- የተቋቋመውን ኮሚቴ ለመደለልና ለማስፈራራት ተጠርጣሪዎቹ እየሠሩ ነው
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ በማያደርጉ የመሬት እና የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ውሎች፣ የተጧጧፈ ዘረፋና ምዝበራ መፈጸሙን በጥናት ያረጋገጠው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት÷ በጥምርና በተናጠል በሕግ ተጠያቂ የሚኾኑ የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች በስም ዝርዝር ተለይተው እንዲቀርቡለት ለአጥኚ ኮሚቴው ትእዛዝ ሰጠ፤ በመሬት፣ በሕንጻዎች፣ በሱቆች፣ በመቃብር ቦታዎች፣ በመኪና ሽልማትና በመሳሰሉት የልማት ሥራዎች ዙሪያ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነጥቦች፣ ለሀገረ ስብከቱ ጥብቅ መመሪያም አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚና የአስተዳደር አካል የኾነው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ መመሪያውንና ትእዛዙን የሰጠው÷ የሀገረ ስብከቱን 48 ገዳማትና አድባራት ያካተተውን የመሬት፣ የሕንጻዎችና የገቢ ማስገኛ ተቋማት የኪራይ ተመንና የመኪና ሽልማት ጥናታዊ ሪፖርት፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ተቀብሎ ያሳለፈውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ ነው።
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ነሐሴ 28 እና 29 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሔዳቸው ስብሰባዎች፣ አጥኚ ኮሚቴው በ33 ገጾች በማካተት በአንድ ጥራዝ ካቀረባቸው 48 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ÷ 15ቱ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ፤ ኹለቱ በመካከለኛ ደረጃ የተቀሩት ስድስቱ ደግሞ በደኅና ኹኔታ ላይ እንዳሉ ተገንዝቧል።
ከፍተኛ ችግር ያለባቸው 15ቱ አብያተ ክርስቲያናት÷ የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም፣ የቦሌ ገርጂ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል፣ የጃቲ መካነ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፣ የደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል፣ የመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል፣ የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ፣ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል፣ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል፣ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል፣ የሰሚት ኆኅተ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፣ የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፣ የብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም፣ የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል እና የየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል እንደኾኑ በቋሚ ሲኖዶሱ የውሳኔ ቃለ ጉባኤው ተዘርዝረዋል።
በተዘረዘሩት ገዳማትና አድባራት፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መገልገያ ከመንግሥት የተሰጡ መሬቶችና በይዞታዎቹ ላይ ለገቢ ማስገኛ በሚል የተሠሩ ሕንጻዎችና ሱቆች፣ የ“ልማት አርበኛ” እየተባሉ በካህናቱና በምእመናኑ ስም መኪናና ቤት የሚሸለሙ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ለምዝበራ እንዳጋለጧቸውና አላግባብ ሀብት እንዳፈሩባቸው በጥናቱ ሒደት በማስረጃ በመረጋገጡ ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እየታየ ክሥ እንዲመሠረትባቸው በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስተዳደር ጉባኤ ተወስኗል።
የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ውሳኔ የተቀበለው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ለሕጋዊ ጥያቄና አካሔድ አመቺነት መሟላት ይገባቸዋል ያላቸውን ነጥቦች በመለየት ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ በዝርዝር አስታውቋል። በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት፣ በጥምርና በተናጠል በሕግ ተጠያቂ የሚኾኑ የሥራ ሓላፊዎች እና ሠራተኞች ስም ዝርዝር ተጣርቶ እንዲቀርብለት ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለአጥኚ ኮሚቴው አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጥቷል።
በተጨማሪም፣ በተጠቀሱት ገዳማትና አድባራት የአካባቢ የመሬት ዋጋ በካሬ ሜትር ስንት እንደኾነ፣ የተሰጠው የኪራይ ውል ዓመት በአሐዝ እንዲገለጽ፣ የቤትና የመኪና ሽልማት የተሰጣቸው አለቆችና የስጦታው ምክንያት ተብራርቶ እንዲቀርብ በአጠቃላይ፣ ለጥናታዊ ሪፖርቱ ግብአት የኾኑት 1500 ማስረጃዎች ለሕጋዊ ጥያቄ አመቺ በሚሆኑበት መልኩ በሚገባ ተጣርተው እንዲዘጋጁ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አጥኚ ኮሚቴውን አዟል።
ገዳማቱንና አድባራቱን በበላይነት በሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፤ ትኩረት እንዲሰጣቸውና በአግባቡ ተግባራዊ እንዲደረጉ የተባሉ ነጥቦች በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የተመለከቱ ሲኾኑ ጠቅላይ ጽ/ቤቱም በውሳኔዎቹ ላይ በመመርኮዝ ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቶባቸዋል። በዚህም መሠረት፣ በገዳማቱና በአድባራቱ የመሬትና የሱቅ እንዲኹም የልማት ይዞታዎች የኪራይ ውላቸው ለአንድ ዓመት ብቻ ይኾናል፤ የተለየ ችግር ካጋጠመም ውሉ በሕግ እንዲቋረጥ ታዟል።
የቦታዎች፣ የሱቆችና የመቃብር ቦታዎች ኪራይ አፈጻጸም በአጠቃላይ የልማት ነክ ጉዳዮች፤ ኮሚቴ ተቋቁሞና ውስጠ ደንብ ወጥቶላቸው እንዲሠሩ፤ ውሎቻቸውም በየደረጃው ተጠንተው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርበው ተቀባይነት ካገኙ በኋላ ተግባራዊ እንዲኾኑ ተወስኗል።
የቤትና የመኪና ሽልማት በቢሮ ደረጃ ለፓትርያርኩ ቀርቦ ሳይታይና በቋሚ ሲኖዶስ ሳይጸድቅ እንዳይፈጸም ታዟል። ከሦስተኛ ወገን ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱ መዋዋል እንደምትችል የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ቋሚ ሲኖዶሱ አጽድቋል።
በጥናቱ ያልተካተቱት ገዳማትና አድባራት ችግር እንደሌሎቹ ተጠንቶ እንዲቀርብም ቋሚ ሲኖዶሱ በወሰነው መሠረት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ መመሪያ በመሰጠቱ፣ ጥናቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው የተጠቆመ ቢኾንም፤ ሒደቱን በማጥላላትና በማንቋሸሽ የተጠመዱ አካላት የአጥኚ ኮሚቴውን አባላት በጎጠኝነትና በጥቅም ኔትወርክ ለመደለል ከመሞከር ጀምሮ በዛቻና በማስፈራራት ለማሰናከል እየሞከሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል።
Source :- http://www.sendeknewspaper.com
Source :- http://www.sendeknewspaper.com
No comments:
Post a Comment