Thursday, October 17, 2013

እነ ‹‹ጀማነሽ› ጭፍራዎቻቸውን በገዳማት ማሰማራት ጀምረዋል


(አንድ አድርገን ጥቅምት 8 2006 ዓ.ም)፡- ከሶስት ዓመት በፊት በአራት ኪሎ ከስላሴ ጀርባ የመሽገው ‹ማህበረ ስላሴ ዘ ደቂቀ ኤልያስ› በመባል የሚታወቀው ማኅበር ምዕመኑን በተለያየ የተሳሳተ አስምህሮዎች በማጥመድ ስራቸውን ሲሰሩ የነበሩት የ‹‹ተዋህዶ ክርስቲያን›› ነን ባዮች በአሁኑ ሰዓት ለጭፍራዎቻቸው የ‹‹ተዋህዶ ክርስቲያን›› እምነት ተከታይና ሰባኪ መሆናቸውን የሚገልጽ መታወቂያ በመስጠት ፤ የሚያስፈልጉ ውሎ አበል እና የተለያዩ ወጪዎችን በመሸፈን ወደ ተለያዩ ገዳማት እያሰረጉና እያስገቡ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ 


አንድ ልጅ እግር እድሜው ሃያዎቹ መጨረሻ የሚገኝ ወጣት ከደብረብርሃን 5 ኪሎ ሜትር አለፍ ብላ የምትገኝው በሳሪያ ቀበሌ ውስጥ ከምትገኝው ኩክ የለሽ ማርያም ገዳም ‹‹ከዋልድባ ገዳም ተልኬ ነው የመጣሁት›› የሚል ምክንያት በማቅረብ ከመስከረም 25 እስከ መስከረም 30 ገዳሙን ለመሳለም እና በገዳሙ ውስጥ የሚገኝውን ጸበል ለመጠመቅ በሄዱት ሰዎች መሃል በመግባት ለበርካታ ቀናት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ሰባኪ በመምሰል ታጥቆ የመጣውን የክህደትና የተረፈ አይሁዳውያን ትምህርት ሲያስተምር ተይዟል፡፡ ከትምህርቱም መካከል ‹ትውልድ አልቋል› ፤ ‹8 ሺ ደርሷል› ፤ ‹ሰንበትና ነቢያት ይከበሩ› ፤ ‹ስለ ሰንበተ አይሁድ› ፤ ‹ትውልድ ሊቀጠፍ ነው› ፤ ‹ኤልያስ ወደ ምድር ወርዷል›  የሚሉ ነበሩ፡፡ የዚህን ሰው ትምህርትን ቀድሞ ከተለያዩ ድረ ገጾች ፤ ከመፅሄት ፤ ከጋዜጣ እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሁን የሚያውቁ ወጣቶች ከባሰና ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር ከእኩይ ተግባሩ ከማገድ በተጨማሪ በእጁ የያዘውን ቦርሳ እና የተለያዩ መገልገያ መሳሪያዎች ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ለተጨማሪ የፖሊስ ጥያቄ ወህኒ ቤት እንዲያርፍ አድገውታል፡፡ ፖሊስም ባደረገው ማጣራት በእጅ በሚያዝ ቦርሳው ውስጥ ቀስተደመና ያለው ከዳዊት ኮከብ ጋር የተዋሀደ ነጭ ልብስ ፤ የዳዊት ኮከብ መሠረቱ የሆነ ትእምርተ መስቀል ፤ ለምዕመኑ ሊበተኑ የተዘጋጁ በርካታ በራሪ ወረቀቶች ፤ ስለ ‹ኦርቶዶክስ› ሳይሆን ስለ ‹ተዋህዶ ክርስቲያን› የሚገልጹ ጽሁፎች ፤ ‹ተዋህዶ ክርስቲያን› የሚል መታወቂያ እና ተጨማሪ ለዓላማው መሳካት ሊጠቀምባቸው ያስታጠቁትን ነገሮች ተገኝተዋል፡፡

ይህ አዲስ መጤ ተለጣፊ እምነት ስር እንደሰደደ ለማወቅ ፖሊስ ዘንድ የሚገኝውን የዚህን ሰው መታወቂያ ማየት ብቻ በቂ ይመስለናል ፡፡ የዚህ ሰው የመታወቂያ ስም  አበበ ነጋሽ ሙሜ ፤ እድሜ 27 ፤ የትምህርት ደረጃ 10ኛ የሚል ሲሆን  ሃይማኖት  የሚለው ቦታ ላይ ‹ተዋህዶ ክርስቲያን› የሚል ጽሁፍ ሰፍሮበት ተገኝቷል ፡፡ የትውልድ ቦታው አበችኛ ወረዳ ጃርሶ ቀበሌ ሲል በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10 እንደሚኖር ከኪሱ የተገኝው መታወቂያ ይገልጻል፡፡ 

ፖሊስ እና ወጣቶቹ ባደረጉት ትብብር ወጣት አበበ ነጋሽ ላይ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ‹‹የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ሳለ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስያን ገዳም ስብከት በማከናወንና የሃይማኖት ተከታዮች ውስጥ ሁከት በማነሳሳት›› የሚል ክስ ቀርቦበት ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ለፍርድ ቤቱም የእምነት ክህደት ቃሉን ተቀብሎታል፡፡  ተከሳሽም ወደዚህ ኩክ የለሽ ማርያም ገዳም እና ወደ ተለያዩ ገዳሞች የተላኩት በአባቶች እንደሆነ ፤ እምነቱ ጎጃም ላይ የተስፋፋ መሆኑን ፤የተላከበት አላማ ለአባቶች የታያቸውን የኤልያስን መውረድ የጊዜውን መድረስ ለማስተማር መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ቃሉን ሰጥቷል ፤ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለማየት ለቀጣይ ሳምንት ቀጠሮ ሰጥቶታል፡፡

በሀገራችን ሕግ መሰረት አንድ እምነት ለማቋቋም የእምነቱ ተከታይ ብዛት ፤ የአምልኮ ቦታ ፤ የእምነቱ ስም እና ተያያዥ ነገሮች አመልካቾች ለሚመለከተው የመንግስት አካል ካቀረቡ በኋላ የቀረበው ጥያቄ ከተቀመጠው ሕግ ጋር በማመሳከር አነስተኛ መስፈርቱን ካሟሉ እንደ እምነት ተቋም እንደሚመዘገብ ይታወቃል፡፡ አሁን ግን እነዚህ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጋር ተጣብቀው ራሳቸውን ‹ተዋህዶ ክርስትያን› በማለት የሚጠሩት አካላት ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ‹ተዋህዶ ክርስቲያን› የሚል እምነት ለማቋቋም ጥያቄ ሳያቀርቡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ጋር በመጣበቅ በአንድም በሌላም መንገድ ጉዳት እያደረሱ ፤ ምዕመኑን ወዳልተፈለገ ውዝግብ ውስጥ እየከተቱት ይገኛሉ ፡፡ ቡድኑ  ወደ አይሁዳዊነት ያዘነበለ አስተምህሮ ይዞ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል አንዱን አንሥቶ ሌላውን ለመጣል የሚሞክር አፍራሽ አካሔድም የያዘ ጭምርነው፡፡ ከዚህ በፊት ያነሱት አቧራ አልበቃ ብሏቸው አሁን ደግሞ ወደ ገዳማት ጭፍራዎቻቸውን በራሪ ወረቀቶች እና የክህደት ትምህርቶችን በመሙላት ውሃውን ከምንጩ ሊያደፈርሱ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ሲጀመር አቧራው ሲነሳ ከወራት በፊት የተነሱበትን አላማ በማየት ማኅበራትና ሰባኪ ወንጌላውያን በብሎግ ፤ በመጽሄት ፤ በሲዲና በአውደ ምህረት ላይ መልስ ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ አሁን ግን መልስ መስጠት እነኚህ ሰዎች ከጥፋት አላማቸው ሊመልሳቸው ስለማይችል ምዕመኑ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ላይ በግልጽም ይሁን በስውር ለሚሰሩት ስራ በመከታተል እንደ ደብረ ብርሃን ወጣቶች  በማጋለጥ ለፍትህ አካላት አሳልፎ በመስጠት ፤ ለሃይማኖት ብረዛ ተግባራቸውም ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ህዝቡም ከዚህ ተነስቶ እንዲማር ማድረግ መቻል አለበት እንላለን፡፡


‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን››

3 comments:

  1. The Angry Ethiopian/ቆሽቱ የበገነውOctober 17, 2013 at 11:58 PM

    Why don't these people go to catholic, pentae, jehova witness and muslim worshiping places and preach them ? What is the need for everybody to give attention to the Ethiopian Orthodox Tewahido bet Kirstian ? Why don't all of these sects preach each other, rather than targeting our Church ?
    The answer is clear - to control Ethiopia, the church has to be destroyed. To make Amara clueless, the church has to be destroyed.

    ReplyDelete
  2. it is good information

    ReplyDelete