Saturday, July 14, 2012

የአልፎንዙ እሾሆች


ከተስፋዬ አዳነ 
(አንድ አድርገን ሐምሌ 7 ፤ 2004ዓ.ም)፡-መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከአርባ በላይ ስሟ የተጠቀሰ፣ ለብዙዎች የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ፣አውሮፓውያን የካህኑ ንጉሥ ሀገር እያሉ የሚጠሯት፣ አፍሪካውያን የጥንካሬያቸው ምስክር የሚያደርጉት የደጋግ ህዝቦች መኖሪያ የቅዱሳን ምድር ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ!!!

ኢትዮጵያችን በተለያዩ ምክንያቶች ቅድስት ሀገር ተብላ ተጠርታለች፣ ምድራችን ክርስትናን ቀድመው ከተቀበሉ ሀገራት መካከል በቀዳሚው ረድፍ ትገኛለች፤... ያኔ ገና መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት በወረደበት እነ ጴጥሮስ በተለያየ ልሳን ህዝቡን ስለ ክርስቶሰ በሚሰብኩበት ወቅት ኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትሯን ልካ ስለ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰብካለች፣ በራሷ አፍሪካዊና ጥቁር ኢትዮጵያዊ ከክርስትና ጋር ተዋውቃለች፤ እኛ ኢትዮጵውያን እንደሌሎቹ ከጣኦት አምልኮ አይደለም ወደ ክርስትና የተሸጋገር ነው፤ ክርስትናን የተቀበልነው እግዚአብሔርን ስናመልክ ቆይተን ነው ፤ ለዚች ሀገርም መጤዎች አይደለንም፡፡ኢትዮጵያ ያለ አምልኮተ እግዚአብሔር የኖረችበት የለም፣ ያለ ደም ክርስትና የተሰበከባት ይህች ቅድስት ምድር ለቅደስትነቷ ምንጭ ለጥንካሬዋ መሰረት፣ ለስልጣኔዋ መነሻ የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስትያንን መነሻ በማድረግ የተለያዩ ወረራዎች ተካሂደውባታል፡፡ ወረራዎቹም አስከፊ የሆነ የሰው ልጅ እልቂትንና ከባድ የሆነ የቅርስ ውድመትን አስከትለዋል፤ እነዚህ ወቅቶች በዋናነት አምስት ሲሆኑ ዘመነ ሰማዕታት ወይም የስደት ዘመን ተብለው በቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይጠራሉ፡፡ 


በዘጠነኛው / በዩዲት /ጉዲት/ የተፈጸመው እልቂትና ውድመት የመጀመሪያው የሰማዕታት ዘመን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዮዲት የክርስትናን ሀይማኖት አጥፍታ የአይሁድ ሀይማኖት ለማንገስ መነሳትዋ የዚህ ወቅት ዋነኛ ግብ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እጅግ ብዙ ካህናትና ምዕመናን ሲታረዱ በርካታ መጽሀፍት ንዋያተ ቅዱሳት እና የአብርሐ ወአጽብሐን / ጨምሮ ምትክ የሌላቸውን ውድ የሀገሪቷንና የቤተክርስቲያንን ቅርሶች አቃጥላለች ዘመኗም አርባ አመት ያህል ነበር፡፡ 

ለአስራ አምስት አመታት ያህል ያለማቋረጥ በትጋትና በንቃት በቅድስት ቤተክርሰቲያን ላይ የተነሳው አሕመድ ግራኝን በሁለተኛው የሰማዕታት ዘመን እናገኛዋለን፤ ግራኝ የተነሳው 16ኛው / ነው፡፡ ግራኝ ያቃጠላችውን አብያተ ክርስቲያናት ቅርሶችንና ክርስቲያኖችን መጠን ለመለካት ቤተክርስቲያን ላይ ሆነ ሐገሪቷ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ማህበራዊ ቀውስ ማንሳት ይሻላል፤ ... የእርሻ ማሳዎች የሚያርሳቸው ጠፍቶ ምድሪቷ በድርቅ ተመታች፣ ህፃናትን የሚያጠምቅ የምዕምናንን ንስሀ የሚቀበል የሚባርክ ካህን ጠፋ፣ ዕቁባትን በየቦታው ማስቀመጥ አንድ ወንድ ከብዙ ሴቶች መውለድን የተለያዩ ገዳማትና የቤተክርስቲያን ይዞታዎች በአህዛቦች መውሰድ የግራኝ ወረራ ዘመን አስከፊነት መገለጫዎች ሲሆኑ ታላቁ ገዳማችን ደብረ ሊባኖስና ገዳማውያኑ በታላቅ የሀይማኖት ፅናት በእሳት የተቃጠሉበት መራራ ወቅት ነበር፡፡ 

የግራኝ ጣጣ ራሱ ላይ ብቻ አላበቃም ፤ እርሱ ከሞተ በኋላም ቀጥሏል፤ ከዐፄ ገላውዲዮስ ጋር ህብረት በመፍጠር የግራኝን ግብአተ መሬት ያፋጠኑት ፖርቹጋሎች ለዚህ ውለታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ የካቶሊክ እምነትን እንዲቀበል ፈለጉ፡፡ የዚህ ጦስ ነው እንግዲህ ሦስተኛውን የሰማዕታት ዘመን የጠነሰሰው እና አልፎንዙን ከነ እሾሆቹ ያስተዋወቀን፡፡ ዐፄ ገላውዲዎስ ከግል ክብራቸውና ጥቅማቸው የጌታቸውን ክብረ እና የቅድስት ቤተክርስቲያንን ጥቅም በማስቀደም የፖርቹጋሎችን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ በእምቢተኝነት ሸኟቸው፤ ከአመታት በኋላ የነገሱት ዐፄ ሱሲንዮስ የግራኝ የነፍስ አባት የሆኑት ቱርኮቹንና በፖርቹጋል ሚሲዮናውያን ወጣ ገባ ማለት ያልተደሰተው የሀገራቸውን ህዝብ ፀጥ ለማሰኘት አምላካቸውን በፖርቹጋሎች ጦር መሳሪያ ቀየሩ፣ እምነታቸውን በሚሲዮናውያን ቁስ ለወጡ ‹‹ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሮም ስር ትተዳደር›› የሚል ዐዋጅን ከቤተመንግስታቸው አስነገሩ፤ በመሞት እንጂ በመግደል ፅድቅ እንደሌለ ከአምላኩ የተማረው ኢትዮጵያዊ ለእምነቱ ሞትን ከቀደሙት አባቶቹ ያጠናው የሀገሬ ህዝብ አዋጁን በመቃወም ቁጣውን ገለፀ ‹‹ ሰማዕትነት አያምልጥህ›› በማለትም ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ ወደ ጎንደር ሱሲኒዮስ አደባባይ ገሰገሰ በአንድ ጀንበርም 8ሺህ ያህል ንፁሐን ክርስቲያኖች ተሰው፤ ለሰባት አመታት ያህልም ህዝቡ አምላኩን ከመካድ እና እምነቱን ከመቀየር ይልቅ በሰይፍ መቀላትን በመምረጥ በእንቢተኝነት ፀንቶ ቆየ እነ አቡነ ሐራ ድንግል፣ እነ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ እነ አቡነ ኖላዊ ሔር እና ሌሎች ቅዱሳን በዚህ ወቅት ቅድስናቸው ተገለጠ፡፡

የቅዱሳን አባቶች ፀሎት እና የሀገሬው ህዝብ እንባ ላይ የእግዚአብሔር ቸርነት ታክሎበት ንጉሱ ከብዙ ህመም እና ሰቃይ በኋላ ወደ ቀልባቸው ተመለሱ ‹‹ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ትመለስ፣ የሮም ሀይማኖት ትርከስ፣ ፋሲል ይንገስ›› የሚል አዋጅ አስነግረው 1625 . ዐረፉ፡፡ 

ከዚህ በማስከተል የምናገኘው 1880 . ‹‹ ድርቡሽ›› የተባለውንና የአህዛብን ሀይማኖት ለማስፋፋት ከሱዳን የተነሳውን ንቅናቄ ነው፡፡ በዚህ ወረራ ወቅት ታላቁ የሀገራችንን ንጉስ አፄ ዮሐንስ አራተኛን ከማጣታችን በተጨማሪ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ከነቅርሳቸው እንዲሁም ካህናትና ምዕመናንን አጥተናል፡፡ 

በካቶሊክ ካህናት ቡራኬና በሚሲዮናውያን ጸሎት እየተመራ በቦምብና በመርዝ ጋዝ ንፁሀን ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሁኔታ የፈጀውን እልቂት አምስተኛው የሰማዕታት ዘመን ተብሎ በቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይጠራል፡፡ ይህ ወቅት 1928 . ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ አመታት የቆየ ሲሆን የኢትዮጵያውያን ደም እንደ ውሃ የፈሰሰበት በሺህዎች የሚቆጠሩ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉበት እጅግ በርካታ የቤተክርስቲያን ቅርሶች በዘረፋ ወደ ቫቲካንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የተጋዙበት ነው፡፡ ይህ ወቅት ልዩ የሚያደርገው... ንፁሀን ኢትዮጵያውያን ላይ ቦምብና የመርዝ ጋዝን ከላይ የሚያፈሱ አውሮፕላኖችን... ከታች እሳት የሚተፉት ታንኮችና መድፎች በካቶሊክ ጳጳሳት የተባረኩና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገንዘብ ድጋፍ የተገዙ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ኢሰብዓዊ የሆነ አስከፊ እና አስነዋሪ ድርጊት ክርስቲያን ነን ከሚሉ ወገኖች እና የእምነት ተቋም መፈፀሙ ያናደደው አንድ ሲዊዲናዊ ጋዜጠኛ የተናገረውን የታሪክ ፀሐፊው ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ‹‹ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ኃይለስላሴ›› በተሰኘው መፅሀፋቸው በገፅ 206 ላይ እንዲህ ገልፀውታል ‹‹ ቅዱስ ሆይ፣ እኔ አንድ ምስኪን ኃጢአተኛ ነኝ ፡፡ እርስዎ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዋና ነዎት፡፡ እርስዎንና ሌሎች ጳጳሳት ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ ቅኝ አገር እንድትሆን ብለው ተናገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች ሀገራቸውን ለመጠበቅ ሲሰበሰቡ የኢጣሊያ አውሮፕላን ጥርግ አድርጎ ቢያጠፋቸው እንደርስዎ አባባል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ስራ ነውን?፡፡ ይህን ሁሉ የምታስተምረን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ናትን?፡፡ ለነገሩ ቤተክርስቲያን ማስተማር የነበረባት ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝን መሆን ነበረበት፡፡ እርስዎ የሚያመልኩት አምሳለ ጣኦት /ሞሶሎኒን/ እንጂ አምላክን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ፀሎት ልታሳርግ አትችልም፡፡ እርስዎ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሞሶሎኒ የሚታዘዙ ሆነዋልና›› በማለት ነበር፡፡

 እነዚህ አምስቱ የሰማዕታት ዘመን አንዱ በአይሁዳውያን፣ ሁለቱ በካቶሊክ ሚስዮናውያን እና ሁለቱ በእስልምና ተስፋፊዎች የተፈፀሙ ሲሆን ዋና ግባቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን ማጥፋት ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአንድ ወቅት በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ የደረሱትን መከራና ፈተና ተመልክቶ  “ሰውን ብትታገልና ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሀል ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱንም ጨረሰ ቤተክርሰቲያንን ግን አልጎዳትምብሎ ነበር፡፡ 

የቅድሰት ቤተክርስቲያን ፈተናዎች ሁለት አይነት መልክ ያላቸው ናቸው፤ የመጀመሪያው ቁሳዊ ዕሴቶቿን ማጥፋት ሲሆን ሁለተኛውና ከባዱ ደግሞ መንፈሳዊ ዕሴቶቿን ማጥፋት ነው፡፡ እነዚህ ጥፋቶች በጦርነትም ያለጦርነትም ይፈፀማሉ፡፡ በሀገራችን የመንፈሳዊ ዕሴቶች ጥፋት ተጠናክሮ መታየት የጀመረው በዐፄ ሱሲንዮስ ወይም በሶስተኛው የሰማዕታት ዘመን ላይ ነው፡፡ ዐፄ ሱሲንዮስ በፖርቹጋል ሚሲዮናውያን አማካኝነት የሀገሪቷን ብሔራዊ ሀይማኖት ወደ ካቶሊክነት ለመቀየር በሞከረበት ግዜ በርካታ የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ዕሴቶች ተበርዘዋል፡፡ የዚህ የቅሰጣና የጥፋት እንቅስቃሴ ዋና ተሳታፊና ነገር ሰሪ ከነበሩት መካከል በዋናነት ፖኤዝ እና አልፎንዙ የተባሉ ሚሲዮናውያን ቄሶች ይገኙበታል፡፡ ለሰባት አመታት ያህል ለቆየው የሀይማኖት ጦርነት እና በአንድ ጀንበር በሱሲንዮስ አደባባይ በግፍ ለተሰውት 8 ሺህ በላይ ንፁሀን የተዋህዶ ልጆች ዕልቂት ምክንያት የሆነው ሚሲዮናዊው ቄስ አልፎንዙ ሜንዴዝ በሱሲኒዮስ ልጅ በዐፄ ፋሲል ትዕዛዝ ከሀገር እንዲወጣ በተፈረደበት ግዜ እንዲህ ብሎ ነበር ከሀገር የወጣው ‹‹ በኢትዮጵያ ሁለት እሾህ ተክዬባታለሁ›› አልፎንዙ በቀደሙት ነገስታት ላይ ይታይ የነበረውን ያለመጠን የበዛ ደግነትና የዋህነትን በመጠቀም ከሀገር ሳይወጣ አሞኛል በማለት የተወሰነ ቀን ትግራይ አካባቢ በመቀመጥ ከጎንደር ላመጣቸው ሁለት ኢትዮጵያውያንቅብዓትና ፀጋ” ብሎ አዲስ እምነት አስተማራቸው፡፡ አልፎንዙ ሁለት እሾህ ያላቸው ቅብዓተ እና ፀጋ የተሰኙትን በእርሱ የተፈለፈሉትን ኑፋቄዎች ነበር፤ ይህ ሚሲዮናዊ ቄስ የኢትዮጵያውያን የእምነት ፅናት ገብቶታል፣ የአንድ ክርስቲያን ደም በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን እንደሚፈጥር በታሪክም ሰምቷል በአይን በብሌኑም አይቷል፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል የንዋያተ ቅዱሳት መውደም ኢትዮጵያውያንን ከእምነታቸው አንዲት ጋት ፈቀቅ እንደማያደርጋቸው ተረድቷል፣ የብራናዎቻችንና የመጻህፍቶቻችን መቃጠል የሀገሬን ልጆች ስለሀይማኖታቸው ከማወቅ እንደማያግዳቸው ተገነዘቧል፤... አዎ አንድ ክርስቲያን ሺህ ክርስቲያኖችን በደሙ ሲወልድ በብራና ያሉ ቅዱሳት መፅሐፍቶቻችንና ታሪካዊ መዝገቦቻችን በእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ አዕምሮ ውስጥ ሲታተም፣ ከእንጨት እና ከጭቃ የተሰሩት አብያተ ክርስቲያኖቻችን በልባቸው ውስጥ እንደማይፈርሱና እንደማይቃጠሉ ሆነው ሲገነቡ አልፎንዙ አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰ፤... የኢትዮጵያውያንን ቁሳዊ ዕሴቶች ማጥፋት ለሀገሬ ልጆች ብርታትና ጥንካሬ እየሆናቸው እንደሆነ ተረዳ በዚህም አላበቃም አንድ ዘዴን ዘየደ... መንፈሳዊ ዕሴቶቻችንን የማይጨበጡት የማይዳሰሱት ሀብቶቻችንን ለማጥፋት ለመበረዝ ወሰነ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ጎንደር ሳለ አብረውት የነበሩትን ሁለት ለሆዳቸው ያደሩ ደብተራዎችን ተጠቀመ አንዱን ቅብዐት ብሎ አንዱን ፀጋ ብሎ በዘመናት እየበዙ የሚሄዱ እሾሆችን ዘራባቸው፡፡ አልፎንዙ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መቀመጥ አላስፈለገውም ደግሞም እርግጠኛ ነበር የዘራቸው ኑፋቄዎች ዕለቱን ባይሆን እንኳን ግዜያቸውን ጠብቀው ቅድሰት ቤተክርስቲያንን እሾህ ሆነው እንደሚወጓት... ያኔ ታዲያ ደረቱን ነፍቶ ‹‹ በኢትዮጵያ ሁለት እሾህ ተክዬባታለሁ›› ብሎ እሾሆቹ ሺህ ሆነው እንደሚበቅሉ በመተማመን ከሀገር ወጣ፡፡ 


ከዚያን ግዜ በኋላ የአልፎንዙ እሾሆች በተለያየ መልኩ የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ዕሴቶች ማጥፋት ወይም መበረዝ ዋነኛ አላማቸው አድረገው ተንቀሳቀሱ ፤እንቅስቃሴያቸውም ዘመኑን የመሰለ ነበር... አዎ በእርግጥም ነው፡፡ የአልፎንዙ የግብር ልጆች የዘመኑን ምቹ ሁኔታ እና የእኛን ግዴለሽነት በመጠቀም የተለየ በሚመስል መልኩ አሁንም ወረውናል፡፡ አልፎንዙ ዛሬም አንደዛ ለሆዳቸው ያደሩ የጎንደር ደብተራዎች በቅድሰት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የሷን ጡት የጠቡ... ሀሁ ብላ ፊደል ያስቆጠረቻቸውን ... መልዕክተ ዮሐንስ አስብላ ንባብ ያስተማረቻቸውን ከሀዲ ልጆችዋን በመጠቀም ከውስጧ ሆነው እንዲወጓት እያደረገ ነው፡፡ 

በየዘመኑ የተለያየ ስም እና አካሄድን በመያዝ ቅድስት ቤተክርስቲያንን የሚወጋው የአልፎንዙ እሾህተሐድሶ” የሚል አሻሚና ግራ የሚያጋባ ስም በመያዝ በእኛ ዘመንም በቅሏል፡፡ተሐድሶ” ቃሉ በደፈናው ሲታይ መልካምነት እና አውንታዊ ትርጉም ያለው ይመስላል አንድን ነገር ማደስ ማስተካከል ማረም የሚል አይነት፤ ይህ ፍቺ ለቅድሰት ቤተክርስቲያን ፈፅሞ አይስማማትም ምክንያቱም እሷ አቡነ ፊሊጶስ እንዳሉትታድሳለች እንጂ አትታደስም፣ እሷ የተበላሸውን ታስተካክላለች እንጂ አትስተካከልም፣ እሷ የተሳሳተውን ታርማለች እንጂ አትታረምም”  እርግጥ ነው ተሐድሶያውያኑ ቅዳሴው ረዝሞባቸዋል፣ ፆም ፀሎቱ ያለመጠን በዝቶባቸዋል፣ ገድሉ ደርሳናቱ ቆርቁሯቸዋል፣ የእነዚያ ቅዱሳን አባቶቻችን ድምፅ ሻክሮባቸዋል፣ የቁርባኑና የንስሐው ነገር አቅለሽልሿቸዋል፣ እንደ ስምኦን መሰሪው ፀጋ መንፈስ ቅዱስን በገንዘብ ይሸጡታል፣ የሰበኩትንና ያስተማሩትን መኖር አቅቷቸው አለማዊ ፍርድ ቤቶችን ስለ ክብራቸው የሙጥኝ ብለዋል፣ ትምክህታቸው ጌታችን ሳይሆን እነዚያ ተራ የአራት ኪሎ ወይዛዝርት እና ምድራዊ ባለስልጣናት ናቸው፣ መዝሙሩን ከዘፈን ደባልቀው ምዕመኑን ግራ አጋብተውታል፣ የሚሲዮናውያኑ ገንዘብ አቅላቸውን አስቷቸዋል፣ እንደ አለቃቸው አልፎንዙ በየመንደሩ እና በየአዳራሹ በግል እና በቡድን ኑፋቄን እየዘሩ ነው፤ ወደድንም ጠላንም የአልፎንዙ እሾሆች ከምንግዜውም በላይ በእኛ ዘመን እየተሳካለቸው ይገኛል፡፡ ይህ የቅሰጣ ተግባር በዚሁ ከቀጠለ ቅድሰት ቤተክርስቲያንን ከነሙሉ ክብሯ እና አቅሟ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፏ አጠራጣሪ ይሆናል፡፡ ይህ አይሆን ዘንድ ከእኛም ከምዕመናኖች ሆነ ከትክክለኞቹ የቤተክርሰቲያኒቱ አመራሮች ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሔር ቅድሰት ቤተክርስቲያን ላይ የተተከለውን የአልፎንዙ እሾህ ነቅሎ ቤተክርስቲያን ከነሙሉ ክብሯ እና አቅሟ ለቀጣዩ ዘመን ያሸጋግር ዘንድ ይህ ትውልድ በእግዚአብሔር ዘንድ ተመርጧል... ይህ ትውልድ እምቢኝ አሻፈረኝ ባለ ግዜና መዳን ለቅድሰት ቤተክርሰቲያን ከሌላ ወገን በሆነ ግዜ ይህ ትውልድ ከእግዚአብሔር ቅጣት አያመልጥም፡፡ 

...
ትዝ ይላችሁ እንደሆነ መፅሐፈ አስቴር ላይ... አስቴር በወገኖቿ ላይ የተላለፈውን የሞት አዋጅ እንድታሽር መርዶክዮስ ባስጠየቃት ግዜ አጉረመረመች... የአስቴርን ማጉረምረም የተመለከተው መርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልዕክት ሰደደላት ... “በዚህ ግዜ ቸል ብትይ ረድኤት እና መዳን ለአይሁድ ኬላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፣ አንቺ እና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤...”

ከፅዮን ምህረት ለኢትዮጵያ

7 comments:

  1. እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን! አፅራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን! በሃይማኖታችን እስከ መጨረሻው ጸንተን የመንግሥቱ ወራሽ የክብሩ ቀዳሽ ለመሆን ያብቃን! አሜን!

    ReplyDelete
  2. ሰላም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦች :-

    ከአምሥቱ የሥደትና የጥፋት ዘመኖች በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ በእኛ ትውልድ የተፈጠሩትንና እግዚአብሔርን በካዱ የኮሚኒስት አገዛዞች የተደረጉትን የኢትዮጵያን ክርስቲያኖችን የመሣደድ ዘመኖች ማካተት ያሻል ብዬ አምናለሁ :- የደርግን የአጽራረ -ቤተክርስቲያን ዘመን እንዲሁም የአሁኑን በዘር ክፍፍል እና በአፅራረ -ቤተክርስቲያን ላይ የቆመውን የወያኔን የጨለማ ዘመን ::

    ReplyDelete
  3. አንድ የጽሁፍ መርማሪ ስለ ተሃድሶ ምንነት ለማወቅ የተመለከቱበትን መመዘኛ ፣ ማንነቱን ለመረዳቱ የሞከሩበትን ስልት አንባቢ ቢመለከተው መልካም ይሆናልና የመክፈቻ አድራሻው ይኸው

    http://kassahunalemu.wordpress.com/2012/03/20/

    ReplyDelete
  4. እየሰማንና እያየን ይሄ የእነ እገሌ ዉንጀላ ነዉ እንጅ እነ እገሌ ችግር ኖሮባቸዉ አይደለም እያልን ግራ የምንጋባ፣ ሀቁን ለማወቅ የማንጥርና በስሜት የመንነዳ ከሆነ ጥፋታችን ይፋጠናል፡፡ ይህ ትውልድ እምቢኝ አሻፈረኝ ባለ ግዜና መዳን ለቅድሰት ቤተክርሰቲያን ከሌላ ወገን በሆነ ግዜ ይህ ትውልድ ከእግዚአብሔር ቅጣት አያመልጥም፡፡

    ReplyDelete
  5. ትዝ ይላችሁ እንደሆነ መፅሐፈ አስቴር ላይ... አስቴር በወገኖቿ ላይ የተላለፈውን የሞት አዋጅ እንድታሽር መርዶክዮስ ባስጠየቃት ግዜ አጉረመረመች... የአስቴርን ማጉረምረም የተመለከተው መርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልዕክት ሰደደላት ... “በዚህ ግዜ ቸል ብትይ ረድኤት እና መዳን ለአይሁድ ኬላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፣ አንቺ እና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤...”

    ReplyDelete