Thursday, March 5, 2015

ስለ ዝቋላ ደብረ ከዋክብት ‹1›


 
ከዲ/ን አባይነህ ካሴ
አስቸጋሪው እሳት ጋብ አለ እንጂ አሁንም አልጠፋም፡፡ ለጊዜው እዚያው ገደሉ ውስጥ ተገትቶ ይገኛል፡፡ እሳቱ ያለበት ቦታ ላይ ለመድረስ ባለመቻሉ ሌሊቱን ሙሉ የዙሪያ ገብ ምንጠራ ሲካሄድ አድሯል፡፡ የገደሉ አካባቢ እያልን የምንጠራው ስፍራ በቀላሉ የሚገመት ሳይኾን ወደ ሃያ ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ቦታ ይሸፍናል፡፡ ቁጥራቸው ፭፻ በላይ የኾኑ ሰዎች እሳቱን ለማጥፋት ወደ ዝቋላ ገዳም ገብተው አድረዋል፡፡ የቦታው ገደላማነት፣ ጨለማውና ጫካው ተደማምሮ እስከመጠፋፋት ተደርሶ ነበር፡፡ከምሽቱ እስከ ሰዓት ድረስ ጨለማው ሳይበግራቸው በእግር በመኪና ወደ ገዳሙ የገቡ መኾናቸው ታውቋል፡፡


ከፍተኛ የኾነ የእኅል ውኃ እጥረት ከመግጠሙ የተነሣ ሳይበሉ ሳይጠጡ ሌሊቱን ሙሉ የተጋደሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ገዳሙ የተቻለውን ያኽል እንጀራ እና ዳቤ ያቀረበ ቢኾንም የሚበቃ አልነበረም፡፡
ከአዲስ አበባ እና ከናዝሬት አካባቢ ሕዝብ ተነቃንቆ እንዲረዳቸው ይጠበቃል፡፡ እስካሁን ያን ያኽል የሚያመረቃ ቁጥር ያለው ሰው ከእነዚህ አካባቢ አለመሄዱ አሳዛኝ ኾኗል፡፡ ከእነርሱ ወዲያ ማን ሊደርስልን ይችላል የሚል የፍቅር ቅሬታ ተሰምቷል፡፡

የተወሠነ የእሳት ማጥፊያ በእጅ ያለ ቢኾንም ወደ ገደሉ ለመቅረብ ባለመቻሉ የተነሣ አሁን እየተደረገ ያለው እሳቱን በገደሉ ውስጥ ገድቦ ለማስቀረት ነው፡፡ አሁን በነፋሱ ጸጥታ ምክንያት ተስፈንጣሪ እሳት የሌለ በመኾኑ ጋብ የማለት ሁኔታ ይታያል፡፡ ኾኖም ግን ከሰዓት በኋላ የመነሣት ልማድ ያለው ነፋስ ከመጣ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ እሳቱ በቀጥታ ከገደሉ ወጥቶ ሽቅብ ወደ ተራራው የመውጣት አቅም እንዳይኖረው በተቻለ መጠን የምንጣሮ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ወደላይ መውጣቱን ትቶ ወደጎን የሚሄድ ከሆነ በቀላሉ ችምችም ወዳለው ደን የመድረስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ይኽ ከሆነ ደግሞ ሽቅብ የመውጣት እና ገዳሙን የመተናኮል አጋጣሚ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ አሁን ወደዚሁ ችምችም ወዳለው ጫካ ሊገባ ሲል የቆመ ሲኾን በሚገባ ተከላክሎ እዚያው ለማስቀረት ካልታቻለ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፊ የኾነ ውድመት ሊከሰት ይችላል፡፡
ከተለያዩ መንግሥታዊ አካላት ሊገኝ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው የሄሊኮፕተር እገዛ ሊቀ ጳጳሱ እንዳሉት እስካሁን ፍንጭም አላገኘም፡፡ በተለምዶ ሺህ እየተባለ የሚጠራው የቢሾፍቱ መኪና መገጣጠሚያ ሁለት ቦቴ ለማሠማራት ቃል መግባቱ የታወቀ ሲኾን በሌላ በኩል መከላከያ ለነገ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ወታደሮች እና ሌሎችም ቁሰቁሶች ሊመድብ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ይኽ ግን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንዳይኾን ስጋት አሳድሯል፡፡

በአዲስ አበባ እና በናዝሬት በዱከም የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እገዛቸው አሁንም እየተጠበቀ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንድ አይሱዙ መኪና ሰው ጭኖ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ለመሄድ የምተነሡ ሰዎች ደብረዘይት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ የመገናኛው ቦታ እንደኾነ ዕወቁ፡፡
ወደስፍራው የሚሄዱ ኹሉ፡- ቆንጨራ፣ መጥረቢያ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ የሚጠጡት ውኃ፣ ስንቅ ቢጤ ቢይዙ ይመከራል፡፡
አይዞን በርቱ እንበርታ!
ጉዳዩ የእኛ ነው ሳንጠብቅ እንርታ

No comments:

Post a Comment