Thursday, October 31, 2013

“የሌለውን ፍለጋ” ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ለተስፋዬ ገብረአብ የሰጠው ምላሽ

(Read in Pdf ) ተስፋየ ገብረ አብ ‹የስደተኛውማስተዋሻ› የተሰኘ መጽሐፍ ማውጣቱንና ባነበውመልካም እንደሆነ ገልጦ አንድ ወዳጄ ‹ስስ ቅጅውን› ከሀገረ አሜሪካ ላከልኝ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች መጻሕፍቱን አንብቤያቸዋለሁ፤በአጻጻፍ ችሎታው የምደሰተውን ያህል እንደ አበሻ መድኃኒት ነገሩን ሁሉ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ምስጢር ስለሚያደርገው፤ በአንዳንድጉዳዮችም ሆን ብሎም ሊያናጋቸው የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ያሉ ስለሚመስለኝ፤ ተስፋዬ ለምን እንደዚህ ይጽፋል? እያልኩ የምጠይቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡

በዚህ መጽሐፉ ውስጥም ያንን ጥርጣሬየን አጉልቶ ሥጋ ነሥቶ እንዳየውየሚያደርገኝ ነገር ገጠመኝ፡፡ ተስፋየ በገጽ 306 ላይ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ› በሚል ርእስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የማያውቀውንነገር ጽፏል፡፡ ስለማያውቀው ነገር የጻፈው ባለማወቁ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አንድም ለማወቅ ባለመፈለጉ፣ አለያም ሆን ብሎ የማፍረስዓላማ ይዞ ይመስለኛል፡፡

ይህን የምለው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖትለመጻፍ ሲፈልግ ሊያነባቸው የሚችላቸው መጻሕፍት በምድረ አውሮፓ እንደ ማክዶናልድ በዝተው ሞልተው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያንባልሆኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ኤንሪኮ ቼሩሊ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔቶች ታሪክ(GliAbbati di Dabra Libanos, 1945)፣ ኮንቲ ሮሲኒ ከሐተታ ጋር ያሳተመውን ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣በዋልድባ ቅጅ (IlGadla Takla Haimanot secondo la redazione Waldebbana, 1896)፣ የዊልያም በጅን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወትና ተአምር (The Life and Miraclesof Takla Haymanot, 1906)፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጸሐፍትም ውስጥ የታደሰ ታምራትንChurch and State in Ethiopia, ማንበብ በተገባው ነበር፡፡


አቡነ ተክለ ሃይማኖትና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ(ጎርጎራ፣ ደብረ ሲና ማርያም)ከዚህም ዘልሎ ጥልቅ ጥናት አድርጌ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ ለሚል ደግሞ እንግሊዝ ምቹ ናትና ሎንዶን ወደሚገኘውብሪቲሽ ሙዝየም ሄዶ በማይክሮ ፊልም የተነሡትንም ሆነ በአካል ያሉትን ብራናዎች ማየት ነው፡፡ እዚያም የማያደርሰው ከሆነ በዋናከተማው በሆላንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙትን የጌታቸው ኃይሌን THE MONASTIC GENEALOGY OF THE LINE OFTÄKLÄ HAYMANOT OF SHOA, (Rassegna di Studi Etiopici, Vol. 29 (1982-1983), pp.7-38)፤የተስፋዬ ገብረ ማርያምን AStructural Analysis of Gädlä Täklä Haymanot(African Languages and Cultures,Vol. 10, No. 2 (1997), pp. 181-198)፤ የሐንቲንግ ፎርድን (G.W.B. Huntingford,"The Lives of Saint Takla Haymanot," Journal of Ethiopian Studies,4(1966), 34-35.) የአሉላ ፓንክረስትን Dabra Libanos Pilgrimage Past and Present, TheMytery of the Bones and the Legend of Saint Takla Haymanot,(the sociologyethnology Bulletin) 1,3 (1994), P. 14-26 ጥናቶችን ማየት ይቻል ነበር፡፡ያም ካልሆነ ወደ ቤልጅየም ሄዶ ፒተርስ አሳታሚ ከጥልቅ ጥናት ጋር የሚያሳትማቸውን የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብት ኅትመቶችማገለባጥ ይቻል ነበር፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ(ጎርጎራ፣ ደብረ ሲና ማርያም)

የገረመኝ ገድለ ተክለሃይማኖትን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ (History)ና የታሪክ አጻጻፍ(Historiography) ታላቅ ቦታ ያለው፣ በኢትዮጵያ ገድላት ጥናት(Hagiography) ቀዳሚ የሆነና በብዙ አጥኝዎች የተጠና ጉዳይ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ አፈርሳለሁ ብሎ መነሣቱነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከማይወጣበት የክርክርአዘቅት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡

ተስፋዬ ጽሑፉን የጀመረው በስድብ ነው፡፡ ኤርትራዊት እናቱ ‹ይዘምሩትነበር‹ ብሎ ያቀረበው ጽሑፍ የራሱን ስድብ በእና ያሳበበበት ነው፡፡ የኤርትራን ቤተ ክርስቲያንና ኤርትራውያን ክርስቲያን እናቶችንከእርሱ በላይ አውቃቸዋለሁ፡፡ ተሰድደው በየሀገሩ ከተበተኑት ጋር አብረን ቋንቋና ድንበር ሳያግደን አገልግለናል፡፡ አሥመራ ከተማከሚገኙት ታላላቅ አድባራት አንዱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በምንም መልኩ አንዲት ኤርትራዊት እናት ተስፋዬበአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የተሳለቀውን ‹መዝሙር› አትዘምርም፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደማቸው የፈሰሰው ሰባት ዓመት ሙሉ ለጸሎትየቆሙበት እግራቸው በጸሎት ብዛት በመቆረጡ እንጂ ሰይጣን ‹ፈንግሏቸው› አለመሆኑን ኤርትራውያን እናቶች በሚገባ ያውቁታል፡፡ የሚገርመውነገር 

ተስፋዬ በጆሮ ጠገብ የሆነ ቦታ የሰማውን መዝሙር አጣምሞት እንጂ መዝሙሩ እንዲህ አይደለም፡፡
ተክለ ሃይማኖት የዓለም ብርሃን ናቸው
ይኼው ለዘላለም ያበራል ገድላቸው
ነው የሚለው፡፡

ተስፋዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ አነበብኳቸው የሚለን አምስትመጻሕፍትን ነው፡፡ የአባ ዮሐንስ ከማ፣ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ የጽጌ ስጦታው፣ የዳኛቸው ወርቁና የኢረይን ሙራይ፡፡ አባ ዮሐንስከማን እንደማያውቃቸው፣ የጻፉትንም ገድል እንዳላነበበ የሚያሳብቅበት ‹ደብተራ› ሲላቸው ነው፡፡ አባ ዮሐንስ ከማ ሰባተኛው የደብረሊባኖስ እጨጌ እንጂ ደብተራ አልነበሩም፡፡ በዚያ ዘመን ‹ደብተራ› ማለት የንጉሡን ደብር(ድንኳን) የሚያገለግሉት ካህናት ናቸው፡፡አባ ዮሐንስ ከማ በዐፄ ይስሐቅ(1407-1423)ዘመንና በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ(1437-1461)የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበሩ ደብረሊባኖስን እንደገና ያሳነጹ ገድለ ተክለ ሃይማኖትንም ያስጻፉ አባት ናቸው፡፡ ተስፋዬ አባ ዮሐንስ ከማ ከ200 ዓመታት ቆይታ በኋላስለ ጻፉ ተሳስተዋል ይላል፡፡ ባታውቀው ነው እንጂ ሙሴ ኦሪትን የጻፈው ዓለም ከተፈጠረ ከሺዎች ዓመታት በኋላ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንገድሎች ዘግይተው የሚጻፉት የአንድን ቅዱስ ቅድስና ለመመስከር ካረፈ ቢያንስ ግማሽ ምእተ ዓመት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ በመቃብሩላይ የሚሠሩት ተአምራት፣ በአማላጅነቱ የሚሠራቸው ተአምራትና ሌሎችም መታየት አለባቸው፡፡ 

ተስፋዬ አላዋቂነቱን እንደ ዕውቀት ስለወሰደው እንጂ የአቡነ ዮሐንስከማ ገድል የመጀመሪያው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አራት ቀደምት ሰዎችጽፈዋል፡፡ 1)በስንክሳር ተጽፎ የሚገኘው(በተለይም በፓሪሱ ስንክሳር) አጭር የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ፣ 2) የትግራይ ተወላጅበሆነው በተክለ ጽዮን የተጻፈው የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት [አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት (በቆብ) የልጅ ልጅናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ መድኃኒነ እግዚእን ሲያመነኩሱ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ ሰባቱ ከዋክብት የተባሉትንናበጣና ዙሪያ የሰበኩትን (አቡነ ዮሐንስ ዘቁየጻ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነዮሐንስ ዘጉራንቋ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልተዋርና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን) ሲያመነኩሱ ነው ምንኩስናን ተቀብለው ለተልዕኮየተሰማሩት፡፡ ለዚህም ነው የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል ዋልድባዎች የጻፉት፡፡] 3)ያልታወቀ ጸሐፊ አጭሩንና የሐይቅ እስጢፋኖስ ቅጅ የሚባለውን ጽፏል፡፡ ይኼኛው ገድል ቀዳሚ ሳይሆን አይቀርም፤አንደኛ የተጻፈው ከሌሎች ቅዱሳን ገድሎች ጋር እስትግቡእ ሆኖ በስንክሳር መልክ ነው፡፡ ሁለተኛ የተጠቀማቸው አማርኛዎች በአሁኑጊዜ ጥቅም ላይ የሌሉ ዓይነት ናቸው፣ 4)አቡነ ዮሐንስ ከማ የጻፈው የደብረ ሊባኖስ ቅጅ ናቸው፡፡

ይህ የአቡነ ዮሐንስ ከማ ገድል ምናልባት ከ1418-19 ዓም ባለውጊዜ ውስጥ በዐፄ ይስሐቅ ዘመን የተጻፈ መሆኑ ይገመታል(EncyclopediaAethiopica, Vol. IV, P. 832) በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ዐረብኛው ገድል በዐፄ ገላውዴዎስ ዘመን(1533-1551) የተጻፈ ይመስላል(Encyclopedia Aethiopica,Vol.IV, P.832)፡፡ ያልተመዘገቡ አያሌ ገድላት በየገዳማቱ መኖራቸውእንደተጠበቀ ሆኖ 22 የብራና ገድሎች በአውሮፓ፣ 20 በኢትዮጵያ የማኑስክሪፕት ቤተ መጻፍት(EMML)፣ 3 በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት፣ 5 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የአቡነተክለ ሃይማኖት ገድሎች ይገኛሉ፡፡ በአንድቅዱስ ላይ የተለያዩ ቅጅዎች መገኘታቸው መረጃዎችን ያሰፋቸዋል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ስለ አንድ ክርስቶስ አራት ዓይነት ወንጌሎችመጻፋቸውን ማስታወስ ይበቃል፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በብዙ ሥራዎቻቸው የተከበሩና የተመሰገኑ ሊቅናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ላነሡት ሃሳብ ግን ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ ገድሎች ሁሉ የአቡነ ተክለሃይማኖትን ገድል ያህል የሚታወቅና የተጠና የለም፡፡ ከሌሎች ጋር እየተነጻጸረም ሆነ በራሱ(Textual analysis) ገድለ ተክለ ሃይማኖት በአውሮፓውያንም ሆነ በኢትዮጵያውያንሊቃውንት ተጠንቷል፡፡ እስካሁን ግን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆኑ ሌሎች የሚሉት ‹ሌላ ገድል› አልተገኘም፡፡ አለቃም ያነበቡት ከሆነ ያነበቡትን፣ ያገኙት ከሆነም ያገኙበትን አልነገሩንም፡፡ምንጭ የላቸውምና ለታሪክ ክርክር ሊጠቀሱ አይችሉም፡፡

ጽጌ ስጦታውም ቢሆን ምናቡንና አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ጠቀሰ እንጂአለ የሚለውን ‹የዚያኛውን ተክለ ሃይማኖት› ገድል ሊያመጣልን አልቻለም፡፡ ዳኛቸው ወርቁ የጻፈው ልቦለድ እንጂ ታሪካዊ ዋጋ ያለውነገር ስላልሆነ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይባስ ብሎ ተስፋዬ ኢለይን ሙራይ ለልጆች ብላ የጻፈችውን ተረት ጠቅሶልናል፡፡ ይህነገር የቦሩ ሜዳን ክርክር ነው ያስታወሰኝ፡፡

 በቦሩሜዳ ክርክር ‹ለኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደት አለው› የሚሉና ‹ሦስት ልደት አለው› የሚሉ ሊቃውንት ተከራክረው ነበር፡፡ በዚህክርክር የሁለት ልደትን ወክለው ከተከራከሩት መካከል የነበሩት መልከአ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ‹ነአምን ክልኤተ ልደታተ› የሚል ንባብከሊቃውንት መጽሐፍ ጠቅሰው ተከራከሩ፡፡ ዐፄ ዮሐንስም የሦስት ልደቶችን ተከራካሪ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስን ‹በል አንተም እንደ እርሱከሊቃውንት መጽሐፍ ሦስት ልደት የሚል ንባብ አምጣ› አሉት በዚህ ጊዜ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ ‹በደብረ ብርሃን ተአምረ ማርያም ይገኛል›አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ‹ከምታስተምረው ከአራቱ ጉባኤ አጣህና ነው ከተአምረ ማርያም ትጠቅሳለህ›› ቢሏቸው ‹ ከጉባኤው መጽሐፍስየለም››  አሉ ይባላል፡፡

የተስፋዬ አጠቃቀስ ከዚህም የወረደ ነው፡፡ አለቃ  ሥነ ጊዮርጊስ የተወቀሱት ለእምነት ክርክር የማይጠቀስ የተአምር መጽሐፍ በመጥቀሳቸውነው፡፡ ተስፋዬም ከዚያ ወርዶ ወርዶ ለታሪክ ክርክር የማይጠቀስ የተረትና የልቦለድ መጽሐፍ ሲጠቅስ ይገኛል፡፡

ተስፋዬ ወግዳ የተሸሸገ ለሕዝብ የማይቀርብ ገድለ ተክለ ሃይማኖት አለይላል፡፡ በሀገራችን ጠንቋይ እንዳይጋለጥ ሲፈልግ የሌለ ነገር ያዝዛል ይባላል፡፡ ተስፋዬም ወግዳ የተደበቀ ገድል አለ አለ፡፡ ወግዳበሰሜን ሸዋ በደብረ ብርሃን ዙሪያ ወረዳ ሥር የሚገኝ ቦታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት በ1964 ዓም ማይክሮ ፊልም መነሣትሲጀምሩ ከሰሜን ሸዋ ነበር የተጀመረው፡፡ እነ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ(አጥንታቸውን ያለምልመው እንጂ) እያንዳንዷን ወረዳ ለቅመው አንሥተውታል፡፡እንኳን በገዳማት አድባራት የሚገኙት በግለሰቦች እጅ የሚገኙትም አልቀሯቸውም፡፡ እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ የሕንድ፣ የግሪክመጻሕፍት አልቀራቸውም፤ እንኳን ገድልና ተአምር የቤተ ክርስቲያንን እምነት የሚቃረኑ መጻሕፍት በክብር ተጠብቀው ነው የተገኙት፡፡ተስፋዬ ወግዳ የማይደረስበት መስሎት መደበቂያ ዋሻ አለ ይላል፡፡ ወግዳኮ ከአዲስ አበባ የ120 ኪሎ ሜትር ጉዳይ ነው፡፡

በማይክሮ ፊልም ቀረጻው ወቅት በሥራ ላይ የተሠማሩት የሀገሬው ተወላጆችነበሩና ያስቸገራቸው ነገር አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ ይህ ‹የወግዳ ገድል› ይገኝ ነበር፡፡ ግን የለምና አልተገኘም፡፡ ይህዓይነት ፕሮፓጋንዳ ዛሬ አልተጀመረም፡፡ በትግራይ፣ በወሎ፣ በጎጃም በተክለ ሃይማኖት ስም ስለሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን የተጻፉ ገድሎችአሉ እየተባለ እንዲሁ በአፍ ታሪክ ይነገራል፡፡ እስካሁን ግን ማስረጃ አምጥቶ ያረጋገጠ አልተገኘም፡፡ የትግራይ ገዳማት የብራናመጻሕፍት በቅርቡ ዲጂታላይዝ ተደርገዋል፡፡ ግን የተባለው አልተገኘም፡፡ በመካከለኛው ዘመን ሌላው ቀርቶ ከማዕከላዊው መንግሥት ተጋጭተውርቀው በነበሩት የደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ገዳም በጉንዳ ጉንዲ እንኳን የደብረ ሊባኖሱን ገድል የመሰለ ቅጅ ነው የተገኘው፡፡
ማንኛውም ክርክር ሲቀርብ ለክርክሩ ብቁ የሆነ ማስረጃ መቅረብ አለበት፡፡ልቦለዱንም፣ ቀልዱንም ለታሪክ ማስረጃ መጥቀስ ቧልት እንጂ ቁም ነገር አይሆንም፡፡

ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚባለውን የታወቀ ታሪክ (official history) ለመቀበል አልፈለገም፡፡ ያ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ አዲስ ማስረጃአምጥቶ ወይም ነባሩን ማስረጃ በክርክር አፍርሶ ያላየነውን ካሳየን እናመሰግነው ነበር፡፡ እርሱ ግን ወይ የታወቀውን አልተቀበለ፣አለያም አዲስ ማስረጃ አላመጣ፣ ከሁለት የወጣ ጎመን ሆነብን፡፡

ሮማውያን የሕግ ሊቃውንት Argumentum ad Contrario የሚል መርሕ ነበራቸው፡፡ ‹አንድን ነገር የታመነውንናየታወቀውን ትተህ በተቃራኒው ያለውን አረጋግጥ› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የሚባለውንና የሚታመነውንተወውና ተቃራኒውን በማስረጃ፣ በተጠየቅና በትንታኔ አረጋግጥ ማለት ነው፡፡ ተስፋዬ ይህንን ለማረጋገጥ ዐቅም አላገኘም፡፡ እንዲሁቧልቱን ብቻ ነገረን፡፡

ተስፋዬ የታሪክ ስሕተቱን የሚጀምረው በሰባተኛው መክዘዐፄ ዳዊት የሚባሉ ንጉሥ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ ሲለን ነው፡፡ ተስፋዬ በቀላሉ የሚገኘውን የሬኔ ባሴን ታሪከ ነገሥት፣ የሥርግውሐብለ ሥላሴን የነገሥታት ዝርዝር፣ የተክለ ጻድቅ መኩሪያን መጻሕፍት አለያም የብላቴን ጌታ ኅሩይን ‹ዋዜማ›፣ የጌታቸው ኃይሌንባሕረ ሐሳብ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1975 አሳትሞት የነበረውን The Dictionary of Ethiopian Biography, ብታይኮ እንዲህ ካለ ስሕተት ውስጥ አትወድቅም ነበር፡፡በኢትዮጵያ ታሪክ ዳዊት በሚል ንጉሥ መጀመሪያ የነገሠው ዐፄ ዳዊት አንደኛ ከ1374-1406 ዓም ነው፡፡ ከየት አምጥተህ ነው በሰባተኛውመክዘ ያደረግከው፡፡

እጂግ የሚገርመው ነገር የሀገራችን ሊቃውንት ‹ጨዋደፋር ነው› እንደሚሉት ተስፋዬም ያለ ምን ጥናት፣ ያለ ምንም ማስረጃ እርሱ ራሱም እንደሚለን ‹ኢትዮጵያ ሳለ የሰማቸውን አፈ ታሪኮችሰብስቦ›(እኔ ግን አይመስለኝም፣ አሜሪካ ሆኖ ፈጥሮ እንጂ) በድፍረት ‹ሦስት ተክለ ሃይማኖቶች አሉ ይላል፡፡ ቢያንስ ለዕውቀትክብር ሰጥቶ ‹ያሉ ይመስለኛል› ቢል እንኳን ምን አለበት፡፡ ለካስ እስከዛሬም በሌሎች መጻሕፍቱ ሲነግረን የነበሩት ‹የመንግሥትምሥጢሮች› እንዲህ የተሰበሰቡ አፈ ታሪኮች ነበሩ ማለት ነው?

ለመሆኑ ተስፋዬ እናዳለው ሦስት ተክለ ሃይማኖቶች  አሉን? ሦስቱስ በገድለ ተክለ ሃይማኖት ተቀላቅለዋልን? ሳምንት እንመለሳለን፡፡


© ይህ ጽሑፍበአዲስ ጉዳይ ላይ የወጣ ነው


1 comment:

  1. The Angry Ethiopian/ቆሽቱ የበገነውNovember 2, 2013 at 4:27 PM

    ተስፋዬ የሚባለው እባብ ጋዜጠኛ ካገር ክወጣ በኋላ ትንሽ ዝናን ያገኘው ህዝባችን የቡና ቤት ወሬ ስለሚወድ ነው። ታሪካችንን በአግባቡ የማወቅ ጥረት ብናደርግ እና ጥሩ መሰረት ቢኖረን ኖሮ፤ እባቡ ጋዜጠኛን ገና ከድሮ ጀምሮ የማሪያም ጠላት አድርገን መልከስከሻ ቦታ እናሳጣው ነበር። ውጭ አገር ያሉትም የዜና አውታር ድህረ-ገፆች በአብዛኛው አጨብጫቢዎችና በተለያየ ጥቅም የለሽ ሮዕዮተ-አለም የተበተቡ ናቸው። ይኼ እባብ ጋዜጠኛ ገና ከመጀመሪያው ጥራዝ ነጠቅ፣ፀረ-ቤተክርስትያን፣ፀረ-አማራ እና ፀረ-ኢትዮጵያ ነበር። ነገር ግን ተቃዋሚ ነኝ ባይ ሰርጎገቦችና ቦለቲካሞች "የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው" የሚል መርሆ በማራመድ፤ በጉያቸው ውስጥ ሊከቱት ፈለጉ። የቦለቲካ ቁማር ስሌታቸው ግን የትም የሚያደርስ ሳይሆን፣ የበለጠ ወደ ኋላ የሚጎትት ነበር።

    ReplyDelete