Monday, October 7, 2013

‹‹አክራሪነት የቤተክርስቲያኒቱ ዓላማና ተልዕኮ አይደለም›› አባ ኃ/ማርያም መለሠ(ዶ/ር)

  • ቤተክርስቲያኗ ቅንጣት ያህል ከሰላም ውጪ ተናግራ አታውቅም ፡፡
  • በክርስትና ‹‹አክራሪነት አለ›› የሚባለው ነገር ያልተለመደ ነው፡፡  ‹‹እየታየ ነው››  የሚባሉ አባባሎች አሉ፡፡ አክራሪነት ሳይሆን ጽንፈኝነት ሊኖር ይችላል፡
  • ጥያቄ፡- መንግሥት የአክራሪነት ዝንባሌ በሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ሥር ባለው ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› ውስጥ እንዳለ ተናግሯል፡፡ ይህን እንዴት ይመለከቱታል ?

ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሠ የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ ከዕንቁ መጽሄት 6ተኛ ዓመት ቁጥር 101 መስከረም 2006 ዓ.ም ዕትም ጋር አጠር ያለ ቆይታ በአክራሪነት ዙሪያ አድርገው ነበር ፡፡ አንባቢያን ዘንድ ቢደርስ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኝነው እንዲህ አድርገን አቅርበነዋል፡፡

ዕንቁ ፡- የአክራሪነት መሰረቱ ምንድነው?
ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም፡-እያንዳዱ ሰው የራሱ የሆነ አመለካከት ይኖረዋል፡፡ ያ አመለካከት በሃይማኖት ፤ በፖለቲካ ፤ በሌሎች አይዲዎሎጂዎች ወይም ጽንሰ ሃሳብ (ርዕዮት) ላይ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ለማስፈጸም እንደፈለጉት ግብና ዓላማ  በዚያ ላይ ያላቸውን አቋምና የተለያዩ ዝንባሌዎች ለአክራሪነት መሰረት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡


ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ አክራሪነት አለ ?
ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም፡- በተለያዩ ሚዲያዎች እንደምንሰማው ጠንከር ያሉ አክራሪነት ባህሪይ  ከሚታይባቸው ሃገሮች ጋር ማነጻጸር ባይቻል አልፎ አልፎ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ከዚህ በፊት  ያልነበሩ አመለካከቶች ፤ ከሌላው የጎላ ባይሆንም በምልክት ይንጸባረቃል፡፡ ይህ ወደ ዋናው የመጨረሻ ጫፍ ላይ እስኪደርስ መጠበቅ የለብንም ፡፡ ቀድሞ ማረም እና ማስተካከል ይገባል፡፡ በአገራችን ተቻችሎ እና ተከባብሮ በሰላም የመኖር ሀብታችን እክል እንዳይገጥመው ፤ የአክራሪነት አመለካከቶች እንዳይዳብሩ ፤ ስር እንዳይሰዱ ማኅበረሰቡ ላይ የበለጠ እንቅፋት እንዳይፈጠር የበለጠ መከላከሉ ተገቢ ነው፡፡

ዕንቁ፡- ምልክቶች የሚሏቸው ቢገልጹልን ?
ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም፡- አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጽንፈኝነት ስሜቶች ናቸው፡፡ በቋንቋ በሚታዩ ግጭቶችና አልፎ አልፎ ባገኙት አጋጣሚ በሃይል  ሕገ-ወጥ መንገዶችን መጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡ የአክራሪነት ዋና አላማ ዓለምን በእነርሱ የአክራሪነት ሕግ ማስተዳደርና ከእነሱ እምነት ውጪ ያለ ሕግ ዋጋ እንደማይኖረው ማሰብ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሚመኩት በሚመራቸው በምድራዊ ኃይል  ፤በትምህርት ጥረትና በማሳመን ብቃት እንጂ በእግዚአብሔር ኃይል አይደለም ፡፡ በተለያየ የአለም ክፍል እንደታየው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ያገኟውን ስፍራዎች ሕገ ወጥ አሸባሪነትና ተግባር ይጠቀሙበታል፡፡ እዚህ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሲሆን ይህ ለሰው ልጅ እንቅፋትና አካል የሆኑ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡

ዕንቁ፡- መንግሥት የአክራሪነት ዝንባሌ በሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ሥር ባለው ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› ውስጥ እንዳለ ተናግሯል፡፡ ይህን እንዴት ይመለከቱታል ?

ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም፡- በእውነት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለ2000 ዓመታት ሰላምን ስትሰብክና ከባዕድ የመጡትን ሃይማኖቶች በሰላም ስታስተዳግድ የኖረች ሃይማኖት እንደሆነች አውቃለሁ፡፡  ቤተክርስቲያናችን ነገም ሆነ ወደፊት የሰላም ባለቤት ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታትን ሰላም ስታውጅ ኖራለች፡፡ ተከታዮቿን ለሰላም ማዘጋጀት ለአገር ልማት ፤ ዕድገትና ብልጽግና ማዘጋጀት የቤተክርስቲያኗ ግምባር ቀደም ተልዕኮ ነው፡፡ ለአገርም በሚያገናኝ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ አብራ ትሠራለች፡፡ ያላትን ተሳትፎ ትገልጻለች፡፡ አንድ ነገር ታይቶ ተመርምሮ እና ‹‹ምልክቶች አሉ›› የሚባል ከሆነ እነዚያን ማጣራትና ትክክል ሆኖ ከተገኝም መታረም ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ቤተክርስያኗ ቅንጣት ያህል ከሰላም እና ከዐዋጅ ውጪ ተናግራ አታውቅም ፤ ልትናገር አይገባም፡፡ ሰላም መሰረታዊ ሀብቷ  እንደሆነ ታስተምራለች፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያኗ  እንደዚህ ዓይነት ነገር በውስጧ ካለ ትፈትሻለች ትመረምራለች፡፡ ስህተቶች ካሉ ታርማለች፡፡ አክራሪነት የቤተክርስቲያኒቱ ዓላማና ተልዕኮ  አይደለም ፤ሊሆንም አይገባም፡፡

ዕንቁ ፡- ከላይ እንደተነሳው አክራሪነት በኦርቶዶክስ ክርስትና ውስጥ እንዳለ ተገልጿል ፡፡ ለጉዳዩ መስተካከል መፍትሄ የሚሉት ?
ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም፡- ብዙ ጊዜ የሌላውን ህልውና የመቀበል ስሜት መኖር መቻል አለበት፡፡ ክርስትና ከየትኛውም ሰው ጋር በሰላም የመኖር መርህ አለው፡፡ ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው ፡፡ ሰው ከሰው ውጪ  መኖር አይችልም፡፡ ሰው ስንል በቋንቋ ፤ በጎሳ ፤ በባህል በኃይማኖትና በተለያዩ ማህበረሰቦች ይካተታል፡፡ ሁሉም የየራሱ እምነት ጠብቆ ፤ ሌላውን አክብሮ መኖር ከሰው ይጠበቃል፡፡ ይህ አንዱ የሰብአዊ መገለጫ ባህርይ  ነው፡፡ ‹‹እኔ ብቻ›› የሚለው አስተሳሰብ ተገቢ አይደለም፡፡  በእርግጥ ይህ በክርስትና ‹‹አክራሪነት አለ›› የሚባለው ነገር ያልተለመደ ነው፡፡  ‹‹እየታየ ነው››  የሚባሉ አባባሎች አሉ፡፡ አክራሪነት ሳይሆን ጽንፈኝነት ሊኖር ይችላል፡፡ በክርስትና ግን መርሁ አያስኬድም፡፡ በሌላው ሃይማኖት ብትሄድ  የሌላውን የመኖር መብት ጸጋ እና ክብር የሚያሳጣ  ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ በማኅበረሰባችን የነበረን ዕሴት እንደመልካም መነሻ ፤ መጀመሪያ እንዲሁም እንደመልካም  ሀብት የምንቆጥረው ከሆነ የሚባሉ  ነገሮች ሁሉ በሀገራችን ሥር የሌላቸው መጤ ናቸው፡፡ የነበረን እሴት በቂ ሀብት ነው፡፡ እኛነታችንን በራሳችን ውስጥ እናገኝዋለን፡፡  ሁሉም ተከባብሮ ተስማቶ እንደነበረውና  እንደቀደመው ባህል  ወግና ልማድ መሄድ አለብን፡፡ አጋጣሚን የምንጠቀም መሆን መቻል የለብንም፡፡ አጋጣሚን ተጠቅሞ ሌላውንም የማጥቃት ነገር ተገቢና አስተማሪ አይደለም፡፡ ትልቁ ነገር ካለፈው ጥፋት ታርሞ በመመለስ የነበረንን ዕሴት እያንጸባረቅን መኖር ነው፡፡ የአመለካከትና የአስተሳስ ለውጥ እንዲኖር በማድረግ ሕዝባችን በሰላም  የተሻለ ኑሮ እንዲኖር  ያስልጋል፡፡  አልፎ አልፎ የግለሰቦች ስህተት  የተቋም አቋም ተደርጎ መወሰድ የለበትም ፤ በአንዳንድ ሰዎች ምክንያት ስህተት ሊኖር  ቢችል እንኳ  ያ ስህተት የግለሰቦች እንጂ የተቋም አይደለም፡፡ ይህ ስህተት የኦርዶክስ ፤ የእስልምና እና  የፕሮቴስታንት አይደለም፡፡ እንደ ተቋምና ሃይማኖት የቆሙለትና የኖሩለት ሰላም ፍቅርና አንድነት ሊኖር ይገባል፡፡ የሰዎች እምነት እንደተጠበቀ ሆኖ  የሌላውን ሃይማኖት በማክበር ለትውልድ የሚጠቅም ሰላማዊ አንድነትን የመጠበቅ  ግዴታ በንቃት ማሰብ አስፈላጊ ሲሆን በማስተዋል ነገሮችን ብንመለከት መልካም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment