Wednesday, October 8, 2014

ስህተቱን የማያምን መንግሥት


አንድ አድርገን መስከረም 29 2007 ዓ.ም


በኢህአዴግ ውስጥ ከተራ አባልነት እስከ ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታነት ድረስ ያገለገለው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ያጸፈውን መጽሐፍ ‹‹የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ›› የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 367-369 ድረስ ያሰፈሯቸውን ሀሳቦች እንደወረደ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ከእለታት በአንድ ቀን እንዲህ ሆነ:-በኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ከሽመልስ ከማል ጋር የጠዋት ስራችን ሀገራችንና አለም እንዴት እንዳደረች ለማወቅ ሚዲያ ሞኒተር የምናደርግበት ነበር፡፡ ይህን እየሰራን እያለ ጸሐፊዬ በኢንተርኮም ደውላ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተላ ሰዎች ሊያናግሩኝ እንደሚፈልጉ ገለጸች፡፡ እንድታስገባቸውም ነገርኳት፡፡ ሁለት ጎልማሳ እድሜ ላይ ያሉ ሰዎች ገብተውተቀመጡ፡፡ አፍታም ሳይቆዩ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጁ አቡነ ሳሙኤል ወደ ኢቲቪና ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት 
አቤቱታ እንዲያቀርቡ እንደላኳቸው ተናገሩ፡፡

ታሪኩ እንዲህ ነበር ፡-
ከሁለት ቀን በፊት የእስልምና እምነት ተከታዮች በአላቸውን ለማክበር በአዲስ አበባ ስቴድዮም በዙሪያው ተገኝተው ነበር፡፡ በስፍራው የተገኝው ጋዜጠኛ ዘገባው ከ1.6 ሚሊየን በላይ ሙስሊሞች እንደተገኙ ገለጸ፡፡ በወቅቱ የስታስቲክስ ኤጀንሲ የአዲስ አበባ ህዝብ 2.7 ሚሊየን እንደደረሰ የተናገረበት ወቅት ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የክርስትና እምነት ተከታዩ ከሰማንያ ሁለት በመቶ በላይ እንደሆነ እጀንሲው አሳውቋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ስቴዲዮም ወጥተዋል ቢባል እንኳ ከግማሽ ሚሊየን አይበልጥም፡፡ በዛ ላይ እንደ አቃቂ ያሉ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ ሙስሊሞች በአላቸውን የሚያከብሩት በአቃቂ ስታዲየም ላይ በመሰባሰብ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በተመሳሳይ በአካባቢያቸው ያከብራሉ፡፡

ሁለቱ መልዕክተኞች ይዘው የመጡት አቤቱታ ተጨምቆ ሲታይ ይህን የሚያመላክት ነበር፡፡ እርግጥም አላስፈላጊ ፉክክር በተገባበት ሁኔታ እንደዚህ አይነት ዜና መልቀቅ ተገቢ አልነበረም፡፡ በየትኛውም መንገድ ቢሆን የስህተቱ ምንጭ መንግሥት መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ አንድም የአዲስ አበባ ሕዝብ ተብሎ የተገለጸው ልክ አይደለም ፤ አልያም በስታዲየም ተገኝ የተባለው ተጋኖ ቀርቧል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያነሱት ጥያቄ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገለጽን፡፡ አጣርተን ምላሽ እንደምንሰጥ ቃል ገብተን አሰናበትናቸው፡፡ እያለ ደራሲው ይቀጥላል….ቀጥሎም
‹‹ በዜና መልኩ ወደ እርምት መስጠት ብንገባ የፖለቲካ ስራችን ይበላሻል፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በአሉ ያለምንም ችግር በመቶ ሺዎች ወጥተው ማክበራቸውን ፤ ይህም በእንከን የለሹ ህገ መንግስት የተገለጸው የሃይማኖት ነጻነት እውን መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ የሚያመላክት ጽሑፍ እንላክላቸው፡፡ የቅዳሜ የኢቲቪ ህትመት ዳሰሳ በዚህ ላይ ሰፊ ትንታኔ እንዲሰጥ አቅራቢዎችን ጠርተን ኦሬንቴሽን እንስጣቸው  ፡፡ ደጋግመው በመቶ ሺዎች በተገበት እያሉ ይናገሩ›› አልን፡
እነሆ የስምኦን ልጅ በረከት ያዘዘንን አደረግን፡፡ አዲስ ዘመን መቶ ሺዎች በተገኙበት በድምቀት እንደተከበረ የጻፍንላትን ለህትመት አበቃች፡፡ የህትመት ዳሰሳ ቋሚ ተሰላፊው ሚዛን ከአሸብር ጋር ሆነው መቶ ሺዎች ሲሉ ዋሉ፡፡ ይህም ሆኖ በሚዲያና ማህበራዊ ድረ ገጾች መብጠልጠሉ ግን አሁንም አላባራም፣፣…… ይለናል  አቶ ኤርሚያስ ለገሰ

በየጊዜው በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚወጡ ጽሑፎች መልስ ይኑራቸውም አይኑራቸው ፤ ለበላይ አካል እንደሚደርሱ ከዚህ ጽሁፍ ለመረዳት ችለናል፡፡(የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር በማዕተብ ዙሪያ ለተነሳው ሃሳብ ማስተባበያ እንደሰጡት)፡፡  አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ካነሷቸው ሃሳቦች ጋር በተመለከተ አንድ አድርገን ይዛ ከወጣችው ጽሁፎች ውስጥ አንዱን ለማንበብ ይህን ይጫኑ፡፡

1 comment:

  1. በየጊዜው በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚወጡ ጽሑፎች መልስ ይኑራቸውም አይኑራቸው ፤ ለበላይ አካል እንደሚደርሱ ከዚህ ጽሁፍ ለመረዳት ችለናል

    ReplyDelete