Monday, December 30, 2013

ፓትርያርኩ ስለ እምነታቸው የከፈሉት ዋጋ



(አንድ አድርገን ታህሣሥ 21 2006 ዓ.ም)፡- ኢትዮጵያ ብዙ መከራዎችን አሳልፋለች ፤ ብዙዎቹ መከራዎች ከውጭ ወራሪዎች ቢደረሱም ከውስጥ ሀይሎችም ከደረሰው ጥቃት ያልተናነሰ መከራ በቤተክርስትያንና በሀገር  ላይ ብዙ መከራ ደርሷል ፤ ይህች ቤተክርስቲያን ከዘመነ አክሱም ጀምሮ አሁን እስካለንበት የኢህአዴግ ዘመን ድረስ ብዙ መንግስታትን አሳልፋለች ፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ነገስታት ለቤተክርስትያን እና ለህዝበ ክርስትያን በርካታ መልካም ተግባሮችን አከናውነው ወደማይቀረው አለም አልፈዋል ፤ ስማቸውም በየዘመኑ በመልካም እየተጠራ ትውልድም የሚዘክራቸው እስከ አሁን ድረስ አሉ ፤ ሌሎች ደግሞ የምትጠፋ መስሏቸው ጦር መዘውባታል ፤ በዘመናቸው ቤተክርስትያኒቷን ለማፍረስ ድንጋይ  አንስተውባታል ፤ አሳት ለኩሰውባታል ፤ ጦር መዘውባታል ፤ እርሷ ግን የመጣውን መከራ ተቋቁማ እጃቸውን ያነሱባትን ወደ ኋላ ትታ አሁን እኛ ትውልድ ላይ ደርሳለች፡፡

በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እውነተኛ ጠበቃ የሆኑ አባቶች ላይ ጫና ሲፈጥር ኖሯል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ከደርግ አምባገነናዊ ከሆነው ስርዓት እስከ አሁኑ ጊዜ ድረስ ከመንግሥት ተጽህኖ ስር ወጥታለች የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ዘወትር መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚሰማውና የሚታየው ነገር የቤተክርስቲያኒቱን ሕልውና የሚያናጋ ክብሯንም የሚቀንስ ነገር እየሆነ መጥቷል ፡፡ በ2001 ዓ.ም በጥቂት ጥቁር ለባሾች ብጹአን አባቶች ላይ በውድቅት ለሊት ሊደረግ የታሰበው ድብደባ እና የአባቶችን ማረፊያ መግቢያ በር በጥቁር ለባሾች የተሰበረው ድርጊት ተደባብሶ ማለፉ ከጀርባው ማን እንዳለ ለማወቅ የስለላ ምሁር መሆን አያስፈልገውም፡፡ አሁንም እየተሰማ ያለው ነገር ደርግ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት  በሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የደረሰውን ነገር እንድናስታውስ ግድ ይለናል፡፡ ብጹዕነታቸው ስለ ቤተክርስቲያን በነበራቸው አቋም ምክንያት በግፈኞች ሕይወታቸውን በግፍ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡ አባቶቻችን ለዚች ቤተክርስቲያን የከፈሉትን ዋጋ ማወቅ በየዘመኑ እግዚአብሔር በጎቹን እንዲጠብቁ ለመረጣቸው አባቶች ቤተክርስቲያኒቱ በምን አይነት ዋጋ ከእነርሱ ትውልድ እንደደረሰች ትልቅ ትምህርት ይሰጣቸዋል ብለን እናምናለን፡፡

አወይ ጊዜ አወይ ጊዜ
ጊዜ ነቃሽ ፤ጊዜ ወቃሽ
መንገደኛ ሁሉን ታጋሽ


 አባታችን ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከደርግ መንግሥት የደረሰባቸው ፈተና እና ስለ ከፈሉትን ዋጋ ለትውልዱ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው ብለን ስላመንን አቅርበነዋል፡፡
 
ኢትዮጵያውያን አብዮትን የምናወቀው በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሳይሆን በውስጡ አልፈን በቃጠሎው ተገርፈን ወላፈኑን ቀምሰን ነው፡፡ በዛን ወቅት የነበረው የሶሻሊስት ርዕዮት አለም አብዮታዊነትን እንደ ታላቅ ነገር ሲሰብክ የነበረ በመሆኑ ብዙ ወጣቶች አብዮተኛ ተብለው ሀገሪቱንም አብዮታዊት ኢትዮጵያ አስብለዋታል፡፡ በዚህች ተአምረኛ ሃገር አብዮታውያን ወንድሞቻችን ጸረ አብዮተኛ የተባሉ ወንድሞችቻቸውንና እህቶቻቸውን ቅርጥፍ አድርገው በልተዋል፡፡ በዚያ ክፍለ ዘመን ‹‹አብዮት ልጆቿን›› ትበላለች በሚል ፈሊጥ ብዙዎች ወጣቶች ጸረ-አብዮት፤ ጸረ ህዝብ ተብለው አይሆኑ ሆነዋል..ጊዜው ጥቁር ጠባሳውን ጥሎ ያለፈው ሁሉም ላይ በመሆኑ የጊዜው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን 2ኛ ፓትርያልክ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የደረሰው በደል ግን ለየት ያደርገዋል፡፡

በዚያ ወቅት ደርግ ቤተክርስቲያኒቱ ጳጳስ እንዳትሾም ትእዛዝ አውጥቶ ነበር። በወቅቱ አቡነ ቴዎፍሎስ የደርግን ትእዛዝ ሽረው ሦስት ጳጳሳትን ሾሙ።ደርግም ትእዛዜን አልሰሙም ብሎ ፓትሪያርኩንና ሦስቱን ተሿሚ ጳጳሳት እስር ቤት ጨመራቸው። በወቅቱ የተሾሙት ጳጳሳት አቡነ ባስልዮስ፤አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ጳውሎስ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ሦስቱ ጳጳሳት ከእስር ሲፈቱ ፓትሪያሪኩ ብቻ በዚያው ቀሩ።

አቡነ ቴዎፍሎስ በእስር ቤት ደረሰባቸውን ፀዋትወ መከራ በዓይን ያዩ በታላቁ ቤተመንግስት አብረዋቸው ታስረው የቆዩ በአፄ /ስላሴ ዘመን በስልጣን ላይ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ የአይን ምስክሮች በተገኝው የቃል መረጃ መሰረት ቅዱስነታቸው መጀመሪያ የታሰሩት ለብቻቸው በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ነበር፡፡ በዚህ ቦታ ጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ ........

በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ አስገብተው እጃቸውንና እግራቸውን ከአልጋ ጋር ጠፍረው አሰሯቸው ፡፡ ቀንም ሆነ ማታ ለሽንት ሲወጡ ካልሆነ በስተቀር ሰንሰለቱ አይፈታላቸውም ነበር በዚህ አይነት ለአራት ቀናት እንዲሰቃዩ ከተደረገ በኋላ ባለስልጣኖች ታስረውበት ወደነበረው ቁጠር አንድ እስር ቤት ወሰዷቸው

ወቅቱ አብይ ፆም ነበር ከጎፋ ገብርኤል ተይዘው ከመጡበት ቀን ጀምሮ ለአርባ ቀናት ያህል እህል የሚባል ነገር አልቀመሱም ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጣታቸውን በውሀ ውስጥ በመንከር ከንፈራቸውን ከማርጠብ በስተቀር ጥም የሚቆርጥ ውሀ እንኳን አልጠጡም፡፡ ምግብ እንዲበሉ አንዳንድ ደርግ ባለስልጣናት እና አብረዋቸው ታስረው የነበሩ አዛውንቶች ለምነዋቸው ነበር ነገር ግን ለመብላት ፍቃደኛ አልነበሩም  እስከ ፋሲካ ማግስት ድረስ ምንም ሳይቀምሱ ቆይተዋል ፡፡ ለፋሲካ ማግስት ግን እስረኞች መካከል አረጋውያኑ አጥብቀውና አስጨንቀው ስለለመኗቸው እህል ሊበሉ ችለዋል፡፡


በወቅቱ ከነበሩ ሰዎች መረጃ መሰረት ደርግ አቡነ ቴዎፍሎስን በእስር ቤት ስቃይ ካሳዩአቸው ሰዎች መካከል አንድ ሻለቃ የፈፀመባቸው ግፍ ሳይፀቀስ አይታለፍም ፡፡ ይህ ሰው እርሳቸውን የማበሳጨት ተልዕኮ ስለነበረው በንቀትአባ መልአክቱ›› እያለ ይጠራቸው ነበር፡፡ ሞራልም የሚነካ አነጋገርም ይናገራቸው ነበር፡፡ ከወርቅ የተሰራ የእጅ መስቀላቸውን ቀምቶ እስከ መውሰድ ደርሶም ነበር፡፡ ከሚተኙበት ትንሽ ክፍል ውስጥ ሰቅለውት የነበረውን የጌታችን እና የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስዕልም በስልጣኑ አውርዶ ወስዶባቸዋል፡፡ የዚህ ሰው ድርጊት ከበስተኋላው የሚገፋፋው ጠላት እንዳለ ያመላት ነበር፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ የነበራቸው አነስተኛ ግላዊ ነፃነት እንኳን እስከዚህ ድረስ ተገፍፎ እንደነበር የሻለቃው ድርጊት ያሳያል፡፡

‹‹ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።›› የማቴዎስ ወንጌል 5፤ (11-12)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በብዙ ስቃይ እያዩ በእስር ቤት የቆዩት እስከ  ሐምሌ 7 1971 . ነበር፡፡ በዚህ ቀን እስረኛው እንዲሰበሰብ ታዞ ሲሰበሰብ አንድ ዘበኛ መጣና የሁለት እስረኞችንና የብፁዕነታቸውን ስም ጠርቶ ብርድ ልብሳቸውን እና የሽንት ቤት ወረቀታቸውን ይዘው እንዲወጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ክፍላቸው ገብተው አጭር ፀሎት ካደረጉ በኋላ ጥቁር ቀሚሳቸውን ለብሰው ነጠላ ጫማ አድርገው ቆባቸውን ደፍተውና ከእንጨት የተሰራ የእጅ መስቀላቸውን ይዘው እስረኞችን ካፅናኑ እና መስቀል ካሳለሙ በኋላ ‹‹ እግዚአብሔር ያስፈታችሁ›› በማለት ተሰናብተዋቸው ወጡ፡፡..

‹‹ጊዜው ክረምት ነበር አባታችን አቡነ ቴዎፍሎስ ተይዘው ወደ ራስ አስራት ካሳ ግቢ አዲስ አበባ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ተይዘው ሄዱ በወቅቱ የለበሱት ጥቁር የሐር ቀሚስ ጥቁር ነጠላ ጫማ ጥቁር የመነኩሴ ቆብ ነበር፡፡ እንደ ወትሮ በአንገታቸው ያጠለቁት ወይም በእጃቸው የያዙት መስቀል ግን አልነበረም ፡፡ በተጠቀሰው ግቢ ውስጥ ወዳለው ቤት እንዲገቡ ሲደረግ ከውስጥ የተደበቁ ኮማንዶዎች ባዘጋጁት ገመድ በድንገገት አንገታቸውን ሸምቀቅ አድርገው በማነቅ ገደሏቸው፡፡ወዲያውም አስከሬን የሚያነሱ ሌሎች ሰራተኞች አስከሬናቸውን አንስተው ከቤቱ ውጪ ባለው ግንብ ስር በስተ ምዕራብ በኩል በተቆፈረው እና በርካታ ሬሳ በተጣለበት ጉድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት››    (በጊዜው ከነበረ ወታደር የዓይን እማኝ የሰጠው ቃል)

ከዚህ በኋላ ቅዱስነታቸው የት እንደደረሱ ምን አይነት ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሳይታወቅ ለ13 ዓመት ተዳፍኖ ቆየ፡፡ ነገር ግን ‹‹ የማይገለጥ የተከደነ ፤ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም›› ማቴ 16፤26 እንደተባለው ጊዜ ሲደርስ በምን አኳኋን እንደሞቱና አስከሬናቸው የት ቦታ እንደተጣለ ሊታወቅ በመቻሉ በእንጦጦ አውራጃ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ከሚገኝው ከራስ አስራት ካሳ ግቢ አስከሬናቸው ተቆፍሮ ወጥቶ በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን በክብር አረፈ፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከአሜሪካ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ በቴዎሎጂ የክብር ዶክትሬት ድግሪ አግኝተዋል ፤  24 ሺህ ሰው በማሳመንና በማጥመቅ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አድርገዋል ፤ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማቋቋም እንደ አንድ መምህር ከክፍል እየገቡ በማስተማር ምሳሌነታቸውን አሳይተዋል ፤  የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ድርጅት መስርተዋል ፤  ቤተ ክርስቲያን ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር ጎን ለጎን መራመድ ትችል ዘንድ ሰባኪያን ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሰለጥኑባቸው የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትን በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ አድርገዋል ፤ አሜሪካ ከሚገኝው  ብሔራዊ የሰብአዊ ጥናቶች መርጃ ድርጅት  የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ በመጠየቅ የብራና መጻህፍት  የማይክሮ ፊልም ድርጅት አቋቁመዋል(አሁን በመንግስት የተወረሰ) ፤ የዘመን ጥርስ የበላቸው በርካታ  በሺህ የሚቆጠሩ የብራና መጻህፍት ጨርሰው ሳይጠፉ ከየገዳማቱና ከየአድባራቱ በማሰባሰብ በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አድርገዋል ፤ ቤተክርስቲያን በራሷ ገቢ የምትተዳደርበት የሰበካ ጉባኤ ሃሳብ በማቅረብ አደራጅተው  በቃለ አዋዲ እንዲመራ አድርገዋል ፤ የሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲቋቋም አድርገዋል ፡፡  አቡነ ቴዎፍሎስ በጠቅላላ ቤተክርስቲያን ያፈራቻቸው አለም አቀፋዊ ብቁ ዲፕሎማት መሆናቸውን ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡

ለብጹዕ አባታችን ለአቡነ ማቲያስ የአቡነ ቴዎፍሎስን ሥራ እና ምግባር እግዚአብሔር አብዝቶ ያድልልን፡፡ 
አሜን

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን



6 comments:

  1. Bereketachew Yedereben, Beabreham Ekif begenet Yasarefelen. Amen

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር ሆይ እንዲህ አይነት ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ አባት ስጠን አሜን።

    ReplyDelete
  3. I read that the current patriarch was arrested. Is that true?

    ReplyDelete
  4. ጌታ፣ ጌታ ሆይ! ለሐይማኖታቸው ጽናት ሴሉ ላለፎት አባት ነፍስ ይማር። ለብጹእነታቸው እንደቸርነትሕ አንተ ጠብቅ።

    ReplyDelete
  5. He holiness was a great father. He is now with saints in the heaven.

    ReplyDelete
  6. አሜን

    ዛሬስ ቤተክርስቲያን ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ ነች?
    የአባታችን የአቡነ ቴዎፍሎስ መስዋእትነት አሁን ሐይማኖታችን ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ እንድትወጣ አድርጓታል?
    ስለዚህ እያንዳንዳችን ቀሪ የቤት ስራ አለብን ማለት አይደል?

    ReplyDelete