- መመሪያያልተሰጠበትየደብሩየሚሊዮንብሮችየበጀትጥያቄእንዲዘገይአዟል
- የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና ምክትላቸውን እያወዛገበ ነው
(Addis Admass ) :- የአራዳው መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ እያሠራው የሚገኘው የሁለገብ ሕንፃ ግንባታ፣ ተደርጎለታል ባለው የዲዛይን ማሻሻያ ሳቢያ በልዩነት የሚያስፈልገው ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለማስገንባት ያቀዳቸው የሌሎች ሁለት ሕንፃዎች ግንባታና በጀት እንዲጸድቁለት ያቀረባቸው ጥያቄዎች፣ ለፓትርያርኩ ቀርበው መመሪያ ያልተሰጠባቸው በመሆናቸው “በአሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ” የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አዘዘ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ፣ በደብሩ ግንባታዎችና የበጀት ይጸደቅልኝ ጥያቄዎቹ ላይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ለአፈጻጸም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሳይላኩለት የቆዩበት ምክንያት እንዲብራራለትም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከትላንት በስቲያ ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ የልማት ዕቅዶቹ በሀገረ ስብከቱ በኩል እንዲጸድቁለት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. መጠየቁን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባስታወሰበት ደብዳቤው፤ ዲዛይኑ ለተሻሻለው ሁለገብ ሕንፃ ማሠሪያ እንዲሁም በስተምሥራቅ የሚገኙት ሱቆች ፈርሰው በምትካቸው ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ መሥራት ይቻል ዘንድ የብር 6 ሚሊዮን በጀት በደብሩ እንደተመደበ፣ በጥያቄው ላይ ለመወሰን ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተሰበሰበው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ቃለ ጉባኤ መረዳቱን ጠቅሷል፡፡
በዕለቱ፣ በምክትል ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር በተመራው የአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ፣ በደብሩ የቀረበው የበጀት ይጸድቅልኝ ጥያቄ፣ “ከባድና ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ” ሊሆን እንደቻለ ተጠቁሟል፡፡ ወጪው ከ61 ሚሊዮን ወደ 152 ሚሊዮን ያደገው የዲዛይን ክለሳ ጥናት፤ በገለልተኛ ባለሞያዎች ተገምግሞ፣ ውጤቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲላክና በዚያው በኩል እንዲጸድቅ፤ የሁለት ተጨማሪ ሕንፃዎች ግንባታ ውሎችም ለአስተዳደር ጉባኤው ቀርበው እንዲታዩና የውሳኔው ቃለ ጉባኤም በምክትል ሥራ አስኪያጁ ሸኚ ደብዳቤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲላክ ከስምምነት ተደርሶበት እንደነበር ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አውስቷል፡፡
ይኹንና ውሳኔዎቹም ኾኑ የውሳኔዎቹ ቃለ ጉባኤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዳልተላከ ጠቅሶ፣ ለሦስት ወራት ሳይላክ የዘገየበት ምክንያት ከተጨባጭ ማስረጃ ጋር እንዲብራራለት የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት አዟል፤ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ደብርን ጨምሮ የ48 አድባራትን የመሬትና የገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃቀምና የኪራይ አፈጻጸም ያጣራው አጥኚ ኮሚቴም፣ ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም በደብዳቤው ግልባጭ መታዘዙን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የቃለ ዐዋዲ ድንጋጌ አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 8፣ ቋሚ ንብረትንና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ ጉዳዮች በሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ አልፎ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደመኾኑ፣ በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያቱ ለሀገረ ስብከቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ እየቀረቡ አመራር ሲሰጥባቸው፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመመሪያው መሠረት ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡
በዚሁ አግባብ፣ በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት የተላለፈው ውሳኔ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ ቀርቦ መመሪያ እስከሚሰጥበት ድረስ የደብሩ የግንባታና የበጀት ይፅደቁልኝ ጥያቄዎች በአሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሀገረ ስብከቱን አዟል፡፡
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ይህን ይበል እንጂ፤ ደብሩ በጥያቄው መሠረት ግንባታውን እንዲቀጥል የሚገልጽ ነው የተባለ ደብዳቤ፤ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ለደብሩ አስተዳደር አስቀድሞ መጻፉን የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የደብሩም ዋና ጸሐፊ እንደኾኑ የጠቀሱት ምንጮቹ፣ በአንድ በኩል ጥያቄ አቅራቢ በሌላ በኩል ውሳኔ ሰጪና አፅዳቂ በመኾን የፈጸሙት ተግባር የተጠያቂነት መርሆዎችንና የአስተዳደር ጉባኤውን ውሳኔ ከመፃረሩም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምክትል ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተካረሩ ለመጡት አለመግባባቶችም አንድ መንሥኤ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ በሕንፃዎች፣ በሱቆችና በባዶ መሬት አጠቃቀምና የኪራይ አፈጻጸም፣ የአሠራር ችግር እንዳለባቸው ከተዘረዘሩት 15 ገዳማትና አድባራት አንዱ እንደኾነ፣ በፓትርያርኩ ትእዛዝ የተሠየመው ኮሚቴ ባካሔደውና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶስ በቀረበው ጥናታዊ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
እንደ ሪፖርቱ፣ የደብሩ ሁለገብ ሕንፃ፣ የዲዛይን ማሻሻያ በሚል ወጪው ከ61 ወደ 171 ሚሊዮን ብር ያደገ ሲኾን አዲስ ተቆጣጣሪ መሐንዲስም በደብሩ ዋና ጸሐፊ ጠቋሚነት ያለጨረታ ተቀጥሯል፡፡ ሀገረ ስብከቱና ሊቀ ጳጳሱ ለአዲሱ የዲዛይን ጥናትና ከብር 110 ሚሊዮን በላይ ላሳየው የዋጋ ጭማሪ ዕውቅናና ፈቃድ ባልሰጡበት ሁኔታ ግንባታው መቀጠሉም አግባብነት እንደሌለው በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡
ቋሚ ሲኖዶስ፣ ጥናታዊ ሪፖርቱን ሙሉ በሙሉ በመቀበል ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በደብዳቤው ገልጾ÷ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብርን ጨምሮ በተዘረዘሩት 15 ገዳማትና አድባራት ተፈጸመ በተባለው ኢ-ፍትሐዊ አሠራር፣ በተናጠልም ኾነ በጣምራ ተጠያቂ የሚኾኑ የአመራር አካላት ከተሰበሰቡት ማስረጃዎች ጋር በንጽጽር እንዲቀርቡለት፤ የሕንፃዎቹ፣ የሱቆቹና የባዶ መሬቶቹ የኪራይ አፈጻጸምና የመካናተ መቃብሩ አጠቃቀም የሚመሩበት መተዳደርያ ደንብ፣ የጨረታ ደንብ፣ የአከራይና ተከራይ የውል ሰነድ በማእከላዊነት በባለሞያዎች ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ፤ ጥናቱ ባልሸፈናቸው ሌሎች ገዳማትና አድባራት ላይም እንዲቀጥል መታዘዙንም አስታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment