Monday, August 24, 2015

ቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሰኛ ሓላፊዎችን አሳልፋ እንደምትሰጥ ፓትርያርኩ ተናገሩ




 በካህናትና ሠራተኞች ስም የሚደረግ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም

  (From Addis Admass) :-   በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት፣ ዘረፋ እና ምዝበራ ጥፋታቸው የተረጋገጠባቸው የአድባራት እና የሀገረ ስብከት ሙሰኛ ሓላፊዎች ለሕግ ተጠያቂነት ተላልፈው እንደሚሰጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ፓትርያርኩ ይህን የማረጋገጫ ቃል የተናገሩት፣ ስለ አድባራቱ የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመን በተካሔደው ጥናታዊ ሪፖርት ላይ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤ ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ ‹‹አድሏዊ እና ግለሰቦችን ለማጥቃት የተደረገ ነው›› በሚል በአንዳንድ አድባራት ተቃውሞ ማስነሣቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለፓትርያርኩ ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ የጥናታዊ ሪፖርቱን የመፍትሔ ሐሳቦች በሙሉ ድምፅ በመቀበል፣ የአድባራቱ ሓላፊዎች ጥፋት በሕግ አግባብ እንዲታይና ክሥ እንዲመሠረትባቸው ያሳለፈው ውሳኔም ሌላ አማራጭ እንዲፈለግለት ፓትርያርኩን ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ 


 ጥናቱ፣ ራሳቸው በሰጡት ትእዛዝ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ ባቋቋመው ኮሚቴ በይፋ መካሄዱን ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ሪፖርቱን ለመቃወም በሚል ካህናትንና ልዩ ልዩ ሠራተኞችን በማደራጀት በጎን የሚቀርብላቸውን አቤቱታ እንደማይቀበሉት ለዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡‹‹ለማንም ሰው ከለላ መኾን አልፈልግም፤ ሽፋንም አልሰጥም፤ ለአንተም ጨምሮ፤›› በማለት አቋማቸውን ያረጋገጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ‹‹በዚኽ አጸያፊ የዘረፋና የምዝበራ ሥራ ውስጥ እጁ የተገኘበትን ሰው ኹሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሳልፋ ትሰጣለች፤ ይኼ የመጨረሻ አቋሜ ነው፤›› ሲሉ የሕግ ተጠያቂነቱ አይቀሬ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡በፓትርያርኩ ጠንካራ አቋም መደናገጥ ታይቶባቸዋል የተባሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በሀገረ ስብከቱ ተከማችተው ለቆዩትና በየአድባራቱ እየተባባሱ ለመጡት የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ችግሮች የአሠራር ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ በማስረዳት፣ ጥናታዊ ሪፖርቱን እንደሚቀበሉትና እንደሚደግፉት ለፓትርያርኩ እንደገለፀላቸው ታውቋል፡፡

ላለፉት ስድስት ወራት 58 አድባራት ላይ ሲካሔድ የቆየው ጥናት፣ ከሓላፊዎቹ ጋር የጥቅም ትስስር ለፈጠሩ ግለሰቦች በሚያደሉ ውሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ መሬት፣ ሕንጻዎች፣ ሱቆች እና ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት ላይ የተጧጧፈ ዘረፋና ምዝበራ መፈፀሙን አረጋግጧል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ንብረቷን ከብክነት ለመታደግ ያወጣችውን የቃለ ዐዋዲ ደንብ ማስከበር የሚገባው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፤ ከድንጋጌው ውጭ ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት የሕግ ጥሰቱ አካል እንጂ የሕግ አስፈጻሚ መኾን
አለመቻሉ የችግሩ ባለቤት እንደሚያደርገው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

No comments:

Post a Comment