የሊቅነቱን ማዕርግ ከፍ አድርገው ከሰቀሉት የቅርብ ጊዜ ሊቃውንት እንደ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ያለ ስመ ጥር አላውቅም፡፡ ሊቅነትን ከምግባረ ሃይማኖት አስተጻምረው፣ አዋሕደው እና አስማምተው የያዙ ዐይናማ ሊቅ ናቸው፡፡ እኒህ ኹለቱን አንድ ላይ ለማስኬድ ብዙ ጊዜ መቸገር አለና! በአካለ ሥጋ በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. ከእኛ ቢርቁም ደማቆቹ የብርዕ ትሩፋቶቻቸው ዛሬም ያበራሉ፡፡ ኵኲሐ ሃይማኖትን እና መድሎተ አሚንን እንደ መጻሕፍተ ሊቃውንት ያልተመለከተ ሊቅ ይኖራል ብሎ መድፈር አይቻልም፡፡ በጽሑፋቸው ውስጥ የሊቁን የትሕትና ቁመና ስንመለከት እጅ እንነሳዋለን፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ወደር የማይገኝለት የሚንቀለቀል ቅናትም ያሳዩናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነገረ መለኮት ትምህርታቸው እንዴት የረቀቁ ሊቅ እንደነበሩ ቁልጭ ብለው ይነበባሉ፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የኾነው ሥራቸው ዛሬም እንደመብራት ያበራል፡፡ የክህደትን ጨለማ ይገላልጣል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ትጋት የሚባለውን ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡ በሽልማታቸውም መልሰው ሸልመውናል፡፡ በደረቡልን ካባ ሲበርደን እንሞቅበታለን፤ ሲሞቀን እንበርድበታለን፡፡
እንደ ማንኛውም የቤተ ክህነት አገልጋይ ሲወጡ ሲገቡ አልከረሙም፡፡ ከሚጠበቅባቸው አልፈው ሔደዋልና፡፡ ሊቅ ናቸው፣ ደራሲ ናቸው፣ ቅድስና አላቸው፡፡ እነዚህ ሦስቱ የሚሟሉለት እንዲሁ በቀላሉ አይገኝም፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ ስለኾኑ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን ከአስመሳዮች እና ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን በጥብዐት እና በሊቅነት ተከላክለው መክተዋል፡፡ በመንፈስም "መብረቅ ይወልድ መብረቀ" እንዲል መጽሐፍ መብረቅ የኾኑትን አለቃ አያሌውን የሚያኽሉ ጉምቱ ሊቅ ተክተዋል፡፡ ተናግረው የሚደመጡ፣ ጽፈው የሚረቱ እኒህን አባትና ልጅ ማየት የጸጋውን ብዛት ያሳያል፡፡
ሙት እስከ ማስነሣት የደረሱ የዘመናችን ቅዱስ ሐዋርያ ናቸውና፡፡ ገድል አልተጻፈላቸውም እንጂ ሌላም ይኖር ይኾናል፡፡ እንዲሁ ደርሶ ሙት እስከማስነሣት አይደረስምና፡፡ የካቶሊካውያንን አንገታቸውን ሰብረው ዝቅ እንዲሉ ያደረጉት ሊቅ የአሁኑ ትውልድ የቱን ያኽል እንደሚያውቃቸው ግልጽ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያውያኑ አባ ዝክሪ እና አባ ጳውሊ፣ በዕጨጌ በትረ ጊዮርጊስ፣ በቦሩ ሜዳው አካለ ወልድ ደግሞም በአለቃ ኪዳነ ወልድ (በቦሩ ሜዳው ክርክር በአፈ ጉባኤነት የቀረቡት ሲኾኑ ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይለያሉ)፣ አለቃ ተክለ ሥላሴ እና መልአከ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ እየተደጋጋመ አናት አናቱን የተቀጠቀጠው የካቶሊክ እና የዘርፎቹ (ቅብዓት እና ጸጋ) እምነት እንዳያገግም ግብአተ መሬቱ የተፈጸመው በዐይናማው ሊቅ አድማሱ ጀንበሬ ጽኑ ተጋድሎ ነው፡፡ ዛሬ ጊዜ ዐይተው ውርውር ማለትን የጀመሩ እንዳሉ ቢታወቅም መቃብራቸው ግን ከተቆፈረ ረፍዶባቸዋል፡፡
እነዚህን ለመሳሰሉ ሊቃውንት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸው ቦታ አነጋጋሪ መኾኑ ይሰማኛል፡፡ ለአንዲት ቅድስት ንጽሕት ተዋሕዶ ያደረጉት ተጋድሎ ለግላቸው እንዳደረጉት ይመስላል፡፡ ስማቸው ከታላላቆቻችንም ከእኛም ከተከታዩም ትውልድ እየተረሳ በከፍተኛ ፍጥነት እየሔደ ይታያል፡፡ አስኪ ምን ማድረግ እንደሚገባን ቆም ብለን እናስብ? መሠረቱ ከሌለ የሚያምረውን ጉልላት ማየት አይቻልም፡፡
አጣዳፊው ጥሪ ግን የዐይናማው ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ አጥማቸው ሊፋረደን አደባባይ ሳይወጣ፣ ታሪካዊ ዕዳ በግንባራችን ላይ ሳይጻፍ በቀረችን ጥቂት ጊዜ በረከታቸውን እንደ ብርሃን እንድንለብሰው የሚተላለፈው አደራ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የታነጸው የእግዚአብሔር ወልድ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እዚያ ቅጽረ ግቢ ውስጥ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የመቃብር ስፍራ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽሩን ለማስተካከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ይህ የሊቁ መቃብር ይነካል፡፡ በዚህም የተነሣ አንሡልኝ ያለበለዚያ እኔ ራሴ አንሥቼ ሥራየን እሠራለሁ ሲል በማስታወቂያ ለፍፎ ነበረ፡፡
ለመውቀስ ከኾነ ብዙ የሚወቀሱ አካላት አሉ፡፡ እኒህን እንደ ፀሐይ የደመቁ ሊቅ ቤተ ክርስቲያን ለማንም ልትሰጣቸው አትችልም፡፡ የተጋደሉላት ለእርሷየሞቱላትም ለእርሷ ነውና፡፡ እንደማንም ተራ ግለሰብ አጽማቸው ክብር ሳይሰጠው ሊፈልስ አይችልም፡፡ እናንተ ዝም ብትሉ . . . ነውና ነገሩ፡፡ ክብርነታቸው ለራሳቸው ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ለራሳቸው አልኖሩም፤ ለቤተ ክርስቲያናቸው እንጂ፡፡ ሀብትነታቸውም ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ ቤተ ሰቦቻቸውም ቢኾኑ እንደ እኛ እንጂ ቅርበታቸው ከእኛ የተለዩ አይደሉም፡፡ እናም በክብር ፍልሰተ አጽማቸው ይከናወን ዘንድ ግድ አለብን፡፡ መጽሐፍ ሁሉም ለበጎ ነው እንዲል እግዚአብሔር አጽማቸውን እንሳለመው ዘንድ ዕድል ሰጥቶናል፤ በዚህ እናመሰግነዋለን፡፡ ስለዚህ የውስጣችንን በውስጣችን ይዘን ብርሃናዊውን ሊቅ እናድምቃቸው፡፡ በገንዘብ፣ በሐሳብ እንደጋገፍ፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክሕነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በጉዳዩ ላይ እያሰቡበት እንደኾነ ሰምተናል፡፡ እንዲህ ነው እንጂ፡፡ የማይረሳ አይረሳም፡፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃምም ከማሳሰብ ጀምሮ በአንክሮ ይኾን ዘንድ ይዘውታል መባልን ሰምቻለሁ፡፡ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አለቃም ያስቡበት ዘንድ ምክረ ሐሳብ ከሥራ አስኪያጁ ተለግሶላቸዋል፡፡ ከኾነም ላይቀር እንዲህ ሲኾን ያምራል፡፡ ጀግናውን ሊቅ በጀግንነት ማዕርግ እናክብራቸው፡፡ በእርግጥ እርሳቸው ከመቃብር በላይ ናቸው፡፡ አጽማቸው በረከት አለውና እንደ አልባሌ አይተውም፡፡
ለክብራቸው በሚመጥን ደረጃ ፍለሰተ አጽሙ ይከናወን ዘንድ ከወዲሁ ይህንን ጉዳይ የሚከታተል አካል ቢዋቀር፡፡ ከበጎ ፈቃደኞች (አሁንም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉ አሉና)፣ ከቤተ ክሕነት፣ ከቤተ ሰቦቻቸው እና ቢቻል ከታላቁ ገዳም ከድማህ ጊዮርጊስ የተውጣጣ ጉዳይ አስፈጻሚ ቢዋቀር ሠናይ ይኾናል፡፡ ከፍልሰተ አጽሙ በተጨማሪ በወጉ የሚዘከሩበት ዕድል አላገኙም እና በልዩ መርሐ ግብር የሚዘከሩበት መንገድ መኖሩ አያጠያይቅም፡፡ የሁሉ እንደኾኑ የምናይበት መድረክ መዘጋጀት አለበት፡፡ ወደፊትም ስማቸው፣ ሥራቸው እና ክብራቸው እንዴት ይሁን የሚለውም ውይይት ይፈልጋል፡፡ ከሰነበተው ዝምታችን ዛሬ የምንሠራው ይልቅ ዘንድ፡፡
አስኪ እኔ ይህን አልሁ እርስዎስ ምን ይላሉ? የጎደለውን ሞልተን መልክ እናስይዘው፡፡ የቀበርናቸውን ሊቃውንት ከፍ እናድርጋቸው !!!
Thanks Dn Abayneh for the useful information.
ReplyDeleteThis is not only about Ethiopian Orthodox Tewahedo Church; it is about all Orthodox and who ever else who believe the right faith about our Savior Jesus Christ and about the fraud people-Catholic...
Our Holly Synod should officially recognize Him as national and as a greatest thinker scholar in this century, and should translate his valuable book