Saturday, October 18, 2014

ሰዶማዊነትና ሰብዓዊ መብት


አንድ አድርገን ጥቅምት 9 2007 ዓ.ም
 አባ ሳሙኤል (ሊቀ ጳጳስ)

   የቅዱስ ሰኖዶስ አባልና
            የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

የእግዚአብሔር ዕቅድና ፈቃድ ከፍጥረታቱ የተለየ ወይም የራቀ አይደለም። ዓለምን የፈጠረው ከሰዎች ጋር ዘለዓለማዊ  መቀራረብ ወይም ግንኙነት እንዲኖረው ፈልጎ ነው። ይህ የሚያልፈው ዓለም (ምድር) እንኳን በጊዜው ቢያልፍ በማያልፈው ሰማያዊ ዓለም ፈጥሮአል። ይህ የሚታየው ዓለም (Physical world) የተፈጠረው ለሰዎች መገልገያ እንደሆነ መፅሐፍ ቅዱስ ይናገራል።ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትምዘፍ1÷28ሰማየ ሰማያት ለእግዚአብሔር ወምድርስ ወሀበ ለእጓለእመሕያው ሰማይ ለእግዚአብሔር መንበሩ ነው ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣትእንዲል። መዝ.13÷16



የብሉይ ኪዳን ጸሐፍት ስለ ሰው የሚገልፅ ብዙ ቃላት ቢጠቀሙም ትልቁን ቁጥር ይዞ የሚገኘውና በብሉይ ኪዳን የመፅሐፍ ክፍል 562 ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው አዳም የሚለው ቃል ነው። ይህ ቃል የሰው ልጆችን ሁሉ ይወክላል። አዳም ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው የፍጥረታት ሁሉ ዘውድ የፍጥረታት ሁሉ የመጨረሻና ከፍተኛ ደረጃ ፍጡር ማለት ነው። ዘፍ. 1÷26-28 2÷7 ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነው።እግዚአብሔር አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሶችንና የሰማይ ወፎችን እንስሳትንና ምድርን ሁሉ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙበማለት ተናግሯል። ዘፍ. 1÷26 ይህ ደግሞ የሚያስረዳው እግዚአብሔር ለሰው ምን ያህል ክብር እንደሰጠው የሚያሳይ ነው። ከዚህም በላይ ምድርን እንዲገዛ ሥልጣን ተሰጥቶታል። አዳም የሚለው ስም የመጀመሪያው ሰው መጠሪያ ስም እንደሆነ ገልፆአል። በብሉይ ኪዳን የመፅሀፍ ክፍል ውስጥ 42 ጊዜ ተፅፎ የሚገኘውና ስለ ሰው የሚገልፀው ቃል በዕብራይስጡኤኖሽየሚለው ሲሆን በአማርኛው  ሰው የሚል ትርጉም ይኖረዋል። ኢዮብ 28÷13 መዝ. 89÷3 ኢሳ. 13÷12 በመጀመሪያ ሰው የሚለው ቃል በመጀመሪያ ለተፈጠረው (አዳም) መጠሪያ ስም የሚያገለግል ነበር።እግዚአብሔር አምላክም ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም። የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለትዘፍ. 2÷18 ሰው የኺለውነ መጠሪያ ኋላ ሁሉን የሚመለከት የአዳም ልጆች የወል መጠሪያ ሆነ።ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንም የሚይዝ የሰው ልጅ እንዳያራሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነውኢሳ. 56÷2 በፆታ ወንድን የሚመለከት ስለ ሰው የሚናገረው የዕብራይስጡ ቃል ኤሽ (ish) የሚለው ነው። ይህ ቃል ኋላ የሰው ልጆችን ሁሉ የሚመለከትና መጠሪያ ሆነ። ወደ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ስንመጣ የምናገኘው አንተሮፓስ (Anthrops) የሚለውን የግሪክ ቃል ነው። ይህ ቃል አዳም ሰውኤሽ” “ኤኖሽ የሚለውን ቃል ሁሉ ጠቅልሎ ስለ ሰው ተፈጥሮና ጠባይ የሚያስረዳ ነው። ይህ ቃል ሰዎች በተፈጥሮአቸው በጠባያቸው ከእንስሳ፣ ከመላእክት፣ ወዘተ እንደሚለዩ የሚያሳይ ብዙ ትርጉም የያዘ ቃል ነው። ሰዎች ከእንስሳ እንደሚለዩ፡- “እንግዲህ ሰው (Anthropos) ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥማቴ.12÷12


እግዚአብሔር የመጀመሪያው ሰው አዳምን ከአፈር (ጭቃ) እንደፈጠረውም ቅዱሳት መፃሕፍት ይናገራሉ። የመጀመሪያዋ ሴት (ሔዋን) ከአዳም ጎን እንደተገኘች ተጽፏል። ማር. 10÷6 ዘፍ. 2÷22 ሰው የተፈጠረው ከዐፈር ቢሆንም ከሌሎች ፍጥረታት የሚለይበት የሰውነት ይዘት (Body components) አለው። ከሰውነት ክፍሎቹም ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙትና ሰውን ከመንፈሳውያን ጋር በመንፈሳዊ ዓለም እንዲኖር ካስቻሉት መካከል (የሚያስብ አእምሮ) ነፍስና አእምሮ ሲሆኑ ሌሎም ተጠቃሾች ናቸው። ሰው ቅዱስ ነው እኔ ቅዱስ እንደሆንኩኝ እናንተም ቅዱሳን ሁሉ።


1.ስለ ሰብዓዊ መብቶችና የስሞችን ግንኙነት መነሻ ሐሳብ
ሰብዓዊ መብት የሰው ልጅ ስብዕና መገለጫ የሆኑ ዕሴቶች መጠበቅን የሚመለከት ነው። ሰብዓዊ መብት ማለት ከቃሉ እንደምናየው ለሰው የተሰጠ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ሰው በመሆኑ ብቻ ሊያገኘው የሚችለው መብትና ጥበቃ ማለት ነው። ሰው ከሰብዓዊ መብቶች አንዱን ቢያጣ ምሉዕነቱ ይቀንስበታል። ለምሳሌ ሰው በሰውነቱ ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስ፣ መረጃ ወይም ትምህርት ሊያገኝ እና በተፈጥሮ ካገኘው ጸጋ ጀምሮ በራሱ ያዳበራቸው በባህል፣ በቋንቋ፣ በአኗኗር ሥርዓት የተገነቡ የማንነት ጥያቄዎች ሊመለሱለት ግድ ይላል። ከእነዚህ አንዱ ቢጎድል በሕይወቱ ክፍተት ስለሚኖርበት እሴቶች ማንም ሰው ተነሥቶ እንዲከበሩለት ይጥራል። ሰብዓዊ መብት ለሁሉም የሰው ልጆች በእኩልነት ሊከበር የሚገባው እነዚሁ የሰወ ልጅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ሰብዓዊ መብት የሚለው ጥምር ቃል በትክክል የሚተረጎመው የሰው ትክክለኛ ተፈጥሮአዊ ጠባይና ባህርይ ከመገንዘብ መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳብ ጋር ነው። ይህንን ለመረዳት አስቀድሞ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበትን ምክንያትና ለሰው የሰጠውን ተፈጥሯዊ ዕሴት መረዳት አይከብድም። ሰው የተፈጠረው ከፍጥረታት ሁሉ የበላይ በመሆንና በፍፁም ልዕልና ነው። በየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ወይም ዓለማዊ ፍልስፍና የሰው ልጅ የፍጥረታት ሁሉ ማዕከልና ገዥ እንደሆነ ተቀባይነት አለው። በክርስትና ሃይማኖት የመፅሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ሰው የተፈጠረው በሰራው አምላክ በልዑል እግዚአብሔር አምሳና አርኣያ ነው (ዘፍ.1÷26) ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምሉዕና የማይገሰስ ሰብዓዊ ልዕልና ክብር አለው። ሰብዓዊ መብትንና ሰውን መረዳት መቻል የሚጀምረው ይህንን ሥነ ተፍጥሮ ከማወቅ፣ ከማክበር፣ ከመጠበቅ ጋር ነው።

ሰብዓዊ መብቶች ከሌላው ሥነ ፍጥረት ሁሉ ተለይተው ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጡ የሰው ሀብቶች ናቸው። ስለዚህ ሰብዓዊ መብት ማክበር ማለት ሰውን ማክበር ነው። ከፍ ብሎም ሰው ማክበር ማለት ፈጣሪን ማክበር ነው፣ ሰውን አለማክበር ደግሞ ፈጣሪን እና የፈጣሪን ሕግጋት/ ሥራዎች አለማክበር ነው፣ ለምሳሌ በኦሪት ዘፍጥረትየሰው ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ ይፈሳል፣ ሰው በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና” (ዘፍጥረት 9÷6) የሚል ትዕዛዝ ይገኛል። ይህም በፈጣሪና በሰው፣ በፈጣሪና በሰብዓዊ መብት መካከል ያለውን ግንኙነት ይገልፃል። ሰብዓዊ መብት በትክክል የሚተረጎመው የሰውን ሥነ ፍጥረት ከማወቅና ከረዳት ነው ካልን፣ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮው ያገኛቸው መብቶች ማለትም ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከት ነው።

የሰው ልጅ በማህበራዊ አኗኗሩ ከሚኖረው የአንድ ሰው ለአንድ ሰው ርስ በርስ የግንኙነት ህግ ጀምሮ፣ የአካባቢ ሕግ፣ ባህልና ልማድ፣ እስከ ዓለም አቀፍ የመንግሥታትና የተቋማት ውሎች ድረስ በራሱ ስምምነትና ጥበብ የሚሠራቸው ሌሎች መብቶችና ግዴታዎች ከራሱ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕግ የሚመነጩ ሲሆኑ፣ ሰብዓዊ መብቶች ግን ሙሉ በሙሉ ከአምላክ የተሰጡ ሊገሰሱና፣ ሊጣሱ፣ ሊናቁና ቸል ሊባሉ የማይገባቸው የተፈጥሮ ፀጋዎች ከእግዚአብሔር ያገኛቸው ሥጦታዎች ናቸው። እነዚህን የሰው ልጆች መብቶች ሳይከበሩ የሰውን ልጅ ሌሎች ሕጎች ማክበር ሰውን ሙሉ አያደርጉትም። ስለሆነም ሰብዓዊ መብቶች ማንኛውም ሰው በሚኖርበት ማኅበረሰብ እንዲከበሩለት የሚፈልጋቸው የፀኑ መብቶች ናቸው። ማንኛውም ግለሰብም ወይም ቡድን፣ ማኅበራዊ አስተዳደር ወይም መንግሥት፣ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ወይም ተቋማዊ መተዳደሪያ ሰብዓዊ መብትን በሥሩ ለሚተዳደሩ ግለሰቦም ሆነ ማኅበረሰቦች ለመስጠትም ሆነ ለመንፈግ ሥልጣን የለውም። የሰው ልጅም ሰው የመሆንን ስጦታ በተፈጥሮው ከፈጠረው አምላክ ያገኘውና ሰው መሆኑ የተረጋገጠባቸው ስለሆኑ ከማንም አይጠብቅም፣ በአንጻሩ ሌላ አካል እንዲነፍገውና እንዲጥስበትም አይፈልግም።

አንድን ማኅበረሰባዊ ወይም ኅብረተሰባዊ ሕግ እና ሥርዓት ፍትሐዊና በሥሩ በአባልነትም ሆነ በዜግነት ለሚኖሩ የሰው ልጆች ትክክለኛ አመለካከት አለው የሚባለው የሰብዓዊ መብቶቹን መከበር ማረጋገጥ መቻሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሰብዓዊ መብቶች መጠበቅና መሟላት ሲያረጋግጥ፣ ከራሱ ሕገ ማኅበረሰብ/ሕግ ጀምሮ በሁሉም ብሔራዊና ማኅበራዊ ሕጎችና የሕግ ማስፈፀሚያዎች ዕውቅና ሊሰጥ፣ ፍትሐዊና ቅን ተቋማትን በማደራጀት ተፈፃሚ እንዲሆኑ ሲያደርግ ነው። ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ መብቶቹ እንዲከበሩላቸው የመጠየቅ መብት ሲኖረው ሰሚው ወይም ተጠያቂው አካል ደግሞ በጥያቄው መሠረት ሊከበሩ የሚገባቸውን መብቶች በማክበር፣ በመጠበቅና ያለመነጣጠል በማሟላት መልስ ሊሰጥ ይገባዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖች በሚል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተዘጋጀ ጥር 2004 . አንቀጽ 16 ገፅ 7 ላይ በዘር በዜግነት ምክንያት ገደብ ሲያደርግ እድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ ወንዶችና ሴቶች ተጋብተው ቤተሰብ የመመስረት መብት አላቸው።

ቤተሰብ የአንድ ሕብረተሰብ መሠረታዊና ተፈጥሯዊ አካል ስለሆነ የሕብረተሰቡና የመንግት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ይላል እንጂ ለሰዶማውያን የሰጠው መብት በግልም ይሆን ቡድን የለም እነሱ የሕብረተሰቡ መብት እየተጋፋ ትውልድን የማበላሸት በሕገወጥ ሰብዓዊ መብት ሽፋን ስህተታቸው ለመሸፈን ይሞክራሉ።

እንደሚታወቀው በምንኖርባት ምድር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድንጋጌዎችን ጨምሮ በልዩ ልዩ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶች ስምምነትና ድንጋጌ የሆኑ የሕግ ሰነዶች እናገኛለን። ይህ ማለት ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን የዓለም ተቋማትና ብሔራዊ/ፌዴራላዊ መንግሥታት ይሰጣሉ ወይም ይደነግጋሉ ማለት ሳይሆን ተቋማቱ ወይም መንግሥታቱ ያላቸው ፍትሐዊነት ለመግለፅና እነዚህን መሠረታዊ ሕጎች ሳይጠብቁ ሌላውን እንጠብቃለን ማለት ስለማያስችላቸው ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅና ማክበር ያለውን አስፈላጊነት ለመግለፅ ነው። በተጨማሪም ሰብዓዊ መብቶችን በዓለም አቀፍና ሕጎችና በብሔራዊ መተዳደሪያዎች ማካተቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግልም ይሁን በቡድን፣ በቃልም ይሁን በተግባር፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዳይፈፀም ጥበቃ ለማድረግ ሲባል ነው። ይህ በማይሆንበት ጊዜ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቱ ካልተከበረለት ምሉዕ የሆነ ስለማይመስለውና ሰው መሆኑ ለማረጋገጥ ሲል ሰብዓዊ መብቱ የሚሟላበትን መንገድ ሊፈልግ ይገኛል።

2.የሰብዓዊ መብቶች ባሕሪያት
ስለ ሰብዓዊ መብቶች እጅግ ብዙ ሃይማኖታዊና ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ትንታኔዎችና ዕውቀቶች ያሉ ሲሆን የሁሉም ድምር ውጤትና ማጠናቀቂያ የሚያሳየው የሰብዓዊ መብቶችና የሰውን ልጅን የማይነጣጠል ዝምድና ነው። ሰብዓዊ መብቶችና ማክበር፣ በአንድ ሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሰው ልጅ በመደበኛነትም ሆነ መደበኛ ባልሆነ አኗኗር በሚገኝበት ቦታና ወቅት ሁሉ በግለሰቦች፣ በቡድኖች፣ በኅብረተሰብ፣ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን መልካምና መልካም ያልሆኑ ግንኙነቶች የሚወስኑ ማለትም አሉታዊ ውጥረቶችንና ግጭቶችን የሚቀንሱ፣ አዎንታዊ ግንኙነቶችን የሚያፀኑ ቁልፍ መብቶች መሆናቸውን ነው። የሰው አመጣጥን የሚያፋልስ ብዙ ተባዙ የሚለው የአምላክ ቃል የሚቃወም ላይ አይደለም።

ወደ ቅዱስ መጽሐፍ ስንመጣ የእስራኤል ንጉሥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ከመላዕክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፣ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፤ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ ባውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሶች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ። አቤቱ ጌታችን፣ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ የተመሰገነ ነውይላል። (መዝ 8÷4-8)

ዳዊት በመዝሙሩ ታስበው ዘንድ ሰውምንድን ነው? ማለቱ ፈጣሪ ከእጆቹ ሥራ መካከል ሰው ለተባለው ፍጡር የሰጠውን ስፍራ በማሰብ የጠየቀው ጥያቄ ነው። ሰው ምንድን ነው? ጥያቄው የሰውን ማንነት? በተለይም በፍጥረት መካከል ያለውን እሴት የሚያመለክት ጥያቄ ነው። ከፊሉን ጥያቄ በጠየቁበት መንፈስ ሆኖ ራሱ ዘማሪው ሲመልስ በክብር በምስጋና የታጀበ፣ በሁሉ ላይ ሥልጣን የተሰጠው፣ በፈጣሪ ሥራ ሁሉ ላይ የተሾመ፣ ሁሉን የሚገዛ አደረግኸው፣ በማለት መልሶታል።

በርካታ የታሪክ፣ የሕግና የማኅበረሰብ ጥናት መረጃዎች የሰብዓዊ መብት ታሪክን ሲናገሩ፣የሰብዓዊ መብት ታሪክ አዋቂዎች በኅብረተሰብ ስልጣኔ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን አስመልክቶ የተነሱ ፅንሰ ሃሳቦችና እንቅስቃሴዎችን ታሪካዊ ሂደት ለማሳየት መነሻ የሚያደርጉት ከጥንት ጀምሮ በሰው ልጅ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ ጥንታውያን ሃይማኖቶችን እና ጥንታዊ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ነው

ይህ ማለት በጥንታዊ ሃይማኖቶች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ፅንሰ ሃሳብ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ነው። ስለዚህ ስለ ሰብዓዊ መብት መፅሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጌ ለመናገር መሞከሬ ትክክለኛ ነገር ነው ማለት ነው። ለምሳሌ በአይሁድና በክርስትና አመለካከት ሰውን ሰው የሚያደርገው እና የሰው የማንነቱ እሴት በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ ፍጡር ከመሆኑ ጋር የተቆራኘ ነው። አስቀድሜ እንደገለፅኩት በእኔ እምነት እግኢአብሔር ለሰው የሰጠውን ቦታ የምንመለከትበት ሌላው ትልቁ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ማስረጃ እግኢዘብሔር ሰውን ሁሉ ያድን ዘንድ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምድር በመላኩ ነው። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ እኛን ያዳነበትን ጥበብ ስናይ ለሰው ልጅ የተሰጠውን ትልቅ ክብር እንገነዘባለን።

ቀደም ሲል በሰብዓዊ መብትና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ግንኑነት ለመግለፅ እንደጠቀስኩት እግዚአብሔር ለኖህ በሰጠው ትእዛዝ ውስጥ ሰው ሰውን እንዳይገድል የቀረበው ብቸኛ ምክንያት ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮአልና የሚል ነው። ቃሉነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ ከሰውም ልጅ፣ ከሰው ወንድም እጅ፣ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልናይላል። ዘፍ. 9÷5-6 ለሙሴ በተሰጡት አስርቱ ትእዛዛት ውስጥም እግዚአብሔርን መውደድና ባልንጀራን መውደድ አልተነጣጠሉም። ከዚህ ኀሳብ ውስጥ ሁለት ነገሮችን ማንሳት ይገባል። እነዚህም እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

መፅሐፍ ቅዱሳዊውና ትክክለኛው የሰብዓዊ መብት ፅንሰ ሃሳብ የሚጀምረው ሰው በራሱ መነሳሳትና ፍላጎት ተስማምቶ ከሰጠው ትርጉም ሳይሆን ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ከፈጠረው ከእግዚአብሔር ነው። ይህ ማለት ለሰው ሕይወት በእግዚአብሔር አምሳል የመፈጠሩን ዕሴት የሚመጥን ክብር ለመስጠት በመጀመሪያ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር መስጠት ይጠይቃል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሰው የሚገባውን መብት በመከልከል ብቻ የሚገለፅ አይደለም። ሰው የሰውነት ክብሩን የሚቀንሱ ነገሮችን መብትን በመጠበቅ ስም ሲያደርግ ሊታይ ይችላል። በሌላ አባባል ሰዎች በሚከለከሉት በሚነፈጉት መሠረታዊ መብቶች አማካኝነት ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን መልክ የተሸከመውን የሰብዕና ክብራቸውን የማይመጥኑ ግብረ ሰዶማዊነትን በነፃነት ስም መፍቀድ የሰውን ስብዕና ሊጣስ ከሚችልበት መንገድ ሌላኛው ነው ማለት ነው። ምናልባት እንዲህ አይነቱ ነገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ብሎ ለማሰብ የሚከብደው ሰው ቢኖር የሰውን ሰብዓዊ መብት ማክበር ነው ብሎ ለማለት ግን አስቸጋሪ መሆኑ ግን አያከራክርም።

በዚሁ አመለካከት ስንራመድ የሰብዓዊ መብት እና የሰው ስብዕና ክብር ተነጣጥሎ የማይታይ ነገር አለመሆኑን መረዳት እንችላለን። ከመጽሐፍ ቅዱስ የጠቀስኩትን ሰው ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ስናስበው ብዙ ነገሮችን ያሳየናል። ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስም በጣም አስፈላጊ ነው። ምናልባት መብታቸው ነው ለሚሉ ሰዎች የቤተሰብ ኃላፊነት የማይሰማቸው ካልሆኑ በቀር በራሳቸው የቅርብ ቤተሰብ ቢከሰት ምን ይሉ ይሆን?

3.የሰብዕና እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት
የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉ ሰው የእግዚአብሔር መልክ ተሸካሚ ለሆነው ለሰው ስብዕና ሊሰጠው የሚገባውን ዋጋ ባለ መስጠት የሚፈጠር ችግር ነው። የሰውን ማንነት ትርጉም ምን እንደሆነ ሳይገባን፣ የሰው ስብዕና ምን ያህል ክብር እና ዋጋ እንዳለው ሳንረዳ የሰውን ሰብዓዊ መብት መጠበቅ አይቻልም። ከእያንዳንዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጀርባ ለሰው የተሰጠ የተሳሳተ ግምትና ትርጉም አለ። ወደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወስዱ ጥቂት የተሳሳቱ መለኪያዎች አሉ። እነርሱም፡-
1.     የሰውን ልጅ ዋጋ በአካላዊ ተፈጥሮውና ይዘቱ እና ብቃቱ ሲለካ ወደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊወስደው ይችላል። ለምሳሌ በልጅና በአዋቂ፣ በወንድና በሴት፣ በወጣትና በሽማግሌ፣ በጤነኛ እና በአካል ጉዳተኛ፣ በነጭና በጥቁር መካከል የመብት ልዩነት ማድረግ የሰው የማንነቱ መገመቻ በአካላዊ ይዘቱ እና በቀለሙ ብቻ አንፃር ሲለካ የሚፈጠር ችግር ነው።
2.      የሰው የስብዕናው ዋጋ ባለው ቁሳቁስ እና በዚያም ለኅብረተሰቡ በሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ብቻ ሲለካ ወደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊወስደን ይችላል። በድሃ እና በሃብታም፣ በሠራተኞች እና በጡረተኛ፣ በባለሥልጣንና ሥልጣ በሌለው፣ መካከል የመብት ልዩነት ማድረግ የሰው የማንነት ዋጋ ባለው ቁሳዊ ሁኔታ እና በኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ሲለካ የሚፈጠር ችግር ነው። ይህ የመብት ጥሰት እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዝቅ አድርጎ በመመልከት አኳያ ሊገለፅ ይችላል። ለምሳሌ ጡረተኛ ሽማግሌና አረጋውያን በታክስ ከፋዩ ኅብረተሰብ እንደ ሸክም ሲቆጠሩ፣ የስብዕናቸው ዋጋ በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠሩ ፍጡራን በመሆናቸው አንጻር አለመለካቱን ያስረዳል።
3.      የሰው በአእምሮው እውቀት ብቻ ሲለካ ወደ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊወስደን ይችላል። ይህ ዓይነቱ መመዘኛ ምን ህል ወደሆነ የሰብዓዊ መብጥ ጥሰት ሊወስደን እንደሚችል ማየት በጣም ተገቢ ነው።


ከዚህ በመነሳት አንድ ሃሳብ ማንሳት ይቻላል። ሰው ምንድንነው? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ሳይገኝ፣ የሰው ስብዕና በምን እንደሚለካ ሳይታወቅ ሰብዓዊ መብትን መጠበቅ አይቻልም። የሰብዓዊ መብትን ምንነት በሚገባ ሳይታወቅ ሁሉን ነገር ከሰብዓዊ መብት ጋር በማገናኘት በማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ደሕንነት ጠንቅ የሆኑ የግብረ ሰዶም ፈፃሚዎችን መብታቸው ነው ለሚሉ መሞከር ትልቅ ጉዳት ነው። በማኅበረሰባችን ውስጥ መረን የለቀቀ የኑሮ ባሕር እንዲሰለጥን በር ይከፍታል። እንግዲህ ስለ ሰብዓዊ መብት መፅሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት እንዲህ ካየን ሰብዓዊ መብትን ከሰዶማዊነት ጋር ለማዛመድ መሞከር ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ደግሞ እንደሚከተለው ማየቱ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

4. ተፈጥሮአዊ፣ የግንኙነት ሕግጋትን ስለመጣስ፣
በመጀመሪያ ሰዶማዊነት ከሰው ተፈጥሮአዊ ጠባይ የወጣ ተግባር ነው። እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ መፍጠሩን አስቀድሞ ነግሮናል (ዘፍ.1÷26) “ለአዳም ሴትን እንፍጠርለትብሎ ወንድን ለሴት ሴትን ለወንድ መፍጠሩን ተናግሯል። ስለዚህ ሰዶማዊ መፈላለግ ፍፁም ከሰው ተፈጥሮ ጋር የማይሔድ ነው። በዚህ የምንረዳው በሶዶማዊነት የሚደረግ ማንኛውም ተግባር ፍሬ አልባ፣ ራስን የማይተካ ከፈጣሪ የተሰጠ ዘርን የመተካት ቡራኬ የተለየ፣ ፈጣሪ ሰውን ብቻ ሳይሆን መላውን ፍጥረት ወንድና ሴት አድርጎ የፈጠረበትን አንደኛውን ምስጢርና ጥበብ ማንቋሸሽ ብቻ ሳይሆን ሰው በገዛ እጁ በሰብዓዊ ክብርና በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራው እኩይ ተግባርን ያመለክታል።

ከሰብዓዊ ክብር አጠባበቅ አንጻር ግብረ ሰዶማዊነት በሰብዓዊ ክብር ላይ የሚደረግ ልዩ ግንኙነት ባሕር ሚሆን ርኩሰትም አለው። በሰብዓዊ መብት አንጻር ደግሞ የዚህን የተከበረ የህጎችና የሁሉም ፍትሐዊ አስተዳደሮች መሠረት የሆነውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው ግብረ ሰዶማዊነት ተፈጥሯዊና ይባስ ብሎም የሰብዓዊ መብትና የፆታ ግንኙነት ምርጫ መብት ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ አለ። ነገር ግን አስቀድመን እንደገለፅነው ሰብዓዊ መብት በምርጫ የሚደረግ፣ ጉዳይ አይደለም። ከመደበኛውና ተፈጥሯአዊ ከሆነው የሰው ልጅ ፍላጎት የወጣ ተፈጥሮን ራሷን እና የማህበረሰብ መብትና የሰው ዘር አመጣጥን የሚጋፋ ነው። በማንኛውም ሕግ ፆታ የሰዎች ምርጫ ሊሆን አይችልም። ፆታ ሰው ከፈጣሪው የሚገኘው ስጦታ ነው። ወንድነት ወይም ሴትነት የሰው ሥራዎች አይደሉም፣ እነዚህን የሰው ተፈጥሯዊ ስጦታዎችን አለማክበር ሰብዓዊ መብትን አለማክበር ነው። ይህን ለብቻው ማፍረስ የማይነጣጠሉ፣ መሠረታዊ፣ ተፈጥሯዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን መታስ ነው። በአንፃሩ ይህንን በመጣስ ሰብዓዊ መብትን አክብረናል የምንል ከሆነ ለሰብዓዊ መብት የሰጠነው ትርጉም ፍፁም የተሳሳተ ነው።

የዩጋንዳ መንግስት የጸረ ግብረ ሰዶም ሕጉ ለፓርላማ ሲቀርብና ፕሬዝዳንቱ ለፊርማ ሲዘጋጁ ምክንያታቸውን እንዲህ በማለት ገልጸዋል።ይህንን ውሳኔ የወሰንኩት በህክምና ባለሙያዎች ምክር ነው። እኔ ግብረ ሰዶማዊነት በተፈጥሮ የሚመጣ ክስተት ወይም ሰው ሲወለድ ያለፈቃዱ የሚያገኘው ከሆነ የሞት ፍርድም ቅጣትም ስለማያስፈልግ ይህንን ለማረጋገጥ የህክምና ባለሙያዎችን በይፋ ጠይቄአለሁ። እነሱም ግብረ ሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ አለመሆኑንና ልማዳዊ ድርጊት ወይም በሰዎች የግል ፍላጎት የሚመጣ ማኅበራዊ ቀውስ መሆኑን አረጋግጠውልኛል። ከመፈረሙ ጥቂት ቀናት በፊትም ስለጉዳዩ አሁንም የህክምና ወይም ሳይንሳዊ ማብራሪያ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። በዚህም ፍላጎታቸው የአሜሪካን ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ ሁኔታውን አረጋግጠው እንዲገልጹላቸው በይፋ ጠይቀዋል። በመጨረሻም በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋገጠ መረጃ መሠረት ግብረ ሰዶማዊነት የተፈጥሮ ስጦታ አለመሆኑን ስላረጋገጥኩ ፀረ ግብረሰዶማዊ ሕጉ እንዲፀድቅ አድርጌአለሁበማለት በፌብሩዋሪ 24 ቀን 2014 . በይፋ ፈርመዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ይህ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕግ ከዩጋንዳ የሕገ መንግሥት ሸንጎ ጀምሮ፣ እንደ አምነስቲ ኢንተርሽናል ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮችን ጨምሮ ተቃውሞ ገጥሞታል። ታላቅ መሪዎች በሕጉ ውስጥ የሞት ፍርድ መኖሩን የተቃወሙት የሕግ ክፍተት እንዳይፈጠር፣ አንዳንድ ሰዎች የጠሉትን ወይም በክፋት ሊወንጅሏቸው የፈለጓቸውን ሰዎች ግብረሰዶማዊ ፈፃሚ ነው በማለት አላስፈላጊ አሉባልታና ክፉ አደጋ እንዳይዳርጓቸው፣ በስም ማጥፋትና ሐሰተኛ ውንጀላዎች ንጹሀን ዜጎች ለእንግልት እንዳይዳረጉ በመስጋት ነው። ስለዚህ በጥላቻ የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ በአንጻሩ ወንጀሎች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከሚገኙ ሀገራት ውስጥ 80 በላይ በሚሆኑ የመንግሥታት ሕግጋት ውስጥ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕግጋት ተካተዋል።
            አባ ሳሙኤል (ሊቀ ጳጳስ)
      የቅዱስ ሰኖዶስ አባልና
            የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ
Source :-ሰንደቅ ጋዜጣ
 

1 comment:

  1. kalune yemiyasetemer yemigesete abate ayasatane ye agelegelute edemaiwen yabezalen

    ReplyDelete