- የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ ከ900 በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልኡካን እያወያየ ነው
- “እንደ ሌላው መድረክ አታስቡት፤ ለዓላማና ለለውጥ የሚደረግ ጉባኤ ነው” /ሚኒስትሩ/
(አዲስ አድማስ ፡- ነሐሴ 30
2007 ዓ.ም) በአዲስ
አበባ ሀገረ ስብከት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች አላግባብ ሀብት ያፈሩና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለምዝበራ ያጋለጡ የአድባራት ሓላፊዎች ጉዳይ በሕግ እንዲታይ የቀረበውን ውሳኔ ቋሚ ሲኖዶስ አጸደቀ፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ መገልገያነት ከመንግሥት የተሰጡ መሬቶች፣ የተገነቡ ሕንጻዎች፣ ሱቆች፣ መካነ መቃብርና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ተቋማት ሕጋዊ፣ ፍትሐዊና ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ በማያደርጉ ውሎች ለሦስተኛ ወገን እየተከራዩ ለግለሰቦች በመሸጥ ላይ እንደኾኑ ጥናታዊ ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡የአድባራት ሓላፊዎች ጥፋት በሕግ አግባብ እየታየ ክሥ ለመመሥረትም፤ ጥናቱ በሸፈናቸው አድባራትና ገዳማት የተደረጉ ሕገ ወጥ ውሎች የተፈጸሙበትን ትክክለኛ ጊዜ፣ የወቅቱን የአካባቢ የመሬት ዋጋ፣ በውል አሰጣጡ የተሳተፉ ሓላፊዎችና የመሳሰሉት ዝርዝር መረጃዎች በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጣርተው መታወቅ እንደሚገባቸው ቋሚ ሲኖዶሱ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጨማሪ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የሀገረ ስብከቱን የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ካህናት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤቶች ሊቃነ መናብርት እና የአንድነት አመራሮች በተናጠል ሲያነጋግር የቆየው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከትላንት ጀምሮ ኹሉንም አካላት ያቀፈ የማጠቃለያ ውይይት በማካሔድ ላይ ነው፡፡
937 ያኽል የቤተ ክርስቲያኒቷ
ልኡካን በሚሳተፉበት በዚኹ የኹለት ቀናት ውይይት፣ በሃይማኖት ተቋማት የውስጥ አሠራር ችግሮች ላይ ያተኰረ ጽሑፍ በሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም የቀረበ ሲኾን በቡድንና በጋራ ውይይት ይካሔድበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደምትና ጥንታዊት መኾኗን ያወሱት ሚኒስትሩ÷ በአካባቢና በጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ የሰው ኃይል አሿሿምና አመዳደብ፣ ግልጽነት በጎደለው የፋይናንስ ዝውውርና አጠቃቀም በውስጥ የሚነሣው አለመግባባት እየሰፋ መምጣቱ ጥያቄ እያስነሣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ከሕግና ሥርዐቱ ውጭ የመንቀሳቀስ ስሜት በራሱ የሚፈጥረው አደጋ እንዳለ ያሳሰቡት ዶ/ር ሺፈራው፣ መድረኩም እንደሌላው መርሐ ግብር የሚታይ ሳይኾን ለዓላማና ለለውጥ የሚካሔድ የምክክር ጉባኤ ነው በማለት ውይይቱን ተከትሎ በተከታይ ሊወሰድ የሚችል ርምጃ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
No comments:
Post a Comment