17 Jun, 2017
By ምሕረተሥላሴ መኰንን
- << በቅርሶች ጥበቃ ሁሉም አካል መረባረብ ያለበት ሲሆን፣ ትውልዱም ለታሪኩና ለባህሉ ተቆርቋሪ መሆን ይገባዋል፡፡ ከየቤተ ክርስቲያኑና የሚሰበሰቡ ቅርሶች በአግባቡ ካልተጠበቁ ዋጋ የለውም፡፡ አሳልፈን እየሰጠናቸው ያለነው እኛው ነን፤›› አባ ብስራተአብ
ኢትዮጵያ በዓለም የሥነ ጽሑፍ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ጥንታውያን መጻሕፍትና የነገሥታት ደብዳቤዎች መካከል የ14ኛው ክፍለ ዘመን አርባዕቱ ወንጌል፣ የ15ኛው ክፍለ ዘመን የጳውሎስ መልዕክቶች፣ የ15ኛው ክፍለ ዘመን ግብረ ህማማትና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኅትመት መጽሐፍ መዝሙረ ዳዊት ይጠቀሳሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በተዘዋዋሪ ከመዘገበው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ያደረጉት ንግግር በተጨማሪ ሦስት የነገሥታት ደብዳቤዎችም (አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ የላኩት ደብዳቤ፣ አፄ ምኒልክ ለሞስኮው ቄሳር ዳግማዊ ኒኮላስ የላኩት ደብዳቤና ከሸዋው ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ለእንግሊዟ ንግሥት የተላከው ደብዳቤ) ተመዝግበዋል፡፡ አምስቱ በማይክሮ ፊልም የተቀረፁ ጥንታውያን መጻሕፍት ደግሞ ታሪክ ዘ ምኒልክ፣ መጽሐፈ ሔኖክ፣ ታሪክ ነገሥት፣ ቅዳሴና ፍትሐ ነገሥት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ቅርስ ከሆኑት እነዚህ ጥንታውያን መጻሕፍት ባሻገር የበርካታ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊዶችና ሌሎችም የእምነት ተቋሞች የቅርሶቹ ቀዳሚ መገኛ ሥፍራ ናቸው፡፡ ጥንታውያኑ መጻሕፍት አገር በቀል ዕውቀትን አምቀው እንደመያዛቸው ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው መረጃ የሚሸጋገርባቸው ድልድዮችም ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ቅርሶች በተመቻቸ ቦታ ባለመቀመጣቸውና ተገቢው ጥንቃቄ ስለተነፈጋቸው ይዘታቸውን ወደ ማጣት እየተቃረቡ ነው፡፡
በጥንታውያን ገዳማትና መስጊዶች የሚገኙ የጽሑፍ ቅርሶች ምዝገባ ሒደትም ብዙ ክፍተት አለው፡፡ ምን ዓይነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት፣ በምን ያህል መጠን፣ በየትኛው ተቋም፣ እንደሚገኙ አለመታወቁ ቅርሶቹ ለስርቆት ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ለጉብኝት፣ ለጥናትና ምርምርና ሌሎችም ምክንያቶች ወደ አገሪቱ የሚመጡ ግለሰቦች ለስርቆቱ ቀዳሚ ተጠያቂ ሲሆኑ፣ ዜጎችም የቅርስን ዋጋ ባለመገንዘብና በገንዘብ በመደለል ይተባበራሉ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በቀዳሚነት በእንግሊዙ ጄኔራል ናፒርና በፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ወቅት የጽሑፍ ቅርሶችን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች ከአገሪቱ ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች በአውሮፓ ሙዚየሞች፣ በቤተ መጻሕፍትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞችም ይገኛሉ፡፡ በጦርነት ወቅት ቅርሶች እንዳይዘረፉና ከተሰረቁም ለባለቤት አገሮች የሚመለሱበት ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ቢኖርም፣ ቅርሶችን የማስመለስ ሒደቱ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ በእርግጥ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመለሰቻቸው ቅርሶች ቢኖሩም፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ካለው የቅርስ ክምችት አንፃር እምብዛም አይደሉም፡፡ ቅርሶችን ከማስመለስ ውጣ ውረድ ከስርቆት መከላከሉ መቅለሉም እሙን ነው፡፡
ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት፣ የተሰረቁ ጥንታውያን መጻሕፍትን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው፣ በሕገወጥ መንገድ የጽሑፍ ቅርሶችን ከአገሪቱ የሚያስወጡ አካሎች መኖራቸው ተመልክቷል፡፡ ቅርሶቹን የሸበቧቸው ችግሮች ከአቀማመጣቸው ይጀምራሉ፡፡ አብዛኞቹ ለሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከአያያዝ ጉድለት ጋር በተያያዘ ለስርቆት መጋለጣቸውም ተያይዞ ይነሳል፡፡
የኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ መምህር አልማው ክፍሌ (ዶ/ር) ዐውደ ጥናቱን በመሩበት ወቅት፣ ‹‹የማንነት መገለጫ የሆኑ ቅርሶች አንዴ ከጠፉ ሊመለሱ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የጽሑፍ ቅርሶች በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በጣልያን፣ በፈረንሣይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቻይና ተወስደዋል፡፡ የቀሩትን መታደግ አለብን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በዐውደ ጥናቱ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ የጽሑፍ ቅርሶችን ሕገወጥ ዝውውር ለመግታት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችና ቅርሶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስመዝገብ ከስርቆት ለመታደግ የሚወሰደው ዕርምጃ ተዳሰዋል፡፡
በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ የመዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ኤክስፐርት መምህር ኃይለሚካኤል ጌታሁን፣ ‹‹የጽሑፍ ቅርሶች ሕገወጥ ዝውውርን ለመከላከል ያሉን የሕግ ማዕቀፎች›› የተሰኘ ጥናት አቅርበዋል፡፡ አጥኚው እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያ ከዓለም መዝገብ ስማቸው ጠፍቶ የነበረውን መጽሐፈ ሔኖክ፣ የእረኛው የሔርማ መጽሐፍና ሌሎችም ቅርሶችን በባህላዊ ቤተ መዛግብቷ፣ በዋሻና በከርሰ ምድር ውስጥ ከወራሪዎች ዘረፋ ደብቃና ጠብቃ አኑራለች፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ባህልና፣ ታሪክ እንዲሁም የማንነት መገለጫ የሆኑት የመረጃ ሀብቶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ ለሕገወጥ ዝውውርና ዘረፋ ተጋልጠዋል፡፡
አጥኚው እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት በዛላንበሳ ከተማና ጅማ ከተማ ከውጪ የመጡ ግለሰቦች በዲጂታል ካሜራና በማይክሮ ፊልም አንስተው ቅርሶችን ያለ ሕጋዊ ፈቃድ መውሰዳቸውን ነው፡፡ እነዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከሚፈጸሙ ስርቆቶች በተጨማሪ ቅርሶችን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ለማስወጣት ሲሞከሩ የተያዙም አሉ፡፡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በኩል ተይዘው በፖሊስ ለኤግዚቢትነት የተቀመጡ 65 ቅርሶች እንዳሉ መምህሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ቀድሞ የተዘረፉ የጽሑፍ ቅርሶች ሐዘንና ቁጭት ሳይለቀንና በተለያዩ አገሮች ያሉ ቅርሶቻችን ሳይመለሱ፣ አሁንም ሕገወጥ የቅርሶች ዝውውር ተጧጡፏል፤›› የሚሉት አጥኚው፣ የቅርስ ባላደራ መሥሪያ ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ኅብረተሰቡም ለጉዳዩ ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት የጽሑፍ ቅርሶችን በያሉበት መካነ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ከማድረግ ባሻገር፣ ባለው የሕግ ማዕቀፍ ሕገወጥ የጽሑፍ ቅርሶች ዝውውር እንዲገታ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ቅርሶችን መጠበቅ አገራዊ ግዴታ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የታተመው የባህል ፖሊሲም ዓለም አቀፍ ደረጃውንስ ለጠበቀ የቅርሶች አመዘጋገብ ያትታል፡፡ ጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች አጠባበቅ፣ የመጻሕፍት አጠራረዝ (ድጎሳ)፣ የአጻጻፍ ሥልትን የመሰነድና የማጥናት ኃላፊነቱም ተገልጿል፡፡
የአብያተ ክርስቲያናት፣ የገዳማት፣ የመስጊዶችና ሌሎችም ቤተ እምነቶችን የቅርስ ሀብት ጠብቆ ለትውልድ ከማስተላለፍ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከአገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚደረግም በፖሊሲው ተመልክቷል፡፡ አዋጅ ቁጥር 209/1992
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ቅርሶችን የመመዝገብ፣ የመንከባከብ፣ የመጠበቅ፣ ስለ ቅርሶች መረጃ የመስጠት እንዲሁም በልዩ ልዩ ሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ የተወሰዱ ቅርሶች ወደ አገር ውስጥ የሚመለሱበትን መንገድ የማመቻቸት ግዴታ ጥሎበታል፡፡
የብራና ጽሑፎች፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎችና ሥዕሎች ለሕገወጥ ዝርፊያ ተጋላጭ ከሆኑ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ቅርሶቹን የማሰባሰብ፣ የመጠበቅና ለጥናትና ምርምር ክፍት የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ተቋሙ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን በዲጂታል ካሜራና በማይክሮ ፊልም የመቅዳት ግዴታም ተጥሎበታል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ እንደሚናገሩት፣ መሥሪያ ቤቱ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ከ11 ዓመት በፊት ስምምነት ከተፈራረመ በኋላ የብራና ጽሑፎች ከአገር እንዳይወጡ በመከልከሉ ዝውውሩ ተገቷል፡፡ ‹‹በማናውቀው መንገድ ካልወጣ የብራና መጻሕፍትን ግለቦችና ተቋምም ይዞ አይወጣም፤›› ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሩ በሕገወጥ መንግድ ቅርስ ለማዘዋወር ሙከራዎች ሲደረጉ የተያዙባቸው ጊዜዎች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት እስላማዊ የሥነ ጽሑፍ ሰነድ በዲሌችኤል ከአገር ሊወጣ ሲል ተይዟል፡፡ አምና በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ አሥር የብራና መጻሕፍትም ተይዘዋል፡፡ አምና በአንድ የገፀ በረከት መሸጫ መደብር 65 ጥንታውያን መጻሕፍት ለገበያ ቀርበውም እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
በአቶ ኤፍሬም ገለጻ፣ ቅርሶችን ያለፈቃድ በዲጂታል ካሜራና ማይክሮ ፊልም ቀድቶ ወደ ውጪ ማውጣትም ሌላው የችግሩ ገጽታ ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከጽሑፍ ቅርሶች ጋር በተያያዘ ማን፣ የት ቦታ፣ ምን ዓይነት ጥናት እንደሚያካሂድ የማወቅ ሥልጣን ቢኖረውም፣ ያለመሥሪያ ቤቱ ዕውቅና በርካታ ምርምሮች ይከናወናሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከክልል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ቢሮዎች ጋር በመጣመር መረጃ ለማሰባሰብ ቢጣጣሩም፣ ያለመሥሪያ ቤቱ ዕውቅና ጥናት የሚያካሂዱ ብዙ ናቸው፡፡
የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1970 የወጣው ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ጥሩ ቢሆንም ቅርሶችን ማስመለስ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይጠይቃል፤›› ይላሉ፡፡ ብዙ ከሥነ ጽሑፍ ውጪ ያሉ ቅርሶችን ወደ ኢትዮጵያ ማስመለስ ቢቻልም፣ ጥንታውያን መጻሕፍትን በማስመለስ ረገድ ሰፊ ክፍተት አለ፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር የምትፈራረማቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች ቅርሶችን ማስመለስንም እንዲያካትቱ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ቢገልጹም፣ በርካታ አገሮች ቅርሶችን ለባለቤት አገሮች ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ እንደ ራሳቸው ቅርስ የሚቆጥሯቸው አገሮችም አሉ፡፡ ዓምና ከለንደንና ከስዊድን የብራና ጽሑፍና ሥዕል መመለሱን አስታውሰው፣ በኤምባሲዎች በኩል ቅርስ የማስመለስ ሥራው መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ቅርሶችን ከአገር ለማውጣት ከሚመርጧቸው መንገዶች መካከል በሕግ እንዳይፈተሹ ፈቃድ የተሰጣቸው (ኢምዩኒቲ ያላቸው) ግለሰቦችን መጠቀም ነው፡፡ በቁጥጥሩ ረገድ ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስዱት ቅርሶቹ የሚገኙባቸው ተቋማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ኅብረተሰቡ በመሆኑ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡
አሁን ያለው የቅርስ ምዝገባ የአንድን የሥነ ጽሑፍ ቅርስ አሠራር፣ ይዘትና ልዩ ባህሪያት በዝርዝር እንደማያስረዳ አቶ ኤፍሬም ይገልጻሉ፡፡ የቅርስ ምዝገባ ሒደት ለቁጥጥር ያለውን አስተዋጽኦ ገልጸው፣ በሒደቱ ቅርሶቹ የሚገኙባቸው ተቋሞች መተባበር እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ በነባራዊው ሁኔታ፣ በተለይም የሃይማኖት ተቋሞች ጥንታዊ የሥነ ጽሕፍ ቅርሶችን በዘመናዊ መንገድ ለመጠበቅና ለመገጠን የሚያሳዩት ተነሳሽነት አናሳ ነው፡፡ በዚህ ክፍተት ደግሞ መዝባሪዎች እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ‹‹በድህነት ሳቢያና ያልተገባ ጥቅም በመፈለግ ለዝርፊያው የሚተባበሩ ሰዎች አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥንታዊ ቅርሶችን የሚሰበስቡ (አንቲክ ኮሌክተርስ) መበራከታቸውም ችግሩን አባብሶታል፤›› ይላሉ፡፡
በሕጉ መሠረት ቅርስ ከአንድ ወገን ለሌላው ሲተላለፍ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማወቅ አለበት፡፡ ቅርሶችን ከአገር ማውጣት ፈጽሞ ቢከለከልም ፈቃድ ተሰጥቶ፣ ለጥናት፣ ለዐውደ ርዕይና የባህል ልውውጥ ዓላማ መውጣት ይችላል፡፡ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001
ለማዘዋወር በተከለከሉ ዕቃዎቹ ዝርዝር ሥር የሚካተቱትን ቅርሶች፣ ፈቃድ ከተሰጠው አካል ውጪ ማዘዋወር አይቻልም፡፡ የገንዘብና ከሰባት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀልም ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ሕግጋት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ለመጠበቅ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ተቀብላለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1954 የተደነገገው ከስምምነቶቹ አንዱ ሲሆን፣ በጦርነት ወቅት ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚከላከል ሰነድ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሌሎች የዩኔስኮ ስምምነት ፈራሚ አገሮች ጋር በጦርነትና በሌሎችም ምክንያቶች የተወሰዱ ቅርሶቿን የማስመለስ መብትን ብትጋራም፣ ምን ያህል ቅርሶችን ለማስመለስ ተጠቅመንበታል? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ለቅርሶቻችን ጥበቃ በማግኘት ረገድ በዓለም አቀፍ መዝገብ ማስፈርን እንደ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጡት፣ የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ባለሙያ አባ ብስራተአብ ጌታቸው ናቸው፡፡
‹‹የጽሑፍ ቅርሶች በክልል፣ በአገር፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ተመዝግበው ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለቱሪዝም መስህብነት ሊውሉ ይችላሉ፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ አልማው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በቅርሶች ጥበቃ ረገድ የአገር ውስጥ የመንግሥትና የግል ተቋሞችም ብዙ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ቻይና ውስጥ ወደ 50 የሚደርሱ የጽላት ስብስቦች ከመኖራቸው ባሻገር በጀርመን፣ በካናዳና በሌሎችም አገሮች ያሉ ተቋማት (ግእዝ የሚያስተምሩትን ጨምሮ) በርካታ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች አሏቸው፡፡
የቅርስ ባለቤት የሆኑት ተቋሞች፣ ታዋቂ ግለሰቦች ወይም ነጮችን በስርቆት ስለማይጠራጠሩ የሚጠይቋቸውን የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ከማዋስና ከመስጠትም ወደ ኋላ አይሉም ሲሉ አንድ የዐውደ ጥናቱ ተካፋይ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ መንገድ ወደ ውጪ የሚወጡት ቅርሶች የውጪ ሙዚየሞች ማደለቢያ ሆነዋል፤›› ብለዋል፡፡
ዩኔስኮ በቅርስነት እንዲመዘግባቸው ስለሚላኩ ቅርሶች የሚገልጹ ሰነዶች ስለ ቅርሶቹ በጥልቅ የማስረዳት አቅም አላቸውን? ሲሉ የጠየቁ ተሳታፊም ነበሩ፡፡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ጥበቃ እንዲያገኙ በሚል ለዩኔስኮ ሰነዶች ሲላኩ፣ ስለቅርሶቹ በቂ መረጃ ተያይዞ መላክ ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሷቸው እ.ኤ.አ. በ2015 በቅርስነት እንዲመዘገቡ የተላኩትን መጽሐፈ ድጓና ባሕረ ሐሳብ ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ‹‹ኢትዮፒክ ሔኖክ›› የሚለው አገላለጽ በስህተት ‹‹ኢትዮጵያዊው ሔኖክ››
(Ethiopic Enoch) በሚል ሲተረጎም ይታያል፡፡ ይህን መሰል የዕውቀት ክፍተቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያን የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ዘርፈው የወሰዱ አገሮች ጽሑፎቹን ለጥናትና ምርምር ክፍት ሲያደርጉ፣ ወመዘክር ግን መረጃ ለመስጠት ውጣ ውረድ ማሳየቱም ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ‹‹በቅርሶቹ በአግባቡ ለመጠቀም ከሚሹ ኢትዮጵያውያን ይልቅ ዓላማቸው ያልታወቀ የውጪ ዜጎች ይታመናሉ፤›› ያሉ ነበሩ፡፡ ቅርሶችን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር ረገድ ሥልጣንና ገንዘብ ያላቸው ሰዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች የሃይማኖት ተቋሞችም ሳይቀሩ እጃቸውን ማስገባታቸው ተተችቷል፡፡
በሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ጥበቃ ዙሪያ የሚመለከታቸው ተቋሞች ተቀናጅተው ከመሥራት መወነጃጀልን ይመርጣሉ ሲሉ የተናገሩ ነበሩ፡፡ የፍትሕ አካላት የቅርስ ዘራፊዎችን የሚቀጡበት ሒደት መጓተቱና ቅጣቱም ማነሱ፣ ቅርሶች አነስተኛ ግምት እንደሚሰጣቸው ያመላክታል ሲሉ የተናገሩም ይጠቀሳሉ፡፡
አባ ብስራተአብ እንደተናገሩት፣ በቅርሶች ጥበቃ ሁሉም አካል መረባረብ ያለበት ሲሆን፣ ትውልዱም ለታሪኩና ለባህሉ ተቆርቋሪ መሆን ይገባዋል፡፡ ‹‹ከየቤተ ክርስቲያኑ የሚሰበሰቡ ቅርሶች በአግባቡ ካልተጠበቁ ዋጋ የለውም፡፡ አሳልፈን እየሰጠናቸው ያለነው እኛው ነን፤›› ብለዋል፡፡ በምንም ያህል ገንዘብ የማይተኩ የማንነት መገለጫ የሆኑ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ጉዳይ ቸል መባል እንደሌለበትም አክለዋል፡፡
Source : ethiopianreporter
No comments:
Post a Comment