Sunday, October 20, 2013

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ


እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ
ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ፡፡

ነብያት በመጋዝ የተሰነጠቁት
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት
ምሥጢሩ ምን ነበር? አበው ይናገሩት፡፡


ይናገር ዝቋላ ግሸን ላሊበላ
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ፡፡
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡
ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት፡፡
ጐበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና፡፡
እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡
የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው?

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
የሃይማኖት ጀግና የትነው የማገኘው?
ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሐ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ፡፡

የት ነው የማገኘው ለሃይማኖቱ ሟች
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች፡፡
የወገን መመኪያ የከሀዲ መቅሰፍት
ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሣ ቀስቅሱት፡፡
እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ጀግና አማረው
በእምነቱ የፀና የትነው የማገኘው?
ብቅ ይበል እንየው እሱ ማነው ጀግና?

በጐችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ
የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?
የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?
ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር
ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን
ትንታግ ምላስም ጭንግፍግፉን
ልሳነ ጤዛ መናፍቅን
ወልደ አርዮስ ዲቃላውን፡፡
በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ
ጀግና ማነው ዝቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት
እስኪ ጎርጎርዮሰ ይምጣና ጠይቁት
ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ
ምሥጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ፡፡

የክርስቶስ ባርያ የአጋንንት መቅሰፍት
ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት
ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት
የጸሎት ገበሬ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ይነሣ ቀስቅሱት
ይነሣ ጊዮርጊስ ይመስክር ምሥጢር
የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ
ዲያብሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ፡፡
ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ
መር ብለው የወጡት ከሥጋ ገበያ
ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡

Source :- Facebook

5 comments:

  1. ቃሎውት ያሰማልን !!!

    እግዚአብሔር ያገልግሎት ጊዚያቹን ያርዝሚልን
    በጣም ልብ የሚነካ መልክእት ነው ያስተላልፋቹት

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሄር፡ይባርካችሁ።
    እሱ፡አምላካችን፡በቸርነቱ፡ይርዳን።
    አሜን።

    ReplyDelete
  3. ይድረስ ለአቡነ ሳዊሮስ
    የሚከተሉት ስንኞች በትትክክል እርሳቸውን ይገልፃሉና እባካችሁ አስነብቡልን

    የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
    የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
    የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
    የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?


    ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
    መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡
    እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት

    ይህ አስተያየት ገና ከመመንኮሰዎት በፊት ከሚያውቀዎት አንድ ወዳጀዎ ነውና ቢያሰተውሉት ይጠቀሙበታል፡፡ አባታችን የመመንኮስ ዓላማና ጥሪ ሳይኖረዎት/ ከብሄራዊ ውትድርና ለማምለጥ ሲሉ ብቻ/ መንኩሰው፣ ከምንኩስና እስከ ጵጵስና ባለው ሕይዎትዎ ምንኩስናውን በስርቆትና በዝሙት አቆሽሸው በየትኛውም መሥፈርት ሳይገባዎት በፖለቲካዊ መንገድ በቄስ በላይ ረዥም እጅ በብሔር ተዋፅኦ ጵጵስና ተሾሙ/ቤተክርስቲያኒቱ በታሪኳ ከሰራቻቸው ስህተቶች አነዱ ነው / እግዚአብሔር ያን ሁሉ ድክመት ታግሦ ለዚህ ሲበቃዎት ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለፖለቲካ አያደሉ/ የኦህዴድ አባል ናቸው/ ቤተክርስቲያኒቱን ማድማት ቀጠሉ ለነገሩ ያሾመዎት ሀይማኖትዎ ሳይሆን የድርጅት አባልነትዎ ስለነበር በአንድ በኩል አይፈረድም፡፡ ነገር ግን ቢያንስ በስምም ቢሆን ጳጳስ ነዎት እንጅ ሚኒስትር አይደሉምና እባክዎ አደብ ይግዙ ያለበለዚያ መጨረሻዎት ያበደ ውሻ ሆኖ እንደሚቀር አይጠራጠሩ ራስዎትን ለማስተካከል እግዚአብሔር አሁንም በቂ ጊዜ እየሰጠዎት ነውና ወደ አእምሮዎ ይመለሱ
    ወዳጅዎ

    ReplyDelete
  4. Kale hiwot yasemaln M/r Zelalem Zewator Technology yet endaleh bakna bagegnh des balegn

    ReplyDelete