Saturday, February 9, 2019

‹‹የቤተ-ክርስቲያን ደውል ተደውሎ ቤት አልቀመጥም›› ብሎ አምልጦ በወጣ ወዲያው “ልጅሽ ሞተ› ተብሎ ተነገረኝ



(አንድ አድርገን የካቲት 03 2011 ዓ.ም )፤- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 21 የሚከበረው የአስተርእዮ ማርያም በዓት ዕለት በሱማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅግጅጋ ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡ ከጅግ-ጅጋ ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ተነስተው 110 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝው እጅግ ጥንታዊቷ ገሪ ቆጨር ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ተጉዘው መንፈሳዊ በዓሉን አክብረው በመመለስ ላይ ያሉ የጅግ-ጅጋ ከተማ ምዕመናን ‹‹ዱደሂሳን›› የሚባል ቦታ ላይ ሲደርሱ ከሱማሌ ገሪ ጎሳ የተወጣጡ ግለሰቦች “የጃርሶ ጎሳ አባላት ከመካከላችሁ አውጡ” በማለት በአራት የሕዝብ መኪናዎች ላይ የድንጋይ ናዳ ማውረድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጥቃት ምክንያት የአንዲት እናት ጥርስ ከመርገፍ ጀምሮ  በአራቱም መኪናዎች ላይ የሚገኙ ምዕመናኖች ላይ  ጉዳት በመድረሱ በጅግ-ጅጋ በዕለቱ ከፍተኛ ውጥረት ሊነግስ አንደቻለ በግጭቱ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለመረዳት ችለናል፡፡


የዚህ ድንገተኛ ጥቃት የተነሳ ግራ የተጋቡት ሦስቱ አውቶቡሶች ወደ ኋላ በመመለስ ያፈገፈጉ ሲሆን ፡፡ አንዱ አውቶቡስ ግን በውስጥ ለውስጥ በእርሻ መሬት አሳብሮ ጅግ-ጅጋ ከተማ ሊገባ ችሏል፡፡  ይህንን በምዕመና ላይ ጥቃት መድረሱን በከተማው ሲሰማ “ወገኖቻችን አለቁ” በማለት የተወሰኑ የጅግ-ጅጋ ከተማ ወጣቶች ድንጋይ ደርድረው መንገድ በመዝጋት ተቃወሙ፡፡ በዚህ ጊዜ በፓትሮል ተጭነው የመጡት የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ተኩስ በመክፈታቸው የሁለት ታዳጊ ወጣቶች ሕይወት ያለፈ ሲሆን በሁለት ግለሰቦች እንዲሁም በልዩ ኃይል እና በወጣች መካከል የነበረው ፍጥጫ ለማብረድ ያህል ገብተው ከነበሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ለመረዳት ችለናል፡፡

“መንታ ወንድሜን ነው የገደሉብኝ”
በጥር 21 ግጭት በሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከተገደለው ወጣት አንዱ የሆነው የ22 ዓመቱ ኪሩቤል ድባቡ ነው፡፡ ኪሩቤል ከወላጅ አባቱ እና ከመንትያ ወንድሙ ጋር በከተማው አስተዳደር የውሃ ስራ ላይ በመስራት ነበር ሕይወታቸውን የሚመሩት፡፡ “22 ዓመታችን ነው ፤ መንትዮች ነን ፤ ጎረቤት የማርያም ጽዋ ስለነበር ምሳ አንድ ላይ በልተን  ከቤት እንደወጣን አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ  ነው መንታ ወንድሜን የገደሉብኝ” በማለት የኪሩቤል መንትያ ወንድም ከእንባው ጋር  እየታገለ የዕለቱን ሁኔታ አስረድቶናል፡፡ “እኔ የሰማሁት ነገር አልነበረም ፤ ከቤት ስወጣ ከተማ ውስጥ ግርግር ተፈጥሯል፤  ተኩስ በተኩስ ነው.. ሆስፒታል ሄጄ ባፈላልግ ወንድሜን አጣሁት” ያለን የሟች ኪሩቤል ወንድም ፤ በዕለቱ ከሰዎች እንደተረዳነው ግን ወንድሙ በጥይት ከተመታ በኋላ  ወደ ካራማራ ሆስፒታል ተወስዶ የነበረ ቢሆንም  በዚህ ግጭት መመታቱን ያወቁ ፖሊሶች  ወደ ሆስፒታሉ እንዲገባ ባለመፍቀዳቸው ወደ ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ሪፈራል ሆስፒታሉም ‹‹ሐበሾች ናችሁ›› በሚል ቅድሚያ ባለማግኝቱ ደሙ ፈሶ ሕይወቱ ሊያልፍ እንደቻለ ተነግሮናል፡፡

“ዱላ ሲገባው ጥይት ሰጥተው የ22 ዓመቱን ልጄ በአጭሩ ቀጭተውብኛል”  ያሉን የኪሩቤል ወላጅ አባት አቶ ድባቡ “አዲሱ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር ጥሩ መሪ ይመስሉኛል ፤ ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል ፤ በዚህ ሰዓት ብዙ ወንጀለኞችን ለፍትሕ እያቀረቡ እንዳሉት ለእኔም ፍትህ እንዲሰጡኝ እጠይቃለሁ የልጄን ደም እፈልጋለሁ” ብለውናል፡፡

በክልሉ ምንም ዓይነት ፍትሐዊነት እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ድባቡ “ልጆቻችን ትምህርት ተምረው ፤ ቋንቋ ችለው የትም ቢሄዱ የመስራት መብት እንኳን የላቸውም ፤ ልጆቻችንን የት እናድርጋቸው? ወዴት እንክተታቸው? የስራ  እድል የላቸውም ፤ bማሕበራዊ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ የላቸውም ፤ አሁን ደግሞ የሚገደሉበት ምክንያት ምንድነው? መንግሥት መሳሪያ ያስታጠቃቸው ድንበር እንዲጠብቁ እንጂ ወገን እንዲያጠቁበት ነው ወይ? እኛስ አርጅተናል ፤ ከዚህ በኋላስ ልጆቻችንን ምንድነው የሚጠብቃቸው? በማለት አዲሱ የክልሉ መንግስት በአፋጠኝ ለልጃቸውን ደም ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

“ተንከራትቼ ባሳደኩት ልጅ መጡብኝ”
በሐዘን ላይ ተቀምጠው ያገኝናቸው ሌላኛዋ እናት ወ/ሮ ቀለሟ ሙሉጌታ ይባላሉ ፤ ጥር 21 ላይ በሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በተተኮሰ ጥይት የተገደለው ልጃቸው ተመስገን የ16 ዓመት ብላቴና እና 9ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ “በዕለቱ ልጄ ተመስገን እስከ 8 ሰዓት ድረስ አጠገቤ ነበር የዋለው” ያሉት ወ/ሮ ቀለሟ “ጥቃት የደረሰባቸው ምዕመናን ከጨቆር ሲመጡ ቤተ-ክርስቲያን ተደወለ ፤ ወጣቱ ሆ ብሎ ወጣ ፤ በዚያ ሰዓት ልጄ ‹የቤተ-ክርስቲያን ደውል ተደውሎ ቤት አልቀመጥም› ብሎ አምልጦ በወጣ በጥቂት ሰዓት ልዩነት ‹ልጅሽ ተመታ› ሲሉኝ አላመንኩም ነበር ፤ ወዲያ ደግሞ ‹ልጅሽ ሞተ› ተብሎ ተነገረኝ” ብለው በዕለቱ የተፈጠረውን ተገር በለቅሶ ነግረውና፡፡ የ16 ዓመቱ ልጃቸው ተመስገን ከአንድ ዓመቱ ጀምሮ ካለ አባት እንዳሳደጉት የነገሩን ወ/ሮ ቀለሟ  “ዛሬ እዚህ ልብስ እጠቢ ሲሉኝ እየሄድኩ ፤ ነይ እንጀራ ጋግሪ ስባል እየበረርኩ ሄጄ ያሳደኩበትን ድካም እግዚአብሔር አልቆጠረውም ፤ ተንከራትቼ ባሳደኩተ ልጄ መጡብኝ” ሲሉ ሀዘዘናቸውን በመሪር ነግረውናል፡፡
“እናታችን ያለ አባት ፤ ያለ ዘመን በድህነት ነው ያሳደገችን” ያለችን የሟች ተመስገን እህት እሙዬ አሁን የሚኖሩበት ደሳሳ የቆርቆሮቤት በጎ ሰዎች አስጠግተዋቸው እንደሚኖሩ ፤ የእናቷ የወ/ሮ ቀለሟ አቅምም እየተዳከመ መምጣቱን አንድ ዐይናቸው ማየት እየተሳነው እንደሆነ ነግራናለች ፤ “እኛ ድኾች ነን ፤ አቅም የለንም ! የአቶ ሙስጠፌ መንግሥት በአፋጣኝ የወንድሜን ገዳዮች ለፍርድ ያቅርብልኝ! ፍትሕ እንፈልጋለን ብላለች፡፡

ምንጭ፡- ፍትሕ መጽሔት አንደኛ ዓመት ቁጥር 14 ፤ የካቲት 03 2011 ዓ.ም   

9 comments:

  1. We absolutely love your blog and find a lot of your post's to be exactly what I'm looking for.
    Do you offer guest writers to write content in your case?

    I wouldn't mind publishing a post or elaborating on many of
    the subjects you write regarding here. Again, awesome website!

    ReplyDelete
  2. These are truly impressive ideas in regarding blogging.

    You have touched some nice things here. Any way
    keep up wrinting.

    ReplyDelete
  3. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  4. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  5. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  6. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  7. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  8. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete
  9. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete