By :- D/n Abayneh Kasse
"አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል" ዘዳ ፯፥፳።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሐዋሳ ለመላዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አርአያ የሚኾን ተግባር በማከናወን ሥራ ተጠምዳለች፡፡ ለአቅመ መናፍቅ ያልደረሱ ነገር ግን እንደ ዲያቆን ታደሰ ወርቁ አጠራር ለሐራጥቃ "አድራሽ ፈረሶች" የኾኑ ሳይሠሩ የሚጎርፍላቸው ገንዘብ እንቡር እንቡር እንዲሉ ዕድል የሰጣቸው ስለኾነ ለጊዜውም ቢኾን የቤት ሥራችን ኾነዋል፡፡ አድራሽ ፈረስ ማለት ተሸካሚ እንደማለት ነው፡፡ ልክ የወባ በሽታን እንደምትሸከመው ቢንቢ ወይም ትንኝ መኾናቸው ነው፡፡ በአፍርንጅ ቃል "vector" የሚለው ሳይገልጠው አይቀርም፡፡ ዛፍን ለመቁረጥ ቅርንጫፎቹን መመልመል እንደሚቀድመው ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም ቅርንጫፎቹን በመመልመል ወደ ጉንዱ ትሔዳለች፡፡ የወባን በሽታ ለመከላከል ወባ ማራቢያዎችን ማጽዳት እንደሚገባው ማለት ነው፡፡ ሐዋሳዎች በዚህ ጉዳይ ላይ በልዩ ትኩረት እየሠሩ ሲኾን በሚያኮራ ውጤትም ወደ ከፍታው ማማ እየተረማመዱ ነው፡፡
በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤቱ ከሰበካ ጉባኤው፣ ሰበካ ጉባኤው ከወረዳ ቤተ ክሕነቱ፣ ወረዳ ቤተ ክሕነቱ ከሀገረ ስብከቱ እንደ ችቦ አንድ ኾነው ጉዳዩን ተያይዘውታል፡፡ እንዲህም በመኾኑ በከተማው ያሉ አድባራት በሙሉ የትግሉ አካል ኾነዋል፡፡ በተለይም የደብሩ ስብከተ ወንጌል ከአስተዳዳሪው እንዲሁም ከበሳሉ ሰበካ ጉባኤ እና የሰንበት ት/ቤት አመራር ጋር በመኾን የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ መሪ አድርገው የሚሔዱት የሰመረ ጉዞ ይበል የሚያሰኝ ድንቅ ፍኖተ ተጋድሎ ይታይበታል፡፡
ልበ ሰፊዎች ናቸው እና ደጋግመው ዕድል ሠጡ፡፡ ተበድለው ይቅርታ ጠየቁ፡፡ ገፊዎችን ተገፊዎች ተቀበሉ፡፡ ንጹሐኑ በደለኞች ተብለው የሰውን ነፍስ ለማትረፍ እነርሱ በአትሕቶ ክርስትና ዝቅ አሉ፡፡ ውስጣቸው እየጤሰ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ሲባል ታገሡ፡፡ አንጀታቸውን እርር ትክን የሚያደርገውን የራሳቸውን እሳት ራሳቸው ዋጥ አድርገውት ሰነባበቱ፡፡ አድራሽ ፈረሶቹ ግን ከድንግላንሳ እስከ ሽምጥ ጋለቡ፡፡ ግልቢያውም ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳት ኾነ፡፡ የዚህ ጊዜ አስከማዕዜኑ? አሉ ተርቦቹ፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ዕድለኛ ናቸው፡፡ እንደእነዚህ ያሉ አስተዋይ ባለ አዕምሮ የኾኑ ልጆች መውለዳቸው፡፡ አቡነ ገብርኤል እግዚአብሔር በሰላም ለሀገራቸው ያብቃቸው እንጂ ለጊዜው ራቅ ያለ መንገድ ሔደዋል፡፡ በአካል ቢርቁም በመንፈስ አብረው ናቸው፡፡ ታማኝ ልጆች ስላሏቸውም ጥብቁን የቤተ ክርስቲያን አጥር የሚነቀንቁትን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተዋቸዋል፡፡
በዕድሜ ዘመኔ ተደርጎ ዐይቼውም ሰምቼውም የማላውቀው ጉባኤ በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከሰኔ ፲፮ እስከ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በሚያስደምም ሁኔታ ተካሔደ። የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የቤተ ክሕነቱ ኃላፊዎች፣ የሁሉም አጥቢያዎች አስተዳዳሪዎች እና ሊቃውንት በተገኙበት እግዚአብሔር የወደደውን አደረገ፡፡ ምእመኑ ከአጎራባች ከተሞች ሳይቀር እየመጣ ይሳተፍ እንደነበር አረጋግጠናል፡፡ የሕዝቡ አመጣጥ አስደንጋጭም አስደሳችም ነው፡፡ በቃ እንደዚህ ዓይነት ኹለት ስሜቶችን ማስተናገድ ተፈጥሯዊ ሳይኾን አይቀርም፡፡ ሲገባም ሲወጣም ድባቡ እንዲያ ነው፡፡ ግን አንዳችም ችግር ሳይገጥመን ተከናወነ፡፡
ዝናብ ዘነበ ሕዝቡ ግን አልበረገገም፡፡ እንዲያውም ይግረማችሁ ብሎ ለመቀመጫ የተሰጠውን የፕላስቲክ ወንበር እየገለበጠ ጃንጥላ አድርጎት አረፈው፡፡ ንቅንቅም ትውርም የሚል የት ተገኝቶ፡፡ ዝናቡም ተሸናፊ መኾኑን ሲያረጋግጥ ወዲያው እልፍ ወዲያው እልፍ ይላል፡፡ ከነበረበት ያልተናቀነቀው ምእመን ወዲያው ወንበሩን ገልብጦ መቀመጫ ያደርገዋል፡፡ ወንበር ኹለት አገልግሎት እንዳለው እዚያ ዐይቻለሁ፡፡ ለመቀመጫነት እና ለጃንጥላነት፡፡ ደግሞ ዝናቡ ተፈላጊ እንጂ የሚጠላ አልነበረም፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ በሐዋሳ ሙቀት እንዳይቀልጥ እግዘአብሔር ያዘጋጀው ድግስ ነበረ እንጂ፡፡ ሰው እንደኾነ ገና በጊዜ ከስምንት አስከ ዘጠኝ ባለው ሰዓት የወትሮዎቹን የልዩ መርሐ ግብራት ያኽል ኾኖ ይከትማል፡፡ በዚያ ሙቀት የግቢው አስፋልት ላይ ለመነጠፍ አያመነታም፡፡ ምን ዓይነት ብርቱ ሕዝብ ነው!
በየዕለቱ ጸሎተ ወንጌል ይደርሳል፤ ጉባኤው ይቀጥላል፡፡ ካሜራዎች የማይዘልቋቸው የቅጽሩ ዛፎች በውስጣቸው ስንቱን ስብስብ አድርገው እንዳስጠለሉት ማን ሊናገር ይችላል? እንደ ሠርገኛ ጤፍ ከላይ ኾኖ ሲታይ የልብ ትርታን ይጨምራል፡፡ ርጋታ እንጂ መቅበጥበጥ እዚያ ቦታ አልነበረውም፡፡ ተርቦቹ የሐዋሳ ልጆች በአጭር ጊዜ ውስጥ እግዚአብሔርን ከፊት ከኋላ አድርገው ተነሡ ተሳካላቸው፡፡
ከተርቦቹ ምን እንማራለን?
እንደ እኔ ዐራት ነጥቦች ይታዩኛል፡፡
፩. ያገባኛል ማለትን፡-
የእነ እገሌ ሥራ ነው ብሎ ገፍተው አልተቀመጡም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት፣ የካሕናት እና የምእመናን ናት፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከጎደለ ሙሉ አትባልም፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴውም የሚለው ይካ (ይበል ካሕን)፣ ይዲ (ይበል ዲያቆን) ብቻ ሳይኾን ይሕ (ይበል ሕዝብ) ደግሞ ይላል፡፡ ለተርቦቹ ይህ ግልጽ ነው፡፡ ስለኾነም እጃቸውን አጣምረው አይቀመጡም፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አጀንዳ የጥቂቶች ብቻ አድርጎ የመመልከት አባዜ የተጫጫነው ሁሉ ከዚህ ሊማር ይገባል፡፡ በእነ እገሌ አዝኛለሁ ተስፋ ቆርጫለሁ አይባልም፡፡ እንዲያ ከተባለ መክሊትን መቅበር ይኾናል፡፡ ዳር ቆሞ መመልከት ያበቃ ዘንድ የሐዋሳ ተርቦች ድምፅ አሰምተዋል፡፡
፪. ብስለትን፡-
የቤተ ሐራጥቃ አድራሽ ፈረሶች ዝላይ በእነርሱ እና በአጎራባቾች አኅጉረ ስብከት አጥር የመነቅነቅ ሙከራውን በጠንካራ መሠረት ለማደላደል ዝናሩን እየጨረሰ ነው፡፡ ዲላ ላይ ጀግናውን አለቃ ቆሞስ አባ ታዬን እስከመደባደብ ደርሰዋል፡፡ የተመለሱ ምክሩን አሻፈረኝ ካሉት ፲፰ቱ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተለይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በጽሑፍ በደሉን አምኖ ይቅርታ ጠይቆ ጉዳዩ እየታየለት ነው፡፡ ለቀሩቱ ግን አዳራሽ በመከራየት ለመቀጠል ሲፈልጉ የዲላ ሕዝብ ቤታችንን ለእናንተ አናከራይም እያላቸው እንደኾነ እና እስካሁን እንዳልተሳካለቸው ይሰማል፡፡ በአማሮ፣ በወናጎ፣ በክብረ መንግሥት፣ በሻኪሶ፣ በነገሌ ቦረና ያሉ ምሽጎች ይታወቃሉ፡፡ የይርጋ ዓለሙ ርደተ መቃብሩ እየተፈጸመ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ስፍራዎች ሰዎቹ የሚቀባጥሩት በኦድዮ እና በቪድዮ ገቢ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ክህደቶቹ አላዋቂ የሚክዳቸው ናቸው፡፡ መናፍቅ የሚባሉት ሊቆች ነበሩ፡፡ እነዚህ ግን ለአቅመ መናፍቅ ያልደረሱ አንዱ የእነርሱን ሪሞት ኮንትሮል በእጁ የያዘው ሲናገር እንደተሰማው "እዚህ ግቡ የማይባሉ" ናቸው፡፡ ስንኳን በእኛ በእነርሱም የተናቁ እንደኾኑ ግን አይገባቸውም፡፡ ዐይኖቻቸው የተተከሉት ገንዘቡ ላይ እንጂ መስቀሉ ላይ አይደለምና ምንም ቢባሉ አይደንቃቸውም፡፡ እንዲህም ስለኾኑ ሌላው ይቅርና "ኢየሱስ እናት የለውም አባት ብቻ ነው ያለው" እስከማለት ደርሰው ይቀባጥራሉ፡፡ ዲያብሎስንም ቀሺም አሥልጣኝ አስባሉት፡፡ እርሱም በመሸማቀቁ ሳያሸማቅቅ እንደማይለቃቸው ይታወቃል ግን ጥቂት ጊዜ በግዱ ይጠብቃል፡፡
እንደዚህ ያለውን ለማግኘት እግዚአብሔር ጥበቡን ለሐዋሳዎቹ ተርቦች ሰጣቸው፡፡ በዚያም ሲቀባጥሩ አገኟቸው፡፡ ማስረጃውንም ሳያባክኑ ተጠቀሙበት፡፡ በዚህ ሥራ ነገሌ ቦረናዎች፣ አማሮዎች እና ሐዋሳዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
፫. ጥምረትን፡-
ያገኙትን ማስረጃ ሁሉ ሰብሰቡ ከአባቶቻቸው ጋር መከሩ፡፡ ወጣቶቹ በዕድሜ እና በዕውቀት ከበለጸጉ የሐዋሳ ልዩ ፈርጦች ጋር መከሩበት፡፡ ከገዳሙ አስተዳዳሪ እስከ ሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ተወያዩበት እና ዕቅድ አዘጋጁ፡፡ አንደኛ የተገኙት ማስረጃዎች ከሌሎች አስረጂዎች ጋር ኾነው ይፋ እንዲደረጉ፣ ኹለተኛ ጉባኤ ማዘጋጀት፣ ሦስተኛ ሕዝብን መቀስቀስ፣ ዐራተኛ ማሰረጃዎቹን በቪሲዲ አቀናብሮ ለምእመናን ማድረስ፣ አምስተኛ ይፋ የማይደረግ ጥብቅ ሥራ መሥራት የሚሉ ዕቅዶች ተነደፉ፡፡ ሁሉም የየድርሻውን ተከፋፍሎ ሥራው ተጀመረ፡፡ ከአምስቶቹ ዕቅዶች ጉባኤ እስከማድረግ ያለው የተጠናቀቀ ሲኾን ቀሪዎቹ ኹለቱ በመሠራት ላይ ናቸው፡፡
ቅንጭብ ቅንጭብ እየተደረጉ ጉባኤው ላይ የተቀረጹ አንዳንድ ማስረጃዎች በማኅበራዊ ሚድያው የተለቀቁ ሲኾን እነርሱ ሙሉውን መልእክት ያስተላልፋሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለኾነም የደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊነቱን ወስዶ የማዘጋጀቱን ሥራ ጀምሮታል፡፡ እስከዚያው ድረስ በትዕግስት መጠበቁ ይበጃል እንጂ በቅንጭብጭብ ማስተላለፉ ያጎድላል፡፡ እናም በየጦማረ ገጹ (ፌስ ቡክ) ያለው የመረጃ ልውውጥ ይህን ግንዛቤ ውስጥ ያካተተ ቢኾን ሠናይ ነው፡፡
፬. ጥብዐትን፡-
ተርቦቹ ንቁዎች ብቻ ሳይኾኑ ጥቡዐንም ናቸው፡፡ እንቅልፋቸውን፣ ሥራቸውን፣ ገንዘባቸውን እያወጡ ይሮጣሉ፡፡ እግዚአብሔር እየቀደማቸው ያሳካላቸዋል፡፡ ፍርሃት የሚባል አልፈጠረባቸውም፡፡ ከአንድነታቸው ጋር የተሰጣቸው ጸጋ ነው፡፡ ብዙ ቦታ ይህ ጸጋ የአንድ ወይም የጥቂቶች ብቻ እየኾነ ውጤት አላመጣም፡፡ በእነርሱ ዘንድ ግን ተጠርጎ ጠፍቶላቸዋል፡፡ እንዲህ ባደርግ እንትኔ እንዲህ ይኾንብኛል ብሎ ነገር የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተደፍራ ፍርሃት የለም ይላሉ፡፡ የሰው አጥር አልነቀነቅንም፤ የእኛን ሲነኩብን ግን ተርብ ነን ይላሉ፡፡
ጽዋውን እየተረከቡ ቄጠማ መጎዝጎዝ ማዩን መቅዳት ያስፈልጋል፡፡
ደስ ይላል፡ ከደስታ ብዛትም ያስለቅሳል
ReplyDeletebetam jegenoch bertu fetari yiredachehu
ReplyDelete