Monday, March 2, 2015

የአራዳ ጊዮርጊስ ደብር በገንዘብ ብክነትና በመልካም አስተዳደር ዕጦት መቸገሩ ተገለጸ


(አዲስ አድማስ የካቲት 21 2007)፡-     ዐድዋን ጨምሮ በተለያዩ ጦርነቶች በመዝመትና በነገሥታት መናገሻነቱ የሚታወቀው ታሪካዊው የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ባለዕዳ በሚያደርግ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ምንጮች ገለፁ፡፡

ደብሩ ‹‹ዳዊት ወንድሙ›› በተባለ የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ በማሠራት ላይ የሚገኘው ባለአራት ፎቅ የንግድ ማዕከል ሕንፃ፣ በሰኔ ወር 2004 .. በውስን ጨረታ በወጣ ማስታወቂያ መሠረት በሰበካ ጉባኤውና በልማት ኮሚቴው ጥምር የጋራ ስብሰባ ለአሸናፊው ድርጅት ተወስኖ የኮንትራት ውሉም በብር 61‚234‚885.02 ጠቅላላ ወጪ ተፈጽሞ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ አማካሪ ድርጅቱም የተቀጠረው በግልጽ አሠራር ተለይቶ መሆኑን፣ ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የደብሩ አስተዳደር በዲዛይን ክለሳ ሰበብ የግንባታ ዋጋውን ከዕጥፍ በላይ በማናር የሥራ ውሉን መቀየሩ ተመልክቷል፡፡ የቀድሞውን አማካሪ መሐንዲስ በማሰናበትም ‹‹የዲዛይን ክለሳና ተያያዥ ሰነዶች ፍተሻ በማስፈለጉ›› በሚል ሰበብ ያለምንም ግልጽ መመዘኛና ውድድር በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በተቀጠረው ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ለተደረገው የፕላን ማሻሻያ 80‚500 ብር የተከፈለ ሲኾን የግንባታ ወጪውም 170 ሚልዮን ብር በላይ ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡

የኮንስትራክሽንን ሕጉን በመጣስ ያለጨረታ የተሰጠው ‹‹የፕላን ማሻሻያ›› የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሀገረ ስብከቱ ባልፈቀደው ‹‹የተከለሰ ዲዛይን›› መቀጠሉ የተገለጸው ግንባታ፣ 80 ሚልዮን ብር ያላነሰ የወጪ ልዩነት ቢታይበትም እንደጭማሪ የተጠቀሱት የአሳንሰርና የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች የተጠቀሰውን ወጪ ምክንያታዊ እንደማያደርጉት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሕንፃው ከጠቅላላ ሥራው በሢሦ ደረጃ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት  ወጪው 25 ሚልዮን ብር በላይ መድረሱ፣ ሥራው በማዕከል ከተፈቀደው ውጭና በተለየ ውል እየተካሔደ መኾኑን ያረጋግጣል ብለዋል - ምንጮቹ፡፡

የደብሩ ይዞታዎች በኾኑ ኹለት ሕንፃዎች ላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት የደብሩ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ጋራ ያደረገው የኪራይ ውል የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ የጣሰ እንደኾነ የደብሩ ሠራተኞች ያስረዳሉ፡፡ የደብሩ አስተዳደር በመስከረም ወር 2007 .. ከባንኩ ጋር በፈጸመው የዐሥር ዓመት የኪራይ ውል፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቅርንጫፍ እና መሀል ፒያሳ ቅርንጫፍ ለመክፈት ብር 12 ሚልዮንና ብር 28 ሚልዮን በድምሩ ብር 40 ሚልዮን እንዲከፈለው መስማማቱ ታውቋል፡፡ 

መዋቅራዊ አሠራርንና የሌሎችን የሥራ ሓላፊነት በማናለብኝነት በመጣስ እየተፈጸመ ነው በተባለው የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛ ተጠያቂ የተደረጉት የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የቢሮ ሠራተኞችንና ባለሞያዎችን በዛቻ ቃል በማሸማቀቅ እንደሚወቀሱ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የሕዝብ ሀብት የኾነችው ቤተ ክርስቲያን ‹‹በልማት እየተመካኘ ተገቢ ባልኾነ የሥራ ሒደት በዕዳ እንዳትዘፈቅ፣ የሠራተኛው የሥራ ዋስትናም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ›› ሲሉ ያሳሰቡት የደብሩ ሠራተኞችና ምእመናኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ታሪካዊውን ደብር የሚታደግ ፈጣንና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ተማፅነዋል፡፡ 

ከመስከረም ወር 2006 .. ጀምሮ የደብሩ አስተዳዳሪ በመሆን የተሾሙት መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃን ስለጉዳዩ በስልክ አነጋግረናቸው፤ ‹‹የምእመናን አቤቱታ እንድትቀበሉና ይህን ጉዳይ እንድትመረምሩ ሥልጣን የሰጣችኹ ማን ነው?›› በማለት በአካል ካልኾነ በቀር በስልክ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልኾኑ በመግለጻቸው ቀጠሮ ለመያዝ ስንሞክር ስልኩን ጆሮአችን ላይ በመዝጋታቸው ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡


No comments:

Post a Comment