Saturday, December 21, 2013

ቤተ ክርስቲያን ካሽ ሬጅስተር ልትጠቀም ነው

  • ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመጠየቅ ልማድ ሊኖራቸው ይገባል
  • ድብቅሙዳየምጽዋትማስቀመጥ፣በዣንጥላናበምንጣፍገንዘብመለመንይከለከላል

(አዲስ አድማስ ታኅሣሥ 12 2006 ዓ.ም)፡-  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽንን ለገቢ መሰብሰቢያነት ለመጠቀም  ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ተገለጸ፡፡  

ዘመኑን ያልዋጀውንና ጥራት  የጎደለውን፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ አሠራርና ቁጥጥር ችግር፤ ግልጽነት፣ ወጥነት፣ ተቀባይነትና ተጠያቂነት ባለው የፋይናንስ አያያዝ ሥርዐት ለመቅረፍና ለማድረቅ ያስችላል፤ በሚል በቀረበው የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ ላይ እንደተጠቀሰው÷ በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ ሕጋዊ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት የሚገባ ሲኾን ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስትር ማሽን እንደሚከናወን ተመልክቷል፡፡


የሀ/ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽን ተጠቃሚ መኾናቸው፣ በገቢ ሒሳብ አሠራርና ቁጥጥር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላል ተብሏል፡፡ በጥናቱ ላይ በመነሻነት ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል የዕለት ገቢዎችና ደረሰኝ አጠቃቀም ተጠቅሷል።  የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ ገቢ ሰነዶች በሕገ ወጥ መንገድ አሳትሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ለግል ገንዘብ ይሰበሰባል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተከለከለ ደረሰኝ ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ታይቷል፤ ከደረሰኙ /ለከፋዩ ከሚሰጠው/ የተለየ መጠን በቀሪው ላይ መጻፍና የግል ጥቅምን ማካበት ይዘወተራል፤ ዘወትርና በክብረ በዓላት በርካታ ገንዘብ ገቢ ቢኾንም በዕለቱ ወደ ባንክ ያለማስገባት ኹኔታ አለ፤ ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመቀበል ልማድ የሌላቸው መኾኑን እንደክፍተት በመጠቀም፣ ለቤተ ክርስቲያን የመጣው ገንዘብ ‹‹በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛል›› በሥራ ላይ ያልዋሉ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሰነዶች (ሞዴላሞዴሎች ሴሪ ንምራ ቁጥር) መሠረታዊ ችግር ተጠንቶ መፍትሔ አልተሰጠም፡፡

በንግሥ፣ በወርኃዊ በዓላትና በዕለተ ሰንበት በሙዳየ ምጽዋት ሳይኾን በተዘረጋ ጨርቅ ላይ የሚሰበሰብ ገንዘብ መኖሩን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ በዚህ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ /ስብከቱ በታኅሣሥ፣ 2003 .. ባስተላለፈው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ የሥራ መመሪያ መሠረት/ የምእመናንና ካህናት ሰበካ ጉባኤ ተወካዮች በሙሉ በተገኙበት ቆጠራ የማይካሄድበትና በተወሰነ መልኩም ሙሉ ገንዘቡ ገቢ የማይደረግበት ኹኔታ በመኖሩ አሠራሩ ለብኩንነት፣ ሐሜትና አሉባልታ መጋለጡን አመልክቷል፡፡ በንግሥ በዓላት ወቅት ጥላ ዘቅዝቀው የሚለምኑ ሰዎች ኹሉም ስለማይታወቁ የተኣማኒነት ችግር አለ፡፡ በስእለትና በሙዳየ ምጽዋት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የውጭ ሀገር ገንዘቦች፣ በመመሪያው መሠረት በዕለቱ የባንክ ምንዛሬ ወደ ብር እየተቀየሩ በተገቢው መንገድ ገቢ አለመኾናቸው፣ በምትኩ ቅያሬው ወጥነት ያለውና ለብኩንነት የተጋለጠ እንደኾነም ተገልጿል፡፡

በቃለ ዐዋዲ ድንጋጌው የተመለከተውንና በዝርዝር የሥራ መመሪያ የተላለፈውን የገቢ አሰባሰብ በተሻለ አሠራር ያጠናክራል የተባለው በፖሊሲና መመሪያ ረቂቁ የሒሳብ ሰነዶች አያያዝ፣ ምዝገባና አወጋገድ መሠረት÷ ለሒሳብ ሥራ የሚያገለግሉ ደረሰኞችና ቫውቸሮች የዋና ተጠቃሚውን ተቋም ስም ይዘው፣ በሀገረ ስብከቱ ምስጢራዊ ኮድ ይታተማሉ፤ የማሳተም ሓላፊነቱም የሀገረ ስብከቱ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍል ሲኾን ይህም በዋና ሥራ አስኪያጁ ፈቃጅነት የሚከናወን ይኾናል፡፡ \

በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ሕጋዊ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት ይገባል፤ ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስተር ማሽን ተፈጻሚ ይኾናል፤ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ከገንዘብ ሰብሳቢ ውጭ መያዝና መጠቀም አይቻልም። ማንኛውም የገንዘብ ስጦታ በገንዘብ ያዡ በኩል መሰጠት ይኖርበታል፤ ስጦታው እንደተበረከተም ወዲያውኑ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሊቆረጥለት ይገባል፡፡ በዐይነት የሚሰጥ ስጦታ በግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይመዘገባል፡፡ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውጭ በሙዳየ ምጽዋት ሣጥን ገንዘብ መሰብሰብ አይቻልም፤ ቋሚ ሙዳየ ምጽዋት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የሚቀመጥበት ቦታ ተጠንቶ፣ በሰበካ ጉባኤው መጽድቅ አለበት፤ ለቆጠራ ካልኾነ በቀር ከተቀመጠበት ማንቀሳቀስ አይቻልም፤ በትከሻና ተይዘው የሚዞሩ ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች ሙሉ መረጃ ተመዝግቦ ይያዛል፡፡ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ሣጥኖቹ ከመከፈታቸው በፊት ሁሉም ቆጣሪዎች የቁልፍ ካዝናውና የቁልፍ ሣጥኖች፣ የሣጥኖቹን ብዛትና እሽጋቸው አለመከፈቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ የተቆጠረ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወዲያውኑ ካልተቻለ ከሌላ ገንዘብ ጋራ ሳይቀላቀል በበነጋው ወደ ባንክ አካውንት መግባት አለበት፤ ዣንጥላን፣ ምንጣፍንና የመሳሰሉትን በመጠቀም ገንዘብ መሰብሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ይኾናል፡፡ዘመናዊው የፋይናንስ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲኾንም በተጭበረበሩ ደረሰኞችና በማይታወቁ የገንዘብ አሰባሰቦች የግል ጥቅምን ማካበት በመከላከል ለክትትልና ቁጥጥር አመች ለማድረግ እንደሚያበቃ ተመልክቷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ /ቤት፣ በልማትና በጎ አድራጎት ተቋማቱ እንዲሁም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚዘጋጁ የፋይናንስ ሪፖርቶች ግልጽነት፣ ወቅታዊነትና ተኣማኒነት/ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ሀገረ ስብከቱ በሚሰበሰበው የኻያ በመቶ ፈሰስና ከአብያተ ክርስቲያናቱ በቅጽ ተሞልቶ በሚላከው ሒሳብ መካከል በየዓመቱ የሚያጋጥመውን ልዩነት ለማስወገድ እንደሚያስችል ተገልጧል፡፡

ይህም በሒደት ከፍተኛ የሀብት ክምችት የሚገኝበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስ አሠራሩና መልካም አስተዳደሩ የሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል በመኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ማእከላዊ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ይኖራት ዘንድ መሠረት ለመጣል፣ የካህናቷን ኑሮ በማሳደግና በማሻሻል ሐዋርያ ተልእኮዋን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም የምትፈጥርበት መሠረት ለመጣል እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡

2 comments:

  1. ግረም ጥናት ነው ። ለአባቶቾ ልቦና ይስጥልን።

    ReplyDelete