Monday, February 23, 2015

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የፓትርያርኩን እገዳ ተቃወሙ



አንድ አድርገን የካቲት 16 2007 ዓ.ም
From:- Addis Admass
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን /ሲኖዶስ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያንን አዋርደዋል፤ አባቶችን ዘልፈዋል›› ያላቸው አለቆች ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ በፓትርያርኩ ትእዛዝ መታገዱ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ሰንበት /ቤቶች ተቃውሞ ገጠመው፡፡
የአ/አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት /ቤቶች አንድነት ባለፈው ሳምንት እሑድ በሀገረ ስብከቱ /ቤት አዳራሽ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባካሔደው የግማሽ ቀን ውይይት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው ‹‹አማሳኝ አለቆች›› ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ባለመፈጸሙ ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፋ ኹኔታ እየታወከችና እየተመዘበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ውሳኔ እንዲቆዩ ማዘዛቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውሳኔውን ለማስፈጸም ባለመቻሉ፣ ‹‹አማሳኝ አለቆች›› በሚል የተገለጹ የአድባራት ኃላፊዎች እንቅስቃሴያቸውን ለሚቃወሙ አገልጋዮች ስም እያወጡ፣ በገንዘብ ኃይል ከሥራቸው እንዲፈናቀሉና ያለፈቃዳቸው እንዲዘዋወሩ፤ የሰንበት /ቤት ወጣቶች የድርሻቸውን እንዳይወጡ ከመዋቅር ውጭ ባደራጇቸው አካላት እየከፋፈሉና በፖሊቲከኛነት እየወነጀሉ ከአገልግሎት በማገድ ለእስርና እንግልት እየዳረጉ እንደኾነ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የአማሳኝ አለቆችቡድኑ ‹‹ፓትርያርኩ በእጃችን ናቸው፤ የምንፈልገውን እናስፈጽማለን›› በሚል ዕድገትና ሹመት ለማሰጠት ወደኋላ እንደማይልና ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ በዋናነት ‹‹ሊያሠሩን አልቻሉም›› ያላቸውን የወቅቱን የሀገረ ስብከቱን ረዳት ሊቀ ጳጳስ የመወንጀል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፤ ከመጪው የግንቦት /ሲኖዶስ ስብሰባ በፊት ከሓላፊነታቸው የሚነሡበትን ተቃውሞ የማጠናከር ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡  /ሲኖዶሱ ‹‹አማሳኝ አለቆች›› ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አለመፈጸሙ፣ ‹‹እነ እገሌ ምን ኾኑ? እኛስ ምን እንኾናለን?›› በሚል እየተዘበተበትና ‹‹በእግሩ የመጣ በመኪና ይሔዳል›› በሚልም ለከፋ ሙስና በር እንደከፈተ ተናግረዋል፡፡

ለሀገረ ስብከቱ የታቀደው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ‹‹አማሳኝ አለቆችና ቲፎዞዎቻቸው የውኃ ሽታ›› መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፤ ያለተጠያቂነት የሚፈጽሙት ቤተ ክርስቲያኒቱን የመለያየትና የመመዝበር ድርጊት የሰንበት /ቤት ወጣቶችን የአገልግሎት ተነሣሽነት እየጎዳ ከመኾኑም በላይ ‹‹የቅ/ሲኖዶሱ ልዕልና ጠፍቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ በግለሰቦቹ እጅ ላይ ያለች አስመስሏታል›› ብለዋል፡፡ ‹‹ወዳልተፈለገ ነገርስ አያመራም ወይ?›› ሲሉም ውይይቱን ለሚመሩት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የአንድነቱ ሊቀ መንበር ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡

‹‹
በሃይማኖት ሕጸጽ የሚጠረጠሩ ሰባክያን ተመድበውብናል›› ያሉ የመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስና የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ አድባራት ሰንበት /ቤቶች ተወካዮች በበኩላቸው፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት በዝማሬና በስብከተ ወንጌል የመሳተፍ መብታቸው አስተምህሮዋን በሚፃረሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎችና ሕገ ወጥ ሰባክያን ስምሪት መታወኩን በምሬት ገልጸዋል፡፡ በሰሚት መድኃኔዓለም በግለሰቦች ፍላጎት የባለጸጋ ልጆች ብቻ ተሰብስበው የሚማሩበት ሁኔታ መፈጠሩን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹የሀብታምና የድኃ›› ብሎ የመክፈል አዝማሚያ መስተዋሉን አስረድተዋል፡፡ የሰንበት /ቤቱ አመራር ይህ ዐይነቱ አካሔድ እንዲታገድ በጠየቀው መሠረት በሀገረ ስብከቱ /ቤት የተሰጠው መመሪያ በደብሩ አስተዳደር ተቀባይነት ባለማግኘቱ የአመራር አባላቱ እስከመታሰር መድረሳቸው በእንባ ተገልጧል፡፡

በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ትምህርትና ቃለ ምዕዳን የሰጡት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ጉበኞች ፈጽሞ እንደማይተኙ ጠቁመው እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴም መረጃው እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ እንቅስቃሴአቸው የተደራጀና በከፍተኛ ገንዘብ የተደገፈ እንደኾነ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸው፣ ‹‹ጥቅማቸው እንዳይዘጋ በሰው ሕይወትም ከመምጣት ወደኋላ አይሉም›› ብለዋል፡፡ ይኹንና ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፓትርያርኩ አንሥቶ ሙስናን ለመዋጋት ወደ ኋላ እንደማትል አረጋግጠዋል፡፡
‹‹
መሾምና መሻር የእናንተ ድርሻ ባይኾንም ስለ ቤተ ክርስቲያን ግን አይመለከታችኹም አይባልም፤ እንዲያውም የሰንበት /ቤት ተማሪዎች የአስተዳደሩ ሐሳብ መጋቢዎች ናቸው፤›› ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፤ ወጣቱ በትጋትና በብልሃት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አጥር ኾኖ ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ከየአጥቢያው በተነሡት ችግሮች ዙሪያም የሚገባውን ያኽል አልሠራም ካሉት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ ኹሉም ራሱን እንዲፈትሽና የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ ውይይቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው አቡነ ቀሌምንጦስ አስታውቀው፤ ‹‹አማሳኞች›› የወጣቱን ጥያቄ ከመንገድ በማውጣት ከግንቦቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ ትንኮሳ ከመፍጠር ስለማይመለሱ እንደ ዜጋም እንደ ሃይማኖተኛም በትዕግሥትና በሰላማዊ መንገድ መዋቅርን ጠብቆ በመንቀሳቀስ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡

ቁጥራቸው 780 በላይ የኾኑ የሰባቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት /ቤቶች ሰንበት /ቤት ክፍሎች ሓላፊዎችና 160 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት /ቤቶች አመራሮች በተገኙበት በዚኹ የውይይት መርሐ ግብር÷ ሰንበት ተማሪው በሃይማኖት ሕጸጽ በሚጠረጠሩና አፍራሽ ተልእኮ ባላቸው ሰባክያን ዙሪያ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋቋመው አጣሪ አካል እንዲያቀርብ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና÷ የውይይት መርሐ ግብሩን እንደ ስጋት ከሚመለከቱ አካላት እንደኾነ የተጠረጠረ ዛቻና ማስፈራሪያ በሀገረ ስብከቱ የሰንበት /ቤት አንድነት አመራሮች ላይ እየተፈጸመ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡ በዕለቱ ውይይቱን ሲመሩ በነበሩት የአዲስ አበባ ሰንበት /ቤቶች አንድነት ሊቀ መንበር ቀሲስ ኄኖክ ዐሥራት ዛቻና ማስፈራሪያው ከደረሰባቸው አመራሮች አንዱ እንደሆኑ የጠቆሙት ምንጮች፤ ‹‹መንግሥት ከኛ ጋር ነው፤ አንተን ለማጥፋት ጥቂት ገንዘብ ይበቃናል›› የሚሉ ግለሰቦች ሳያቋርጡ በስልክ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዳደረሱባቸው ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment