- ‹‹በመዝባሪ ላይ አልደራደርም፤ እስከ መጨረሻው ከፊት ለፊት ነኝ››
- የቤተክርስቲያኒቱን መሬት እና ሕንጻ በአዲስ አበባ የመሬት ገበያ አንጻር ሊታሰብ ከማይችልበት ዝቅተኛው በካሬ ሜትር 0.37 ሳንቲም፣ ከፍተኛው ብር 70 ያለጨረታ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የኪራይ ውል የተፈጸመባቸው ውሎች ተገኝተዋል፡፡
(አዲስ አድማስ ነሐሴ 02 2007 ዓ.ም)፡- በአዲስ አበባ
ሀገረ ስብከት የአድባራቱን ሰፋፊ መሬቶችና የገቢ ማስገኛ ተቋማት እየመዘበሩ ራሳቸውን ያበለጸጉ የአስተዳደር ሓላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ
ማትያስ መመሪያ ሰጡ፡፡
የአስተዳደር ሓላፊዎቹ የአድባራቱን ሰፋፊ መሬቶችና የንግድ ተቋማት ያለጨረታ ከገበያ ዋጋ በታች ከ15 ዓመት
እስከ ዕድሜ
ልክ በመዋዋል የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅሞች አሳልፈው በመስጠት ራሳቸውን አበልጽገዋል- ተብሏል፡፡
ፓትርያርኩ መመሪያውን የሰጡት፣ ላለፉት ስምንት ወራት
በሀገረ ስብከቱ አድባራትና አንዳንድ ገዳማት የመሬት፣ የሕንፃና የልዩ
ልዩ ገቢ
ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመንን ሲያጣራ የቆየው ኮሚቴ ያዘጋጀው ጥናታዊ ሪፖርት ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ
ጋር ከትላንት በስቲያ ከቀረበላቸው በኋላ
ነው፡፡
በፓትርያርኩ መመሪያ የተቋቋመው ኮሚቴው፣ በ51 አድባራት መሬት፣ ሕንፃና ሕንፃ ነክ ጉዳዮች ላይ ባካሔደው ጥናት የተጠቆሙት የመፍትሔ ሐሳቦችና በዋና ሥራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ
ማቴዎስ ሰብሳቢነት የሚመራው የአስተዳደር ጉባኤ
የተስማማባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች በሙሉ ተፈጻሚ እንዲኾኑ አቡነ
ማትያስ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በጥናቱ ሒደት የኮሚቴውን አባላት በጥቅም ለመደለል ከመሞከር ጀምሮ
በማስፈራራትና ስም
በማጥፋት የማጣራት ሥራውን ለማስተጓጐል ሲጥሩ
የነበሩ ሐላፊዎች፣ በመፍትሔው አተገባበር ላይም
ዕንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ ለሚለው ስጋት
ፓትርያርኩ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ወደ ኋላ ወደ ጎን የለም፤ ወደፊት ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ሀብት ምዝበራ ከማንም ጋር
አልደራደርም፤ ከጎኔ
ኹኑ፤ እስከ
መጨረሻው ከፊት
ለፊት ነኝ››
ሲሉ በቁርጠኝነት ተናግረዋል፡፡
በጥናታዊ ሪፖርቱ እንደቀረበው፤ የገቢ ማስገኛ የንግድ ተቋማቱ፣ ከአዲስ አበባ የመሬት ገበያ አንጻር ሊታሰብ ከማይችልበት ዝቅተኛው በካሬ ሜትር 0.37 ሳንቲም፣ ከፍተኛው ብር 70 ያለጨረታ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የኪራይ ውል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ይህም ጥቂት ሙሰኛ የደብር ሓላፊዎችና ግለሰብ ነጋዴዎች ሚልየነር እንዲኾኑበት ዕድል በመስጠት ቤተ ክርስቲያኒቱን የበይ ተመልካች እንዳደረጋት ተገልጧል፡፡
የአድባራት አለቆች፣ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞችና የሰበካ ጉባኤ አባላት በተገኙበት በተካሔደው ማጣራት ለጥናት ቡድኑ መረጃ በመስጠታቸውና ጥያቄ በማንሣታቸው ከመመሪያ ውጭ ከሓላፊነታቸው የታገዱት፣ የአራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ዋና ተቆጣጣሪ መጋቤ ጥበብ ወርቁ አየለና የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ሒሳብ ሹም ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም ወደ ቀድሞ የሓላፊነታቸውና ቦታቸው እንዲመለሱ በአስተዳደር ጉባኤው ተወስኗል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፤ ሙሰኛ ሓላፊዎችን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ተቋማቱ ለሦስተኛ ወገን እየተላለፉ የተሰጡበትን ውሎች በመሰረዝ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም የሚያስከብርና የሚያስቀድም ወጥ አሠራር እንዲዘረጋ ተወስኗል፤ ተቋማቱም በየአጥቢያው በተናጠል የሚተዳደሩበት አካሔድ ቀርቶ በማዕከል የሚመሩበት ሥርዐት እንደሚበጅ የተጠቆመ ሲኾን፤ ይህንንም የሚያስፈጽም ጽ/ቤትና ፓትርያርኩ የሚሰበስቡት ቦርድ እንደሚቋቋም ታውቋል፡፡
የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው አዲስ አበባ፣ ጥናቱ ባልሸፈናቸው ሌሎች አድባራትና ገዳማትም እንዲቀጥል አቡነ ማትያስ ያዘዙ ሲኾን በመጪው ዓመት ጥቅምት በሚካሔደው 34ኛው ዓመታዊ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤም በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገበር በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲወሰንበት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment