Monday, March 30, 2015

የአ/አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ሹመት ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሱን እያወዛገበ ነው




  • ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያርኩን ምደባዎች በደብዳቤ ተቃውመዋል
  •   ቋሚ ሲኖዶሱ፤ጠቅ/ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡትን አቤቱታ መመልከት ጀምሯል
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ ስኪያጅ መሾማቸውን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገለጸ፡፡ኹለቱ ሥራ አስኪያጆች ለሀገረ ስብከቱ መመደባቸው የተገለጸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ከፓትርያርኩ ልዩ /ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በደብዳቤ በተሰጠ መመሪያ ነው፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ሓላፊዎችን የመምረጥና የመመደብ ጉዳይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መያያዙን፣ በዚኽም መሠረት ሲሠራ እንደቆየ በመመሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለቱ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆች ምደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲያደርሷቸውና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡

ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአድራሻ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጧል፡፡ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የሥራ አስኪያጆቹ ሹመት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዐዋዲው እና ከሀገሪቱ የሕግ አሠራር ውጭ መኾኑን በመግለጽ ምደባውን በትላንትናው ዕለት ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ የተቃወሙ ሲኾን፣ ፓትርያርኩ ከሕግ አግባብ ውጭ የሰጡትን መመሪያ እንደገና እንዲያጤኑት መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነታቸው ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እንጂ ለፓትርያርኩ ኾኖ እንደማያውቅና ሊኾንም እንደማይችል የገለጹት አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የፓትርያርኩ አካሔድና የሥራ አስኪያጆች ምርጫ ‹‹የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ያልተለመደና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ አሠራር በእጅጉ የሚፃረር ነው፤›› ብለዋል፡፡

 አቡነ ማትያስ የሰጡት መመሪያ ተቀባይነት የሚኖረውም ተሿሚዎቹ በሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመርጠው ከቀረቡ በኋላ ምርጫቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር የጋራ ስምምነት ተደርሶበት በፓትርያርኩ ሲሾሙ እንደኾነ በተቃውሟቸው አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከልዩ /ቤታቸው በሰጡት መመሪያና በሥራ አስኪያጆች ምርጫዎቻቸው እንደማይስማሙና ምደባውንም ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ያስታወቁት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ ‹‹ይህ አሠራር ከትዝብት ላይ የሚጥል መኾኑን ተረድተውልን ለቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ አሠራርና ለኹላችንም ሰላም ሲባል ውሳኔዎን እንደገና እንዲያጤኑ በታላቅ አክብሮት አሳስባለኹ›› ብለዋል - በተቃውሞ ደብዳቤአቸው፡፡

የፓትርያርኩን መመሪያ እንዲያስፈጽሙ በአቡነ ማትያስ መመሪያ የተሰጣቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ትላንት ከቀትር በፊት በተደረገው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ መመሪያውን በመቃወም አስተያየታቸውን በቃል ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩም አጀንዳው ውሳኔአቸውን የሰጡበት በመኾኑ መታየት የለበትም በሚል ቢቃወሙም ቋሚ ሲኖዶሱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቃውሟቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙ ተገልጧል፡፡ ከትላንት በስቲያ በድንገት ይፋ የኾነው የሀገረ ስብከቱ ተተኪ ሥራ አስኪያጆች ምደባ፥ ‹‹የመልካም አስተዳደር ሒደቱን ማቀላጠፍ›› በሚል ከኹሉ አቀፍ የትምህርት ዝግጅት፣ ከሥነ ምግባርና ከብሔር ተዋፅኦ መስፈርቶች አንጻር ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሳቸውን ላለፉት ሦስት ወራት ሲያወዛግብ መክረሙን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

Source :- Addis Admass

5 comments:

  1. ኧረ በሕግ….ምንጭ፣ ምንጭ፣ ምንጭ…….

    ReplyDelete
  2. ay yegna bete kihnet neger hulgize techekachikew eske meche yihon?EGZIABHER selamun yawurdln

    ReplyDelete
  3. selam amlk yadriglen

    ReplyDelete
  4. አረ አባቶች ግዴላችሁም ሁሉም ለበጎ ነው ባይሆን በውሳኔው ላይ ድጋፍ በማድረግ እርዷቸው እንጂ አትቃወማቸው። ትክክል ናቸው አኮ!!!!!! ችግሩ አኮ በረዳት ሊቀ ጳጳሱም (ለውጥ እንዲያመጡ በቅርቡ የተሾሙ) ሆነ የጠቅላይ ቤተክነቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አላጤናችሁትም ነበር። ደግሞስ ምደባው በናንተም በኩል አለፈም አላለፈም ዋናው አኮ ትክክለኛ ምደባ አድርጎ ያለውን ችግር መፍታት ነው። ምነው ወንጀሉ እኮ መለክና ቅርጽ ቁመና አውጥቶ ከዚህ በፊት ከሚታወቁት የሙስናና የሙዳየ ምጽዋት ግልበጣ በጣም አይን ባወጣ አኳኋን አየተካሄደ ነው። ክቡሩን የሰው ህይወት አስኪያሳጣ ድረስ። ሙዳየ ምጽዋት ተከፍቶ ተሠርቋል አልተሠረቀም በሚል ምስክርነት ከምዕመናን የተሠበሰበውን ገቢ እሠርቃለሁ አትሰርቅም ኑፋቄን በቤተክርስቲያን ውስጥ እዘራለሁ አትዘራም በትክክል የሚሰሩትን አገልጋዮች ከቦታቸው አንስቶ የሚያውቁትንና የጥቅም ተጋሪን በመመደብ በሚመጣ ክርክር ሌሎችም ብዙ በርካታ ችግሮች ። ይህ የሆነው ደግሞ በቤተክህነት ዋናዋና ቦታዎች ላይ ዘመድ አለኝ ወይም ወሳኝ ሰው ለአላማችን ማስፈፀሚያ የሚረዳን ሰው አለን በማለት በማንአለብኝነት በሚሰራ ዘረፋና ወንጀል ነው። በጉቦና በመማለጃ ካለቦታቸውና ካለዕውቀታቸው የሚያወናብዱ ስንቶች አሉ። በማይመጥናቸው ቦታ ላይ እየተመደቡ። ካለበለዚያም ደግሞ አዲስ መቼም ጥሩ ነው። የበፊቶቹ ብዙ ስላስለቀሱና ስልጣናቸውን በአግባቡ ሰላስተጠቀሙበት(ስላልሰሩበት) ወይም እንደው እስቲ ይረፉም ተብሎ አዲሶቹ ቢመደቡስ ምን አለበት? ምን ያሟግታል። እባካችሁ እኛ በጣም ድብልቅልቅ ያለ አሰራር ሰልችቶናል። ተነሱ በቃ ይበቃቸዋል። እሱን ጉዳይ ተዉትና ወደሌላ ስራ ግቡ። መቸም ይህ ሁሉ ክርክር በዘርና በብሔር ልዩነት ምክንያት እንደማይሆን ተስፋችን ነው። እናንተን ስንለምን ጎን ለጎን አምላካችን እንዲረዳን እየፀለይን መሆኑን ተረዱ።

    ReplyDelete