ወይ ገንዘብና ዝናን ወይ ዲያብሎስን አሊያም ደግሞ ሶስቱንም በአንድነት እያገለገሉ ያለ ይመስለኛል፡፡ የዚህ አይነቱ ግብር እንኳን በመንፈሳውያን ቀርቶ በአለማውያንም ቢሆን ፀያፍ ነው፡፡


የክርስትና እምነት መጽሐፍ እና ትእዛዛት እንኳን ሰባኪያኖች ምእመናኖችም ቢሆኑ ለሌሎች አርአያ እንጂ መሰናከያ እንዳይሆኑ በጥብቅ ያስተምራል፡፡ ይሄ እውነት ሆኖ ሳለ ስለአንዳንድ ሰባኪያኖች ግን ከፈጣሪ መንገድ ይልቅ አለማዊ (አጋንታዊ) መንገድን እየተከተሉ ነው፡፡ ይሄ ድርጊታቸውም በአሁኑ ወቅት ብዙ ምዕመናንን ከቤተክርስትያን  እያሸሸ እንደሆነ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡


ከወራት በፊት በአንዳንድ የኦርቶዶክስ  ሰባኪያኖች፤ ፕሮቴስታንት ሰባኪያኖች ላይ እና አንዳንድ የኦርቶዶስክ ሰባኪያኖች፤ በአንዳንድ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት ሰባኪያኖች መካከል የሚደረገው ክርክር መሰል ምልልስ የእየራሳቸውን እምነት ተከታዮች ከማደናገሩም ባሻገር እናገለግለዋለን የሚሉትን ፈጣሪያቸውን ጭምር የሚያሳዝን እየሆነ ነው፡፡አንዱ አንዱን ለማውገዝ ካሴት እስከማውጣት እና መጽሐፍ እስከማሳተምም ደርሰዋል፡፡ ይሄ ለሃገርም ቢሆን የሚጎዳ ነው፡፡ ሀገሪቱ የሚያምነውም የማያምነውም መሆኗን በቅድሚያ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ቀዳማዊ አፄ /ስላሴ እንዳሉት ሀገር የጋራ ነው፤ ሃይማኖት የግል ነውና፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ በተመሳሳይ እምነት ውስጥ ያሉ ሰባኪያኖች እርስ በእርሳቸው በአለማዊ ሚዲያ ሳይቀር መወነጃጀላቸው ነው፡፡ የእነዚህ ሰባኪያን ድርጊት ለአለም መማሪያ እና መዳኛ ከመሆን ይልቅ መዘባበቻ ከሆነም ውሎ አድሮአል፡፡ ሰባኪያኑ የተሰጣቸውን አገልግሎት በአግባቡ መወጣት አልቻሉም፡፡   በእርግጥ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ የተሳሳቱት ሰባኪያኖች ብቻ አይደሉም፡፡ እንዲያውም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የየእምነቶቹ የበላይ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ሲጀመርም ለአገልጋዮችም ሆነ ለምእመናኑ አርአያ ሊሆኑ አልቻሉምና ነው፡፡ የተጠቀሱት ሃይማኖት መሪዎች በሙሉ ከእግዚአብሔር ይልቅ ቄሳርን የሚያገለግሉ እና የሚፈሩ ናቸው፡፡ የእረኝነት ተልእኮአቸውን ከመውጣት ይልቅ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ አስፈፃሚ በመሆን ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጽሐፍቶችን ከመስበክ ይልቅ የመንግስትን የትራንስፎርሜሽን እቅድ መስበክ የሚቀናቸው ነው፡፡ እናም ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ... በሚልም ሰባኪያኖም እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ ቄሳርን፣ ገንዘብን፣ ዝናን፣ ሰይጣንን... ማገልገልን እንደ አማራጭ ውሰዱ፡፡



ከላይ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እና የሐዋርያው ፊልጶስ ግንኙነት ሁሉም ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ የነቢዩን ኢሳያስ የትንቢት መጽሐፍ ሲያነብ ሳለ፤ ፊልጶስ በጌታ መንፈስ ተገፍቶ ወደ ጃንደረባው በመጠጋት ..በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?.. ሲል ጠየቀው፡፡ ጃንደረባውም ..የሚመራኝ ሳይኖር ይሄ እንደት ይቻለኛል?.. ብሎ ሲመልስለት ፊልጶስ ያደረገው ነገር ቢኖር ጃንደረባው ተሳፍሮበት ወደነበረው ሰረገላ በመግባት ሀዋርያዊ ተልእኮውን መወጣት ነው፡፡ አዎ.. የፊልጶስ ጥያቄ እና የጃንደረባው መልስን በሚገባ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ካስተዋልነው በኋላ ደግሞ ልናሰምርበት ግድ ይለናል፡፡

እነሆም እናንተ በአለማዊ እና በግል ጉዳይ ተጠምዳችሁ ያላችሁ ሰባኪያን ሆይ፡- መንፈሳዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባችኋል፡፡ ከቶስ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ አስተማሪ ለእኛ እንዴት ሊገለጥልን ይችላል? እናንተ ካላስተማራችሁን እንደ ፊልጶስ ካልተረተራችሁልን ቅዱስ ቃሉን እንዴት ልናስተውለው እንችላለን?



ሌላው በጣም አሳዛኝ ጉዳይ የፈጣሪን መንገድ እሰብካለው የሚል ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላደረበት ካልሆነ የሚያቃልለው እራሱን ብቻ ሳይሆን ፈጣሪውንም ጭምር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሊሰብክ የተዘጋጀው ያልገባውን እውነት እንደሆነም ያሳብቅበታል፡፡ እርስ በእርስ የሚሰዳደብ የፈጣሪ አገልጋይም በየትም ቦታ የለም፡፡ በመንፈሳዊያን ዘንድ ልክ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እዛና እዚህ ሆኖ መወነጃጀል ምእመናንን ማሰናከል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ‹‹የሰውን ልጅን ከምታሰናክል የወፍጮ ድንጋይ በአንገት ታስሮ ወደ ባህር ብትወረወር ይሻልሃል›› ይላል፡፡ ይሄ እውነት ያልገባው ሰባኪ ምን ሊሰብክ ወደ አውደ ምህረቱ እንደሚወጣ ማሰቡ በራሱ ይከብዳል፡፡ ለምዕመናን የፊልጶስን አይነት ሰባኪን (አስተማሪን) እንጂ እርስ በእርሱ የማይከባበር እና የሚሰዳደብ ሰባኪን አይፈልግም፡፡ ወደ ፈጣሪው መንገድ የሚመራውን እንጂ ወደ ጥላቻ የሚነዳውን ሰባኪ አይፈልግም፡፡ ማንም ሰው ወደ አምልኮ ስፍራዎች የሚሄደው እንደ ጃንደረባው ተደስቶ ለመመለስ እንጂ ልቡ ተሰብሮ ለመመለስ አይደለም፡፡ ይበልጥ የፈጣሪውን መንገድ አውቆና ገብቶት ይመለስ ዘንድ ነው ወደ ቤተክርስትያን የሚሄደው፡፡ የፈጣሪ አገልጋይ ነን፤ የእውነት መንገድ ሰባኪነን እስከአላቸው ድረስ በድርጊታቸውም ፈጣሪያቸውን መምሰል እንደሚጠበቅባቸው ማስተዋሉ አስፈላጊ ነው፡፡ አሊያ ሁሉም ነገር ግብዝነት ይሆንና ከጊዜ በኋላም የሚያደምጣቸው አንድስ እንኳ አታገኙም ሌላው ቀርቶ የማይኖሩትን ህይወት መስበኩስ ቢሆን እንዴት አድርጎ ነው ሰሚን ሊለውጥ የሚችለው?


ሁሉም አውደ ምህረት የእግዚአብሔር ነው አዲስ አበባ ላይ እና ገጠር ያሉ አብያተክርስትያናት ላይ በአውደምህረቱ ላይ ቆሞ መስበክ ሁለቱም እሱን ባለቤቱን ማገልገል ነው ፡፡ አሁን ግን እየሰማን እና እየየን ያለነው Business ያለበትን ፤ ጥሩ ውሎ አበል የሚከፈልበትን ቤተክርስትያን ማሳደድ ተይዟል፡፡ ማንን ነወ እያገለገሉ ያሉት? በነፃ የተሰጣቸውን ያለ ክፍያ ማተላለፍ እንዳለባቸው መፅሀፉ ይናገራል፡፡ ለአባቶቻችን የሲኖዶስ አባላት ክብር ይግባቸው እና ከዓመታ በፊት በአዳራሽ ሲያደርጉት የነበረው ጉባኤ ቢቀጥል ዛሬ የት ነበርን?


የሆነ ሆኖ የየትኛውም ሰባኪ በድፍረት ለመስበክ ከመሞከሩ በፊት እራሱን መለወጥ መቻል አለበት፡፡ ‹‹እኔን ምሰሉ›› የሚለውን የፈጣሪውን ቃልም ሊተገብረው ይገባል፡፡ ይሄ ከሆነ በኋላ ነው ሌሎችን ለመለወጥ ሌሎችን ለማሳመን መስበክ ነው ያለበት፡፡ እነሆም እግዚአብሔር አምላክ ለእንዲህ አይነቶቹ ሰባኪያኖች ራሳቸውን ለመለወጥ የሚያስችል ልቦና ይስጣቸው፡፡ አሜን ይስጠን፡፡


በሚቀጥለው ፅሁፍ  በቅን ልቦና ሰባኪዎቻችንን የሄዱበትን መንገድ እናመላክታችኋለን ........
  • ምህረት አብ
  • አጥማቂው ግርማ
  • በጋሻው ደሳለኝ(ሰባኪ የነበረ)
  • ባህታዊ ገ/መስቀል(ከዓመታት በፊት መነጋገሪያ የነበሩ ሰው)
  • ሌሎችም



No comments:

Post a Comment